Saturday, 12 January 2013 09:42

የ‘ማሽላ’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዓል እንዴት ከረመ? ስሙኝማ… ያልተጻፈ ህግ ስናወጣ እኮ አሪፍ ነን፡፡ የምር…ነገሬ ብላችሁልኝ እንደሁ ማንኛውም የአንድ ቀን በዓል ወደ ሦስት ቀን ተመንዝሯል— ዋዜማ፣ በዓልና ማግስት! እናላችሁ…በበዓል ማግስት አይደለም የግል ተቋማት አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶች አካባቢ እንኳን “አልገቡም…” የሚባል ነገር እየበዛ ነው— ‘የደላን’ ይመስል! ብቻ እንኳንስ ገና በሰላም አለፈላችሁማ!
የገናን ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለእንትንዬው ስጦታ መስጠት ይፈልግና ለጓደኛው ያማክረዋል፡፡
“ለገርሌ ለገና ምን ስጦታ ብሰጣት ይሻላል? የሚያስደስታት ነገር እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡”

“አንተን ትወድሀለች?”
“እንክት አድርጋ ነዋ!”
“አንተን ከወደደች ምንም ነገር ስለምትወድ ያገኘኸውን ነገር ግዛላት፡፡”
ይኸውላችሁ የወዳጅ መካሪ እንዲሀ ነው፡፡ ከገና ሳንወጣ…ባል ሆዬ ከመሸ ‘ቸስ’ እያለ ነው ቤቱ የሚገባው፡፡ እናማ ሚስት የልጆቿ ነገር ሆኖባት ነው እንጂ ሰልችቷታል፡፡ (የ‘ልጆቻቸው ነገር’ እየሆነባቸው ስንት መከራ የሚችሉ እናቶችን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡)
ታዲያላችሁ የዚቹ ሴትዮ ጓደኛ “ለመሆኑ ለገና ለልጆችሽ ምን ስጦታ ትሰጫቸዋለሽ?” ብላ ትጠይቃታለች፡፡ ምን ብላ መለሰች መሰላችሁ… “አባታቸው አምቡላውን እየገለበጠ በሌሊት መምጣት ካልተወ አዲስ አባት እሰጣቸዋለሁ፡” ብላ እርፍ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…መቼም ዘንድሮ ድፍን አገር በ‘ኮንሰልታንሲ’ ተጥለቅልቋል፡፡ ጠይቃችሁ “ይሄን እንኳን እኔ አላውቀውም፣ ባለሙያ ብታማክር ይሻላል…” ምናምን የሚባል ነገር የለም፡፡ ህክምናማ ተዉት…“አንተ ዘላለም ጨጓራ እንዳልክ፣ እየው ምን የመሰለ የነቀምት አረቄ ትገዛና፣ ጧትና ማታ ሁለት ሁለት መለኪያ ጅው ማድረግ ነው… እንዴት ነው ነገሩ፣ በዛው ‘ጅው’ ማለት የመጣ እንደሆንስ!
እኔ የምለው….በተለይ የሰው የግል ህይወት ውስጥ እየገባን ምክር በምንሰጥ ሰዎች…አለ አይደል…መአት የቤተሰብ ምሰሶ ተናግቷል፡፡ አሁን፣ አሁን የምንሰጣቸው ምክሮች “እስቲ ረጋ በዪና አስቢበት፣” “ቆይማ ከመወሰንህ በፊት ከልብህ ጋር በደንብ ተነጋገር…” ምናምን አይነት የማረጋጋያ ነገሮች እየቀሩ ነው፡፡
“እባክሽ ይሄ ሰውዬ እኮ አስቸገረኝ…” ስትል…አለ አይደል… “መሀላችሁ ምን ገባ?” “ችግሩ ምን እንደሆነ ለምን በደንብ አትጠይቂውም?” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም… “ትተሽው ሂጂያ! ዕዳ አለብሽ እንዴ… ደግሞ ጥንቡን ለጣለ ለዛሬ ወንድ!” አይነት ምክር ነው የሚሰጠው፡፡
ደግሞላችሁ…“ይሄን ሰሞን ጠባዩዋ እየተለወጠብኝ ነው…” ሲል…አለ አይደል…“የገጠማት ከባድ ነገር ሊኖር ስለሚችል ረጋ ብለህ አማክራት…” ከማለት ይልቅ “ታዲያ ወደዛ ደምፕ አድርጋታ! እንደውም አንተ ነህ ከአንዲት ሴት ጋር ሦስት ዓመት ሙሉ እኝኝ ያልከው…” አይነት ነገር ‘ምክር’ ነው የሚሰጠው፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮ የምንሰጣቸው ምክሮች እየመረሩብን ተቸግረናል፡፡
“አንቺን የመሰልሽ ልጅ፣ መልክ አለሽ… ቁመና አለሽ… ይኸው ጓደኞችሽ ሁሉ የሚያብረቀርቅ መኪና ሲያሽከረክሩ አንቺ ዘለላምሽን! አሁንማ የታክሲውም እያስቸገረሽ ወደ አውቶብስ ወርደሻል አሉ…” አይነት ምክር አለላችሁ፡፡
ደግሞላችሁ…“እንዴ የምትሰቃዪው ምን ዕዳ አለብሽ! ድሮም በቂ ደሞዝ የሌለው የመንግሥት ሠራተኛ አታግቢ ስንል አልሰማ ብለሽ ይኸው ተንገብግበሽ ማለቅሽ ነው…” የምንል መካሪዎች በዝተናል፡፡
ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ምክር ስንሰጥ እያወራን ያለነው ምክር እየሰጠነው ስላለው ሰው ሳይሆን ስለ ራሳችን ነው፡፡ “አንተ ዘላለም በሲ.ፒ.ኤ. ደሞዝ መከራህን ከምታይ ለምን አንዱ ኤን.ጂ.ኦ. አትገባም!” አይነት ምክር…አለ አይደል…ኤን.ጂ.ኦ. የሚሉት ነገር “እንትን ሲኒማ ቤት ልግባ…” ተብሎ ሰተት ተብሎ የሚገባበት ነገር ይመስላል፡፡
ስሙኝማ…የምክር ነገር ካነሳን አይቀር፣ የሰሞኗ ምክር እንዴት ነች! ማለት ይሄ ‘ማሽላ ብትቀላቅሉበት’ ምናምን የተባለው ነገር…ለነገሩ ማሽላ የሚባል ነገር መኖሩን ልንረሣ ምንም አልቀረን ነበር!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ማሽላ አይደለች እያረረች ትስቃለች የምትባለው፡፡ የምር…ለተረትነት እኮ ስታገለግለን ኖራለች፡፡ አሁን ይኸው…‘ዘመን ተለወጠ’ና ተረትነቷ ቀርቶ መጣችላችሁ፡፡
ስጋት አለን…አሀ፣ ስጋታችንን መናገር አለብና! ምን መሰላችሁ… ምንም ነገር የማያውቀው ‘የዋሁ’ ጤፍ፣ ‘ምስኪኑ’ ጤፍ…አለ አይደል… እያረረች የምትስቅ ማሽላ ስትቀላቀለው የሚሆነውን አስቡልኝማ፡፡ የምር…ሰዉ እኮ ደህና የነበረው (‘መሬት’ የነበረው…ማለት ይቻላል) ባህርዩ በአንድ ጊዜ ልውጥ የሚለው እያረረ የሚስቅ ‘የሰው ማሸላ’ እየተቀላቀለበት ነው፡፡
እናላችሁ…‘ንፁህ’ ነገር ምናልባት በማር ጠጅ እንጂ በሰው ባህሪይ እየቀረ ነው፡፡ ሰላምታ ሲሰጥ ግንባሩ መሬቱን ለመንካት ምንም የማይቀረው የነበረው ሰው… የሆነ ‘እያረረ የሚስቅ’ ነገር ይቀላቀልበትና እጁን ለመዘርጋት እንኳን መጠየፍ ሲጀምር አስቸጋሪ ነው፡፡ “ይሄ እንጀራ ጤፍ ብቻ ነው ብለሽ ነው!” እያልን ስንጠራጠር የነበረው ነገር ሁሉ ይኸው ‘እውቅና’ ሊያገኝ ነው፡፡ እንደውም…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ከትንሽ ጊዜ በኋላ ምግብ ቤት ያዘዝነው ተጋሚኖ ምናምን ሲቀርብልን…አለ አይደል… “ይሄ እንጀራ ማሸላ ምናምን ቀላቅላችሁበታል እንዴ!” ምናምን አይነት ጥያቄ ስናቀርብ ምን መልስ ሊሰጠን ይችላል መሰላችሁ… “ጎሽ የእኛ ዘመናይ…ታዲያ ንፁህ ጤፍ እንጀራ ሊቀርብልህ ነበር!”
የምር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…አንዳንድ ነገሮች ‘ሳይነካኩ’ እንደለመድናቸው ቢቆዩ አሪፍ አይመስላችሁም! ለምሳሌ ጤፍ… በቃ ላለፉት ሺህ ዓመታት እንደነበረችው ብትቆይ አሪፍ ነበር፡፡
ስሙኝማ…ማሸላ ስትነሳ የሆነች ዘፈን ትዝ አለችኝ…
ማሽላዬ ወማዬ በላው
እንኳን ወማዬ ይብላው ነጎዴ
የሰው ነገር አትስማ ሆዴ፡፡
ይቺ ‘የሰው ነገር አትስማ ሆዴ…’ እንዴት ለዘንድሮ የምትስማማ አባባል ነች! ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺ አንድ ነገር ሲጎድል ‘ማሟያ’ መፈለግ በጤፍ ብቻ ሳይሆን በሌላም ይካተትልንማ! ለምሳሌ የማይጥም አለቃ ጎን የምትጥም ኤክስኪዩቲቭ ሴክሬታሪ ትቀመጥልን! ቂ…ቂ…ቂ…እናላችሁ አስቸጋሪ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…
በካብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ
በዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ
በምድር ላይ ብሠራ እረኛው መከራ
የት ውዬ የት አድር ብዬ፡፡
ይሄን ያለችው ወፍ ነች አሉ፡፡ ምን ታድርግ! ዙሪያዋን ብታየው ሊበላት ሊሰለቅጣት ያሰፈሰፈ ብቻ ነው፡፡ (ዘንድሮ ብዙዎቻችን ዙሪያችን ያለው ነገር እንደሚያሳድርብን ስሜት ማለት ነው፡፡)
መጪዎቹ በዓላት ይመቿችሁማ!
ብቻ እንደ ማሸላ አይነት ‘የሚቀላቀሉ’ ነገሮች አንሰው ንፁህ፣ ያልተነካኩ ነገሮች የሚበዙበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6325 times