Print this page
Saturday, 12 January 2013 09:43

ጭንቀት/ውጥረት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(12 votes)

ስልጣኔ ወለድ ሞት የሚያስከትል የጤና ችግር
ዓለማችን በየጊዜው በምታሳየው የስልጣኔና የቴክኖሎጂ ዕድገት ልክ የጭንቀት/ውጥረት ችግሮችም በየጊዜው እያደጉና እየተስፋፉ መሄዳቸው፣ ስልጣኔ ለጭንቀት/ውጥረት ችግሮች መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በ2009 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ በዓለም ላይ 38 በመቶ የሚጠጋ ህዝብ በጭንቀት/በውጥረት ችግሮች የተጠቃ ነው፡፡ ከመጠን ያላለፈ ውጥረት የተለያዩ የዕለት ተዕለት ሥራዎቻችንን በሃላፊነት ለማከናወን እንድንችል ያደርገናል፣ ሰውነታችንን ለማንቃት ወይንም ራሳችንን ለነገሮች ዝግጁ ለማድረግ ይጠቅመናል፣ እንዲሁም ሊገጥመን ከሚችል አደጋ ወይም ችግር ለማምለጥ የሚያስችል ቅድመ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይረዳናል፡፡

ጭንቀትና ውጥረትን በተሻለ መልኩ በተረዳነው ቁጥር ለመቋቋም ያለን አቅም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ጭንቀት/ውጥረት በሽታ የሚሆነው ከግለሰቡ ሁኔታዎችን የመቆጣጠር አቅም በላይ ሲሆን ነው፡፡ ይህ ከቁጥጥር በላይ የሆነ ወይም ሥር የሰደደ ጭንቀትና ውጥረት ከሃሳብና ከስሜት ጋር ለተያያዙ የጤና ቀውሶች በማጋለጥ ለአዕምሮ ጤና መቃወስ ይዳርጋል፡፡ 
ውጥረት በራሱ ችግር ባይፈጥር እንኳን ለተለያዩ በሽታዎች መከሰት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚችልና በህይወታችን ውስጥ አግባብ ያልሆኑ ውሣኔዎችን እንድናሳልፍ በማድረግ ለተመሰቃቀለ ህይወት ይዳርገናል የሚሉት የሥነ ልቡናና የአዕምሮ ህክምና ባለሙያው ዶ/ር የወንደወሰን ታደሰ፤ ጭንቀት እንደበሽታ ተቆጥሮ ተገቢ ህክምና ካላገኘ ሞትንም ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፣ ጭንቀት እንደአንድ የውስጥ ደዌ ወይንም እንደአንድ የውስጥ ጤና ችግሮች መነሻነት ታይቶ ትኩረት ማግኘትና ህክምና መስጠት የተጀመረው እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ወዲህ ነው፡፡
ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ በየጊዜው የተለያዩ ጥናቶችም ተደርገውበታል፡፡ እነዚህ በየጊዜው የተደረጉ ጥናቶችም የጭንቀትና ውጥረት ችግሮች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱና ውስብስብ የጤና ችግሮችንም እያስከተሉ መሆናቸውን አመላካች ናቸው፡፡
እንደጤና ባለሙያው ገለፃ፤ ጭንቀት በግለሰቦች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ችግሩ በተለያዩ ሰዎች ላይ በልዩ ልዩ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፡፡
ይህ ደግሞ በሽታውን በቀላሉ ለመገንዘብና የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ እንዳይቻል ያደርገዋል፡፡
የጭንቀቱ/ውጥረቱ መጠን በግለሰቡ ላይ በሚፈጠረው ችግር ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን ይህም የግለሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያዛባ ወይም ደግሞ ከግለሰቡ የሰውነት አካላት አንዱን ክፍል ብቻ ለይቶ የሚጐዳ ሊሆን ይችላል፡፡
ጭንቀት በተለያዩ ሰዎች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ቢችሉም መገለጫ መንገዳቸው ግን እንደየግለሰቡ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ/ባህርይ ሊለያይ ይችላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጭንቀት/ ውጥረት ሲከሰትባቸው በውስጣቸው መቆጣጠር የማይችሉና ቁጡ የሆኑ ንዴታቸው በፊታቸው ላይ የሚነበብባቸው ሰዎች ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች ለደም ግፊት፣ ለልብ ህመምና ለጨጓራ አልሰር በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ጭንቀታቸውን በውስጣቸው አፍነው መያዝ የሚችሉ አይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ገጽታቸውን ሲመለከቷቸው ፍፁም የተረጋጉና ደስተኛ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡
ይሁን እንጂ ውስጣቸው በጣም የተረበሸና በውጥረት የተሞላ ነው፡፡ ይህ እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ ውስጣዊ ህመምን ይቀሰቅስባቸዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው ለአዕምሮ ጤና መቃወስ የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡ የስነልቡናና የአዕምሮ ሐኪሙ ዶ/ር የወንድወሰን ታደሰ፤ የጭንቀት/የውጥረት ችግሮችን በሦስት ደረጃዎች ይከፋፍሏቸዋል፡፡ ጭንቀቱ/ውጥረቱ ምንም ጉዳት በማያደርስበት ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ይህም ግለሰቡ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ንቁ ሆኖ እንዲተገብራቸው የሚቀሰቅስ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ጭንቀት ይባላል፡፡
ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ ግለሰቡ ጭንቀቱን መቋቋም ከሚችልበት ደረጃ ሳያልፍ የጭንቀቱ መጠን ግን ከቀድሞው ወይም ከመጀመሪያ ደረጃው ከፍ ያለ ሲሆን የሚታይ የጭንቀት ዓይነት ነው፡፡ ግለሰቡ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ጥንቃቄ የተሞላበት ሕይወት መኖር እንደሚገባው አመላካች የማንቂያ ደወል ነው፡፡ ሶስተኛው ደረጃ የጭንቀት ዓይነት ከመቋቋም አቅም በላይ የሆነና በግለሰቡ ላይ የጤና ችግር ማስከተል የሚጀመርበት ደረጃ ሲሆን በዚህ ደረጃ ላይ ያለ ሰው ተገቢ ህክምና ካላደረገና በአኗኗር ዘይቤው ላይ ለውጥ ካላደረገ ችግሩ ለሞት ሊዳረግ ይችላል፡፡ አብዛኛው ህብረተሰብ በአንደኛና በሁለተኛው ደረጃ ላይ በተጠቀሱት የጭንቀት ደረጃዎች ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት የሥነልቡና እና የአዕምሮ ሃኪሙ ዶ/ር የወንድወሰን፤ አብዛኛዎቻችን ችግሩ ጐልቶ ካልወጣና አልጋ ላይ የሚያውል በሽታ እስካላመጣብን ድረስ ችግሩን አምኖ ለመቀበል እንዲሁም የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድና ህክምና ለማድረግ ፍቃደኞች አይደለንም ብለዋል፡፡ በጊዜው መፍትሔ ያገኘ የጭንቀት ችግር በግለሰቡ ላይ የከፋ የጤና ችግር ሳያስከትል ሊወገድ እንደሚችል የሚናገሩት ዶ/ሩ፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የችግሩ ተጠቂ ጉዳዩን በቸልታ በማየት የጭንቀቱ ደረጃ ወደ ሦስተኛውና ከፍተኛ የጤና ችግር ሊያስከትል ወደሚችለው ችግር እንዲያድግ ካደረገው መፍትሄው ከባድ ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡ ሰውነታችን ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የሚያመነጫቸው ያልተመጣጠኑ ኬሚካሎች የሰውነታችን ክፍሎችን የአሠራር ሥርዓት በማዛባት ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለልብ ህመምና ለጨጓራ አልሰር በሽታዎች እንድንጋለጥ ያደርጉናል፡፡ ጭንቀትንና ውጥረትን የመቋቋም አቅማችን ዕድሜን፣ ፆታንና ዘርን በመሳሰሉ ወሳኝ ምክንያቶች ሊለያይ ይችላል፡፡ ጭንቀትን የመቋቋም ብቃት ከዘር ሊወረስ የሚችል መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
