Saturday, 02 February 2013 19:20

“ለህፃናት ቦታ አለን!”

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(3 votes)

በባህላችን ለህፃናት እምብዛም ትኩረት አይሰጥም፡፡ የሰርግ ጥሪ ካርድ ላይ እንኳን “ለህፃናት ቦታ የለንም” የሚል ማሳሰቢያ የተለመደ ነው፡፡ በቂ መዝናኛ ቦታዎች የሉም፡፡ የህፃናት ምግብ ላይ ያተኮሩ ሬስቶራንቶች መኖራቸውን አላውቅም፡፡ ትያትር ቤቶችና ፊልም ቤቶችስ? እስካሁን የታሰበባቸው አይመስሉም፡፡ ከተከፈተ ስድስት ወር ያስቆጠረው “ኪሩ የህፃናት ፀጉር ቤት” ትኩረቴን የሳበው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ፀጉር ቤቱ ያለበት ህንፃ አካባቢ የህፃናት ሆስፒታል አለ፡፡ እዚያው ህንፃው ላይ ደግሞ የህፃናት የሙዚቃ መሣሪያ መማርያ መኖሩን አይቻለሁ፡፡
“ለህፃናት ቦታ አለን” ማለት የተጀመረ ስለመሰለኝ ቴሌ መድሃኔአለም አካባቢ የሚገኘውን ፀጉር ቤቱን ደጋግሜ ጐበኘሁት፡፡ ፀጉር ቤቱ ዕድሜያቸው ከአንድ አመት እስከ አስራ ስምንት አመት ላሉ ወንዶች እና ሴቶች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ፀጉር ቤቱ ውስጥ የተለያዩ ቀለሞች የተሞላ የዶቃ ማስቀመጫ፣ ቲያራ የህፃናት ቅባቶች፣ የጆሮ ጌጦች እና ሎራፖፖች በመደርደሪያ ላይ ተሞልተዋል፡፡
ግድግዳው በተለያዩ የአሻንጉሊት ስዕሎች፣ መስታወቶች እንዲሁም በደማቅ ቀለማት ባሸበረቁ ፍሬሞች ተውቧል፡፡ የፀጉር ቤቱ ባለቤት ከሆኑት ወ/ሮ ነፃነት ጌታቸው ጋር ተገናኝቼ በህፃናት ፀጉር ቤቱ ዙሪያ ያወጋነውን እነሆ ብያለሁ፡-

