Saturday, 26 January 2013 15:06

ያልተገላገሉት ምጥ!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

የእርግዝናዋን መጨረሻ ሣምንታት ያሣለፈችው በጭንቅ ነበር፡፡ የበላችው ምግብ አለመርጋት፣ ከፍተኛ ራስ ምታትና ከባድ የወገብ ህመም በእርግዝና መጠናቀቂያ ሣምንታት አካባቢ የገጠሟትና ለከፍተኛ ሥቃይ የዳረጓት በሽታዎች ነበሩ፡፡ እርግዝናዋን የምትከታተልበት ጤና ጣቢያ ውስጥ ያገኘቻት የጤና ባለሙያ ችግሩ በአብዛኛው በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ችግር መሆኑንና በሒደት እንደሚተዋት ስለነገረቻት፣ ህመሟን ችላ የምትወልድበትን ቀን መጠባበቅ ጀመረች፡ ይህ እርግዝና ከእሷ ፍላጐት ውጪ የተከሰተ በመሆኑ ደስተኛ አልነበረችም፡ቀደም ሲል የወለደቻቸው የስምንት፣ የሰባት፣ የአምስት፣ የሶስትና የአንድ ዓመት ከአራት ወር ዕድሜ ያላቸው ልጆቿ ለእሷ ቤተሰብ ከበቂ በላይ እንደሆኑ ታምናለች፡ ባለቤቷ መርካቶ ውስጥ በአንድ የልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ ተቀጥሮ የሚያገኘው ወርሃዊ ደመወዝ እነዚህን ልጆቿን እንኳን በአግባቡ ለማሣደግ እንዳላስቻላት ታውቃለች፡፡

በየወሩ እየጨመረ የሚሄደው የሸቀጦች ዋጋ ናላዋን ሲያዞራት፤ ከግለሰብ ተከራይተው የሚኖሩባት ሁለት ክፍል ቤት የኪራይ ዋጋ በየሶስት ወሩ እያደገ አቅሟ ከሚቋቋመው በላይ ሆኖባታል፡፡ አራት ወንድሞችና ሶስት እህቶች ያሉት ባለቤቷ፤ የልጆቹን ቁጥር የእሱ ወላጆች ከወለዷቸው ልጆች ቁጥር ማነስ እንደሌለበት በማመኑ፣ የባለቤቱን የወሊድ መከላከያ ልጀምር ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጐታል፡፡ “እያንዳንዱ ልጅ የራሱን እድል ይዞ ነው የሚወለደው” ባይ ነው - ባለቤቷ፡፡ በየዓመቱ ለመስቀል ወላጆቹን ለማየትና በዓሉን ለማክበር ወደ አገሩ ሲሄድ አዳዲስ ልጅ፣ አዳዲስ ፊት ለወላጆቹ ማሣየት ይፈልጋል፡፡ ቢያንስ ባለቤቱ እርጉዝ ሆና ቤተሰቦቹ እንዲያዩዋት ይመኛል፡፡ የባለቤቷ እናት /አማቷ/ ሴት ልጅ ሌጣ ትሆን ዘንድ አይገባም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ሆዷ ገፋ ብሎ ወይም ህፃን እያጠባች ካላዩ “ምነው ሥራ ፈታሽ … የሴት ሆድ እኮ ባዶ አያድርም” ይሏታል፡፡ የእነሱን ቃል ለማክበርና የባለቤቷን ፍላጐት ለማሟላት በዓመት በዓመት የወለደቻቸው አምስት ልጆቿ ለእሷ ከአቅሟ በላይ ናቸው፡፡

