Saturday, 02 February 2013 19:51

መሰልጠንና ማሰልጠን የማይሰለቻቸው አዛውንት!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

በ2005 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ዋዜማ (የከተራ ዕለት) በጃንሜዳ በመብራት መስመር ዝርጋታ ላይ ተሰማርተው ነው ያገኘናቸው፡፡ የ67 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ማስተር ቴክኒሽያን መንግሥቱ ከበደ ለአውሮፕላን ቴክኒሽያንነት ያበቃቸውን ጨምሮ 10 የሚሆኑ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ከመሆናቸውም ባሻገር ተጨማሪ ሙያ ለመማር አሁንም ዝግጁ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከባለታሪኩ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡

ብርሃኑ ሰሙ ማስተር ቴክኒሽያን ካስባልዎት ሙያ እንጀምር … በ1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው የተወለድኩት፡፡ እኔን ጨምሮ ሦስት የወለዱት ወላጆቼን በሞት ሳጣ የተወለድኩበት ሾላ ገበያ አካባቢን በመተው አክስቴ ዘንድ ቀጨኔ መኖር ጀመርኩ፡፡ በመድሐኒዓለም፣ በአምሃ ደስታና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተምሬያለሁ፡፡ የ11ኛ ክፍል ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ደብረ ዘይት አየር ኃይል ተቀጠርኩ፡፡ ወታደራዊ ስልጠናውን በአሥመራ ለስድስት ወራት ተከታትለን ስንጨርስ ወደ ደብረ ዘይት አየር ኃይል በመመለስ ለሦስት ዓመታት የተሽከርካሪዎችና የአውሮፕላን ጥገና ተማርን፡፡ በዚህ ሙያ ለ25 ዓመታት ሳገለግል ደረጃ በደረጃ ዕድገት እያገኘሁ ነው ለማስተር ቴክኒሽያንነት የደረስኩት፡፡ የዕድገት እርከኑ ምን ይመስላል? የመጀመሪያው ዙር ኤፒፒ፣ ጁኒየር፣ ሲኒየር፣ ሊዲንግ ክራፍትማን ይታለፋል፡፡ በመቀጠል በተመሳሳይ ስያሜዎች የቴክኒሽያንነት ማዕረግ ይሰጣል፡፡ ማስተር ቴክኒሽያን የአንድ ዓመት ልዩ ስልጠና ከተወሰደ በኋላ የሚሰጥ የመጨረሻው ማዕረግ ነው፡፡ ተግባራዊ ሥራዎቹስ ምን ነበሩ? ካምቦራ በሚባልና ከእንግሊዝ በመጣ አውሮፕላን ላይ ነው በሙያዬ መሥራት የጀመርኩት፡፡ ለተለያየ ሥራ በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ብዙ ቦታዎች ሄጃለሁ፡፡ በዚሁ ሥራና ኃላፊነት በ1969 ዓ.ም በተከሰተው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ከተሳተፈው ቡድን ጋር ነበርኩ፡፡ ሚግ አውሮፕላን ለማምጣት ወደ ራሽያም ሄጃለሁ፡፡ ከአገር ውጭ የት የት ሄደዋል? እንግሊዝ፣ ራሽያ፣ አሜሪካንና የመን ሄጃለሁ፡፡ በአየር ኃይል ለ25 ዓመታት ሲያገለግሉ ደሞዝዎ ስንት ደርሶ ነበር? መጨረሻ ላይ 720 ብር ደርሶ ነበር ለቤት ተብሎ ተጨማሪ 100 ብር ይሰጠኝ ነበር፡፡ የብር የመግዛት አቅም እንዳሁኑ ስላልወደቀ ደሞዜ በወቅቱ ብዙ የሚባል ነው፡፡ በዚህ ደሞዝ ቤተሰቤን እያስተዳደርኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በዩኒቨርስቲው ለ4 ዓመት ያህል የአካውንቲንግ ትምህርት ተከታትያለሁ፡፡ ከመደበኛ ሥራዬ ጎን ለጐን በደብረዘይት ከተማ የሚገኙ ሕፃናትን ሰብስቤ እግር ኳስ በማሰልጠን ለውድድር ደርሰውልኝ የወረዳው ሻምፒዮና ሆነዋል፡፡ የሕፃናቱ ቡድን አውራሪስ የሚባል መጠሪያ ነበረው፡፡ እግር ኳስ ለማሰልጠን የሚያበቃ ስልጠና ወስደው ነው ወይስ በፍላጎት ነበር የሚያሰለጥኑት? ተማሪ እያለሁ እንደማንኛውም ልጅ እግር ኳስ መጫወት ያስደስተኝ ነበር፡፡ ለተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በሩጫ ውድድር እሳተፍ ነበር። በአየር ኃይል ተቀጥሬ መሥራት ከጀመርኩ በኋላም በተመሳሳይ መልኩ የስፖርት ተሳትፎዬ ስለ ቀጠለ፣ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚሰጡ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ በእግር ኳስ እስከ ፌደራል ዳኝነት ያደገ የ18 ዓመት አገልግሎት ሰጥቻለሁ። በፌዴሬሽኑ የተሰጠውን የወጌሻነት ስልጠናም ተከታትዬ አጠናቅቄያለሁ፡፡ ከደብረ ዘይት ውጭስ የእግር ኳስ ስልጠናን የት የት ሰጥተዋል? አቶ ሸዋንግዛው አጎናፍር የሚባልና