Saturday, 02 February 2013 13:12

የምስስሎሽ ሙቀጫ!

Written by  በዶ/ር ፍቃዱ አየለ ከየተቦን Feke40ayema@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሰንበት ለንባብ በበቃችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለምን ይዋሻል በሚል ርዕስ ለሰነዘርኩት ሃሳብ የመልስ አስተያየት ወጥቶ አነበብኩኝና ለዛሬ መጣጥፌ ምህኛት ሆነኝ፡፡ የዚያ አስተያየት ፀሃፊ ማንነታቸውን በታህሳስ 27 ከፃፉት ሰው ለመለየትም ለመደመርም ባለመፈለጋቸው እኔ ይደመሩ ዘንድ መርጬላቸዋለሁ፡፡ የድምሬ ሰበብ ደግሞ ለምን ይዋሻል ብዬ ለጠየኩት ጥያቄ ገና ጨምረን እንዋሻለን የሚል አንደምታ ባለው ተመሳሳይ ክንፍ መከነፉ ነው፡፡ በአንድ ላባ እንደመብረር ዓይነት፡፡ ታዲያ እኝህ ፀሃፊ ያለፈውን መጣጥፌን ‹‹ቅሽምና›› ለማሳየት አስረግጠው የጨነቋቆሩ ሲሆን ‹‹የተለመደው ጭፍንነቴ›› እምብዛም ያልደነቃቸው ለመምሰል የተጣጣሩት ጥረት በመጣጥፋቸው ውስጥና ውጭ ድምፅ አውጥቶ መጮሁ እንደገረመኝ መደበቅ አልሻም፡፡ ከመጨፈኔ በፊት ማያዪን ማጥራቴ ልብ ይባልልኝማ፡፡ ዳሩ ግን መጨፈን የሚቻለው አይን ሲኖር ብቻ መሆኑን ጠቆም አድርጌ ሊታይ ብቻ ሳይሆን ሊፈጠጥበት የሚገባውን ጉዳይ ላተኩርበት ተነሳሁኝ፡፡ ያለ አይን እንደማይፈጠጥ ሁሉ ያለ ዓይን አይጨፈን አይደል! ያለፈው ሳምንቱ ባለ ጎታታ ርዕስ መጣጥፍ (‹‹ሃይማኖታዊ ትረካዎች በአማልክት ልደት ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ›› የተባለለት) ለምን ይዋሻል ብዬ የመፃፌን መነሻ ሃሳብ ያለ ጥርጥር የደረሰበት እንደሆነ አድርጎ መንደርደሩን ፍሬን አስረግጬ ወጌን ልጀምር፡፡ ለምን ይዋሻል የተፃፈበት ዋና ምክንያት ፀሃፊው ነቄነታቸውን ለማሳየት አሳጥረው እንዳስቀመጡት ሆረስ ከድንግል አለመወለዱን ለማብራራት  ብቻ ሳይሆን ሆረስና ታሪኩ አፈ-ታሪክና ውሸት፣ ኢየሱስና ታሪኩ ታሪክና እውነት መሆናቸውን በጥቂቱ ለማስተጋባት ያክል ነው፣ እንጂ ሆረስ የድንግል ጭልፊት ልጅ መሆኑንማ በጮክታ ማወጄ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ የታህሳሱም የጥሩም ፅሁፎች ደፋ ቀና ማለት ከሞቱ ዘመናት ያለፋቸውን እምነተ-ኑፋቄዎች ማጣቀሻ አድርጎ፣ በሞቱት የአህዛብ አማልክት አፈ-ታሪካዊ ቅብጥርጥሮሽ ውስጥ ለመደበቅ የሚደረግ ታላቅ መፍጨርጨር ውጤት መሆናቸውን ከኮተታኮተቶቻቸው መረዳት ብዙም አይቸግርም፡፡ ለማንኛውም ለእምነቴ ጥብቅና መቆሜ በፀሃፊው ዘንድ እከሌ ከተባለ ሃይማኖት ጳጳስ ይልቅ በልጦ መጦዙ ‹‹የአላማዬን ግብ መምታት ያሳየልኝ ሃቅ ነው›› እያልኩ ጡዘቱን በደስታ መቀበሌን ያለመሳቀቅ አበስራለሁ፡፡ ዳሩ ግን የእነ ሆረስን ታሪክ የእውነተኛው ታሪክ ምንጭ ለማድረግ የሞከረ ማመን ያቃተው ጳጳስ ካለ የምተማመንበትን ‹‹የመንፈስ ሰይፍ›› በተባለው ጳጳስ ላይም መምዘዜ መጠርጠር የለበትም፡፡ ያ ሰይፍ ደግሞ የእግዚአብሄር ቃል