Saturday, 19 January 2013 12:03

የግርማ በዳዳ አስጨናቂ ጥያቄ "አበበችን ያየ አለ?"

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(4 votes)

 በአጭሩ አይ ኦ ኤም (IOM) እየተባለ የሚጠራው አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተቋቋመው በመላው አለም የሚገኙ ስደተኞችን ለመርዳት ነው፡፡ ይህንን ዋነኛ አላማውን ከግብ ለማድረስም በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ቢሮዎቹን ከፍቶ እንደ አቅሙ ደፋ ቀና ይላል፡ ፡ በየመን የሚገኘው ይሄ የስደተኞች ድርጅት ግን ራሱ ስደተኛ ነው፡፡ በየመን የሚገኙትን ስደተኞች እንደፍላጐቱና እንደ እቅዱ ለመርዳት የሚያስችል የሚያወላዳ የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ አቅም የሌለው፣ የለጋሾችንና የበጐ አድራጊዎችን እጅ አይቶ የሚኖር ምስኪን ድርጅት ነው፡፡ በየመን ከሚገኙት ስደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር የያዙትና በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን የእኛን ሰዎች ለመርዳት የቻለውን ያህል ቢፍጨረጨርም፣ በየቀኑ ለሚጐርፉት አዲስ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እርዳታ ለመስጠት ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት ልክ እንደ ስደተኞቹ ድርጅቱም እርዳታ ለማግኘት ለመሯሯጥ ተገዷል፡፡ ሰንአ ሄዳችሁ ወደ ድርጅቱ ቢሮ ጐራ ብትሉ፣ በእንዴት ያለ ችግር ውስጥ እንዳለና ሠራተኞቹ እነዚያን እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የወደቁ ስደተኛ የእኛን ሰዎች ለመርዳት እየፈለጉ ነገር ግን ካቅማቸው በላይ ሆኖ በስደተኞቹ ብሶትና ምሬት ተማረው አብረዋቸው ሲያዝኑና ሲያነቡ ልትመለከቷቸው ትችላላችሁ፡፡

በየመን የሚገኙትን ስደተኞች ለመርዳት ከሚንቀሳቀሱት በርካታ ድርጅቶች ውስጥ የተሻለ አቅም አላቸው የሚባሉት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ እርዳታ የሚደገፉት የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል እና Mixed Migration Secretariat (MMS) ከነአጋሮቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶችም ቢሆኑ ከአይ ኦ ኤም ጋር ሲወዳደሩ በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ ለማለት እንጂ በየመን የሚገኙ ስደተኞች በተለይ ከሁሉም የሚበዙትና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ነገር ከአቅማቸው በላይ እየሆነባቸው እንደመጣ ሳይደብቁ በግልጽ ይናገራሉ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ቀድሞውኑ አለመጠን የከፋውን የስደተኞች ችግር ይበልጡኑ እንዲከፋና ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ እያስገደዱት ያለው በየቀኑ ወደ የመን የሚጐርፉት በመቶዎች የሚቆጠሩት የእኛው ሰዎች ናቸው፡፡ ሰንአ ከተማ ወደሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል ቢሮ የእንግዶች መቀበያ ክፍል ጐራ ብትሉ፣ የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል ከተባበሩት መንግስታት የስደኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የመስክ ተቆጣጣሪዎች ቡድን ጋር በመሆን ያጠናቀሩት የየመን የስደተኞችን ሁኔታ የሚያስረዳ መረጃ የያዘ ትልቅ የግድግዳ ላይ ቻርት ታገኛላችሁ፡፡

ይህ በግድግዳ ላይ የተሰቀለ ትልቅ የመረጃ ቻርት አንዱ ክፍል፣ ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ ብቻ ሁለት መቶ ሠላሳ ሺ ኢትዮጵያውያን በስደተኝነት ወደ የመን መግባታቸውንና አብዛኞቹም በሠንአ፣ በኤደንና በሀራድህ ከተሞች እንደሚገኙ የሚገልጽ መረጃ ይዟል፡፡ የተወሰነው ክፍል ደግሞ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ውስጥ እጅግ የሚበዙት ምናልባትም ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ወደ የመን የገቡት በህገወጥ መንገድ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሰንአ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል ቢሮ ውስጥ ያገኛችሁትን ይህን ዝርዝር የስደተኞች መረጃ፣ ኤደን ከተማ በሚገኘው የመስክ ቢሮው ውስጥም ታገኙታላችሁ፡፡ የዚህን ድርጅት መረጃ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ ደግሞ፣ ስልሳ ሰባት በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደሚገኙባት ወደ የመን ዋና ከተማ ሰንአ ብቅ ማለትና ሁኔታውን መመልከት አያስፈልጋችሁም፡፡ ኤደን ከተማ በቂያችሁ ናት፡፡ ኤደን ከየመን ታላላቅ ከተሞች ውስጥ ከዋና ከተማዋ ከሠንአ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ትልቋ ከተማ ናት፡፡ የኢትዮጵያን ስደተኞች በመያዝ በኩልም ከሰንአ ቀጥላ ሁለተኛዋ ናት፡፡ ኤደን የየመን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ብቻ ሳትሆን ከፍተኛ የየመን ወጪና ገቢ ንግድ የሚስተናገድባት ትልቅ የወደብ ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡ የኤደን ከተማ ልክ እንደ ሰንአ ሁሉ በውስጧ ሲዘዋወሩ በጥቂት ሜትሮች ርቀት የሚያጋጥሙትን ኢትዮጵያውያንን ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት በየመን ይገኛሉ የተባሉትን ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር ማገናዘብ ይህን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ለዚያውም "ረግቶ - ኗሪ" (Stable population) የሚባሉትን የኤደን ከተማ ኗሪ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማየት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሠንአ ከተማ ቀጥላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ረግቶ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የያዘችው ከተማ ኤደን ስለሆነች ነው፡፡

ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይልቅ እነዚህኞቹ ተለይተው ለምን ረግቶ ነዋሪ ስደተኛ እንደተባሉ ለማወቅ ከፈለጋችሁ ደግሞ የተለየ ጥናትና ምርምር ማድረግ ጨርሶ አያስፈልጋችሁም፡፡ አኗኗራቸውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ እነዚህ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በኤደን ከተማ በተለያየ የተሻለ" ስራ ላይ ተሠማርተው፣ የራሳቸውን ቤተሰብ መስርተውና ልጆች አፍርተው፣ አንዳንዶቹም የራሳቸውን የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋም የተሻለ ጥሪትም ቋጥረውና ተረጋግተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነዚህን የተረጋጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በበርካታ ቁጥር የምታዩባቸውን የኤደንን ዋና ዋና የንግድ አካባቢዎች ለቃችሁ ባሳቲን እየተባለ ወደሚጠራው ሠፈር ስትሄዱ ግን ሁሉም ነገር ይቀየርባችኋል፡፡ በኤደን የሚኖሩ አብዛኞቹ ስደተኞች ታጭቀው የሚገኙት በዚህ የባሳቲን ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወደ የመን የተሰደደ የሚመስላችሁ ወደዚህ ወደ ባሳቲን ሰፈር ስትመጡ ነው፡፡ በባሳቲን ሠፈር ውስጥ እንደ አንዳች ነገር ከሚርመሰመሱት በህገወጥ መንገድ ወደ የመን የገቡ ስደተኞች ውስጥ ቁጥራቸው ከሰማኒያ አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው፡፡ ወደዚህ ሰፈር ስትመጡ መጀመሪያ የሚቀበላችሁ ቋንቋ አረብኛ እንዳይመስላችሁ፡፡ በዚህ ሰፈር ውስጥ መጀመሪያ የሚቀበላችሁ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው፡፡ በኤደን የባሳቲን ሠፈር እንደዚያ ታጭቀው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከቁጥራቸው መብዛት በተጨማሪ ተለይተው የሚታወቁበት ሌላም ነገር አላቸው፡፡ ይኸውም የኑሮአቸው ሁኔታ እጅግ አስከፊ መሆን ነው፡፡

ከእነዚህ ስደኞች ውስጥ አብዛኞቹ የጐዳና ተዳዳሪዎችና የእለት ምግባቸውን ለማግኘት በየአውራ ጐዳናው ላይ ተሠማርተው አላፊ አግዳሚውን ሲለምኑ የሚውሉ ናቸው፡፡ በባሳቲን ሠፈራ አውራ ጐዳና ዳርና በየጥጋጥጉ ላያቸው ላይ የተበጣጠሰ አዳፋ ሸሚዝና ሽርጥ አድርገው የተኙ አስር ስደተኞችን ካገኛችሁ ስምንቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በዚህ ሰፈር ውስጥ አውራ ጐዳና ላይ የሚለምኑ አስር ለማኞችን ካገኛችሁ ደግም ዘጠኙ ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም፡፡ ይህ ወደ ኤደን ጐራ ማለት የቻለ ማንኛውም ሠው፣ በባሳቲን ሰፈር የአንድ ሰአት ጊዜ እንኳን ሳያጠፋ በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችለው ተራ እውነት ነው - መራራ እውነት!! ሌላም አንድ ጉዳይ አለ፡፡ በኤደን ከተማ የሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል የመስክ ቢሮ፣ በኤደን የባሳቲን ሰፈር ውስጥ የሚኖሩትን የኢትዮጵያ ስደተኞች በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ እንዲሠጣችሁ ብትጠይቁት፣ በብርሀን ፍጥነት የስደተኞቹን የጾታ፣ የብሔርና የሀይማኖት ስብጥር በዝርዝር ያቀርብላችኋል፡፡ በዚህ መሠረት ታዲያ በባሳቲን ሰፈር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አብዛኞቹ ወንዶች፣ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች መሆናቸዉን ትረዳላችሁ፡፡ በባሳቲን ሰፈር ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አንዱ የሆነው የጂማ ዞን የሶከሩ ወረዳው ግርማ በዳዳ (ስሙ የተቀየረ) ድንገት በሰፈሩ ስትዘዋወሩ ካያችሁና ፊታችሁ አዲስ ከሆነበት፣ ወደ እናንተ እየሮጠ በመምጣት "አበበቺን ካን አርጌ ጂራ?" እያለ በኦሮምኛ ልባችሁ እስኪወልቅ ይጠይቃችኋል፡፡ (አበበችን ያየ አለ ማለቱ ነው) ግርማ በዳዳ ማነው? እንዴት እዚህ ሰፈር ተገኘ? አበበችስ ምኑ ናት? በሚቀጥለው ሳምንት አሰቃቂውን የግርማን ታሪክ አስነብባችኋለሁ፡፡ ቸር ያገናኘን!!

Read 1841 times Last modified on Saturday, 19 January 2013 12:13