Sunday, 20 January 2013 12:46

28 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል:: አምስቱ የምርጫ ምልክት ወስደዋል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(0 votes)

በመጪው ሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ የአፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ በምርጫው ፍትሃዊነት እና በሌሎች 18 አጀንዳዎች ላይ ሊወያዩ እንደሚገባ በማመን ፒትሽን ተፈራርመው ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ ካስገቡ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች አምስቱ የምርጫ ምልክታቸውን የወሰዱ ሲሆን 28ቱ ፓርቲዎች በቅርቡ ሕዝባዊ ስብሰባ እንደሚጠሩ አስታወቁ፡፡

የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የፓርቲዎች ሰብሳቢ አቶ አሥራት ጣሴ እንደገለፁት፤ ፓርቲዎቹ ጥር 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሦስት በላይ የአዳራሽና የመስክ ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት ያቀዱ ሲሆን ለአዲስ አበባ መስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ፈቃድ ክፍል ደብዳቤ ለማስገባት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን በመቃወም ፒትሽን ከፈረሙት 33 ፓርቲዎች ውስጥ አምስቱ የምርጫ ምልክታቸውን እንደወሰዱ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡ 

፡ የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ግምባር(ኢፍዲሃግ)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት(ኢዲህ)፣ የባህር ወርቅ መስመስ ሕዝቦች ዲሞክራሲ ድርጅት(ባመህዴድ)፣ ዱቤና ደጀኔ ብሄረሰብ ዲሞክራሲያዊ (ዱብዴፓ) የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ(ሲአንፓ) የምርጫ ምልክት መውሰዳቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

“በሲዳማ ዞን ሕዝብ ጥያቄ በምርጫ ለመሳተፍ ተገደናል” ያለው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ በበኩሉ የምርጫ ምልክት ወስዶ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ ቢሆንም በትግል ከ28ቱ ፓርቲዎች ጎን እንደሚሰለፍ ገልጿል፡፡

የ28ቱ ፓርቲዎች ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ “የምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ጥያቄዎች ሳይመልስ ዐዋጁን ጥሶ ሕጋዊም፣ ሞራላዊም፣ ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠንከር ወሳኝነት ያላቸውን ፓርቲዎች በመተው የሚያደርገውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመቃወም ሕዝባዊ ስብሰባ እንጠራለን” ብለዋል፡፡ የሕዝባዊ ስብሰባው ዓላማ ሁለት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስራት፤ አንደኛው የምርጫ ቦርድን ህገወጥ እንቅስቃሴ መቃወም ሌላው በሀገሪቱ በወቅቱ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር መወያየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 ‹‹ምርጫውን እርስዎም ይሞክሩት አናደርገውም፤ ቴክኒካሊ እኛ እየወጣን ነው›› ያሉት አቶ አስራት እንደ “በ2002 ዓ.ም ምርጫ ህብረ ብሄራዊና ብዙ ተከታዮች ያሏቸውን የፓለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ ለማድረግ ቦርድ ከኢህአዴግ ጎን እየሠራ ነው” ብለዋል።

ቀድሞ ሲል በ33ቱ ፓርቲዎች ውስጥ ተካተው ከነበሩት አንዱ የሆነው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ጸሃፊ አቶ ለገሰ ላቃሞ፤ ‹‹የምርጫ ምልክቴ የሆነውን አውራ ዶሮ ከምርጫ ቦርድ የወሰድኩት ሐዋሳን ጨምሮ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄው የክልል ጥያቄ ስለሆነ ሕዝቡ በዚህ ምርጫ ተሳትፎ በምርጫ ካርድ መብቱን ሊያስከብር ስለሚፈልግ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ ምርጫ እንድንገባ ወስኗል›› ብለዋል፡፡ በምርጫ ይሳተፉ እንጂ ከ28ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትግል ጎን እንደሚቆሙ አቶ ለገሰ ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወር በኋላ ለሚደረገው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ 19.5 ሚሊዬን ሕዝብ የምርጫ ካርድ መውሰዱን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

Read 2755 times Last modified on Sunday, 20 January 2013 13:28