የህፃናት ፀጉር ቤት የመክፈቱ ሀሳብ እንዴት መጣ?
ከተማ ውስጥ ልጆችን በመንከባከብ በተለይ የሥራ ውጥረት ያለባቸው ወላጆችን ጫና የሚያቃልል ቆይታ ስራ መሠራት እንዳለበት ያየሁት ልጅ ከወለድኩ በኋላ ነው፡፡ ልጆች ጊዜ ይፈልጋሉ፤ ወላጆች ሥራ ውለው ደክሟቸው ሲመጡ ይህን ስራ የሚያግዛቸው ሰው ከሌለ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው የሞግዚት እና የቤት ሠራተኛ እጥረት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በሚል ነው የጀመርኩት፡፡
ከአዋቂዎች ፀጉር ቤት በምን ይለያል?
በመጀመሪያ አገልግሎቱን የምንሰጠው ለህፃናት፣ ለልጆች ነው፡፡ ለወንዶች ቁርጥ፣ ለሴቶች ደግሞ ካስክ እና ሹሩባ ብቻ ነው የምንሠራው፡፡ አገልግሎት የምንሰጠው ከአንድ አመት በላይ ከሆኑ ህፃናት ጀምሮ እስከ 18 ዓመት ወጣቶች ቢሆንም የሰባት ወር ልጅ ሹሩባ ልትሠራ መጥታ ተሠርታ ሄዳለች፤ የዘጠኝ ወር ልጅም የተሰራችበት ጊዜ አለ፡፡
ልጆች የተለየ እንክብካቤ ይፈልጋሉ፤ የመቅበጥበጥና የመሰላቸት ባህርይ ሊያሳዩ ይችላሉ፡ከዚህ አንፃር ሥራው አያስቸግርም?
ልጆች ልዩ ትኩረት ስለሚፈልጉ እንደየባህርያቸው በመያዝ አገልግሎቱን እንሰጣለን፡፡ ብዙዎቹ አንዴ ከመጡ በኋላ ተሰርተው መሄድ ነው የሚፈልጉት፡እያለቀሱ ጀምረው እያለቀሱ ጨርሰው የሚሄዱ አሉ። ሲጀምሩ አመመን ብለው እየለመዱት የሚመጡም አሉ፡፡
እየተሠሩ እንቅልፋቸውን የሚተኙም አሉ፤ እየተንከባከብን ሰርተን እንጨርስላቸዋለን፡፡ ያው እንደትልቅ ሰው እሺ ብለው ላይሰሩ ይችላሉ። እንደየፀባያቸው እያጫወትን እያባበልን ነው የምንሰራቸው፡፡
ተሰርተው እስኪሄዱ ባለው ጊዜ እንዳይሰላቹ የምታደርጉላቸው ነገር አለ?
የተለያዩ የልጆች መጫወቻዎች እንዲሁም ዘፈኖች አሉን፤ ታሪክም እናወራላቸዋለን ልጆቹም ራሳቸው መጫወቻቸውን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ራሳቸው ዘፈን ይዘፍናሉ ወይም ታሪክ ያወሩልናል። ከለር መደርደርም ይጫወታሉ፡፡ እና ብዙ ተረት እናወራለን፡፡
ካስክ ውስጥ ገብቶ መቆየት ለትልቅ ሰውም ከበድ ይላል፡፡ ህፃናቱ እንዴት ነው አያስቸግሩም?
የምንጠቀመው የልጆች ቢጐዲን ነው፤ የምንሠካውም ፕላስቲክ ነው፡፡
ቆዳቸው ተከፋፍሎም አያገኛቸውም፤ አያቃጥላቸውም፤ ስለዚህ ምንም አይጐዳቸውም፡፡ ካስክ ውስጥ ለመቆየት አይቸገሩም።
ለመግባትም እምቢ አይሉም፡፡ አንዷ ገብታ እስክትወጣ በጉጉት ነው የሚጠብቁት፡፡ ሙቀቱም ለነሱ በተመጠነ ሁኔታ ነው፡፡
እኛ ደግሞ በብዛት ካስክ አንሰራም፤ ሹሩባ ነው የምንሠራው፡፡ ከመሠልቸቱ የተነሳ “አይበቃኝም? አቃጠለኝ” የሚሉ ህፃናት አሉ፡፡ እያባበልን ፀጉራቸው እስኪደርቅ እናቆያቸዋለን፡፡
ልጆች እቃዎችን መነካካት መጠየቅ ይወዳሉ፡፡ እንዴት ነው ይህን ባህርይ የምታስተናግዱት?
ልጆች መጠየቅ ይወዳሉ፤ ትኩረት ሰጥተን እንመልስላቸዋለን፡፡ መነካካት ይችላሉ፤ አንከለክላቸውም፡፡ በዚህ በኩል ምንም አይነት ችግር የለብንም፡፡ የሚለኮስ ነገር አንጠቀምም። የሚጐዳቸው ነገር እንዳይነኩ እንጠብቃቸዋለን። ወላጅ ሃላፊነት ሰጥቶን ስለሚሄድ በጥንቃቄ ይዘን ሠርተን ለወላጆቻቸው እናስረክባለን፡፡
የሹሩባውን ዲዛይን እነሱ ናቸው እናንተ የምትመርጡት?
ለልጆች የሚሆኑ የተለያዩ ዲዛይኖች አሉ፡፡ የቤቱ ልዩ የምንለውም አለን፡፡ ልጆች ሁሉም ነገር ያምርባቸዋል፡
ደክሟቸው የሚተኙ ልጆች የሉም?
የሚተኙ ልጆች አሉ፡፡ በመተኛት የታወቁ ሶስት ህፃናት ደንበኞች አሉ፡፡ እናቶቻቸው አቅፈዋቸው ይተኛሉ ይሠራሉ፡፡ አልቅሰው ደክሟቸው የሚተኙም አሉ፡፡ በዛው ታቅፈው ይወሰዳሉ፡፡
የሚሸጡ ዕቃዎችም አሏችሁ…?
መደርደሪያው ላይ ያሉት የህፃናት ነገሮች ስለሆኑ ወላጆቻቸውን ጠይቀው ያስገዛሉ፡፡ ሳያስገዛ የሚወጣ ህፃን የለም፡፡
የስራ ሠዓትሽ እንዴት ነው?
እስከ ለሊቱ ስድስት ሰአት ሰርቼ አውቃለሁ። የአመት በአል ሰሞን በጣም ወረፋ አለ፡፡ ስራ የሚበዛው ቅዳሜና እሁድ ነው፤ ልጆቹ በጨረሱ ሠዓት ነው የምንዘጋው፡፡
ደንበኛ ያላቸው ህፃናት አሉ?
አሉ፡፡ እከሌ ትስራኝ ብለው ይመርጣሉ፡፡ ወላጆቻቸው ሂሳብ ሲከፍሉ “እሷ ናት የሠራችን፤ ቲፕ ስጫት” ይላሉ፡፡ ከት/ቤት ጓደኞቻቸው ጋር በአጋጣሚ ሲገናኙ ይቦርቃሉ፡፡
የፀጉር ቤቱ የአገልግሎት ዋጋ ምን ያህል ነው?
የወንዶች መቆረጫ ሰላሳ አምስት ብር፣ የሴቶች ሹሩባ (ኖርማል) ሀምሳ ብር፣ የሴቶች ሹሩባ (ስፔሻል) ሰማኒያ ብር ድረስ ይሄዳል፡፡ ወንዶች የተለያዩ ቁርጦች ይቆረጣሉ፡፡ ባላቶሊ፤ በስታይል መቆረጥ የሚፈልጉ ወንዶች ምርጫ ነው፡፡
ቤቷ ጠበብ ትላለች፡፡ ምን አስበሻል?
ለማስፋት አስቤያለሁ፡፡ ከዛ ውጪ የልደት ዝግጅቶችን ማሰናዳት (ኦርጋናይዝ ማድረግ) ጀምረናል፡፡ ቅርንጫፍ ለመክፈትም አስቤያለሁ፡፡ ፊትን በቀለማት ማስጊያጥ (face paint) እንሰራለን፣ ዴይኬር ለመክፈትም አስበናል፡፡
ከህፃናት ጋር ስትሰሪ ብዙ ገጠመኞች ይኖርሻል ብዬ እገምታለሁ…
ልጆቹ የሚያወሩት ነገር ሁሉም ያስቀኛል። በጣም የሚገርመኝ እሱ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ሁለት ህፃናት አብረው መጥተው እየተሠሩ አንዷ “አንቺ ወሬ ታያለሽ?” ስትላት ሌላዋ “ወሬ አይታይም ይሰማል እንጂ” አለቻት፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ የአምስት ዓመት ወንድ ልጅ ፀጉሩን ሊቆረጥ መጥቶ፣ ፀጉሯን ልትሠራ የመጣችን ልጅ “በጣም እንደምታምሪ ታውቂያለሽ?” አላት፤ እኔ በጣም ገረመኝ፤ ልጅቷ ደነገጠች፡፡

Read 4062 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:59