Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 07 November 2011 12:36

መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ... ሃብት ይባክናል በኢትዮጵያ፣ በቻይና፣ በህንድ፣ በአሜሪካ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያው መንግታዊ ፋብሪካ ለ25 አመታት በተከታታይ ከስሯል - ሰሞኑን ኢዜአ እንደዘገበው። በቻይና ሲከስሩ የቆዩ የመንግስት ፋብሪካዎች እየተዘጉ በየአመቱ በሺ የሚቆጠሩ አመፆች ይፈጠራሉ። በምስራቅ ጀርመን፤ በመንግስት ፋብሪካ የተሰሩ መኪኖች አገልግሎት ሳይሰጡ እየተበላሹ ያስቸግሩ ነበር። በህንድ መንግስት ተቋቁሞ የነበረ የማዳበሪያ ፋብሪካ ምንም ሳያመርት የሰራተኞችን ደሞዝ ከፍሏል - ለአመታት። አምና በአሜሪካ መንግስት ድጎማና ብድር የተሰጣቸው ፋብሪካዎች ከስረው እየተዘጉ ነው - ብሉምበርግ እንደዘገበው።

መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፤ የሃብት ብክነትንና ሌሎች ጥፋቶችን እንደሚያስከትል የሚጠቁሙ መረጃዎችን ከየአገሩ መጥቀሴ ደስ የማይላቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል፤ አንዳንዶቹም እስከ መቆጣት ሊደርሱ ይችላሉ - “እስቲ የማይነፃፀሩ ነገሮችን አታነፃፅር። የኢትዮጵያ ሌላ፤ የአሜሪካ ሌላ!” በማለት። 
በእርግጥም፤ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ በህክምና ዶክተርነት ወይም በዩኒቨሪሲቲ አስተማሪነት ከመስራት ይልቅ፤ አሜሪካ የፓርኪንግ ጠባቂ ወይም የታክሲ ሾፌር ሆኖ መኖር ይሻላል ብለው የሚሰደዱ ሰዎችን እናያለን።... እርዳታ ጠያቂና የረሃብ ተጠቂ የበዛበትን አገር፤ በየአመቱ የእርዳታ እህል ከሚልክ አገር ጋር ማነፃፀር አላዋቂነት ወይም ቀሽም ብልጣብልጥነት እንደሆነ ይገባኛል። ስለኢትዮጵያዊያን ረሃብ እየተወራ፤ “አሜሪካ ውስጥምኮ በረሃብ የሚቸገሩና እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች አሉ” የሚል ማነፃፀሪያ ብትሰሙ ... ጆሯችሁን ለመድፈን ብትጣደፉ አይገርመኝም። ይህም ብቻ አይደለም።
የፕሬስ ነፃነትን የሚያፍኑ፤ የንብረት ባለቤትነትን የሚገድቡ፤ የታክስ ጫናን የሚያከብዱ ህጎችና አንቀፆች በተዘጋጁ ቁጥር፤ ትችትና ተቃውሞ ቢሰነዘሩም፤ ብዙውን ጊዜ ህጎቹ አይስተካከሉም። ትችቶችን የመስማት ትእግስት ያለቀበት፤ ትችትን የማስተናገድ ሃላፊነት ያስጠላው የሚመስለው “ልማታዊ መንግስታችን”፤ ብዙውን ጊዜ ምላሽ በመስጠት “ጊዜ ማባከን” አይፈልግም። ምላሽ ሲሰጥስ?
