Saturday, 02 February 2013 15:42

የይሁዳ አንበሳ በሮማ አደባባይ

Written by  ባይህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

በዓለም ላይ በየጊዜው የተነሱ ቅኝ ገዢዎች በደካሞች አገሮችና ክልሎች ላይ እየዘመቱ መንግሥታቱን በማስገበር ሥልጣኔያቸውንና ከተሞቻቸውን አውድመዋል፤ባህላቸውንና ታሪካቸውንም ደምስሰዋል፡፡ ተሸናፊው አገር ያፈራውን ምርትም ሆነ በከርሰ ምድሩ የሚገኘውን በረከት ያለርህራሄ ማጋበሳቸው አልበቃ ቢላቸው፤ የያዙትን አገር ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች፣ የጥበብ ውጤቶች፣ መዛግብትና ሰነዶች ዘርፈዋል፡፡ እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች ዛሬ የቀድሞ ቅኚ ገዢዎች አገራት ታላላቅ ሙዚየሞች፣ አብያተ መጻሕፍትና አደባባዮችን በማድመቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ የቅኝ ግዛት እርግማን ያልደረሰባት አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በ1888 ዓ.ም በወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ላይ በዐድዋ የተጎናጸፈችው ድል ነጻነቷን በብርቱ መሠረት ላይ ያጸና ከመሆኑም በላይ፤ የድሉ ብሥራት በአፍሪካና በካሪቢያን በአስከፊ የቅኝ አገዛዝ ስር ለሚማቅቁት የጥቁር ሠው ዘሮች የነጻነት ብርሐንን ለመፈንጠቅ ችሏል፡፡ ይህ አንጸባራቂና ታሪካዊ ድል የአገሪቱ ሕዝብ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ቅርስ በወራሪ አውሮፓዊ እንዳይረክስ፣ እንዳይከለስና፣ እንዳይዘረፍ ለመጠበቅ አስችሏል፡፡ ይህን ኩሩ፣ ኃያልና ለነጻነቱ ቀናዒ የሆነ ጀግና ሕዝብ ለማስገበር ያደረገችው ከንቱ ሙከራ ዐድዋ ላይ የከሸፈባት ኢጣሊያ፤ በሽንፈቱ ሳቢያ የደረሰባትን ሀፍረትና ውርደት ለመበቀል አመቺ ጊዜ ስትጠባበቅ ቆይታለች፡፡

የዐድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ ልክ ከ40 ዓመት በኋላ፤ ኢጣሊያ እንደ ተዋጊ አውሮፕላንና ታንክ የመሳሳለውን ዘመን ያፈራው የጦር መሣሪያ ሠራዊቷን በገፍ አስታጥቃ በኢትዮጵያ ላይ ዘመተች፡፡ ወረራውን “በቅኝ ግዛት ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ጦርነት ነው” ሲሉ በጊዜው የኢጣሊያ ንጉሥ የነበሩት ቪክቶር ኢማኑኤል ተናግረውለት ነበር፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት ሠራዊቱን ካስታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ ባሻገር፤ በጦርነት ላይ እንዳይውል በዓለም የተከለለውን ጅምላ ጨራሽ መራዥ ንጥረ ነገር ጭምር በአውሮፕላን እየነሰነሰ ነበር የገሠገሠው፡፡ ይህ የፋሺስት የፈሪ በትር ለብዙ መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን እልቂት ምክንያት መሆኑ የማይካድ ቢሆንም በሰንካላና ጊዜው ባለፈበት መሣሪያ ወራሪዎቹን እየጣሉ የወደቁ ጀግኖቻችን ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ በዱር በገደል ተሰማርተው በወራሪው ላይ አደጋ እየጣሉ በተፋለሙት የኢትዮጵያ አርበኞች የተነሳም፣ አምስቱ የወረራ ዓመታት ለፋሺስት ኢጣሊያ የሥጋት እና የፍርሃት እንጂ የሠላምና የመደላደል አልነበሩም፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ በጭካኔ እርምጃው እየገሰገሰ የአዲስ አበባን ከተማን ከያዘ በኋላ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቄሣር ግዛት መሆንዋን አወጀ፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላም እንደ ማንኛውም ወራሪ ፋሺስቶችም የኢትዮጵያ ጥንታዊነት፣ ነጻነትና አንድነት ምልክት የሆኑትን ታሪካዊ ቅርሶች፣ የጥበብ ውጤቶች፣ መዛግብትና ሰነዶች በመዝረፍ ወደ ሮማ ያጓጉዙ ጀመር፡፡ ከነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች ውሥጥ የአክሱም ሐውልት እንዲሁም በርካታ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳትና የብራና መጻሕፍት ይገኙበታል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የኢጣሊያ ፋሺስቶች ካተኮሩበት ቅርስ መካከል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አርማ የሆነው አንበሳ የተቀረጸበት የይሁዳ አንበሳ ሐውልት አንዱ ነው፡፡ ይህ ሐውልት ቆሞ የነበረው አዲስ አበባ ከሚገኘው የምድር ባቡር ኩባንያ መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ሲሆን፤ በፋሺስቶች ከመሠረቱ ተነቅሎ ወደ ሮማ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ ሐውልቱ ፋሺስቶች ኢትዮጵያን ከመውረራቸው ትንሽ ቀደም ብሎ የቆመ እንደመሆኑ እንደ አክሱም ሐውልት ጥንታዊነት ባይኖረውም፣ ለወራሪዎቹ የኢትዮጵያ መንግሥትን አምሣያ የወከለ ምልክት ተደርጎ በመቆጠሩ ከተዘረፉት ቅርሶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህ ሰባት ሜትር ተኩል ርዝመት ያለው ሐውልት፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጫፉ ላይ የታሠረበትን ዘንግ በፊተኛው እግሩ ትከሻው ላይ አስደግፎ በኩራት የሚራመድ ግርማ ሞገስ ያለው አንበሳ ከነሐስ የተቀረጸበት ሲሆን፣ የአንበሳው ምስል በጥርብ ድንጋይ በተገነባ ከፍተኛ መሠረት ላይ ቆሟል፡፡ የአንበሳውን ሐውልት ከተሸከመው መሠረት ግድግዳ አራት ገጾች ላይ የዳግማዊ ምኒልክ፣ የልዑል ራስ መኮንን፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና የዐጼ ኃይለ ሥላሴ ምሥል ተቀርጾበት ነበር፡፡ ሐውልቱ የፈረንሳይና ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኩባንያ ለዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያነት በፈረንሳይ አገር ያስቀረጸው ሲሆን መስሪያ ቤቱ ፊት ለፊት ከሚገኘው አደባባይ ላይ ቆሞ ተመርቆ የተገለጠው ሕዳር 22 ቀን 1922 ዓ.ም ነበር፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና ንጉሥ ተፈሪ (በኋላ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ) ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ የይሁዳ አንበሳ ሐውልት በ1932 ዓ.ም ግድም ከመሠረቱ ተነቅሎና ተጓጉዞ ኢጣሊያ ከደረሰ በኋላ ከራስ አሉላ ጋር ሲዋጉ ለተገደሉ ኢጣሊያውያን መታሰቢያ ከተሰራው ሐውልት ግርጌ እንዲቆም ተደርጎ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ ይህ ሐውልት ምርኮኛ መሆኑ እንዲታወቅና የተሸከመውንም የነጻነትና የጥንታዊነት ታሪክ ለማዋረድና የነጻ አገር ምልክትነቱን ለመፋቅ ታስቦ የፋሺስቶች አርማ እና የኢጣሊያ ባንዲራ ተቀርጾ እንዲለጠፍበት ተደርጎ ነበር፡፡ በዓለም ሠላም ወዳድ ኃይሎች ጥረት ፋሺዝምና ናዚዝም ከዓለም የፖለቲካ መድረክ ተዋርደው ለዘላለሙ ወደ ከርሰ መቃብራቸው ሲወረወሩ፤ ነጻነታቸው የተገፈፈባቸውና የተዋረዱ መንግሥታት በተራቸው ቀና ብለው የሚራመዱበት ጊዜ መጣ፡፡ የእንግሊዝና የአሜሪካ ሕብረ ብሔር ኃይሎች ፋሺስቶችን ከምድረ ኢጣሊያ በመጠራረግ በ1937 ዓ.ም የሮማ ከተማን ተቆጣጠሩ፡፡ ሕብረ ብሔሩ ኃይል የመሠረተውና ኢጣሊያን በጊዜያዊነት ይመራ የነበረው “አላይድ ኮሚሽን” የተባለው ጥምር አስተዳደርም የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ የመጣ መሆኑን በመረዳቱ ከቆመበት ሥፍራ ተነቅሎ ወደ እናት አገሩ እንዲመለስ አዘዘ፡፡ በ1939 ዓ.ም በፓሪስ ከተማ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ አገሮችና በኢጣሊያ መካከል የሠላም ስምምነት በተፈረመበት ወቅት፤ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ላደረሰችው ጉዳት የጦር ካሣ ለመክፈልና የዘረፈችውን ቅርስም ለመመለስ ግዴታ ገብታ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ከኢጣሊያ ጋር እንደገና ስትመሰርት፤ በኢትዮጵያ በኩል ቀዳሚ አጀንዳ የነበረው የጦር ካሣ እና የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶችና የጥበብ ውጤቶች መመለስ ጉዳይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አዲሱ የኢጣሊያ መንግሥት ፋሺስቶች የዘረፉትን ቅርስ መመለስ፤ በጦር ካሣ እንዲከፍል ከተወሰነበት ገንዘብ በላይ ከባድ ሆኖ አገነው፡፡ የኢጣሊያ መንግሥት ንብረቶቹን ለባለ መብቱ መመለስ ሙዚየሞቹንና አደባባዮቹን የሚያራቁት መስሎ ስለታየው፤ ቅርሶቹን በዓይነቱ አሰርተን እንስጣችሁ ወይም በለውጡ በሀገራችሁ ሆስፒታል ወይም ትምህርት ቤት እንገንባላችሁ በማለት በድፍረት እስከመጠየቅ ደርሶ ነበር፡፡ በኢጣሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር የነበሩት አቶ አማኑኤል አብርሃም የመንግሥታቸውን የማያወላውል አቋም ለኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ሲያስታውቁ፤ “ይህ ሐውልት (በተለይ የአክሱምን) ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተጠረበ ደንጊያ ብቻ ሆኖ አይታየውም፡፡