የቀድም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የነበረ ከሚኖርበት አሜሪካ መጥቶ፣ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ የእግር ኳስ ቡድን ሲመሰርት፣ በምክትል አሰልጣኝና በወጌሻነት ሰርቻለሁ፡፡ የየካ ክፍለ ከተማና የ”ትውልድህን አገልግል” የእግር ኳስ ክለቦችንም በተመሳሳይ መልኩ አገልግያለሁ፡፡ በአዋሬ አካባቢ የሚንቀሳቀስ “ሻላ” የሚል መጠሪያ የነበረው የእግር ኳስ ክለብንም አሰለጥን ነበር፡፡ የአዲስ ኮሌጅ ክለብንም አሰልጥኛለሁ፡፡ ተመሳሳይ አገልግሎት የሰጠሁባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነሱን መዘርዘሩ እንዳያሰለች … ከአየር ኃይል በጡረታ ሲገለሉ በቀጥታ ወደ ስፖርት ነው የገቡት? አይደለም፡፡ በመጀመሪያ በግንባታ ሥራ ተቋራጮች ዘንድ በመቀጠር በተቆጣጣሪነት ሰርቻለሁ። በመቀጠል በአንድ ጋራዥ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ሳሪስ አካባቢ ቤት ተከራይቼ ምግብ ቤት ከፍቼ ነበር፡፡ ከስድስት ወር በኋላ አከራዮቼ ቤቱን እንፈልገዋለን ሲሉኝ በፈረንሳይ ለጋሲዮን በተመሳሳይ ዘርፍ ለመስራት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ጡረታ ሲወጡ እንደ አበቃላቸው አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ እኔ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን ከመሞከሬም ባሻገር ብዙ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ ያለኝን ተሳትፎም እያሳደግሁ ነው የመጣሁት። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ የባህል ስፖርት ውድድር ሲኖር በዳኝነት አገለግላለሁ፡፡ በቅርቡ የወሰዷቸው ስልጠናዎች ምንድን ናቸው? በ1998 ዓ.ም ግንበኝነትን ተማርኩ በ1999 ዓ.ም የአናጢነት ስልጠና ወሰድኩ፡፡ በ2002 ዓ.ም ኤሌክትሪሲቲ ተምሬ አጠናቀቅኩ፡፡ በ2004 ዓ.ም የቧንቧ ጥርስ አወጣጥ ዘዴን በመማር በብረታ ብረት ሥራ ውስጥ የነበረብኝን ጉድለት አሟላሁ፡፡ በሰለጠኑባቸው ሁሉም ሙያዎች አገልግሎት ይሰጣሉ? የሰው አቅም ውስን ስለሆነ በማውቀው በሁሉም ሙያዎች ላይ ልሳተፍ ብልም አልችልም፡፡ መምረጥ ስለነበረብኝ አሁን በኤሌክትሪክና በቧንቧ ሥራዎችና በባህል ስፖርቶች ዳኝነት ላይ ትኩረት አድርጌ እየሰራሁ ሲሆን በተጨማሪም የሕፃናት ታዳጊዎችና ወጣቶች በሦስት የተከፈለ ምድብ ያለው የእግር ኳስ ምድብ አቋቁሜ በማሰልጠን ላይ እገኛለሁ፡፡ “የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ እግር ኳስ ክለብ” ተብሎ የሚጠራው ስብስብ በተለይ የወጣቶቹ ቡድን ለአዲስ አበባ ሻምፒዮን ተመዝግቦ በመወዳደር ላይ ይገኛል። በክለቡ ኮሚቴ አባልነት የሚሰሩ አባላት በየወሩ አንድ መቶ ብር ያዋጣሉ፡፡ ለአዲስ አበባ ውድድር ለመመዝገብ የተጠየቅነውን 5ሺህ ብር የአካባቢው ሕብረተሰብና የልጆቹ ወላጆች ናቸው አዋጥተው የሰጡን፡፡ ከእግር ኳስ ጋር በተያያዘ እርስዎ በእነማን ሰልጥነዋል? በእርስዎ ሰልጥኖስ ታዋቂ የሆነ ማን አለ? ከቀዳሚዎቹ በመንግሥቱ ወርቁ፣ ከአሁኖቹ ደግሞ በሰውነት ቢሻው ሰልጥኛለሁ፡፡ ከእኔ ሰልጣኞች መሐል የአየር ኃይል የበረኛ አሰልጣኝ የሆነው ቅጣው ሙሉ አንዱና ለውጤታማነት የበቃ ነው፡፡ ቤተሰብ መስርተዋል? ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ ሁለቱም ልጆቼ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ሥራ ይዘዋል፡፡ ልጆቼ ተቀምጠህ እረፍት ውሰድ ሲሉኝ፤ “ብቀመጥ እጎዳባችኋለሁ ብሰራ ግን እበረታለሁ” ስላልኳቸው ሀሳቤን ተቀብለውታል፡፡ እኔ ተስፋ መቁረጥ የሚባለውን ነገር አላውቀውም፡፡ ወጣቶችም ተስፋ ሳይቆርጡ በየጊዜው ዕውቀትና ችሎታቸውን ለማሳደግ መልፋት አለባቸው የሚል መልዕክቴ በዚህ አጋጣሚ ይድረስልኝ፡፡ ማንም ሰው ራሱን ማሳመን ከቻለ መሥራት የማይችለው ነገር የለም። ሰው ያጣውን ሳይሆን ያለውን ነገር ማየት ከቻለ ለስኬት የሚያበቃው መንደርደሪያ ላይ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ከተንደረደርን ደግሞ ፈጥነንም ይሁን ዘግይተን ያለምነው ግብ ላይ መድረሳችን አይቀርም፡፡

Read 2273 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 17:11