Saturday, 02 February 2013 13:09

አልተዋሸም አልልም!

Written by  ጤርጢዮስ ከቫቲካን
Rate this item
(1 Vote)

በዘንድሮ የገና በዓል ዋዜማ በወጣችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ታህሣሥ የበርካታ አማልክት የልደት ቀን” በሚል ርዕስ በተፃፈው ፅሁፍ ሀቀኝነት ላይ የነበረኝን ጥርጣሬ ለመግፈፍ “ጌታዬና አምላኬ” እያልኩ የማመልከው የኢየሱስ ታሪክ ፀሀፊው በስምና በአገር ለይተው ከጠቀሷቸው ሌሎች አማልክት ታሪክ ጋር እንዲያ ሆኖ የተመሳሰለበትን “ተአምር” ስላገኙበት ምንጭ ጥቆማ ይሰጡኝ ዘንድ ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ እኔ ባለኝ መፅሀፍ ቅዱሳዊ መረጃ መሠረት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ማንነትም ሆነ የ “ሰውነት” ታሪክ የእርሱና የእርሱ ብቻ የሆነ ወጥነት (Originality) ያለው ክስተት መሆኑን አምኜ ብቀበልም፣ በተገቢ ምክንያትም አምናለሁና የነገሩን ተዓማኒነት ለማጣራት ስለሁኔታው መጠየቄም ልክ ነበር፡፡ ሆኖም በሳምንቱ ምላሹን ያገኘሁት ስማቸውን ሳይጠቅሱ ስለ አማልክቱ ዓለም የልደትና ሞት መኮራረጅ ከፃፉልን ሰው ሳይሆን ከዶክተር ፈቃዱ አየለ “ለምን ይዋሻል?” ርዕስ ሥር ነው፡፡ ዶክተሩ በተለይ ኢየሱስን በልደት፣ በጥምቀት፣ በተአምራትና በሠይጣን አልፎ በመሠጠት፣ መስቀል ላይ በመሞት፣ ሞቶ በመነሣት ወ.ዘ.ተ ይመስለዋል ስለተባለው የግብፁ ሆረስ ከድንግል አለመወለድ የፈለፈሏቸው የዚያው ሠፈር ታሪኮች እኒያ ስም የለሽ ፀሀፊ “ዋሽተውናል” ለማለት ታሪካዊ መንደርደሪያ ስለሆነኝ መደሰቴን መሸሸግ አልችልም፡፡ ግና የቀሩትን “ተመሳስሎዎች” ምንነት ለማወቅ የዶክተሩን የ“ሳምንት ጠብቁኝ” ቀጠሮ ታግሦ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡

ለነገሩ ጊዜው እንደ ጄት ይሮጣልና እነሆ ሌላው ቅዳሜ ደርሦ የዶክተሩን ቀጣይ ፅሁፍ ለማንበብ ጓጉቼ አዲስ አድማስን ገለጥ፣ ገለጥ ሳደርግ እኚያ “ስም የለሽ” ያልኳቸው ፀሀፊ “ቶማስ ሀ” ከተሰኘ መጠሪያቸው ጋር “ሃይማኖታዊ ትረካዎች በአማልክት ልደት ብቻ ሣይሆን በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ” የሚል ሽንጠ ረዥም ርዕስ ያለው የመከላከያ ፅሁፍ ይዘው መምጣታቸውን ተመለከትኩ፡፡ ደግሞ ገለጥ-ገለጥ አድርጌ “ለምን ይዋሻል?” (ቁጥር ሁለት) መኖር አለመኖሩንም አረጋገጥኩ፡፡ ከርዕስ አመራረጣቸው አንፃር ቶማስ፣ ለዶ/ር ፈቃዱ የ “ለምን ይዋሻል?” ርዕሰ ጉዳይ በቂ መልስ ለመስጠት የሚችሉበት የታሪክ አቅም እንዳላቸው አስመስለዋልና ምን ዓይነት ማጠናከሪያ አግኝተው እንደሆነ ለማወቅ ቀድሜ ያነበብኩት የእርሳቸውን ፅሁፍ ነው፡፡ ይሁንና ቶማስ አስቀድሞ ከነገሩን የተለየ ምንም ይዘው አልመጡም፡፡ እንዲያውም በመጀመሪያው ፅሁፋቸው የኢየሱስ የሆነውን ሁሉ በስም ለጠቀሷቸው ሌሎች አማልክት ሰጥተው በፃፉበት ድፍረት አላገኘኋቸውም፡፡ ከክርክርም ይልቅ ይበጀኛል ያሉት ፈረንጆቹ “Issue divert” የሚሉትን ሆን ብሎ አቅጣጫን የማስለወጥ ዘዴ ነው፡፡

