Saturday, 02 February 2013 16:17

በሰለጠነ ባለሙያ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 20% አይሞላም

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“... እንግዲህ የእናቶች ጤና ሲባል በቅድሚያ እናቶችን ለጉዳት የሚዳርጋቸው የእናቶቹ ወደ ሆስፒታል ያለመምጣት ችግር ነው፡፡ ይህ ምክንያቱ የተለያየ ሲሆን አሁን አሁን ግን መንግስት የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞችን ለህብረተሰቡ ቅርብ በሆነ ሁኔታ እያሰማራ እና እናቶቹም ስለጤናቸው እንዲማሩ እየተደረገ ስለሆነ የተሻለ ነገር አለ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ አይካድም፡፡ እናቶች ለህክምና ወደሆስፒታል ሲመጡም አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ መገኘት ይገባቸዋል፡፡ የህክምናው ባለሙያ ክህሎትና የመሳሰሉት ሁሉ የእናቶችን ጤንነት ለመጠበቅ አንዱም ሳይዛባ በተሟላ መንገድ መገኘት ይገባቸዋል፡፡ ... የጤና ባለሙያው በቂ የሆነ ችሎታ ኖሮት በበቂ መሳሪያ እየታገዘ ህክምናውን እንዲሰጥ ሁኔታዎች መሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ የእናቶች ወደሆስፒታል መምጣት አለመምጣት ምንም ልዩነት የለውም፡፡ ምናልባት ልዩነት ሊባል የሚችለው ወደሐኪም ሳይሄዱ ከእቤት መሞት ወይንም ሐኪም ቤት ሄዶ መሞት በሚል ሊገለጽ የሚችል ብቻ ነው...” ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ /የጽንስና ማህጸን ሕምና እስፔሻሊስት የእናቶችና ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ዶ/ር አብነት ሲሳይ በደብረማርቆስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ገለጹ፡፡

እንደ ዶ/ር አብነት ገለጻ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ አይክ ኢትዮጵያ ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የእናቶችን እና ሕጻናትን ጤንነት በሚመለከት ለሚሰራው ስራ ከተመረጡ ሁለት ሆስፒታሎች አንዱ ሆኖአል፡፡ ደብረማርቆስ ከአማራ ክልል ከትግራይ ደግሞ አድዋ ሆስፒታል ተመርጠው ከተወሰኑ ወራት ወዲህ ስራ የጀመሩ ሲሆን ከሕብረተሰቡ ጋር በተቀናጀ ሁኔታ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ንቃተ ህሊናን የማዳበር ስራ ተሰርቶአል፡፡ በጤና ተቋም ወይንም ወደ ሆስፒታል በመቅረብ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 20ኀ የማይሞላ በመሆኑ ይበልጡኑ እናቶችን ለማዳን ወደ ህብረተሰቡ መውረድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ወደህብረተሰቡ ለመድረስ ደግሞ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ዋናዎቹ ድልድዮች በመሆናቸው በደብረማርቆስ ዙሪያ ያሉትን ሙያተኞች ጠርተን የፕሮግራሙን አላማ ከማስረዳት ጀምሮ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞቹ እናቶችን ከጤና ኬላ ወደ ጤና ጣብያ እንዲያስተላልፉ ከዚያም ከፍ ወዳለ ሆስፒታል የመቀባበልን ሁኔታ በተቀናጀና ስርአት ባለው መንገድ እንዲሰራ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ በማድረግ ስራው ተጀምሮአል፡፡

