Saturday, 02 February 2013 15:59

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችና እግር ኳስ በደቡብ አፍሪካ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችና እግር ኳስ በደቡብ አፍሪካ
በደቡብ አፍሪካ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው። የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድል እንዲቀናው ስታዲየም ገብተው ድጋፋቸውን በመስጠት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ ድጋፍ አሰጣጣቸውም ከጨዋታው ቀጥሎ የዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛውን ቀልብ ከሳበ ጉዳይ አንዱ ሆኖ አልፏል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የስፖርት አምድ አዘጋጅ ግሩም ሰይፉ በደቡብ አፍሪካ ጨዋታዎቹ በተካሄዱበት ስታዲየም ተገኝቶ ከጥቂቶቹ ኢትዮጵያውያን ጋር እንዴት ደቡብ አፍሪካ እንደገቡ፣ ስለሚገኙበት ሁኔታ እና ስለሰጡት ድጋፍ ጠይቋቸው እንደሚከተለው መልሰዋል፡፡
“ኤርትራዊ ብሆንም ዋልያዎቹን ደግፌአለሁ”
ሰናይ ነጋ

የተወለድኩት በደሌ የሚባል ስፍራ ኢሊባቡር ውስጥ ነው፡፡ከልጅነቴ ጀምሮ ኳስ ስለምወድ እጫወትም ነበር፡፡የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን እዚያው ኢሊባቡር ውስጥ ተማርኩ፡፡ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በአየር ጤና እና በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትያለሁ፡፡በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተነሳው ግጭት ኤርትራዊ በመሆኔ ከቤተሰብ ጋር ወደ ኤርትራ ሄድኩ፡፡ኤርትራ የገባሁት የ23 ዓመት ወጣት ሆኜ ነበር፡፡ በኤርትራ ለ11 ዓመታት በውትድርና ቆየሁ፡፡
የውትድርና ህይወት ሲያማርረኝ በሽሬ በኩል አቋርጬ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እህቴ ስለነበረች እርሷ ጋር ለ15 ቀናት ቆየሁ፡፡
ከዚያ በኋላ በሞያሌ አድርጌ ናይሮቢ ገባሁ፡፡ከሁለት ዓመት የናይሮቢ ቆይታ በኋላ በአውሮፕላን ደቡብ አፍሪካ ገብቼ እዚህ ከነበሩ ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በንግድ ሥራ ተሰማርቼ እየሠራሁ ነው፡፡ኳስ ጨዋታ ብዙም አልከታተልም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲመጣ ግን እዚህ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ስለምሠራ፣ የነበረው መንፈስ ግጥሚያቸውን እንዳይና ቡድኑን ለመደገፍ አነሳሳኝ፡፡ዜግነቴ ኤርትራዊ ቢሆንም የተወለድኩበት ያደግኩበት እና የተማርኩበት አገር ኢትዮጵያ ስለሆነች “ዋልያዎቹን” ደስ ብሎኝ ደግፌአለሁ፡፡

Read 5352 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:56