ያም ሆኖ “ሃይማኖታዊ ትረካዎች በአማልክት ልደት ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ” በማለት ያቀረቡት ትንተናም ቢሆን የአንዱን ዘመንና ህዝብ ታሪክ ከሌላው ጋር በመደባለቅ ሣይሆን ከአጠቃላዩ የሰው ልጅ አፈጣጠርና የህይወት ፍለጋ ጋር ተመዛዝኖ ነው መቅረብ ያለበት፡፡ መለኮታዊ መረጃና መጠሪያ ከመሻት አንፃር የግብፃውያኑ መሻት ከዕብራውያኑ የተለየ አለመሆኑም ግልፅ ነው፡፡ ግና የግብፅቹን ኦሲሪስ እና ሆረስ ከዕብራዉያኑ ያህዌና ኢየሱስ የአምላክነት ሁኔታ ጋር አንድ አስመስሎ ማቅረብ ስሙ “አላዋቂነት” ይባላል፡፡ ዕብራዊው ኢየሱስ የግብፃዊው ሆረስ ሙሉ ቅጂ ሊሆን የሚችልበት ተዓምርም በዕድል ስሌትም ሆነ በየትኛውም ሳይንሳዊ ዘዴ ታሪክ መስሎ ቢቀመር “ጤናማ ዓዕምሮ” ላለው ሰው ተዓማኒ ሊሆን አይችልም፡፡ በኢንካርታና በኢንሳይክሎፒዲያ ዕውቅና የተሰጠውም እንኳ ቢሆን “ጤናማ ልብ” ላለው ሰው ትርጉም አይሰጥም፡፡ እንኳን አፈ ታሪክ ራሱ ታሪክም እንኳ በአንዳች ምክንያት ለጥርጣሬ ሊዳረግ እንደሚችል ሳስብ ትዝ ያለኝ አንድ ስሙ የተዘነጋኝ ዝነኛ የታሪክ ፀሀፊ ነው፡፡ በትውስታዬ ቋት ውስጥ ለጊዜው ያገኘሁትም ዝነኛ የታሪክ ፀሀፊነቱና አደረገ የተባለው ነገር ነው፡፡

