Saturday, 19 January 2013 14:36

“አይ አም ኤ ታክስ ፔየር…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ! እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱና ለነቢዩ መሀመድ የልደት በዓላት በሰላም አደረሳቸሁማ! ስሙኝማ…ይሄ የአገልግሎት አሰጣጥ ነገር ግራ እያጋባ አይመስላችሁም! አንድ ሰሞን እንደዛ ሰዉ ሁሉ 'እንዳልሾረ' አሁን ነገርዬው ሁሉ ባለቤት የሌለው እየመሰለ ነው፡፡ "ደንበኞች አቤቱታ እንዳያቀርቡብኝ…" ብሎ ስጋት እየቀረ ነገርየው "እና ምን ይጠበስ!" እየሆነ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ስሙኝማ…ይሄ ሥራዎች ሁሉ በዘመቻ ወይም እንደ ሰሞኑ 'ኤሌክሽን' ምናምን ሲመጣ ብቻ ትኩረት የመስጠት ነገር…አለ አይደል…ባህል እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ እኔ የምለው…አለቃ ምናምንን ሳይሆን ሥራ የሚከበርበት ዘመን አይናፍቃችሁም! ሳትለምኑ፣ ሳትለማመጡ፣ "እባክህ፣ እንትን መሥሪያ ቤት የምታውቀው ሰው ይኖራል?" ሳትባባሉ ጉዳያችሁ በዘመቻ ሳይሆን በቋሚነት የሚፈጸመበት ዘመን አይናፍቃችሁም! "ከከሰስክ ሁሉም አድመውብህ አበሳሀን ያሳዩሃል…" መባባላችን አክትሞ በ'ኮንፊደንስ' "እየጠየቅሁ ያለሁት የማይገባኝን ሳይሆን መብቴን ነው…" የምንልበት ዘመን አይናፍቃችሁም! ነገሮች ለተወሰኑ ወራት ብልጭ ካሉ በኋላ በዛው ድርግም ብለው የሚጠፉበት የ'እንቁልልጭ' ነገር ቀርቶ ሥራዎች በቋሚነት የሚቀጥሉበት ዘመን አይናፍቃችሁም! መአት ነገር መደርደር ይቻላል፡፡"ሄደህ ክሰስና ምን እንደምታመጣ አያለሁ!" የሚል የበታች ሠራተኛ ድፍረት "ከጀርባው ምን አቃፊ፣ ደጋፊ ቢኖረው ነው!" ያሰኛችኋል፡፡ (ጥያቄ አለን… የድሮዎቹ 'የለውጥ ሀዋርያት' አይነት የሲ.ፒ.ኤ. ፕሳ እና ጽሂ መዝገቦች የማያውቃቸው 'የሥራ ሀላፊነቶች' ያሏቸው ሰዎች አሉ እንዴ! አሀ…እቅጩ ይነገረንና… አለ አይደል… ከእነማን ጋር 'ቦሶቻችንን' ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉር (የራስ ጸጉር ባለበት ቦታ ብቻ የሚሠራ! ቂ…ቂ…ቂ…) ማማት እንደምንችል፣ እነማን ሲመጡ ወሬያችንን ወደ አርሴና ማንቼ 'መለወጥ' እንዳለብን እንወቃ! እና…ይሄ አገልግሎት አሰጣጥ ነገር…አለ አይደል… 'ከርሞ ጥጃ' ነገር እየሆነ ግራ እየገባን ነው፡፡ ሌላው ችግር ምን መሰላችሁ…"ለአለቃህ እነግራለሁ…" "ለበላይ ሄጄ አመለክታለሁ…" ምናምን ማለት እንኳን እየጠፋን ነው፡፡ "ጭራሽ ይዘጉብንና ጭራሽ ስንንከራተት እንኖራለን…" ብለን እንፈራለና! ደግሞም እንዲሀ አይነት ነገር እንክት አድርጎ ይሆናል፡፡ ልጄ… ፈሪ ይኑር፣ ፈሪ ይኑር ቢሻው አተላ መሸከም ይወዳል ትከሻው፣ ምናምን ግጥም ድሮ ቀርቷል፡፡ ልክ ነዋ…መፍራት የወኔ ጉዳይ ሳይሆን የ'ስትራቴጂ' ጉዳይ ነው፡፡ እግረ መንገድ ግን በዚህ ሁሉ መሀል… አለ አይደል… በተሰማሩበት ቦታ የሚፈልግባቸውን አገልግሎት የሚሰጡ መአት ሠራተኞቸ አሉ፡፡ ከኑግ ጋር ሰሊጡን አብሮ መውቀጥ አሪፍ አይደለም፡ ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ሰውየው የሆነ የገንዘብ ተቋም በኃላፊነት ደረጃ የሚሠሩ ነበሩ አሉ፡፡ እናላችሁ… የዛ "ምን ጊዜ ተጩሆ ምን ጊዜ ደረሱ…" የሚባልበት ዘመን ሰው ሆነውላችሁ ዕድሜ ያቺን ስሜት ገና አላበረደውም፡፡ ታዲያማ…አንድ ቀን በሚሠሩበት ቦታ የሆነ ደንበኛ ጭቅጭቅ ቢጤ ይፈጥራል፡፡ እሳቸውም ከቢሯቸው ባላቸው አቅም ሊያግባቡት ይሞክራሉ፡፡ ሰውየው ጉዳዩ ከተጠናቀቀለት በኋላ ሁሉ 'እላፊ‚ ነገሮች መናገር ይቀጥላል፡፡ እና…እንግዲህ 'ሲሉ ሰምተን' የምንላቸው ነገሮች አሉ አይደል… "ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ…" ይልና እሳቸውን እንደ መገፍተር ይሞክራል፡፡ ይሄን ጊዜ "መገን የአራዳ ልጅ እነ ድንጋይ ኳሱ…" ቢጤ ነገር ብልጭ ትልባቸውና "ሰምታይምስ ስታፍ ኢዝ ዘ ኪንግ… " ይሉና በውቤ በረሀ 'አፐር ከት' ይዘርሩታል፡፡ እናላችሁ… በአለቆቻቸው ይጠሩና ምንም ነገር ቢገጥም ለበላይ ማሳወቅ እንጂ በራሳቸው ምንም እርምጃ መውሰድ እንደሌለባቸው ሲነገራቸው ምን አሉ መሰላችሁ… "ደንበኛ ስለመታኝ መልሼ እንድመታው እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ ብዬ ማመልከቻ ላስገባ ነው?" አሉላችሁ፡፡ እናማ…አገልግሎት ሰጪ እንዲህ 'ጭራ እንደሚያስበቅሉ'… ሁሉ እኛ ተገልጋዮችም ቀዩን መስመር የምናልፍበት ጊዜዎች መአት ናቸው፡፡

እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቅርቡ ነው አሉ፡፡ በአንድ ገንዘብ ምናምን በሚሰበስብ መሥሪያ ቤት አንድ ደንበኛና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኛ በሆነ ጉዳይ ሳይግባቡ ቀርተው አንድ ሁለት ይባባላሉ፡፡ ሠራተኛው ይበልጥ ትህትና ነበረው አሉ፡፡ እናማ ሰውየው…አሁንም 'ሲሉ ሰምተን' እንደሚባለው… "አይ አም ኤ ታክስ ፔየር" ("ግብሬን የምከፍል ሰው ነኝ…" የማለት አይነት…) ይልላችኋል፡፡ ይሄኔ ሠራተኛው ምን አለ አለመሰላችሁ… "ታዲያ ምን አባክ ላድርግህ!" ቂ…ቂ…ቂ… ልጄ አገሪቱ የእኛዋ ጦቢያ፣ ሰዎቹም እኛዎቹ ጦቢያኖች ነና! (ኩረጃ የሚሠራው ለ'ቫለንታይን ዴይ' ብቻ ነው እንዴ!) እናላችሁ…የራፕ ምትን ከአንቺ ሆዬ ጋር 'ለመደባለቅ'፣ ካልጠፋ ምትክ ትራንስፎርሜሽን፣ ቢ.ኤስ.ሲ. ምናምን የሚሉ ቃላትን ለመጠቀም፣ ለ'ታንስክ ጊቪንግ ዴይ' ልዩ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራም ለማዘጋጀት… ምናምን እንጂ ለአቅመ "ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ…" "አይ አም ኤ ታክስ ፔየር" ገና የደረስን አይመስልም፡፡ አሀ…እነኚህ ነገሮች ከመብት መከበርና ማስከበር ጋር የተያያዙ ናቸዋ! መብት ለማስከበር መለኪያዎቹ ፈራንካ ወይም ትልቅ የቆዳ ወንበር ወይም የ'እንትና ዘመድነት' የማያስፈግበት ዘመን ይምጣልንማ! እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የፈራንካን ነገር ካነሳን አይቀር፣ የዚህ አገር 'ሀብታምነት' የማሳያ መንገዶች የሚገርሙ እየሆኑ ነው፡፡ የምር…ሀብታምነትን የማሳያ ፉክክሮች…አለ አይደል…አፈ ታሪክ አይነት ሊመስሉ ምንም አልቀራቸው፡፡