አሁን በሆዷ ይዛ ጭንቅ ውስጥ የገባችበት ልጅ ስድስተኛዋ መሆኑን የነገረቻት የጤና ጣቢያ ነርስ፣ የአለምን ችግር አልተረዳችላትም፡፡ “ይበልሽ የራስሽ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ልጅ በዚህ ዕድሜሽ መፈልፈልሽ ምን ይሁን ብለሽ ነው” ብላ ወሽመጧን በጥሳዋለች፡፡ በራሷ ፍላጐትና ምርጫ ያደረገችው ይመስል፡፡ ይህቺው የጤና ባለሙያ አለም ስለቤተሰቦቿ በተለይም ደግሞ ስለባለቤቷ በእሷ የወሊድ መከላከያ መጠቀም አለመጠቀም ላይ ያለውን አቋም የነገረቻትን ሰምታ ባለቤቷን ጠርታ ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልነበረም፡፡ ብቻ ለእርግዝና ክትትል ወደ ጤና ጣቢያው በሄደችባቸው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ሁሉ አለምን ታመናጭቃታለች፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍል ከተማ፣ በተለምዶ አንፎ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለዓመታት የኖረችው አለም፤ ወደዚህ ሠፈር የመጣችው የቤት ኪራይ ዋጋ ቅናሽ በመሆኑ ነበር፡፡ አለም ባንክ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ እሷ ወደምትኖርበት አንፎ ለመሄድ በእግር ከ40-50 ደቂቃ ይወስዳል፡፡ ስድስተኛ ልጇን እርጉዝ የሆነችው አለም፤ አንድ ሌሊት ለዘጠኝ ወራት ሲያስጨንቃት የኖረውን ፅንስ ትገላገል ዘንድ ምጧ መጣ፡፡ በቤቱ ውስጥ ከባለቤቷ፣ ከህፃናት ልጆቿና ለዓይን ህክምና ከገጠር ከመጡት የባለቤቷ እናት ሌላ ማንም አልነበረም፡፡የእናታቸው ድንገተኛ የሌሊት ጩኸት ከእንቅልፋቸው ያባነናቸው ህፃናት፣ ልጆቿ የተኛችበትን አልጋ ከበው በጭንቀት የምትወራጨውን እናታቸውን ያዩዋታል፡፡ አዲሱን የልጅ ልጃቸውን ለማየት የጓጉት የባለቤቷ እናት፤ ሰውነቷ በላብ ተነክሮ እንደእሣት የምትፋጀውን አለም ሆዷን በቫዝሊን ያሻሉ፡፡ ጭንቋ እየበዛ ሲሄድና የሰውነቷ ትኩሣት ሲጨምር ባለቤቷ ተደናገጠ፡፡