ይህ ሰው የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆኑ የቆየውን ዘመን ታሪክ ብዙ ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዞ ሲፅፍ-ሲፅፍ-ሲፅፍ ኖረና ድንገት አንድ ቀን እርሱ በሚኖርበት አፓርትመንት ላይ የሚኖር ጎረቤቱ ሞቶ መገኘቱን ተከትሎ ግርግር ሆነ፡፡ እናም ይህ የታሪክ ፀሀፊ ወደ አንዱ ሰው ጠጋ ብሎ ሟች የሞተበትን ምክንያት ጠይቆ መልስ አገኘ፡፡ ትንሽ እልፍ ብሎ የጠየቀው ሰው መልስ ግን ከመጀመሪያው ስለተለየበት ሌላ ሦስተኛ ሰው ጠየቀና ሌላ ሦስተኛ መልስ አገኘ፡፡ አራተኛውም የነገረው የተለየ ነበር፡፡ ይሄንን ተከትሎ ወደዚህ የታሪክ ፀሀፊ ዓዕምሮ የመጣው ነገር ደግሞ ብዙ ዓመታትን የኋሊት ተጉዞ የመረመራቸውን ታሪኮች እውነተኝነት መጠራጠር ነበር፡፡ ተጠራጥሮም ዝም አላለም፡፡ ያለው ይህንን ነው፡፡ “እዚህ አጠገቤ ያለው ጎረቤቴን አሟሟት ለማወቅ ከጠየቅኋቸው አምሥት ሰዎች አምሥት የተለያየ ምላሽ ካገኘሁ የሃምሣ ዓመታት ታሪክማ በጭራሽ …” አለና ለዘመናት የደከመባቸውን ሥራዎቹን አውጥቶ አጋያቸው፡፡ ምንም እንኳ ሳይንሳዊ ዘዴን ተከትሎ የሠራቸው ቢሆኑም አመድ እስኪሆኑ አቃጠላቸው፡፡ እኔ ግን ይህንን ስል ታሪክን፣ ኢንካርታን፣ ኢንሳይክሎፒዲያን መናቄ ይሆን? በፍፁም አይደለም፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ዋጋ እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ አፈ ታሪክም ቢሆን ሆረስ በግብፃውያኑ ዘንድ የአምላክ ልጅ ተብሎ ገድል የተፃፈለት መሆኑንም እያስተባበልኩ አይደለም፡፡ ሆኖም ቶማስ በዘረዘሩልን ሁኔታ ኢየሱስን ቁርጥ የሆረስ ግልባጭ አድርጐ ማቅረብ ስሙ “ዋሾነት” ነው፡፡

እሳቸውም ቢሆኑ ደፍረው አልዋሸሁም አላሉም፡፡ ለየትኛውም ትውልድ ታሪኩ ዋጋ እንዳለው አውቃለሁ፡፡ ሆኖም እንዲህ ባሉ ያልታመኑ አሊያም ቸልተኞች መዳፍ ውስጥ ሲገባ ከልክ በላይ ሊበራረዝ እንደሚችል ማጤን ጥሩ ነው፡፡ ለምሣሌ “የግብፁም ሆረስ እንደ ኢየሱስ ከድንግል ተወልዷል” ብለው የፃፉልን ቶማስ፤ ሆረስ ከድንግል አለመወለዱን ለመግለፅ ዶ/ር ፈቃዱ ከሁለት ሺህ በላይ ቃላት መጠቀማቸውን ሲወቅሱ እንጂ ታሪኩ በገዛ እጃቸው መበረዙን ለመቃወም በቂ ሙግት ሲያቀርቡ አልታዩም፡፡ ዋናውን ጉዳይ ትቶ ፊደል ቆጠራ ውስጥ መግባት የልጅ ሥራ በመሆኑም ያንን ትተው እንደ አዋቂ ላቀበሉን የተሳሳተ መረጃ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባ ነበር፡፡ ስለ ፊደል ቆጠራ ቢነሣ ግን እንደ ቶማስ ለብሽሽቅ ያልሆነ ቁምነገር ትዝ አለኝ፡፡ ታሪክን ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ጥንቃቄን የሚመለከት ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ የመፅሀፍ ቅዱስ መፅሀፍቶች በአደራ ተሰጥተዋቸው የነበሩት እስራኤላውያን፣ ቀዳሚዎቹን ጥቅሎች በጥንቃቄ ያስቀምጧቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው ይገለብጧቸው ነበር፡፡ መፅሀፎቹን የመገልበጡ ሥራ የሚካሄደው በከፍተኛ ጥንቃቄና በጣም በሰለጠኑ ፀሀፍት የነበረ ሲሆን ፀሃፍቱ በመገልበጡ ሂደት ሥራቸው ላይ ስህተቶች እንዳይኖሩ በፅሁፉ ውስጥ ያሉትን ፊደላት ይቆጥሩ ነበር፡፡