አንዳንዴ አሜሪካንና አውሮፓን እያንቋሸሸ፤ “ህጎቻችንና አንቀፆቻችን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ላይ ተመስርተው ስለተዘጋጁ ትክክለኛ ናቸው” ብሎ ይመልሳል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ “ህጎቻችን፤ በአውሮፓና በአሜሪካ ህጎች መሰረት የተቀረፁ ስለሆኑ ትክክለኛ ናቸው” በማለት ይከራከራል።
“ይሄ አንቀፅ ከጀርመን የተወሰደ ነው፤ ያኛው አንቀፅ ከካናዳ፤ የወዲያኛው አንቀፅ ከእንግሊዝ የተገለበጠ ነው፤ የወዲህኛው ደግሞ ከአሜሪካ...” የሚል ማነፃፀሪያና መከራከሪያ ከመንግስት በኩል ሲቀርብ መስማታችሁ አይቀርም። እንዲህ አይነት ማነፃፀሪያ፤ አስቂኝ ገፅታ ቢኖረውም፤ በጥቅሉ አሳዛኝ እየሆነባችሁ ላለመስማት ብትሸሹ፤ “ኖርማል” ነው - “ኖርማል ስህተት፤ ቅጥ ያለው ስህተት”። “አሜሪካም ውስጥ ረሃብተኞች አሉ” የሚለው ማነፃፀሪያ ግን፤ “ቅጥ የለሽ ስህተት” ነው - ለዚህም ሊሆን ይችላል እጅጉን እየከነከናችሁ ልትሸሹት የምትሞክሩት። ነገር ግን፤ ጆሮን ለመድፈንና ለመሸሽ ከመሞከር ይልቅ፤ የማነፃፀሪያው አሳዛኝነት የት ላይ እንደሆነ ለይቶ ማውጣትና መፍትሄውን አበጅቶ ለማስተካከል መጣር ይሻላል፤ ተገቢም ነው።
የማነፃፀሪያው ዋነኛ ስህተት፤ ምን መሰላችሁ? ጠቅላላውን ነገር (the Whole) ከነጠላ ነገር (the Part) ጋር ማምታታት ነው። እንዲያውም፤ በጣም የተለመደ ስህተት በመሆኑ ስሞች ወጥተውለታል - fallacy of composition እና fallacy of division. በምሳሌ እንየው። አሜሪካ በጥቅሉ ስትታይ፤ በስልጣኔና በብልፅግና ደህና በመራመድ፤ እንዲሁም ትክክለኛ ህጎችን በመያዝና ነፃነትን በማስፈን ረገድ፤ ከአውሮፓ ጭምር በእጅጉ የተሻለች አገር ነች - ብዙዎች በስደት የሚገቡባት። አሜሪካ ውስጥ የምናገኛቸው ህጎችና አሰራሮች፤ በአውሮፓ ጋር የተሻሉና በአመዛኙ... በአብዛኛው... ጥሩ ናቸው እንደማለት ነው። “ሁሉም የአሜሪካ ህጎችና አሰራሮች ጥሩ ናቸው” ማለት አይደለም - አንዳንዶቹ ጥሩ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥሩ አይደሉም። በርካታ መጥፎ ህጎች እንዳሉ ምንም አያከራክርም።
መጥፎ ህጎች የትም አሉ
ለምሳሌ፤ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ባይሆን እንኳ በከፊልና በተዘዋዋሪ የቢዝነስ ስራ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርጉ ህጎች አሉ በአሜሪካ - ኪሳራንና የሃብት ብክነትን የሚያስከትሉ ህጎች። “ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ የነፋስ ተርባይኖችን በማስፋፋት፤ የአካባቢ ጥበቃን ማበረታታት” በሚል ሰበብ የተዘጋጁ ህጎችን መጥቀስ ይቻላል። በድንጋይ ከሰል፤ በኒዩክሌር ሃይል ወይም በውሃ ግድብ አማካኝነት በርካሽ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እየተቻለ፤ ከእጥፍ በላይ ወጪ የሚያስከትሉ የነፋስ ተርባይኖች እንዲስፋፉ ድጎማ የሚሰጥ መንግስት፤ የዜጎችን ሃብት እያባከነ ነው። ለነገሩ፤ “የአካባቢ ጥበቃ” በሚል ፈሊጥ የሚፈጠር ብክነት፤ ከአሜሪካ ይልቅ በአውሮፓ ይብሳል። በከፍተኛ እዳ ከተዘፈቁት የአውሮፓ መንግስታት መካከል አብዛኞቹ፤ ለነፋስ ተርባይኖች በገፍ ድጎማ በመስጠት ብዙ ገንዘብ ሲያባክኑ የነበሩ ናቸው ይላል - ሚሰስ ኢንስቲቱይት የተሰኘው የኢኮኖሚ ጥናት ተቋም።