ከዚህ በፊት ከወለደቻቸው ልጆቿ መካከል አራቱን በቤት ውስጥ በሠላም ነበር የተገላገለችው፡፡ አምስተኛዋንና ትንሿን ልጇን ብቻ ነበር በኮልፌ ጤና ጣቢያ የተገላገለችው፡፡ ጐረቤቷ የነበሩ ሴቶች ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ለእርግዝና ክትትል ደብቀው ጤና ጣቢያ ወስደዋት ነበር እነዚሁ ሴቶች ህመሟና ጭንቋ ሲበረታ ወደ ሃኪም ዘንድ መሄድ እንዳለባት በመወትወታቸውና የእሷም ፍላጐት መሆኑ ሲበዛበት ባሏ ጤና ጣቢያ እንድትሄድ ፈቅዶ እዚያ ተገላገለች፡፡ ግን ሁሉንም ልጆቿን ስትወልድ እንዲህ እንደ አሁኑ አይነት ድካምና ላብ፣ እንዲሁም ትኩሣት ፈፅሞ አይቶባት አያውቅም፡፡ ባለቤቷ ተጨነቀ፡፡ ዓይኑ እያየ ቤት ውስጥ ከምትሞትበት ወደ ሃኪም ዘንድ ሊወስዳት መሆኑን ለእናቱ ነገራቸው፡፡ ምን ሲደረግ አሉ እናቱ፡፡ እኔ ስምንት ልጅ የወለድኩት ከቤቴ ነው፡፡ ምን ሆና ነው ሃኪም ዘንድ የምትወስዳት? አይደረግም! ብለው ተሟገቱት፡፡ ዓለም በደከመ ዓይኗ ለመነችው፡፡ የሚስቱ የጭንቅ ድረሱልኝ ጩኸት እንዲወስን አደረገው፡፡ ብድግ ብሎ ጐረቤቱ የሆነውን ባለጋሪ ሊቀሰቅሰው ሄደ፡፡ አንፎ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለከተማው እጅግ በቀረበና አለም ባንክ በተባለው ሰፈር አዋሳኝ ቢሆንም ትራንስፖርት የለውም፡፡ አለም ባንክ ከተባለው ሰፈር አንፎ ለመድረስ በ3 ብር የጋሪ ትራንስፖርት መሄድ የግድ ነው፡፡ መንገዱ ወጣ ገባና አስቸጋሪ በመሆኑ እንኳንስ በምጥ ጭንቅ የተያዘች ሴትን ቀርቶ እኔ ነኝ ያለ ጐበዝን ይፈትናል፡፡ ግን አማራጭ የለም፡፡ ጐረቤቷ ባለጋሪ ተጠርቶ መጣ፡፡ አስፋው ሚስቱን ከባለቤቱ ጋር ተጋግዞ ጋሪው ላይ ጫናትና ህፃናት ልጆቹን ለእናቱ አደራ ሰጥቶ ወደጤና ጣቢያው ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፡፡ ከአለም ባንክ ታክሲ ማዞሪያ ማለፍ ያልተፈቀደለት ባለጋሪ፤ እነ ዓለምን ለአንድ የኮንትራት ሚኒባስ አሣልፎ ሰጥቶ ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ ሌሊቱ ወደ ንጋቱ ተቃርቧል፡፡ ከዓለም ባንክ ኮልፌ ጤና ጣቢያ ለመድረስ ለሚኒባሱ 180 ብር ከፍለውታል፡፡ ጤና ጣቢያው ሲደርሱ ዓለም አቅሟም ድምጿም ደክሞ ነበር፡፡ በክሊኒኩ በራፍ ላይ ባገኘው አግዳሚ ወንበር ላይ ዓለምን አስተኝቶ ካርድ ለማውጣት ወደ ካርድ ክፍል ሄደ፡፡ ሠራተኛዋ አልነበረችም፡፡ ለደቂቃዎች ቆሞ ጠበቃት፡፡