እነሆ የቶማስን ሁለተኛ ፅሁፍ አንብቤ ስጨርስ ወደ ዶ/ር ፈቃዱ “ለምን ይዋሻል?” (ቁጥር ሁለት) ተሻገርኩ፡፡ በእርግጥም ቶማስ በብዙ እንደዋሹን አስተዋልኩ፡፡ ምክንያቱም ቶማስ ስለ ግብፁ አምላክ ልጅ ሆረስ የኢየሱስ አምሣያነት የሰጡን የተሳሳተ መረጃ ሆረስ ከድንግል አለመወለዱን የሚመለከት ብቻ አልነበረም፡፡ ዶክተሩ ከዘረዘሯቸው የሙግት ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ የሆረስ ልደት ዲሴምበር ከመሆኑ ይልቅ በግብፃውያኑ የወር አቆጣጠር “እሆያክ” ከተሰላ በፈረንጆቹ ኖቨምበር ነው፡፡ በየትኛውም የሆረስ ታሪክ ውስጥ ሆረስ በተወለደ ጊዜ በምሥራቅም ይሁን በምዕራብ የታየ ኮከብ የለም፡፡ ስጦታ አበረከቱለት የተባሉት ሦስት ነገሥታት በሆረስ አፈታሪክ ውስጥ የሉም፡፡ የተወለደው ከድንግል ነው መባሉ ሀሰት ነው፡፡ 12 ተብለው በቁጥር የተለዩ ሃዋርያት አልነበሩትም፡፡ “ሆረስ ተጠመቀ” የሚል የሆረስ ታሪክ ጨርሶ አይገኝም፡፡ በ12 ዓመቱ አስተማረ የተባለው “ህፃኑ ሆረስ” እንኳን አስተማሪ ሊሆን ጭራሹኑ ግብፅን የማስተዳደር ብቃት እስኪላበስ እናቱ ሸሽጋው ነበር፡፡ ቶማስ “ሞቶ ተነሣ” ያሉት ሆረስ፤ በተቃራኒው ከአጎቱ ጋር ሰማኒያ ዓመታት ሙሉ ሲፋለም አንዴም አለመሞቱ፣ አለመሰቀሉና ከሞት አለመነሣቱ በዶ/ር ፈቃዱ ፅሁፍ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ “በመስቀል ተሰቅሎ መሞት፣ ከዛም መቀበር፣ ደግሞ መቃብር ፈንቅሎ መነሳት በእውነተኛው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተከሰተው አንድ ጊዜና በአንድ ሰው ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል፡፡