ሐውልቱ ለኛ የሁለት ሺህ ዓመት ታሪካችን መታሰቢያ ነው፡፡ እንደዚህ ከመሆኑም የተነሣ በብር የሚለወጥ፣ ባንድ ሆስፒታል ወይም በማናቸውም ዕቃ ምትክ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በልዋጭ እናስቀረው እያላችሁ መጠየቃችሁም፤ ለሕዝባችን ስሜትና ለክብሩ ምንም ዋጋ የሰጣችሁ መሰላችሁ አለመታየታችሁን የሚገልጽ ስለሚመስል ቅር ያሰኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የክብራቸውን ምልክትና የአባቶቻቸውን ቅርስ በብር የሚለውጡ አለመሆናቸውን ለምን አትረዱም? ይህ ሐውልት (እና ሌሎቹም ቅርሶች) ሕዝባችን በወደቀበት ሰዓት በምርኮ ስም የመጣ ነው፡፡ አመጣጡን ስናስብ የመንፈስ ሕመም እንጂ የደስታ ስሜት አይሰጠንም…እናንተም፤ ምክንያት በማብዛትና በደረሰብን ግፍ ላይ የበለጠ ስድብ ከምትጨምሩብን፣ ለእውነተኛ ወዳጅነት ማሕተም እንዲሆን በቶሎ ብትመልሱልን በሁሉም ረገድ የተሻለ ይሆን ይመስለናል” የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ አዲሱ የኢጣሊያ መንግሥት የተዘረፉትን ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ የወረራ ማስታወሻ የሆነ ጌጣቸውን አንስቶ እንደመስጠት ስለቆጠረው ጉዳዩን በቁም ነገር ሊያስብበት አልፈለገም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የተዘረፉት ቅርሶች ያሉበት ሥፍራ በግልጽ ይታወቅ የነበረ ሲሆን፤ ግዙፉ የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ግን፣ የአሜሪካና የእንግሊዝ ጥምር ኃይል ኢጣሊያን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ከአደባባይ ላይ እንዲነሳ ከወሰነበት ወዲህ የተቀመጠበት ቦታ በግልጥ አይታወቅም ነበር የኢጣሊያ መንግሥትም ሐውልቱ የደረሰበት ቦታ አይታወቅም በማለቱ የሚገኝበትን ትክክለኛ ሥፍራ ለማመልከት አልተቻለም ነበር፡፡ የሐውልቱን አድራሻ መጠቆም ባለመቻሉ እና ቅርሱም የጥበብ ሥራ እንጂ ጥንታዊነት ስለሌለው፤ የኢጣሊያ መንግሥትም አምሣያውን አሠርቼ እሰጣለሁ በማለቱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሀሳቡን ወደ መቀበል አዘንብሎ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ አምባሳደር አማኑኤል አብርሐም ሐውልቱ የሚገኝበትን ሥፍራ የሚጠቁም ሰው ቀደም ብለው አሰናድተው ኢጣሊያን ሲያሰልሉ ስለነበር፣ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ የይሁዳ አንበሳ ተደብቆ የሚገኝበትን ሥፍራ ለማወቅ ተቻለ፡፡ ሐውልቱ በአንድ ሰዋራ ስፍራ ላይ ተቀብሮ የተገኘ ሲሆን፣ መረጃው ለኢጣሊያ መንግሥት ተላልፎለት ከተቀበረበት ተቆፍሮ ሊወጣ ቻለ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ሐውልቱን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የኢጣሊያ መንግሥት ዳተኝነት በማሳየቱ ይህ ቅርስ ወደመጣበት አገሩ እንዲመለስ ለመወሰን ከአሥር ዓመት በላይ ፈጅቶበታል፡፡ በመጨረሻም ይህ ታሪከኛ ሐውልት በ1957 ዓ.ም ከኢጣሊያ “ሊብሬቶ ኮሎኮ ቱሪንስ” በተባለ መርከብ ተጭኖ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞውን መጀመሩ ተሰማ፡፡ ሆኖም በአረቦችና በእሥራኤል መካከል በፈነዳው ጦርነት ሳቢያ የስዊዝ ቦይ በመዘጋቱ የተነሳ የመርከቡ ጉዞ ተስተጓጉሎ ሐውልቱ ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለስ እንደገና ብዙ ጊዜ ቆየ፡፡ ሐውልቱ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከኢጣሊያ ተነስቷል ከተባለ ከአራት ዓመታት ዘግይቶ በመሆኑ የስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ሲዘጋ ሐውልቱን የጫነው መርከብ ወደ ኢጣሊያ የተመለሰ ይመስላል፡፡ መጋቢት 26 ቀን 1961 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በተከናወነ ሥነ ሥርዓት ከ36 የስደት ዓመታት በኋላ ወደ አገሩ የተመለሰውን የይሁዳ አንበሳን ሐውልትን የኢጣሊያ አምባሳደር በጊዜው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ለነበሩት ዶክተር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ አስረከቡ፡፡

የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ወደ ነበረበት ትክክለኛ ሥፍራ እንደገና እስኪመለስ ድረስ ሶስት ዓመታት ያህል ያለፈ ሲሆን የተመረቀበት ጊዜም ከ42 ዓመታት በፊት ከተገለጠበት ቀን ጋር ተገጣጥሞ ነበር፡፡ ሕዳር 24 ቀን 1964 ዓ.ም አፄ ኃይለ ሥላሴ እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው በተገኙበት የሐውልት ምረቃው በደመቀ ሥነ ሥርዓት ተከናወነ፡፡ ይህንን ሐውልት ሁለት ጊዜ የመመረቅ እድል የገጠማቸው ዐጼ ኃይለሥላሴ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ቆፍረው ቢቀብሩትም ሆነ ቢያወድሙት ታሪክ አይደመስስም ብለው ነበር፡፡ ወራሪ ጠላት የሚደመስሰው ነጻነትንና መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ታሪክን እና ጥንታዊ ቅርስን ጭምር እንደሆነ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የቆዩት የኢጣሊያ ፋሺስቶች ድርጊት ቋሚ ምሥክር ነው፡፡ ዛሬ በሺህ ዓመታት የሚቆጠር ታሪክ እንዳለን የሚነግሩልንን ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶቻችንን ከመዘረፍ ለማዳን የቻልነው ነጻነታችንን ሳናስደፍር በመቆየታችን የተነሳ ነው፡፡ ምንም እንኳን በኢጣሊያ ፋሺስቶች የተዘረፉብንን ቅርሶቻችንን በሙሉ ለማስመለስ ባንችልም፤ የተወሰኑትንም ቢሆን ተፍጨርጭረን ለማግኘት መቻላችን ከራሳችን አልፎ ታሪካዊ ሐብቶቻቸውን በጉልበት ለተነጠቁ ሕዝቦች መነሳሳትን እንደሚፈጥር ይገመታል፡፡

Read 3836 times