ሠራተኛዋ መጥታ ካርድ ወጥቶ አለም ምርመራ ወደሚያደርግላት ሐኪም ዘንድ ለመቅረብ ከአንድ ሰዓት በላይ ጊዜ ወስዶባታል፡፡ የመረመራት ሃኪም ያለችበትን ሁኔታ ሲመለከት ደነገጠ፡፡ የደም ግፊቷ 190/240 ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ዓለም ልጇን በምጥ መገላገል እንደማትችል የተረዳው ሃኪም፤ በኦፕሬሽን መገላገል ትችል ዘንድ ወደ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ሪፈር አላት፡፡ጤና ጣቢያው የራሱ አምቡላንስ ቢኖረውም ዓለምን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ግን አልፈቀደም፡፡ ባለቤቷ በኮንትራት ታክሲ ዓለምን ይዞ ወደ ሆስፒታል በረረ፡፡ በመንገድ ግንባታ ሰበብ የፈራረሱና የተዘጉ መንገዶች፣ የተጨናነቀው የትራፊክ ፍሰት እንደልብ አላስኬድ ያለው ባለታክሲ፤ ጥቁር አንበሣ ሲደርስ ዓለም ትንፋሿ ፈፅሞ ደክሞ ነበር፡፡ በባሏ ሸክም ከታክሲ ላይ ወርዳ ስትሬቸር ላይ የተኛችው ነፍሰ ጡር እና በምጥ ጭንቅ ላይ የነበረችው እናት፤ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ውስጥ ምርመራ ሊያደርግላት በተዘጋጀው ሐኪም ዘንድ ስትደርስ እቅታዋን ዋጠቻት፡፡ እኩለ ሌሊት ላይ የጀመረው የዓለም የምጥ ጭንቅ እኩለ ቀን ከመድረሱ በፊት በሞት ተጠናቀቀ፡፡ አሣዛኟ እና ከ10 ዓመት በታች የሆኑ አምስት ልጆቿን በትና፣ የረባ ህክምና እንኳን ሣታገኝ በሆዷ እስከተሸከመችው ፅንስ ለዘለዓለሙ አንቀላፋች፡፡ የዚህችን አሣዛኝ እናት ታሪክ ያጫወተኝ ባለቤቷ አቶ አስፋው ዘርጋ ነበር፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ያረገዘችውን ፅንስ እንኳን ሣትገላገል በሞት ለተለየችው ባለቤቱ ሞት ምክንያት የሚያደርገው ወደ ሆስፒታል ይዟት ለመሄድ መሞከሩን ነው፡፡ እናቴ ያለችኝን ሰምቼ ቢሆን ኖሮ፣ ሚስቴ እዚሁ ቤቷ በሰላም ትገላገል ነበር፡፡ የእናቴን ቃል ረግጬ ይዣት ሄጄ በመንገድ መንገላታት ለሞት አበቃኋት ባይ ነው፡፡ ሐኪሞቹ ለሚስቱ ሞት መንስኤው ከፍተኛ የደም ግፊት እንደሆነና ገና ምጡ እንደጀመራት ህክምና ብታገኝና በኦፕሬሽን እንድትገላገል ቢደረግ ኖሮ፣ የእሷንም ሆነ የፅንሱን ህይወት ለማትረፍ ይቻል እንደነበር ነግረውታል፡፡

አሁን አስፋው እናታቸውን ያጡ አምስት ልጆችን የማሳደግ ከፍተኛ ሃላፊነት ወድቆበታል፡፡ ከምዕተ አመቱ ግቦች አንዱ የሆነውንና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሚዲያ ያለውን ሚና ለማጐልበት ታስቦ ሰሞኑን በጤና ጠበቃ ሚኒስቴር ለሚዲያ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ በነበረው አውደ ጥናት ላይ እንደተገለፀው፤ በአገራችን በየአመቱ 2.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ያረግዛሉ፡፡ ከእነዚህ ሴቶች መካከል በሰለጠነ ባለሙያ ማለትም በነርስ፣ በአዋላጅ ነርስ፣ በጤና መኮንን ወይም በሀኪም ታግዘው የሚወልዱት 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 90 በመቶ የሚሆኑት ማንም ሳይረዳቸው በቤታቸው የሚወልዱ ናቸው፡፡ በአገራችን ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68 ሴቶች፣ በየሰአቱ ደግሞ 3 ሴቶች ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የአብዛኛው እናቶች ሞት የሚከሰተው በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከ85 በመቶ በላይ ለሚሆነው የእናቶች ሞት ዋንኛ መንስኤዎች የደም መፍሰስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የተራዘመ ምጥ ኢንፌክሽንና ውርጃ ናቸው፡፡ እንደ ጤና ጥበቃው መረጃ መሰረት፤ እያንዳንዱ እርግዝና ለሞት የሚዳርግ ችግር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ይህንን ችግር አስቀድሞ መተንበይ አይቻልም፡፡ ስለዚህም ማንኛዋም ነፍሰ ጡር ሴት ምጥ እንደጀመራት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ወደ ህክምና ተቋማት የሚደርሱት ዘግይተው በመሆኑ ህይወታቸውን መታደግ ሳይቻል ቀርቶ ለሞት ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ነፍሰጡር ሴቶች የራሳቸውንና የህፃኑን ህይወት ከሞት ሊታደግ የሚችል በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎትን እንዳይጠቀሙ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ዋንኞቹ ሦስቱ መዘግየቶች እየተባሉ ይጠቀሳሉ፡፡