ኢትዮጵያም እንደአቅሚቲ ሃብት እያባከነች ነው። የነፋስ ተርባይን የሚመነጨውንና በውሃ ግድብ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ሃይል ማነፃፀር ትችላላችሁ። በግልገል ጊቤ 3 ግድብ አማካኝነት ኤሌክትሪክ የሚመነጨው፤ 120 ሜጋዋት በመቶ ሚሊዮን ዩሮ ሂሳብ ነው። 120 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ የነፋስ ተርባይኖች እየተተከሉ ያሉት ግን፤ በ210 ሚሊዮን ዩሮ። ከመቶ ሚ. ዩሮ በላይ በነፋስ ተርባይኖች ይባክናል ማለት ነው - ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ። እንዲህ አይነት ብክነቶችን የሚያስከትሉ ህጎች፤ በኢትዮጵያም ሆነ በአውሮፓ፤ በህንድም ሆነ በአሜሪካ... ያው ጎጂና መጥፎ ናቸው።
መጥፎነት በላይ ያፈነገጡ፤ ጭራሽ “ያበዱ ህጎችና አሰራሮች”ም ይኖራሉ - በአሜሪካ። “የመንግስትን ብክነት የሚቃወሙ ዜጎች ማህበር” (CAGW) የሚያወጣቸውን አመታዊ ሪፖርቶች መመልከት ትችላላችሁ። “ቤት ውስጥ የደን ልማት ማስፋፋት” በሚል ለተጀመረ ፕሮጀክት 50 ሚ. ዶላር፤ የሻይ ማንቆርቆሪያ ሙዜየም ለማቋቋም ግማሽ ሚ. ዶላር ከመንግስት ተመድቦ እንደነበር የማህበሩ የ2010 ሪፖርት ይገልፃል። ይህንን ብክነት የሚፈቅድ የበጀት ህግ፤... ሰፈሩ ሌላ አይደለም - “ያበዱ ህጎች ሰፈር” እንጂ። እንዲህም ሆኖ፤ አሜሪካ በስልጣኔና በነፃነት ደህና ተራምዳለች ማለት... “የአሜሪካ ህጎችና አሰራሮች፣ በአብዛኛውና በአመዛኙ ከሌሎች አገራት የተሻሉ ናቸው” እንደማለት ነው - በርካታ መጥፎ ህጎችና አሰራሮች ቢኖሩም። በአፍሪካ ደግሞ፤ አብዛኞቹ ህጎችና አሰራሮች አንድም መጥፎ ናቸው፤ አልያም ያበዱ ናቸው።
የሆነ ሆኖ፤ የጥቅል እና የነጠላ ምዘና እንደሚለያዩ በቀላሉ ማየት የቻልን ይመስለኛል። በአንድ በኩል፤ “በአመዛኙና በአብዛኛው ሲታይ” ... እያልን የምናከናውነው “ጥቅል ምዘና” አለ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ “በተለይ ይሄኛው ህግ፤ በተለይ እነዚህኛዎቹ አንቀፆች” ... እያልን የምናካሂደው፤ “ነጠላ ወይም ዝርዝር ምዘና” አለ።
የሁለቱ ልዩነት በእጅጉ ግልፅ ከመሆኑ የተነሳ፤ የሁለቱን ልዩነት አለማወቅ ወይም ለማምታታት መሞከር፤ “ቅጥ የለሽ ስህተት” ይሆናል። “የአሜሪካ ህጎችና አሰራሮች በአብዛኛው ጥሩ ናቸው” በሚል ሰበብ፤ አሜሪካ ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ መጥፎ ህጎችንና ያበዱ አንቀፆችን ለቃቅሞ እንደማምጣት ቁጠሩት። ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ፤ ጥሩ ጥሩውን እየመረጠ ከማምጣት ይልቅ፤ መጥፎ ህጎችንና ያበዱ አንቀፆችን ለቃቅሞ ካመጣ በኋላ፤ “ይሄ ከእንግሊዝ፤ ያኛው ከአሜሪካ” እያለ ይዘረዝራል - እንደ አሜሪካና እንደ አውሮፓ ጥሩ መባል አለብኝ እንደማለት። ምን ዋጋ አለው? በእነዚህ መጥፎ ህጎችና አንቀፆች አይደሉም፤ አሜሪካና አውሮፓ ከሌሎች አገሮች ልቀው የተገኙት። ለዚህም ነው፤ መጥፎ ህጎችንና አንቀፆችን ይዞ ለመቀጠል፤ አሜሪካን ወይም አውሮፓን በማነፃፀሪያነት መጥቀስ፤ ቅጥ የለሽ ስህተት የሚሆነው።
“አንተምኮ፤ ኢትዮጵያን፣ ህንድን፣ አሜሪካን፣ ቻይናንና የቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመንን በማነፃፀሪያነት በመጥቀስ፤ ተመሳሳይ ስህተት ውስጥ ገብተሃል” የሚል ስሜት ከተፈጠረባችሁ፤ ነጥቡን ስታችሁታል። አምስቱንም አገራት የጠቀስኳቸው፤ ትክክለኛ አመዛዘንን ለማሳየት ነው - መንግስት እጆቹን ወደ ቢዝነስ አለም ሲያስገባ ጥፋትን እንደሚያስከትል ለማሳየት - በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ፤ በህንድም ሆነ በቻይና። ይህም፤ “የአሜሪካ መንግስትኮ፤ ቢዝነስ ውስጥ ጣልቃ ይገባል። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስትም በሰፊው ቢዝነስ ውስጥ እየገባ ቢፈተፍት ጥፋት አይደለም” የሚል ንፅፅር፤ ፈር የለቀቀ ስህተት መሆኑን ያሳያል። መንግስት ኢኮኖሚ ውስጥ እየገባ ሃብት እንዲያባክን መንገድ የሚከፍት መጥፎ ህግ፤ በየትም አገር ጎጂ ነው። የመጥፎነቱና የጎጂነቱ ደረጃ ግን ይለያያል። ከአሜሪካ ጀምረን መረጃዎቹን እንያቸው
“በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ መኪኖች እንዲበራከቱ ማበረታታት” በተሰኘው የባራክ ኦባማ ፖሊሲ መሰረት፤ የአሜሪካ መንግስት ባለፉት ሁለት አመታት ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቷል - ለተለያዩ ኩባንያዎች ብድር ወይም ድጎማ በመስጠት። እነዚህ እንክብካቤ የሚያገኙ ኩባንያዎች፤ ለብድርና ለድጎማ የተመረጡት ጠንካራ ስለሆኑ አይደለም። ጠንካራና አትራፊ ቢሆኑ ኖሮማ፤ ድጎማ ባላስፈለጋቸው፤ ራሳቸውን ችለው ከግል ባንኮች ብድር መውሰድ ባላቃታቸው ነበር። በመንግስት በኩል ብድርና ድጎማ የሚያገኙት፤ ራሳቸውን ችለው ለመቆም ስላልፈለጉ ወይም ስላልቻሉ ነው (በሌላ አነጋገር ምርታማ ስላልሆኑ)። ያው መንግስት ምርታማ ላልሆኑት ኩባንያዎች የሚያቀርበው የድጎማ ገንዘብ፤ በቀረጥና በታክስ የተሰበሰበ ገንዘብ ነው - ከሌሎች ምርታማ ኩባንያዎች ተነጥቆ የተወሰደ። እንዲያም ሆኖ፤ “የመንግስት ድጎማና ማበረታቻ፤ የአዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በማስፋፋት ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው” በማለት ዘወትር የሚደሰኩሩት ባራክ ኦባማ፤ ተደጓሚ ኩባንያዎችን በምሳሌነት ሲጠቅሱና ሲጎበኙ ከርመዋል። ኩባንያዎቹ ግን፤ በመንግስት ድጎማ አማካኝነት ምርታማ ለመሆን አልበቁም። ያለተጨማሪ ድጎማ ህልውናቸው መቀጠል አይችልም። ከ110 ሚ. ዶላር በላይ ድጎማ የተመደበለት ኢነርዋን የተሰኘ ኩባንያ እንዲሁም ከ500 ሚ. ዶላር ብድር በመንግሰት በኩል የተፈቀደለት ሶሊንድራ የተሰኘ ኩባንያ፤ በኪሳራ ስራ ለማቆም እንደወሰኑ ሰሞኑን ቢዝነስ ዊክ ዘግቧል። የተሰጣቸው ድጎማና ብድር ቀልጦ ቀርቷል - ባክኖ። ነገር ግን፤ እነዚሁ ኩባንያዎች በተጨማሪ ድጎማና ብድር፤ ሌላ የብክነት ዙር የመቀጠል እድል የላቸውም። የመንግስት ኩባንያዎች ቢሆኑ ኖሮ ግን፤ ብክነቱ እንዲህ በአንድ አመት ውስጥ አይቋጭም ነበር። በመንግስት ኩባንያዎች የሚደርሰው ብክነት፤ በደረጃው ከፍ ይላል።
የህንድ መንግስት እኤአ በ1980 ገደማ ያቋቋመው የማዳበሪያ ፋብሪካ፤ ለማሽኝ ግዢና ተከላ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ሲሆን፤ 1200 ሰራኞች ነበሩ። ኔክድ ኢኮኖሚክስ በተሰኘው መፅሃፋቸው የሚታወቁት ቻርለስ ኼላን፤ የድርጅቱ ሰራተኞች በየእለቱ በስራ ገበታቸው ይገኙ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በየወሩም ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር።
ለ12 አመታት ምንም የተቀየረ ነገር አልነበረም። ነገር ግን፤ ፋብሪካው በእነዚህ አመታት ውስጥ፤ አንዲት ኬሻ ማዳበሪያ አላመረተም፤ አልሸጠም። ቢሆንም... ከስሮ አልተዘጋም። ለማሽኖች ጥገና፤ ለጥሬ እቃ መግዣና ለደመወዝ ክፍያ ገንዘብ ወጪ ማድረጉን አላቋረጠም። ከመንግስት የድጎማ በጀት ይመደብለታል - ከአመት አመት በከንቱ የሚባክን ገንዘብ።
ፋብሪካው በህንድ መንግስት እጅ በቆየባቸው 12 አመታት የገንዘብ ብክነቱ አልቆመም። ከዚህም የባሰ አለ። ሰሞኑን ኢዜአ እንደዘገበው፤ የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በረዥም አመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርፍ ያስመዘገበው ዘንድሮ ነው። ከ25 አመታት በላይ፤ በየአመቱ ይከስራል። ግን የመንግስት ስለሆነ፤ በኪሳራ አልተዘጋም። ገንዘብ እያባከነ መቀጠል ችሏል።

 

Read 4442 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:41