ይባላል፣ እሱም እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መላእክት ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን ይላል፣ እንኳንስ ጳጳስ ይቅርና፡፡ ስለዚህ ያመንኩትን ያመንኩት የሆነ ጳጳስ ወይም የሆነ ፓስተር ወይም የሆነ ቄስ ስላመነልኝ አይደለም፡፡ ‹‹ያመንኩትን አውቃለሁ›› ተብሎ እንደተፃፈው እንዲያ ሆኖልኝ እንጂ፡፡ የሚያምነውን የማያውቅ ጳጳስ ካለ ጵጵስናው ከእጅ ወደ አፍ መሆኑን ለራሱ ለጳጳሱና እንዲህ አይነት ጳጳሶችን ማጣቀሻ ለሚያደርጉ ሁሉ እግረ መንገዴን መልክት ባስተላልፍላቸው ቅር መሰኘት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለማንኛውም ‹‹ከሆረስም፣ ከሚትራም፣ ደግሞ ቁጥራቸው የትየለሌ ከሆኑ በእየቀኑ እየሞቱ ከሚነሱ፣ ሞት መጫወቻ ካደረጋቸው ጥንተ-አማልክት ጋር ከቶ ሊወዳደር የማይገባው አምላክ አለ ብዬ›› ጳጳስም ይሁን፣ ተጨባጫዊም ይሁን፣ ከሃዲም ይሁን ካሻው ደግሞ ምንምየለማዊ ይሁን ለሁሉም በልክ በልኩ የተሰፈረለትን የእውነት ማስተሰሪያ መሰንዘሬ አይቀሬ ነው፡፡ የጥብቅናዬ እውነትነት መሰረቱ የማይሻረው ቃል ነውና፡፡‹‹ሰማይና ምድር ያልፋሉ የእግዚአብሄር ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል›› ተብሎ ተጽፏል እኮ፡፡ ቃሉ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ከመደብዘዝ ይልቅ እየደመቀ መፍካካቱ የዘላለማዊነቱ ማሳያ ፍንጭ ነው፡፡ እንግዲህ በስመ ልደቱ የመዋሸቱ መዘዝ የብዕር ሰበቃው ሰበብ መሆኑ ግልፅ የሆነ ቢሆንም የቅጥፈቱ ስፋት ዘርፈ ጀርጋጋነት በአመሳሳዮቹ በኩራት እየተለፈፈ ነው ፡፡ እናም መመሳሰሉ በአማልክት ልደት ብቻ የማያበቃ እንደሆነ በረዥሙ ተለግቶ አነበብን፡፡ እያንዳንዱን ቅጥፈት መዳሰሱ እጅግ ውድነቱን ከቀን ቀን እያናረ የሚሄደውን ጊዜ ማራከስ ይሆናል ብዬ ስለደመደምኩ የ “copy cat ” (ነገረ-ኩረጃ) አራማጆች ለምን ይሄን ምስስሎሽ ያለልክ እንደሚያንቋልጡት በአጭሩ መዘከር አዋጭነቱ ስለታየኝ ነገሬን በዛ ላይ አተኮርኩ፡፡ስለዚህ የተጽፏል ማጣቀሻ መዘዛዬ ከታላቁ ቃል ይሆን ዘንድ መረጥኩኝ ፡፡ ጊዜ ሲፈቅድ ደግሞ ኮተታ ኮተቱን ላንኳትተው እችል ይሆናል፡፡ የብዙ እምነት አልባውያንን መሰረት እየነቀነቀ ለማያቋርጥ ንጭንጭ የሚዳርገው ይሄ ክርስትና የተባለ የእኔ እምነት፣ ከየአቅጣጫው ‹‹አለን›› ከሚሉትም ፣ከየመቃብሩ ‹‹ጠፉ›› ከተባሉትም የእምነት አይነቶች የሃሰትም የእውነትም ክስና እርግማና ሲወርድበት ይሄው ሁለት ሺህ አመታትን ጠረማምሶ በስፍራው እንደተሰየመ ገኖ ይታያል፡፡ ለዚህ በምክንያት ደርዳሪው ልክ ምክንያቶቹም አእላፋት ናቸው፡፡ የነገሬ ትኩረት ግን ከክርስትና በፊትም ከክርስትና በኋላም እየተነሱ የወደቁ ብዙ ሙታን-እምነቶች ለክርስትና በህይወት መቆየት መሰረት የመደረጋቸው ሸፍጥ ላይ ይሆናል፡፡ ረዣዥም እድሜ አላቸው የሚባሉ ዛሬም ድረስ ተከታዮች ያላጡ እምነቶች እንዳሉ ቢታወቅም፣ በእምነት አልባውያን መንደር የማያቋርጥ የህሊና ጥዝጣዜ ሰበብና የጥያቄ ምንጭ ሆኖ የሚያስጨንቅ የእምነት አይነት ግን በክርስቶስ ላይ የተመሰረተው ክርስትና ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ክርስትና በዋናነት በመምህሩና በትምህርቱ ላይ እንጂ በተከታዮቹና ትምህርቱን በአስፋፉት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ የሆነው ክርስቶስን … ›› ተብሎ እንደተጻፈው ማለት ነው፡፡ እሱ የልዩነቴ መጀመሪያም መጨረሻም ነው፡፡ ክርስትና ሊመረምረውና እውነቱን ሊፈልግ በአጭር ታጥቆ ለተነሳ ሁሉ ራሱን ክፍት ያደረገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን መርምሬአለሁ ያለ ሁሉ ለሚደርስበት ድምዳሜ ተጠያቂው መርምሬአለሁ ባዩ እንዲሆን ነገርን ያመቻቸ ትልቅ የህይወት ትምህርት ነው፡፡ ስለሆነም ከመፅሃፉ በእምነት እውነትን የቀሰመ ሁሉ ስለ ክርስትና የተባለው ቢባል የተባለውን አባባል ልክነትና ልክ-አልባነት በራሱ መረዳት መጠን በቀሰመው የእውነት ክፋይ ልክ ያብራራል እንጂ እንዲህና እንዲያ ተብያለሁና ከማይዝግ ብረት የተሰራ ሰይፌን ሳሉልኝየሚልበት የእምነት አይነት አይደለም፡፡ ክርስትናን በዚህ ስነ-እንቅስቃሴያዊ በሆነ ነፍስና መንፈስ ላይ ባላተኮረ ወራዳ አካሄድ ለማስዋጥ የተደረገ ታሪክ ሁሉ ትክክለኛውን ክርስትና እንደማይገልጥ፣ ከጵጵስና በላይ ክብደት በተሰጠው ጥብቅናዬ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ጵጵስናም ይሁን ‹‹ፕስትርና›› ያለ ክርስቶስ ክርስትና አይደለም፡፡ ይህ የክርስትና ትምህርት ለመፈተን፣ ለመመርመር፣ ለመተቸት፣ ለመታመን እና ደግሞ ላለመታመን ክፍት የመሆኑ ምስጢር በእምነት አልባውያን ዘንድ የህሊና መናወዝን መዘዝ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ አለማመን መብት የመሆኑን ያህል ማመን ደግሞ ከዛ የላቀ መብት መሆኑ የሚያንገበግበው እምነት አልባ ከሃዲ፣ እንደዚህ አይነቱን እምነት በመወረፍ የውስጥን ትግል ለማስታገስ መሞከሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህኛውም እምነት ተሳቦ ለሰው ልጅ የመመርመር፣ የመፈተንና ብሎም የመሄስ፣ የመወረፍ ባስ ሲልም የመዝለፍ የነፃ-ፈቃድ ባህሪ ስፍራ የማይሰጡ የእምነት አይነቶችን በዚሁ እምነት በኩል ለመድረስ መሞከር የተለመደ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የተመሳስሏቸው ቁርርታው አንዱ ሰበብም እሱ ነው፣ የተልባን ጫጫታ በምስስሎሽ ሙቀጫ ለመደለዝ፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ ሆኖ ሳለ በዘመናት መካከል ከውስጥም ከውጭም በደረሰበት ከፍተኛ ስደት ከመጥፋት ይልቅ እየሰፋ የሚገኘው በክርስቶስ ላይ የተመሰረተው የእምነት አይነት ከሚሰነዘሩበት አሉባልታዎች አንዱ ምስስሎሽ (copycat) ነው፡፡ ምስስሎሹ ባለፈው ሳምንት እንደ ፃፉት ፀሃፊ በልደት በዓሉ ብቻ ሳይሆን ስፍር ቁጥር በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ጭምር መሆኑን የቻሉትን ያህል አዥጎድጉደውታል፡፡ ዋናው ጉዳይ ምስስሎሽን እያነጠሩ አውጥቶ በማሳየት ብቻ የሚያበቃ ሃቅ ሳይሆን ‹‹ የጠፉትም ፣ያሉትም ፣ደግሞ ምንአልባት የሚመጡትም እምነቶች ተመሳሳይነት ስላላቸው ወይ አንዱ ሌላውን ኮርጇል አሊያም ደግሞ አንዱ የሌላው ውጤት ነው፣ ስለዚህ ልዩነት የሌላቸው ከእጅ አይሻል ዶማ ናቸው›› ብሎ የነገር ቁፋሮ ለመቆፈር፣ ከዛም አቅም የፈቀደውን ያህል ድንጋይ ለመፈንቀል ነው፡፡ ፍጻሜውም ‹‹በምስስሎሽ ሙቀጫ›› ወገብ እስኪቀጥን ደፋ ቀና እያሉ ውድ ህይወትን መውቀጥ ነው፡፡ ዓለምን አትርፎ ህይወትን ማጣት የዚህ ዓይነት ወቀጣ ውጤት ነው፡፡ አንዱን እምነት ከሌላው አነፃፅሮ ምስስሎሾቹን በማሳየት ብቻ እፎይ ብሎ እንቅልፍ የተኛ እምነተ ቢስ ወይም ከሃዲ የለም፡፡ የምስስሎሹ ጨዋታ የፍፃሜ ፊሽካው ሁልሽም ያው ነሽ፣ ስለሆነም ከክህደት የማትሻይ አፈ ታሪክ መሆንሽን ማመን ይገባሻል የሚል ግልብ ድምዳሜ ነው፡፡ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በኢንካርታ ውስጥ ገብቶ መንከራተት ወይም በኢንሳይክሎፒዲያ ገጾች መካከል ተወሽቆ ማድፈጥ ብቻውን በቂ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የድምዳሜው ማረግረጊያ ክህደት ነውና፡፡ ክህደት ያለማመን ውጤት እንጂ የንባብ ውጤት አይደለም፡፡ የካደ ለክህደቱ ድንዳኔ ሲል ያነባል ያነበንባል እንጂ ተነቦ የሚያስክድ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ኢንካርታም ኢንሳይክሎፒዲያም እንዲያ ናቸው፡፡ ከተነበበ ግን መነበብ ያለበት እውነትን ፍለጋ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ እውነት በትምህርትም በስብዕናም ከየጥበብ ደጃፉ ትጣራለችና አትታጣም፡፡ ግልጥልጥ ያለችውን እውነት አለማየት እሱ ጨለምተኝነት ማሳረጊያው ቢሆን ለምን ይገርማል፡፡ እንግዲህ ያመነም ያላመነም በውስጡ የሚመላላሱት መሰረታዊ ጥያቄዎች አንድ መሆናቸው መልስን የመሻት ፍላጎቱ አቅጣጫም እንዲመሳሰል ምክንያት ሆኗል፡፡ ታዲያ ይህ መመሳሰል የሰውነት መገለጫ ከመሆን አልፎ እዚህም እዚያም የሚመሳሰሉ ነገሮችን አመንጭተዋልና እከሌ የተባሉት አፈ ታሪኮች ወይም ጥንተ-እምነቶችና እምነተ-ኑፋቄዎች የእከሌ ሃይማኖት መሰረት ናቸው ማለት ከሰውነት ሰፈር በፈቃደኝነት መገለል ነው፡፡ ‹‹የምስስሎሹ›› መረጃው የዚያ ሩቅ ዘመን የድንጋይ ፅሁፍ ፣የመቃብር ፅሁፍ ወዘተ ነው ብሎ ወደ ሙታን መንደር መገስገስም ሙት ምላሽ ከመሆን የዘለለ ሚና አይኖረውም፡፡ የዚህ አይነቱ ስሌት ድምዳሜን ማፋለሱ መጠርጠር የለበትም፡፡ ቺንፓንዚ የተሰኘው ትልቅዬ ጦጣ ሁኔታው ሁሉ የሰው ይመስላል እና ሰውና ቺንፓንዚ ምንጫቸው አንድ ሊሆን ይችላል ብሎ ወናፉን