Saturday, 26 January 2013 15:03

የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተአምራቶች

Written by  መሐመድ
Rate this item
(79 votes)

ፈጣሪ ከፍጡራኑ ጋር ለመገናኘትና መለኮታዊ ህጉንና መልእክቱን ለማስተላለፍ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልደት ድረስ አንድ መቶ ሃያ አራት ሺህ ነብያት ልኳል፡፡ ታድያ ነብዩ መሐመድ የመጨረሻውና መደምደምያው ነብይ ናቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ ሰ.ዐ.ወ አልተማሩም፡፡ ነገር ግን አላህ መልአኩ ጅብሪል (ገብርኤል) አማካኝነት መለኮታዊውን ዕውቀት በውስጣቸው አስርፀዋል፡፡ ስለ ነብዩ መሐመድ መልካም ስብዕና፣ ጥሩ ጸባይ፣ ፍርድ አዋቂነት፣ ርህራሄና ይቅር ባይነት ብዙ ነገር መግለፅ ቢቻልም የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ እሳቸው የሰሩትን እና ያሳዩትን ተአምራት መግለፅ ብቻ ስለሆነ እሱን አልፈዋለሁ፡፡ ነብዩ መሐመድ የተገኙበት የአረቡ ማህበረሰብ በወቅቱ በከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የነበረ ሲሆን ማህበረሰቡ በባዕድ አምልኮ፣ በስካርና በቁማር የተዘፈቀበት ወቅት ሲሆን ዑመር ኢከኑ ኸጣብ፣ ከባዕድ አምልኮ ወደ እስልምና ከተመለሱ በኋላ የተናገሩትን መጥቀስ በጊዜው የነበረውን እውነታ ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡ “አንድ ነገር ያስቀኛል፡፡ አንድ ነገር ደግሞ ያስለቅሰኛል፡፡ የሚያስለቅሰኝ ከጣፋጭ የተሰራ ጣኦት ይዘን በበረሃ ውስጥ ስንጓዝ ራበንና በላነው፡፡” በማለት ቅድመ ኢስላም የነበረው ማህበረሰብ ለፈጣሪ የነበረውን አመለካከት ሲገልፁ፤ የሚያስለቅስዎትስ ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ፤ “ከጦርነት ስመለስ ሚስቴ ሴት ልጅ ወልዳ ጠበቀችኝ፡፡

እንደ አገሩ ባህል መሰረት ከነህይወቷ መቅበር ነበረብኝ፡፡ ልቀብራት ጉድጓድ ስቆፍር “አባቴ አባቴ” እያለች ጺሜ ላይ የነበረውን አቧራ ታራግፍልኝ ነበር፡፡ እንደዚያ እያለች ቀበርኳት” በማለት ማህበረሰቡ በወቅቱ ለሴት ልጅ የነበረውን አመለካከት ገልጸዋል፡፡ ሴትን እንደንብረት ማየት፣ የአባትን ሚስት መውረስ፣ ሚስትን በቁማር ማስያዝ፣ ሴት ልጅ ስትወለድ ከነህይወቷ መቅበር ቅድመ እስልምና የነበረ የወቅቱ የዘቀጠ አስተሳሰብ ሲሆን በዚህ የጀህልያ (የድንቁርና) ዘመን ነበር፡፡ ነብዩ መሐመድ ነውየተወለዱት፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላኩት ተአምራት ለመስራትና ለማሳየት አልነበረም፡፡ የታላቁንና መለኮታዊውን ሐይል የአላህን ትዕዛዝ ለማስተላለፍ እንጂ፡፡ ይህ ሲባል ግን ምንም ተአምራት አላሳዩም ማለት አይደለም፡፡ ያሳዩዋቸውን ተአምራት ከመዘርዘራችን በፊት ዋናው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተአምራት ለሳቸው የተሰጠው ወይም በጅብሪል አማካኝነት በስርፀት ወደሳቸው የገባው ቁርአን ወይም የአላህ ቃል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አላህ በገለጸላቸው መሰረት የተናገሩት “ሐዲስ” ሲሆን በጊዜው ሊታወቁ ቀርተው ሊታሰቡ የማይችሉትን እውነቶች በአንደበታቸው መናገራቸውና እነዚህን እውነቶች ሳይንስ በቅርቡ ያረጋገጣቸው መሆናቸው ናቸው፡፡ ከነዚህ የቁርአንና የሐዲስ እውነቶች ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡ “እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መሆናችንን አያውቁምን? ህያው የሆነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን፡፡ አያምኑምን? (አል፤ ነንብያ 30) እንግዲህ ይህ የቁርአን አንቀጽ የሚያሳየው ስለ (big bang) ቲዎሪ ሲሆን ከ13.7 ቢሊዮን አመታት በፊት መላው ዩኒቨርስ በአንድ ነጠላ አቶም ውስጥ ታምቆ እንደነበርና በከባድ ፍንዳታ እንደተለያየ ሳይንስ በቅርቡ ደርሶበታል፡፡