” የሚል ልብን በእምነት የሚያሞቅ መቋጫም ተበጅቶለታል፡፡ እኔም “አሜን!” ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ በባለፈው ጊዜ ጽሑፌ የቶማስ የአማልክት ቀን ትርክቶች የየሃይማኖቶቹን ጭብጥ ሳይመረምር የአንዱን ነገር ሙሉ በሙሉ ወስዶ ሌላው ላይ የመለጠፍ (Copy - paste) አካሄድ መከተሉንም ሆነ “የፀሐፊው ዓላማ ምን ይሆን” በማለት መገረሜን ጠቆም ያደረግሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይኸውም አምላክ“ የሚለውን ቃል ፍቺ በመወሰን ረገድ ቋንቋው ይለያይ እንደሆነ እንጂ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረና እንቅስቃሴውን የሚመራ፣ አንድ የማይታይ መለኮታዊ ኃይል ያለ መሆኑን በማመን ረገድ በዓለም ላይ የሚገኙ ሁሉም የሃይማኖት ወገኖች ይስማማሉ፡፡ ይሁንና ወደ ዝርዝር ሁኔታው በሚገባበት ጊዜ እያንዳንዱ ሃይማኖት የየራሱ ሃይማኖታዊ መመሪያና የየራሱ ሥነ -መለኮት አለውና ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቶማስ የአፃፃፍ ስልት የተዋሸነውን ትተን የግብፁ ሖረስና ዕብራዊው ኢየሱስ ይመሳሰላሉ በተባሉበት “የአምላክ ልጅነት” አፈ ታሪክና ታሪክ አኳያ እንኳ ብንሄድ ሁለቱ በባህርያቸው የሰማይና የምድር ያህል ርቀት ያላቸው መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ይሁንና በየዘመናቱ የአንዱን ሃይማኖታዊ ትምህርት ከሌላው ጋር በመቀየጥ የሚደሰቱ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፡፡ ለምሣሌ በክርስትና መጀመሪያዎቹ መቶዎች አካባቢ “ግኖስቲክ” የሚባሉ ቡድኖች ተነስተው፣ የክርስትናን መሠረታዊ የእምነት ትምህርቶች በሌሎች እውቀቶች ለመበረዝ ብርቱ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ የዚህ ኑፋቄ ጀማሪዎች “አዋቂ” የሚባለውን የትልቅነት ካባ በላያቸው ለመደረብ ሲሉ “ግኖስቲክ” የሚለውን ስያሜ ለራሳቸው የሰጡት “ግኖሲስ” (ዕውቀት) ከሚለው የግሪክ ቃል በመምዘዝ ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች “መዳን በማወቅ እንጂ በእምነት ዓይደለም” ባዮች በመሆናቸውም ትምህርታቸው “ግኖስቲሲዝም” ይባላል፡፡ መነሻቸውን የክርስትና ሃይማኖት ያድርጉ እንጂ ብዙ አስተምህሯቸው ከግሪክ ፍልስፍናና ከምሥራቃውያኑ የጥንቆላ ልማድ ጋር የተቀየጠ በመሆኑ ምክንያት በቤተክርስቲያን ተቀባይነት ያገኙ አልነበሩም፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሃዋርያትን ስም በመውሰድና በማስመሰል የፃፏቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው “ድብቅ” የሚባሉ አዋልድ መፃሕፍት ነበሯቸው፡፡ ከነዚህም መካከል የማርያም ወንጌል፣ የቶማስ ወንጌል፣ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በነገራችን ላይ ዘመነኛው ዓለም በቸረው ታላቅ ዝና የምናውቀው ዳን ብራውን፤ “ዚ ዳቬንቺ ኮድ” በተሰኘው መጽሐፉም ሆነ በሌሎች መሰል ሥራዎቹ ስሙ የገነነው በተባ ብዕረኝነቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የብራውንን ስም ታላቅ ያደረገውና አንዳች ልዩ ምሥጢር ከምድር ከርስ ውስጥ ፈልፍሎ እንዳገኘ ሰው ተቆጥሮ ብዙዎችን ጉድ…ጉድ…ያስባለው እጅግ ጥንታዊ ቢሆኑም ሃሰተኝነታቸው ከታወቀ የግኖስቲኮች ድርሳናት የቀዳቸውን የፈጠራ ታሪኮች እውነት አስመስሎ በልብ ወለድ መልክ በማቅረቡ ነው፡፡ “ግኖስቲኮች” እንደሆኑ በግልጽ ባይቀመጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኘው፣ ሃዋርያው ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ በሰደደለት ሁለተኛ ደብዳቤው ምዕራፍ 2፥18 ላይ ሄሜኔዎስ እና ፊሊጦስ የተባሉ ሁለት ሰዎችን በስም ጠቅሶ “እነዚህም ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኗል እያሉ ስለ እውነት ስተው የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ” በማለት ጥቆማ ከሰጠው በኋላ፣ እሱ ግን እንዲህ ከመሰለው ለዓለም ከሚመች ከንቱ ልፍለፋ እንዲርቅ መምህሩ ለተማሪው የሰጠውን ምክር ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እኔ እንደ አማኝነቴ እጅግ የላቀ ቦታ በምሰጠው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ያለውን መረጃ ካገኘሁ፣ ጥያቄዬን መልሶልኛል ያልኩት የዶክተር ፈቃዱ አየለ ታሪክን ከአፈታሪክ የመለየት ድንቀኛ ትንታኔ ተጽፎ ባይሆን እንኳ “የአምላክ ልጅነትም ሆነ ሞቶ መነሳት ከአሁን በፊት ሆኗል” ብለው የፃፉትን ቶማስ “ዋሽተውኛል!” ለማለት በቂ የሆነ የእምነት ድፍረት አለኝ፡፡ አበቃሁ!

Read 2138 times