Print this page
Saturday, 02 February 2013 14:27

ያልታከመ ውሃና መዘዙ!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት ይሞታል ከአዲስ አበባ በ396 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እገኛለሁ፡፡ ሥፍራው በሐረሪ ክልል የሶፌ ወረዳ አፈር ዳባ ቀበሌ ገንደ ነገዬ እየተባለ የሚጠራ መንደር ነው፡፡ ወደዚህ ስፍራ ለመምጣቴ ዋንኛ ምክንያቱ በአካባቢው በሚታየው ከፍተኛ የውሃ ችግር ምክንያት ነዋሪዎቹ ከሶስት እና አራት ሰዓታት በላይ በእግራቸው ተጉዘው የሚያገኙትን የጉድጓድ ውሃ በምን መልኩ ለመጠጥነት እንደሚያውሉት ለማየትና ከንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ነው፡፡ ወደ ሥፍራው ተጉዤ ሁኔታውን ለመመልከትና የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማነጋገር ሁኔታዎችን ያመቻቸልኝ ደግሞ በwater Aid Ethiopia ሥር የሚገኘው የwash movement ነው፡፡ ከሐረር ከተማ ወጣ ባለ አካባቢ ከሚገኘውና አፈር ዳባ እየተባለ ከሚጠራው መንደር ለመድረስ ከሐረር ወደ ጅጅጋ ከሚወስደው ዋና አስፋልት መንገድ ላይ ከመኪና ወርዶ ለሁለት ሰዓታት በእግር መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ወጣ ገባውን መንገድ ጨርሰን ከመንደሩ ስንደርስ ጠዋቱ ተጋምሷል፡፡ የአካባቢው ፀጥታና የፀሐይዋ ግለት ሥፍራውን አስፈሪ ድባብ አልብሰውታል፡፡ እዚህም እዚያም ፈንጠርጠር ብለው ከተሰሩት ጐጆዎች ውስጥ ህይወት ያለም አይመስልም፡፡ ሁሉም ነገር ፀጥ እረጭ ብሏል፡፡ በድካም የዛሉ እግሮቻችንን እየጐተትን ወደ አንደኛው ጐጆ በራፍ ተጠጋንና መጣራት ጀመርን፡፡

ጥሪያችን ምላሽ ያገኘው ከተደጋጋሚ ጩኸት በኋላ ነበር፡፡ የአካባቢውን ቋንቋ በምታውቀው ጋዜጠኛ ጓደኛዬ እየተመራሁ ወደ ቤቱ ጐራ ማለት እንድንችል ይፈቅዱልን እንደሆነ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ሴና…ሴና…“የሚል ፈቃድ ተሰጠንና ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ከሣር የተሠራችና እርጅና የተጫጫናት ናት ጐጆዋ፡፡ የጐጆዋን አብዛኛውን ሥፍራ የያዘው እንደአልጋም፣ እንደወንበርም፣ እንደጠረጴዛም የሚያገለግለው ሰፊ መደብ ነው፡፡ በዚህች መደብ ላይ የቤቱ አባወራና እማወራ፣ በላይ በላይ የተወለዱት ስምንት ሕፃናትን ጨምሮ በእንግድነት ወደቤቱ የሚመጡ ሰዎች ሁሉ ያርፉባታል፡፡ እኛ ስንገባ ከቤቱ አባወራ ሌሎች አምስት ሰዎች መደቡ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ እማወራዋ ህፃን ልጇን እንደታቀፈች ከመግቢያው በራፍ ላይ ቁጭ ብላለች፤ ቤቱና አካባቢው በጣም ቆሽሿል፡፡ ማንነታችንንና የመጣንበትን ጉዳይ ለቤቱ አባወራ ለአቶ ጀማል አህመድ ነገረን ጨዋታ ጀመርን፡፡ አቶ ጀማል በዚህ ሥፍራ መኖር ከጀመረ አራት አስርት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሶፊያ የሱፍ ከምትባለው ባለቤቱ ስምንት ልጆችን አፍርቷል፡፡ በዓመት በዓመቱ የሚጨምረው የልጆቹ ቁጥር ፈጽሞ አያሳስበውም፡፡ በሰበብ አስባቡ ከሚከሰተው ሞት ተርፈው ለፍሬ የሚበቁት ጥቂቶቹ ናቸውና የልጆቹን ቁጥር ገና እንደሚጨምር ያምናል፡፡