አንድ ወዳጄ የነገረኝን ስሙኝማ… እዚሁ ከተማ አንድ ውስኪ ቤት ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… አንዱ ሀብታም የውስኪ ቤቱ ባለቤትየዋ ላይ…የቀረ የአራዳ አባባል ለመጥቀስ… 'ጆፌ ጥሏል'፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ማታ ጓደኞችን ይዞ ሲገባ እሷዬዋን ሌሎች እነ ሬሚ ማርቲንን ምናምን ጠርሙሶች የደረደሩ ሰዎች ከበዋታል፡፡ (ለጣይ ፈንጋይ እንደሚያዝለት ሁሉ ለሀብታምም ሀብታም ያዝለታል መሰለኝ፡፡ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ…ምልክት ቢሰጣት ከአንገት ሰላምታ በላይ ካለችበት ንቅንቅ ስላላለች ይበሽቃል፡፡ ታዲያላችሁ…እሱም ጎርደን ጂን ጠርሙስ ያወርድና ሴትዮዋን ይጠራታል፡፡ ይሄኔ ሴትዮዋ ትመጣለች፡፡ እሱም መጀመሪያ አንዱ ጓደኛውን "የት አገር ነው ያለነው?" አይነት የሦስተኛ ዲቪዥን ጉራ ነገር ጣል ያደርግላችሁና ምን ያደርጋል…ከኪሶቹ የኢትዮዽያ ብር፣ ዶላር፣ ዩሮና ፓውንድ አውጥቶ ይደረድርና ለሴትየዋ ምን ቢላት ጥሩ…"የአገርሽን ገንዘብ መርጠሽ ውሰጂ!" አዎ…እዚቹ ከተማ ውስጥ ነው እንዲሀ አይነት ነገር የሚደረገው! በነገራችን ላይ በመጨረሻ በጨረታው አሸነፈ አሉ፡፡ የገንዘብ ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ…ሰበሰብ ብለው ሳለ ከመሀላቸው አንዱ ምን ይላል… "እዚህ አካባቢ በላስቲክ የታሰረ ብር የጠፋው አለ?" ብሎ ሲጠይቅ አንደኛው ተጣድፎ "እኔ ጠፍቶኛል…" ይላል፡፡

ሰውየው ምን ቢለው ጥሩ ነው… "እንግዲያውስ ብሩ ታስሮበት የነበረውን ላስቲክ አግኝቼልሃለሁ፡፡" ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ የኳሳችን ነገር… አንድዬ ከአጠገባችን አይለየንማ፡፡ (እግረ መንገዴን ሳላነሳ እንዳላልፍ…አንዳንዴ ከሰሞኑ ኳስ ጋር የተያያዙ ዘገባዎችንና ዝግጅቶችን ስንሰማና ስናይ "ይሄ ኳስ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዳይ ብቻ ነው ወይስ ሌላ ነገር አለው?" አይነት ጥያቄዎች ይመጡብን እንደነበር ይመዝገብልንማ! አንዳንዶቻችንም ሲቪያችንን ለማድለቢያ እንደ ምቹ ነገር የቆጠርነው ያስመስልብን እንደነበር ልብ ይባልማ!) እናማ… ልጆቹ የአቅማቸውን ተጫውተው የፈለገ ውጤት ቢመጣ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ማለት ነው፣ አለቀ፡፡ ልኩን ያላለፈና እውነታውን ያገናዘበ በራስ መተማመንም አሪፍ ነው፡፡ (ከሽልማቱ ጋር የአንዳንድ ሰዎቻችን የቃለ መጠይቆች ቋንቋ እየተለወጠ የ'ኦቨርኮንፊደንስ ቃና' ሰማሁ ልበል!) እናማ…የኳስ ነገር የኳስ ነገር ነውና…አለ አይደል… ለእኔ ለአምደኚስት ተብዬው (ቂ…ቂ…ቂ…) በአንደኛ ዙር የመሰናበትም ሆነ ለዋንጫ የመድረስ ዕድሎች እኩል ናቸው፡፡

ልጆቹን የእኛ ጸሎትና የአንድዬ እርዳታ አይለያቸውማ! እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ቬንገር የኢትዮዽያን ስም በሁለት አረፍተ ነገር አንድ ሁለቴ ጠቀሱ ተብሎ እንደ 'ሰበር ዜና' ሲደጋገም የነበረው ነገር ግርም አይላችሁም! እና ምን ይሁን! የኳስ አሰልጣኝ ናቸው፣ ስለ ኳስ ያወራሉ፣ እናም ስለ አፍሪካ ዋንጫ ሲያወሩ እኛም ተሳታፊዎች ስለሆንን ስማችንን መጥቀሳቸው "ከኢትዮዽያ አምስት ተጫዋቾች ለአርሴናል ላስፈርም ነው…" ያሉ ይመሰል ይሄን ያህል ሽፋን ማግኘቱ ግርም ይላል፡፡ በነገራችን ላይ ቬንገር እኛን የጠቀሱበትን 'መንፈስ'…አለ አይደል… 'ቢትዊን ዘ ላይንስ' በሚሉት አይነት ጠለቅ ብሎ ማየቱ ጥሩ ነበር፡፡እናማ…ለአቅመ "ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ…" "አይ አም ኤ ታክስ ፔየር" ያብቃንማ! በድጋሚ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችና ለመላው ሙስሊሞች መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንላችሁማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2958 times