አንድ ሰው በጭንቀት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ምልክቶች ዋንኞቹ በፊት ገጽታ ወይንም በሰውነት አካላታችን ላይ የሚታይ ያልተለመደና ለየት ያለ ገጽታ፣ የአተነፋፈስ ስርዓት መቀየር/ቁና ቁና መተንፈስ፣ ጥርስን ማንገጫገጭና የመሳሰሉ በግለሰቡ ላይ በግልጽ ይስተዋሉበታል፡፡ በጭንቀትና ውጥረት ውስጥ ያለው ግለሰብም በራሱ ውስጥ የሚያያቸው ለውጦች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም ቀደም ሲል ያልነበረ የራስ ምታት መከሰት፣ በቂ እንቅልፍ ማጣት፣ በትናንሽ ነገሮች መበሳጨት፣ ቅብጥብጥና ነጭናጫ መሆን፣ ራስን መጣል፣ የምግብ ፍላጐት ማጣት፣ ብቸኝነትን መፈለግና ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ መሥጋት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሥራ ብዛትና የእንቅልፍ ማጣት ለጭንቀት/ውጥረት ችግሮች መባባስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የሚናገሩት ዶ/ር የወንድወሰን፤ ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ የአዕምሮ ጤና እስከማቃወስ ያደርሳል ብለዋል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ሥራና ኃላፊነት፣ ብስጭት፣ ሀዘንና መከፋት በራሳቸው ውጥረትን ፈጣሪዎች እንደሆኑም ዶክተሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠውና በጊዜው እርምጃ ካልተወሰደበት ግለሰቡን ለከፋ የአዕምሮ ጤና መቃወስ ችግርና ለሞት ሊያደርሰው እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡
በጭንቀትና ውጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ ዋንኛ መፍትሔው የአመለካከትና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ማምጣት እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
ከእነዚህ የጭንቀትና ውጥረት ማስወገጃ ዘዴዎች መካከል ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፣ የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ የዕለት ተዕለቱን መተግበር፣ ቅድሚያ የሚገባውን በማስቀደም ነገሮችን በሒደት ከፋፍሎ መሥራት፣ ሲጋራና አልኮል የመሳሰሉ ሱሶችን ማስወገድና በቂ እንቅልፍ ለማግኘት መሞከር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፣ ቋሚ የእረፍት ጊዜ እንዲኖር በማድረግ አዕምሮን ነፃ የሚያደርጉበት ሰዓት መወሰን፣ ሥራዎችን ሌሎች ሰዎችም እንዲሳተፉበት ማከፋፈል፣ ሁሉንም ተግባር እኔ ብቻ ልከውነው አለማለት፣ ምሉዕነትን አለመጠበቅ ወይንም በሥራዎ ላይ የሚያጋጥሙ ጥቃቅን ስህተቶችን አምኖ መቀበል ለጭንቀት ችግሮች እንደመፍትሔ ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ጭንቀትና ውጥረትን ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ ከሚረዱ ህክምናዎች መካከል Rises Medicine (በመድሃኒት መልክ የሚሰጥ ህክምና) አንዱ ሲሆን ይህም በጭንቀቱ ምክንያት የተከሰቱ እንደ ደም ግፊት፣ የልብ ህመምና የጨጓራ አልሰር እንዲሁም የአዕምሮ መታወክ በሽታዎችን በመድሀኒት ማከም ነው፡፡
ሌላው የጭንቀትና ውጥረት በሽታ ህክምና preventive የሚባለውና ታማሚው በአኗኗር ዘይቤው ላይ መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት፣ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት የሚያደርግበት ህክምና ነው፡፡ ይህም ለግለሰቡ ጭንቀት ወይም ውጥረት መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን ለይቶ በማወቅ፣ የመከላከል አቅሙን ማሳደግ ሲሆን ህክምናውም ከመድሃኒት ይልቅ የአካል እንቅስቃሴ፣ ዮጋ ስፖርትና መዝናናትን ያጠቃልላል፡፡ በጭንቀትና ውጥረት ሳቢያ ለከፋ የጤና ችግር፣ ለአዕምሮ መቃወስና ለሞት ከመዳረጋችን በፊት በባለሙያዎች የሚሰጡትን የመፍትሔ እርምጃዎች በመውሰድና በአኗኗራችን ላይ መሠረታዊ ለውጥ በማድረግ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንዲሉ፡፡

Read 17154 times