Saturday, 12 January 2013 09:25

የገና እለት ከቧንቧ የፈሰሰው “ደም” ሰፈርተኛውን አደናገጠ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(6 votes)

በተለምዶ አጠራሩ አስራ ስምንት ልኳንዶ 07 ሰፈር በሚባለው አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የገና በአል እለት ውሃ ከሚቀዱበት ባንቧ ድንገት ደም በመፍሰሱ መደናገጣቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የአካባቢው ውሀ ለሁለትና ለሦስት ቀን እንደሚጠፋ የገለፁት የአካባቢው ነዋሪ ወ/ት ህይወት መለሠ፤የገና በአል ሰሞን ውሃ ሳይጠፋ መቆየቱንና የበዓሉ እለት ጠዋት ላይ ውሀ ሲቀዱ ከቧንቧው ደም መሠል ነገር በመፍሰሱ መደናገጣቸውን ይናገራሉ፡፡ የእሳቸው ቤት ቧንቧ ብቻ መስሏቸው እንደነበር የገለፁት ወ/ት መሠል፤ በኋላ ግን ጐረቤቶቻቸውም ተመሳሳይ ነገር እንደገጠማቸው ማወቃቸውን ተናግረዋል፡ቀዩ ፈሳሽ ለሁለት ቀናት ከቧንቧው ይፈስ እንደነበር ጠቁመው አሁን የጠራ ውሃ ቢመጣም በቧንቧው ውሃ ለመጠቀም ውስጣቸው እሺ እንዳላላቸው ይገልፃሉ፡፡

ከእሳቸው ቤት ቧንቧ ቀጠን ያለ ደም መሠል ፈሳሽ ይወርድ እንደነበር የገለፁት ነዋሪዋ፤ የአንዳንዶቹ ግን ወፍራም እንደነበር ተናግረዋል፡፡  ለ25 አመታት በአካባቢው እንደኖሩ የገለፁት አቶ ሸረፋ አበበ በበኩላቸው፤ የገና ዕለት ጠዋት ንፁህ ውሃ ከቧንቧ ቀድተው ፊታቸውን መታጠባቸውን ገልፀው፤ ከዛ በኋላ ግን የተደቀነው መዘፍዘፊያ ሙሉ በሙሉ በደም ተሞልቶ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ ምናልባት ልጆች እርድ የነካው ሠሀን አስቀምጠው ይሆናል በሚል ሌላ እቃ መደቀናቸውን የሚናገሩት አቶ ሸረፋ፤ሆኖም ከቧንቧው የሚወርደው ነገር እንዳልተለወጠ ይገልፃሉ፡፡ በእኔ ቤት ምን መጣ በማለት ከጐረቤቶቻቸው ጋር መጠያየቃቸውንና ችግሩ የሳቸዉ ቤት ብቻ ሳይሆን የአካባቢው በሙሉ መሆኑን እንደተረዱ ገልፀዋል፡፡ ከቧንቧ ውሀው ስለሚፈሰው ደም ምንነት ለማጣራት አቶ ሽመልስ ቢያድግልኝ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ወደ ውሃና ፍሳሽ በመሄድ ለመሥሪያቤቱ ሰራተኞች እንደነገሯቸውና “መጥተን እናያለን” ቢሉም ሳይመጡ እንደቀሩ የልኳንዳ ሰፈር ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በአንዳንድ ቤቶች ቧንቧዎች ደም ነው የተባለው ፈሳሽ ለሁለት እና ለሦስት ቀናት ሲፈስ እንደቆየ ለማወቅ ችለናል፡፡ 
በአብዛኞቹ ቤቶች አሁን የጠራ ውሃ እየወረደ ቢሆንም ነዋሪዎች ለመጠቀም መቸገራቸውን ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ተስፋለም ባዩ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “አንዳንዴ በህብረተሰቡ የጥንቃቄ ጉድለት ከሚከሰት የውሃ መበከልና በአፈር የመደፍረስ ሁኔታ በቀር እንዲህ ያለ ችግር ገጥሞን አያውቅም፤ ምናልባት ከበዓል እርድ ጋር በተገናኘ የተፈጠረ ሊሆን ይችላል” ብለዋል፡፡ሆኖም እንዲህ ያለ ችግር ገጥሞናል ብሎ ያመለከተ የለም በማለት አስተባብለዋል- ም/ኀላፊው፡፡

Read 7226 times