እንግዲህ ከ14 አመት በፊት የነበሩ ማንበብና መፃፍ የማይችሉት ነጋዴዉ መሐመድ፤ ይህንን ሳይንሳዊ እውነት እንዴት ሊያውቁት ቻሉ ብለን ስንጠይቅ መልሱ አንድና አንድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አላህ ገልጾላቸው፡፡ ከአቡ ሰላማ በተወራ ሐዲስ መሰረት፤ በእርሳቸውና በተወሰኑ ሰዎች መካከል በአንድ ቁራጭ መሬት ሰበብ ጭቅጭቅ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ ለምዕመናን እና ዓኢሻ (ረ.ዓ) ሲነግሯት፤ “አቡ ሰላማ ሆይ! ከሰዎች ምንም አይነት መሬት ያለ አግባብ እንዳትወስድ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ከአንድ ሰው አንድ ስንዝር መሬት በጉልበቱ ወይም በብልጠት ተጠቅሞ የወሰደ ሰው፤ እስከ ሰባት ምድር ድረስ (በወሰደው መሬት ልክ) በአንገቱ ላይ ይጠመጥምበታል፡፡ ሳሌም አባቱን ጠቅሶ ባወራው ሐዲስ፤ ነብዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ከሰዎች ቁራጭ መሬት በጉልበት (በስልጣን) ያለ አግባብ የወሰደ ሰው በፍርዱ ቀን ሰባት ምድር ድረስ (ውስጥ) ይሰምጣል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሐዲሶች የሚነግሩን አላህ ግፍና ጭቆናን ምን ያህል ከባድ ወንጀል አድርጐ እንዳስቀመጠው ሲሆን ሰባቱ ምድር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፡፡ የሥነ-ምድር (Geology) ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ምድር ከሰባት ክበቦች (Zones) የተሰራች ስትሆን እነርሱም ከውስጣዊው ክፍል ጀምሮ እስከ ውጫዊው ድረስ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡ 1. ጠጣር የሆነው (ታችኛው) ውስጣዊ የምድር ክፍል (Core) ይህ የምድር ክፍል ጠጣር ሲሆን የተሰራውም 90% ከብረትና 9% ከኒኬል ነው፡፡ እንዲሁም ካርቦን ፎስፈረስ ሲልከን ኦክስጂን በድምሩ 1% ብቻ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የክበቡ አጋማሽ (Diameter) በግምት 2402 ኪ.ሜ እንደሆነ ይገመታል፡፡