የመጀመሪያው መዘግየት ተብሎ የሚጠራው እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ በሰለጠነ ባለሙያ ታግዘው ለመውለድ በጊዜ ውሳኔ ላይ አለመድረስ ነው፡፡ ይህም በገንዘብ እጥረት፣ በባህል ተፅእኖ፣ በግንዛቤ እጥረት ሊከሰት ይችላል፡፡ የፅሁፋችን መነሻ የሆነችው ሴት ታሪክ እንደሚያሳየን፣ ምጡ በጀመራት ጊዜ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለባት ወይስ የለባትም በሚለው ጉዳይ ባለቤቷና የባለቤቷ እናት ሲወዛገቡ ነበር፡፡ በዚህ ውዝግብ ሳቢያም አለም በጊዜ ወደ ጤና ተቋሙ እንዳትሄድ ሆናለች፡፡ ሁለተኛው መዘግየት የሚባለው ደግሞ እናቲቱ ወደ ጤና ተቋሙ እንድትሄድ ከተወሰነ በኋላ ከቤቷ ተነስታ ጤና ተቋሙ እስክትደርስ ድረስ የሚኖረው መዘግየት ነው፡፡ በተለይ በገጠራማውና ትራንስፖርት ፈፅሞ በማይኖርባቸው አካባቢዎች ችግሩ የጐላ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ውስጥም አንዳንድ እናቶች የዚህ ችግር ሰለባ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ የባለታሪካችን አለም ባለቤት ሚስቱ ወደ ጤና ተቋሙ እንድትሄድ ከወሰነ በኋላም ከቤቱ ጤና ጣቢያ ድረስ የሚወስዳት ትራንስፖርት ባለመኖሩ በጋሪና በኮንትራት ታክሲ ሲጉላላና ሲቸገር ቆይቷል፡፡ ይህም ሚስቱ በጊዜ እርዳታ የሚያደርግላት ሃኪም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ ሦስተኛው መዘግየት የምንለው ደግሞ እናቶች ጤና ተቋማት ከደረሱ በኋላ የሚገጥማቸው መዘግየት ነው፡፡ ይህም በባለታሪካችን አለም ላይ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የተለያዩ መሰናክሎችንና እንቅፋቶችን አልፋ ጤና ተቋሙ የደረሰችው አለም፤ የካርድ ክፍል ሠራተኛዋ አልገባችም በሚል ምክንያት ለደቂቃዎች የህክምና እርዳታ ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ይህም አለም በወቅቱ እርዳታ እንዳታገኝና ህይወቷ ለመትረፍ እንዳትችል አድርጓታል፡፡

እነዚህ ሶስት መዘግየቶች በርካታ እናቶችን ያለ አግባብ እንድናጣቸው የሚያደርጉን ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ማንኛዋም ነፍሰ ጡር ሴት በእርግዝና ወቅት ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የእይታ ብዥታ፣ የእጅና የፊት ማበጥ፣ ከፍተኛ የሆድ ህመም፣ የደም መፍሰስ፣ ከምጥ በፊት የሽርት ውሃ መፍሰስና ትኩሳት ካጋጠማት ወይንም ከእነዚህ ምልክቶች አንዱን እንኳን ካየች በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የህክምና እርዳታ ማግኘት ይገባታል፡፡ ምልክቶቹን እያዩ ቸል ማለት ወይንም ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት እንደ አለም ያለ አሳዛኝ ሞትን ያስከትላልና ፈፅሞ ልንዘናጋ አይገባም፡፡ ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ ያለውን ጠቀሜታ አውቆ፣ ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄድ የሚደረገውን ቅስቀሳ ያህል በጤና ተቋማቱ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎትና የባለሙያዎችን ስነ ምግባርም ዞር ብሎ ማየትና መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ማንኛዋም እናት ህይወት ለመስጠት ህይወቷን ማጣት የለባትምና!!

Read 4871 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 15:13