በተቅማጥና በሆድ ቁርጠት ህመም ከተያዙት ሁለት ልጆቹ አንደኛው በእናቱ እቅፍ ውስጥ ነበር፡፡ እንደ አቶ ጀማል ገለፃ፤ ልጆቹ ለተደጋጋሚ የሆድ በሽታዎችና ተቅማጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በየጊዜው በሚያጋጥማቸው በዚህ በሽታ ሳቢያም የስምንትና የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆቹ ወደትምህርት ቤትም ሆነ እንደወንድሞቻቸው ለከብት ጥበቃ ወደ መስክ አይወጡም፡፡ ዕለት ከዕለት እየመነመነ የሚሄደው ሰውነታቸው ልጆቹን ከዕድሜያቸው ሦስት እና አራት አመት ያነሱ አስመስሏቸዋል፡፡ የአቶ ጀማል አህመድ ህፃናት ሴት ልጆችና ባለቤቱ ከዕለት ተግባሮቻቸው የሚቀድመው ከመንደራቸው ሦስት ሰዓት ርቀት ያለውን መንገድ በመጓዝ ለመጠጥና ለምግብ ማብሰያ የሚሆን ውሃ ማምጣት ነው፡፡ ውሃው ደግሞ የሚገኘው ከጉድጓድ ነው፡፡ ውሃው በአንድ ቦታ ላይ የታቆረና የማይንቀሳቀስ በመሆኑ የተለያዩ የውሃ ውስጥ ትላትሎችንና ነፍሳትን ያፈራል፡፡ ይህንኑ ውሃ እነጀማል ለመጠጥ፣ ለምግብ ማብሰያ፣ ለመታጠቢያና ለከብቶቻቸው መጠጥነት ይጠቀሙበታል፡፡ ዕድሜያቸውና የጤንነት ሁኔታቸው ፈቅዶ ትምህርት ቤት የገቡት የአቶ ጀማል ልጆች፣ በየተራ ውሃ ለመቅዳት ከት/ቤት ይቀራሉ፡፡ የምግብ እጥረትና ንፁህ የመጠጥ ውሃ እጦት ባኮሰመነው ደካማ ሰውነታቸው የሶስት ሰዓታት መንገድ በእግር ተጉዘው የሚያመጡት ውሃ ለቤቱ ብርቅ ነው፡፡ እናታቸው ወ/ሮ ሶፊያ የሱፍ በእሷና በሕፃናት ልጆቿ ጉልበት ወደ ቤት የሚመጣውን ዝልግልግ፣ በትላትልና በአልቅት የተሞላውን ውሃ ለማጣራት የለበሰችውን ሻርፕ ሣብ አድርጋ ታጠላለች፡፡ በሻርፕዋ ላይ ጠለው የሚቀሩት ጥቃቅን ነፍሳትና ትላትሎች ውሃው ከቆሻሻ ለመጣራቱና ንፁህ ለመሆኑ ማረጋገጫዎቿ ናቸው፡፡

በሶፊያ ሻርፕ ተጠሎ ለመጠጥ ዝግጁ የሆነውን የጀሪካን ውሃ ተመለከትኩት፡፡ እጅግ ያሳቅቃል፡፡ ውሃውን እንኳንስ ለመጠጥነትና ለምግብ ማብሰያነት ለማሰብ ይቅርና እንዲሁ በዓይን ለማየትም ይቀፋል፡፡ ውሃውን ለእኔ ልታሳየኝ ጀሪካኗን ስታነሳ የተመለከተወ ልጇ፤ ውሃ ጠማኝ አላትና በጣሳ ቀድታ ሰጠችው፡፡ ሰቀጠጠኝ፡፡ ህፃኑ ውሃውን እንዳይጠጣ ብከላከልም “ታዲያ ምን ይጠጣ” ለሚለው ጥያቄዋ ምላሽ አልነበረኝም፡፡ ግን ቢያንስ ውሃውን አፍልታ በማቀዝቀዝ እንድታጠጣው መምከሬ ግን አልቀረም፡፡ ሁኔታዬ ያስገረማት ሶፊያ፤ ልጇ ውሃውን እንደለመደው፣ ሁልጊዜም የሚጠጣው ይህንኑ ውሃ እንደሆነና በጤንነቱ ላይ የደረሰ የከፋ ጉዳት አለመኖሩን ነገረችኝ፡፡ ይህንን አባባሏን ግን ባለቤቷ አልተቀበለውም፡፡ በአካባቢየቸው ከፍተኛ የውሃ እጥረት መኖሩን፤ ይህም በተለያዩ ቆሻሻዎች የተበከለና በዓይን ለማየት እንኳን የሚቀፍ ውሃን ለመጠቀም እንዳስገደዳቸውና እሱም ሆነ ልጆቹ ለተቅማጥና ለተደጋጋሚ የሆድ ውስጥ በሽታዎች እንደተዳረጉ ነገረኝ፡፡ በአካባቢያቸው የጤና ጣቢያም ሆነ ሆስፒታል ባለመኖሩና መኖሪያቸው ከመኪና መንገዱ እጅግ የራቀ በመሆኑ ህመም ሲሰማቸው ወደጤና ጣቢያ ለመሄድ አይችሉም፡፡ በዚህ ሣቢያም በመንደራቸው በርካታ ህፃናት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ካለማግኘት ጋር በተያያዙና በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ምክንያት ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ክልል ኮምቦልቻ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ በእንግድነት ወደ እነ ጀማል ቤት መጥተው ያገኘናቸው አቶ የሱፍ አብዱላሂ፤ በመንደሩ ውስጥ ህብረተሰቡ ለመጠጥነት ሲጠቀምበት ያዩት ውሃ በጣም እንዳስደነገጣቸው ነግረውኛል፡፡ በአካባቢው የሕፃናት በሽታ የተለመደ ጉዳይ እንደሆነና በርካታ ልጆችም በተለያዩ የሆድ ህመሞች ሳቢያ ለህልፈት እንደሚዳረጉ ገልፀውልኛል፡፡ ማሙድ አህመድ፣ አብዱላኢ ደኑር፣ ፋጤ ጀማልና ሃድራ ቃሲም የተባሉት የአፈርደባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ገንደ ነገዬ መንደር ነዋሪዎች፤ በተቅማጥና ሆድ በሽታዎች ሣቢያ ልጆቻቸውን ሞት የነጠቃቸው ነዋሪዎች እንደሆኑም ነግረውኛል፡፡ በመንደሩ ውስጥ እየተዘዋወርኩ በጐበኘኋቸው ቤቶች ውስጥ ሁሉ ያየኋቸውና በጨርቅ ተጥለው ለመጠጥነት ዝግጁ ናቸው የተባሉት የጀሪካን ውሃዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎችን የያዙና ለጤና እጅግ አደገኛ እንደሆኑ በዓይን ብቻ በማየት ለማወቅ ይቻላል፡፡ ውሃው እንደተልባ የሚዝለገለግ፣ ቀለሙ የወየበ፣ ጥቃቅን ቆሻሻዎችና የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት የሚርመሰመስበት ነው፡፡ በመንደሩ የነበረኝን ቆይታ አጠናቅቄ ስወጣ ወደክልሉ ጤና ቢሮ በመሄድ ኃላፊዎቹን ለማናገር አሰብኩ፡፡ የጤና ቢሮው ኃላፊዎች፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት የሚችለው የክልሉ የውሃ ሃብት ቢሮ እንደሆነ ነግረው አሰናበቱኝ፡፡ በሐረሪ ክልል ውሃ ሀብት ቢሮ ተገኝቼ በጉዳዩ ላይ ኃላፊውን ለማነጋገር ያደረግሁት ሙከራ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የገጠር ውሃ ማጐልበት ክፍልን እንደሆነ ተነግሮኝ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል የተባለው የክልሉ የገጠር ውሃ ማጐልበት ቢሮ ኃላፊን አግኝቼ በጉዳዩ ላይ ለማነጋገርና ሊወሰድ የታሰበ እርምጃም ካለ ለመጠየቅ ያደረግሁት ሙከራም ኃላፊው የሉም በሚል ምክንያት አልተሳካልኝም፡፡