ይህ ሰባተኛው የምድር ክፍል መሆኑ ነው፡፡ 2. ፈሳሽ የሆነው ላይኛው ውስጣዊ የምድር ክፍል (Core) ይህ ፈሳሽ የሆነው የምድር ክፍል ውስጣዊውንና ጠጣሩን የምድር ክፍል አክቦ የያዘ ሲሆን ውፍረቱ 2275 ኪሜ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ይህ አካል ስድስተኛው የምድር ክፍል ነው፡፡ 3. ዝቅተኛው ማንትል (Lower Mantle) ይኸኛው ጠጣር የሆነና ቀላጭ (Molten) የሆነው የውስጠኛው የመሬት ክፍል (Liquid outer core) የሚያከብብ፣ ውፍረቱ 2215 ኪሜ እንደሆነ የሚገመት አምስተኛው የምድር ክፍል ነው፡፡ 4. መካከለኛው ማንትል (Middle Mantle) ጠጣር የሆነ የመሬት ክፍል ሲሆን ውፍረቱ ወደ 270 ኪሜ እንደሆነ ይታሰባል - አራተኛው የምድር ክፍል፡፡ 5. የላይኛው ማንትል (Upper Mantle) ይህ የመሬት ክበብ ከፊል ቀላጭ (Semi Molten) ሲሆን በአንፃራዊነት ከፍተኛ እምቅታ (Density) ያለው ነው፡፡ ውፍረቱ ከ65-120 ኪሜ ሲሆን ሦስተኛው የምድር ክፍል መሆኑ ነው፡፡ 6. ዝቅተኛው አለታማ የመሬት ክበብ (Lower Rockey Crust) ውፋሬው በደረቅ መሬት የብስ ከ40-60 ኪሜ ሲሆን ባህሮችና ውቅያኖሶች ክፍሎች ከ60-80 ኪ.ሜ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ይህ ክበብ ሁለተኛው የምድር ክፍል ነው፡፡ 7. ላይኛው አለታማ የመሬት ክበብ (Upper Rockey Crust) ውፍረቱ ከ5-8 ኪሜ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሆኖም በባህሮችና በውቅያኖሶች ስር ከሆነው ከ60-80 ኪሜ በአማካይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የላይኛው የመርሰ ምድር ንጣፍ፣ በአብዛኛው ከጥቁር ድንጋይ የተሰራ ሆኖ በላዩ ላይ ወፍራም የአለት ንጣፎች ያሉት አንደኛው የመሬት ክፍል ነው፡፡

እስካሁን ያየነው ትንታኔ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሁለት ሐዲሶች በተለይም ደግሞ በፍርድ ቀን ሰባት ምድር ድረስ ይሰምጣል ከሚለው ጋር እንደሚስማማ ሲሆን በሚከተሉት የቁርአን ምዕራፎች እንዴት እንደሚታገዝ እንመልከት፡፡ “ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን፣ ሰማያትም (እንደዚሁ) አንድ አሸናፊ ለሆነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለፁበትን ቀን (አስታውሱ) “አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፡፡ ከምድርም መሰላቸውን (ፈጥሯል) በመካከላቸው ትእዛዙ ይወርዳል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ቻይ መሆኑን፣ አላህም በነገሩ ሁሉ በእውቀት ያከበበ መሆኑን ታውቁ ዘንድ (ይህንን አሳወቃችሁ፡፡) (አል-ጦለቅ 12) አነስ ኢብን ማሊክ (L.O) እንዳወሩት፤ የመካ ሰዎች ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተአምር እንዲያሳዩዋቸው ጠየቅዋቸው፤ እርሳቸውም ጨረቃ ተገምሳ በሁለት ቦታ እንድትወድቅ በማድረግ አሳዩዋቸው፡፡ በመካከሉም የሂራ ተራራ በግልፅ ይታይ ነበር፡፡ ይህ ሐዲስ በብዙ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች የተረጋገጠ ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ አብደላህ ኢብን ዑመርና አብደላህ ኢብን አበስ እንዲሁም ሌሎች ይገኙበታል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ፕሮፌሰር ዘግሉል አል ነጂር፤ ዌልስ በሚገኘው የከርዲፍ ዩንቨርስቲ የህክምና ፋከልቲ ገለፃ እያደረገ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ መስሊም በሱራ አል ቀመር (በጨረቃ ምዕራፍ) መጀመርያ ላይ ስላለውና ስለጨረቃ መገመስ ስለሚተርከው ጉዳይ ጠየቀው፡፡ ሰውየው የፈለገው ይህ የቁርአን ምዕራፍ የያው ሃሳብ እንደሳይንሳዊ መረጃ ሊወሰድ ይችል እንደሆነና ይህን ክስተት የሚደግፍ ሌላ ሳይንሳዊ መረጃ ይገኝ እንደሆነ እንዲገልፅለት ነበር፡፡ ናሳ የተባለው የአሜሪካ የህዋ ምርምር ማህበር፤ ሰዎችን ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ ሳይንቲስቶች በጨረቃ ላይ የያዩትን ለብዙ ሰዎች ቢገልፁም የሚያምናቸው አላገኙም፡፡ ይህም ጨረቃ ከብዙ አመታት በፊት ለሁለት ተገምሳ የነበረና መልሳ የተገጣጠመች የሚመስሉና የሚያመለክቱ ጠንካራ ማስረጃዎች እንዳሉ ነው፡፡