እንደሚያናፍል ዝግመተ ለውጠኛ፣ የሃይማኖት ቅድመ ምስስሎሽ አተካራውም ከዚያው የሚመደብ መሆኑ ብዙ ማመራመር የለበትም፡፡ ስለዚህ ውሃ፣ ሰማይ፣ አፈር ወዘተ የመሳሰሉ ቃላት በየሃይማኖት የፍጥረት አመጣጥ ትረካ ውስጥ ስለተገኙ አንዱ ከአንዱ ብዙም የማይለዩ ናቸው ብሎ መሬት ያልነካ ችካል መቸከል ይቻል ይሆናል፣ ዘለቄታው ግን የእውነት ሽውታ ሽው እስኪልበት ብቻ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አማኙ ከእምነተ ቢሱ ይልቅ እውነትን ለመጨበጥ የተሻለ እድል የሚኖረው፡፡ እምነተ ቢሱ ረዳት የማይሻና ብቁ አድርጎ ራሱን የቆለለ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከልብ ድንዳኔው የሚታደግ አምላክን አጣጥሎ ራሱን አግንኖ በውሸት ውቅያኖስ ብቅ ጥልቅ ይላል፡፡የማያስተውለው ልባቸው ጨለመ ፣ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮዎች ሆኑ ተብሎ እንደተፃፈው ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው የእምነተ ቢሶችና የከሃዲያን እምነት አልባ ደረቅ ምክንያታዊነት ልጓም አልባ ልቅነትን አስከትሎ እኔ ለራሴ አምላክ ነኝ ወደሚል ድምዳሜ የሚዘቅጠው፡፡ ይሄን ድምዳሜ ለማፅናት ህሊናን የሚሸነቁጥ የእምነት ምስጢር ሁሉ በከንቱነት ጡጫ እየተቀጠቀጠ ልክ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ እዚህ ግብ ላይ የመድረሻው አንዱ መንገድ ምክንያታዊ የሚመስል ቅጥፈትን መጋት እና ማስጋት ነው፡፡ በእምነት ላይ ከተቃጡት እንዲህ አይነት አተካራዎች አንዱ ‹‹ምስስሎሽ›› ነው፡፡ይህ ግን ‹‹ በእውሸት እውቀት የተባለ ለዓለም የሚመች ከንቱ መለፍለፍ›› ተብሎ እንደተጻፋው ከመሆን አያመልጥም፡፡በተረፈ በየሃይማኖቱ ያሉትን ምስስሎሾች በየሃይማኖቱ ካሉ ልዩነቶች ይልቅ ማናፈሱ ዋንኛ ሰበብ፣ ክህደት እውቀትን ተመስሎ አናት ላይ መውጣቱ ነው፡፡ ሃይማኖቶች የሚመሳሰል ነገር ባይኖራቸው ኖሮ ሃይማኖት ተብሎ የጋራ ስም ባልወጣላቸው ነበር፡፡ ክህደታዊው ጨለምተኝነት (ጭፍንነት አላልኩም ያለ ዓይን ስለማይጨፈን) መሰረቱ ሁሉን አመሳስሎ በአንድ ጥይት ጭጭ ማድረግ ከመሆኑ የተነሳ ትኩረቱ ምስስሎሽ ላይ ነው፡፡ እውነትን ፈላጊው ደግሞ የእምነትን ልብ ሲቀዳጅ ልዩነቱ የት ነው ብሎ የልዩነቱን ሰበቦች አመንዥኮ ተፈጥሯዊ ብቃቱን በወሳኝነቱ ወደር አልባ የሆነውን እምነትን በእውነት እጀታነት በመጨበጥ ልክ ያልሆኑትን ጥሎ ልክ የሆነውን ያነሳል፡፡ የእምነትና ምክንያት ቁርኝትም እዚህ ላይ ግለቱን ጨምሮ እውነትን የመጨበጥ መሰረት ይሆናል፡፡ በምስስሎሽ ሙቀጫ ሲቀጠቀጥ ቢውል ፍንክች የማይል እውነት አለና፡፡ ‹‹እውነትን ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል›› ተብሎ መጻፉ ለዚያ ነው፡፡ ‹‹እውነትም ህይወትም ደግሞ እሱ ነው›› አንድዬ፡፡ እሱ ሰላማችንን ያብዛልን ብዬ ልሰናበት፡፡

Read 1966 times