እነዚያ ህፃናት፣ ደካማ አረጋውያንና ሴቶች በአጠቃላይ የአካባቢው ነዋሪዎች በትላትልና በአልቅት የተሞላውንና ለማየት እንኳን የሚያስፀይፈውን ያልታከመ ውሃ በጨርቅ እያጠለሉ ይጠጣሉ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በሚያወጣቸው መረጃዎች መሰረት፤ በታዳጊ አገራት በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት የሚሞቱ ህፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት ሳቢያ ይሞታል፡፡ በአገራችን ከ50 በላይ የሚሆነው የጤና መታወክ የሚከሰተው በቀላሉ ልንቆጣጠረው በምንችለው የተበከለ ውሃና ምግብ ሳቢያ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ውሃን ሳያክሙ ለመጠጥም ሆነ ለምግብ ማብሰያነት መጠቀም የሚያስከትለውን የጤና ችግርና መዘዙን አስመልክቶ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኢያሱ ታመነ ሲናገሩ፡- “እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ አገራት ከንፁህ የመጠጥ ውሃና ከተበከለ ምግብ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የተቅማጥ በሽታ ለህፃናት ሞት ዋንኛው መንስኤ ነው፡፡ የተቅማጥ በሽታ በባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ ፕሮቶዞዋ እና ሌሎችም ጀርሞች አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ በሽታው በህፃናት ላይ ጐልቶ የሚታይ ሲሆን በወቅቱ ህክምና ካልተደረገበትና በተቅማጥ መልክ ከሰውነት ውስጥ የሚወጣውን ፈሳሽ የሚተካ ነገር ካላገኘ ለህልፈት የሚያበቃ በሽታ ነው፡፡ ንጽህናውን ያልጠበቀ፣ ባክቴሪያ፣ ቫይረስና ጥገኛ ትሎች የሞሉበትን ውሃ መጠቀም ትንሹ አንጀታችን እንዲቆስልና የተቅማጥ በሽታ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡

ከውሃ መበከል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች በቀላል ህክምና በአጭር ጊዜ ለማዳን ቢቻልም በርካቶች በዚህ ሳቢያ ህይወታቸውን ሲያጡ ይስተዋላል፡፡ ይህም ለበሽታው ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠትና በጊዜ ህክምና ለማግኘት ካለመቻል ጋር ተያይዞ የሚከሰት ችግር ነው” ብለዋል፡፡ በአገራችን የተለያዩ ክልሎች በተለይም በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ንጽህናው የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የገለፁት ባለሙያው፤ የተገኘውን ውሃ ግን በተለያዩ መንገዶች በማከም ለመጠጥነትና ለምግብ ማብሰያነት ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተበከለ ውሃና ንጽህውን ባልጠበቀ ምግብ ሳቢያ የታይፎይድ በሽታ፣ ኮሌራና፣ የጉበት ብግነት (Hepatites) ሊከሰቱ እንደሚችሉና እነዚህ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ከሰው ወደሰው ሊተላለፉ የሚችሉ ገዳይ በሽታዎች እንደሆኑም ዶ/ር ኢያሱ ጠቁመዋል፡፡

Read 3489 times