ኢማም አድዱይለሚ በ”አልፈርድወስ” ኢማም አስሲዩጢ በ”ጀሚዕ አልጀማዋዕ” መፅሐፍታቸው ላይ እንደገለፁት፤ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡፡ “አላህ አራት የተባረኩ ነገሮችን ከሰማይ ወደ መሬት አውርደዋል፡፡ እነርሱም ብረት፣ እሳት፣ ውሃና ጨው ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ይህ ሐዲስ ደካማ ከሚባሉት ሐዲሶች የሚያስመድበው ቢሆንም ታላቅ የሆነ ሳይንሳዊ ሐቅን የያዘ በመሆኑ ወደጐን ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በነበሩበት ጊዜ የነበሩ ሰዎች፤ የእሳት የውሃንና የጨውን ከሰማይ መውረድ ቢገነዘቡም የብረትን ጉዳይ ግን ብዙም አልተረዱትም ማለት ይቻላል፡፡ ሰፋፊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የከዋክብት ህይወት ኡደት (Life cycle) ብዙ እርከኖችን እንደሚያልፍ ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህ ደረጃዎች ከዋክብት በጣም በሚያንቦገቡጉት ጊዜ በሳይንሳዊው አጠራር “Novas” እና “Supernovas” የሚል ሲሆን የክዋክብቱ ውስጣዊ (core) የሚኖረው የሙቀት መጠን በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የእነዚህ ኖቫስ እና ሱፐር ኖቫስ የሚሰኙ የክዋክብት ደረጃዎች ተወርዋሪ ኮከብ የምንላቸው በውስጣቸው የኒኩልየር መዋሃድ ይከናወንባቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው እነዚህ የህዋ አካላት ሙሉ በሙሉ ወደ ብረትነት እስኪቀየሩ ድረስ ነው፡፡ በዚህ ሽግግራዊ ሂደት አጠቃላዩ የከዋክብቱ ሃይልና ጉልበት (Energy) ወደ ፍንዳታ (Explosion) እስኪደርሱ ድረስ እየገፋቸው ሄዶ በመጨረሻም ተፈረካክሰው በመላው ዩኒቨርስ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በእኛም ፕላኔት ምድርም የተለያዩ ተወርዋሪ የጠፈር አካላት (ሙሉ ለሙሉ ብረታማ የሆኑ) ወደ መሬት ከባቢ አየር በሚወድቁበት መንገድ ነው ብረት ወደ መሬት የሚወርደው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ እንግዲህ የቁርአንና የሐዲስ መለኮታዊነት በሳይንስ ሲረጋገጥ ከማያሳየው ከብዙው በጣም በጥቂቱ ሲሆን አንባቢ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ጐግል ዌብሳይት ውስጥ ያሉትን የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ተአምራቶች በተመለከተ የተፃፉትን፡- Splitting of the Moon Food Multiplication Water Multiplication Supplication for Rain Light to guid companions Crying of the stem of the date – palm free Glorification of Allah by the prop het’s heals The expulsion of a liar’s corpse by the earth The speech of the wolf The prophets Night journey to Jerusalem and ascent to the Heavens የሚሉትን ክሊክ አድርገው ቢያዩ የበለጠ መረጃ ለማወቅ እንደሚረዳቸው አምናለሁ፡፡ ምንጭ - ሳይንሳዊ ተአምራት በነብዩ ሐዲሶች

Read 28386 times