Saturday, 12 January 2013 09:28

ከ800ሺ ብር በላይ የሚያወጣ የቤቶች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(12 votes)

ልማት ጽ/ቤት ንብረት ተዘርፏል
በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ለግንባታ የሚያገለግሉ ብረቶች በተደጋጋሚ መዘረፋቸውን የተናገሩት የጽ/ቤቱ የቀድሞ ንብረት ቁጥጥር ሠራተኛ ወ/ሮ አልማዝ ወ/አማኑኤል፤ ከ800ሺ ብር በላይ የሚያወጣ የፅ/ቤቱ ንብረት ቢዘረፍም እስካሁን ጉዳዩ በሃላፊዎች ቸልተኝነት እልባት እንዳላገኘ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ንብረቶቹ በተደጋጋሚ የተዘረፉት ረጲ ከሚገኘው የጽ/ቤቱ ዋና መጋዘን እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ አልማዝ፤ንብረቶቹ ቆጠራ እንዲካሄድባቸው እንዲሁም ያለውና የጠፋው ተለይቶ እንዲታወቅ ለፕሮጀክቱ ጽ/ቤት በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ይናገራሉ፡፡


የጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ለኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በ22/8/2000 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ መጠናቸው የማይታወቅ ብረቶች መጥፋታቸውን ጠቁመው፣ ምርመራ እንዲደረግና ጉዳዩንም አቶ ዳዊት ደበበ የተባሉ የመ/ቤቱ ባልደረባ እንዲከታተሉ መመደባቸውን ወ/ሮ አልማዝ ለአዲስ አድማስ ያቀረቡት ሰነድ ያሳያል፡፡
በ02/9/2000 ዓ.ም ደግሞ የጽ/ቤቱ የሎጂስቲክ አስተዳደር ዋና ክፍል ሃላፊ፣ንብረቱ መሠረቁን በማረጋገጣቸው ባለሙያዎች ተመድበው ቆጠራ እንደተደረገና በቆጠራውም ቁጥሩ ያልታወቀ በርካታ ብረት መጥፋቱ እንደተረጋገጠ ጠቁመዋል፡፡
“ይህን ጉዳይ ለሚመለከተው ሁሉ በደብዳቤ በማሣወቄ፣ ጉዳዩ በ20/5/2001 ዓ.ም በልደታ ምድብ ችሎት የታየ ቢሆንም ምስክሮች ተሟልተው ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ሲቀርቡ መዝገቡ ይንቀሳቀስ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ሂደቱ ተድበስብሶ ቀርቷል” ብለዋል- ወ/ሮ አልማዝ፡፡ ይህ ጉዳይ በእንጥልጥል እያለ በ7/3/2001 ዓ.ም በመጋዘን ውስጥ የቡድን ዘረፋ ሲፈጽሙ የተገኙ ስድስት ተጠርጣሪዎች ከነአይሱዙ መኪናቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ፍ/ቤት ቀርበው እያንዳንዳቸው የአስር ወር እስራት እንደተፈረደባቸው ወ/ሮ አልማዝ ተናግረዋል፡፡
ለስራና ከተማ ልማት ቢሮ በተደጋጋሚ ኦዲት ልደረግ በማለት መጨቃጨቃቸውን የጠቆሙት የቀድሞ የንብረት ቁጥጥር ሠራተኛዋ፣ቢሮው ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ትዕዛዝ አስተላልፎ ኦዲት መደረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁሉ ዘረፋ እየተፈፀመ ጉዳዩን የሚከታተለው አጥቶ ንብረት መባከኑን፣ የተሠረቁ የብረት አይነትና መጠን አቅርበው ችላ መባላቸውን ለሚመለከተው ሁሉ አቤት እያሉ በነበሩበት ወቅት በ17/4/2004 ዓ.ም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በተጻፈ ደብዳቤ፣ በኦዲት ቆጠራው የታዩ ጉድለቶችን እንድትተኪ የሚል ትዕዛዝ መውጣቱንና ግምቱም ከ800ሺህ ብር በላይ እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ አልማዝ፣ በዚህም ሞራላቸው መነካቱን እና እስከመጨረሻው ፍትህ ለማግኘት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡
ግለሰቧ በ2001 ዓ.ም በተሠራ መዋቅር ምክንያት በንብረት ተቆጣጣሪነት ይሠሩበት ከነበረው ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ተዛውረው በተመሳሳይ የስራ ምድብ ላይ የሚሠሩ ሲሆን፣ በወቅቱ ይሠሩበት ከነበረው ጽ/ቤት የጠፋው ንብረት ጉዳይ ዕልባት ሳያገኝ መዛወራቸው አግባብ እንዳልሆነ የኦዲተሮች ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ጉዳዩ ተፈፀመ በተባለበት ወቅት በጽ/ቤቱ የአቅርቦትና ቁጥጥር ሃላፊ የነበሩትን አቶ ሠለሞን መስፍንን በስልክ ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ፣ “በወቅቱ ተፈፀመ በተባለው ጉዳይ ላይ ግለሰቧ ባመለከተችው መሠረት ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ደብዳቤ ጽፈን አሳውቀናል” ብለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ረጺ ከሚገኘው የጽ/ቤቱ ዋና መጋዘን ብረት ሲዘርፉ ተይዘው ስለመታሠራቸው የጠየቅናቸው አቶ ሠለሞን፣“በደረሰን ጥቆማ መሠረት ተጠርጣሪዎቹ መጋዘኑ ውስጥ በመያዛቸው ክስ ተመስርቶ መታሠራቸውን አውቃለሁ፣ያም ቢሆን ሊጭኑ ሲሉ ተይዘው ለፍርድ ቀረቡ እንጂ ስለመዝረፋቸው የማውቀው ነገር የለም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከአቅርቦትና ቁጥጥር ሃላፊነታቸው በመዋቅር ተዛውረው፣በአሁኑ ወቅት የአነስተኛና ጥቃቅን ቢሮ ሃላፊ በመሆን የሚሰሩት አቶ ሰለሞን፣ “አብዛኞቻችን በመዋቅር ምክንያት ስለተዘዋወርን ጉዳዩ አይመለከተኝም” በማለትም ገልፀዋል፡፡ የንብረቱ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ወ/ሮ አልማዝ እንዴት ወደ ሌላ ክ/ከተማ ተዛወሩ በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ መዋቅር ሲሠራ ወ/ሮ አልማዝ ቦታ እንዳጡና ስራ በማጣት ሊጉላሉ ስለማይገባ ወደተባለው ክ/ከተማ በተመሳሳይ ስራ መዛወራቸውን ብቻ እንደሚያውቁ፣ ከዚህ በላይ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉም አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክተን የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ለሆኑት አቶ ነስሩ ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ጉዳዩን እስከመጨረሻው ባለመከታተሏ የንብረት ጉድለቱ በኦዲተሮች ተረጋግጧል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Read 4834 times