እናቶች ብዙውን ጊዜ በእርግዝና ጊዜ ክትትል ሲያደርጉ ቢቆዩም ለመውለድ ወደሆስፒታል ወይንም ክትትል ሲያደርጉ ወደቆዩበት ጤና ተቋም የሚሄዱት በጣም ጥቂቶች የመሆናቸው ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ መልኩን በመቀየር እናቶች በወሊድ ጊዜ ወደሆስፒታል ለመሄድ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ዘዴ መምከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህንንም በተገቢው ለማስፈጸም እንዲያስችል ከኢሶግ እንዲሁም ከአይክ ጋር የሚሰራው ስራ የእርግዝና ክትትል ስታደርግ የቆየች እናት በመሀከል ብትሰወር ወደየት እንደደረሰች ፣ወልዳ ይሁን ወይንስ? በምን ምክንያት ? የሚለውን ለይቶ ማወቅና እናቶች ያሉበትን ሁኔታ በሚገባ ተረድተው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማስቻል የሚደረግ ክትትልን ይጨምራል፡፡ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር 5/ጤናጣቢያዎችን ባካተተ መልኩ የእናቶችንና የጨቅላዎችን ሞትና ደህንነት ሁኔታ በክትትል ይመዘግባል ፡፡ በዚህም መሰረት ከአንድ ወር በፊት ስለነበረው አሰራር በዶ/ር... ያለምወርቅ እንደቀረበው ሪፖርት ከሆነ በጤናጣቢያዎቹ ለሚኖረው አገልግሎት አንድ አምቡላንስ ተመድቦ አስፈላጊ በሆነበት ቦታና ሰአት እናቶችን ወደሆስፒታል ማመላለስ ተጀምሮአል፡፡ ሆስፒታሉ በየወሩ ከየጤናጣብያዎቹ ጋር በየወሩ በስብሰባ የሚገናኝ ሲሆን ችግሮችንም ከስር ከስሩ እየተከታተሉ መፍታት የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጤናጣብያዎቹ ለእናቶች ማበርከት ያለባቸውን አገልግሎት ጠንቅቀው እንዲያውቁና እንዲተገብሩ ለማስቻል ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየወሩ በሚኖረው ዳሰሳ የእናቶችን እና ጨቅላዎችን ሞት በተመለከተ በማዋለጃ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሆስፒታሉ በተለያዩ ክፍሎችም ያለው ሁኔታ በሪፖርት እንዲካተት ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእናቶችንና ጨቅላዎችን ሞት በመመዝገቡ ረገድ በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች ያለውን ብቻም ሳይሆን እናቶች በቤታቸው እንዳሉ የተከሰተ ነገርም ካለ በቀበሌና በኤክስንሽን ሰራተኞች አማካኝነት እንዲመዘገብ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ በደብረማርቆስ ሆስፒታል እንደውጭው አቆጣጠር በኦክቶበር ወር 150/አንድ መቶ ሀምሳ እናቶች የወለዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከጤና ጣብያዎች እስከ ሰማንያ ኪሎ ሜትር ከሚደርስ እርቀት በቅብብል የመጡና እራሳቸውም ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ይገኙበታል፡፡ በአጠቃላይ ወደ 27 የሚሆኑ እናቶች ወደሞት አፋፍ ደርሰው የነበሩ ሲሆን ነገር ግን በሆስፒታሉ የተመዘገበ የእናቶች ሞት የለም፡፡ ለሞት አፋፍ እንዲደርሱ ከሚዳርጉዋቸው ምክንያቶችም አንዱ ደም መፍሰስ ሲሆን ሁለት እናቶች የማህጸን መተርተር የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ሁለት እናቶች ደግሞ ከማህጸን ውጭ ያረገዙ ሲሆን ውርጃም የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እናቶች ከወለዱ በሁዋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ አብዛኛውን ለሞት አፋፍ የመድረስ ሁኔታ ማለትም 25 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት የደም ግፊትም ያጋጠመ ሲሆን አስፈላጊውን ሕክምና በማግኘታቸው ከሞት ተርፈዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የትራንስፖርት፣ የምግብ እጥረት እና የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ባለመጠቀም ምክንያት እና ብዙ የወለዱ እናቶችም ለከፋ አደጋ ተጋልጠው ተገኝተዋል፡፡ ወደ ሀያ የሚሆኑ እናቶች በልጅነታቸው ግርዘት የተፈጸመባቸው ሲሆን በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ምክንያት በምጥ ጊዜ ለሚከሰቱ ሕመሞች የተጋለጡም አሉ ፡፡

ለሞት አፋፍ የደረሱ እናቶች እድሜ ከ20-40 የሚደርሱ ሲሆኑ የልጅነት ጋብቻም ለችግር ከሚያጋልጡ መካከል ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍም ህብረተሰቡን በማስተማሩ ረገድ በአቅራቢያው ያሉት የጤና ባለሙያዎች የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ በደብረማርቆስ ሆስፒታል የእናቶችን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ምክንያት ለማወቅ በሚደረገው አሰራር ያጋጠሙ ችግሮችን በሚመለከት የሕመምተኞች የቅብብል ሁኔታ አንዱ ሲሆን ሌላው የኤሌክትሪክ መስመር አለመኖር ነው፡፡ በማዋለድ ረገድ አንዳንድ ተጨማሪ መሳሪያዎች እንደቫኪዩም የመሳሰሉ ማለት ነው እጥረቱ እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ ነገር ግን መፍትሔውን በሚመለከት አንዳንድ ጤና ጣቢያዎች ያለባቸውን የቅጽ እጥረት እራሳቸው በመፍጠር ተገቢውን መረጃ አያይዞ ወደሆስፒታል የመላክ አሰራር ተጀምሮአል፡፡ የኤሌትሪክ አገልግሎትንም በሚመለከት ለአንዳንድ ጤና ጣቢያዎች በቻርጀር የሚሰራ መብራት ለመስጠት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ የህክምና መርጃ መሳሪያዎችም በተቻለ መጠን በጎደለበት ቦታ እንዲሰጥ ሆስፒታሉ የራሱን መፍትሔ ዘርግቶአል፡፡ በአጠቃላይም ከጤናጣቢያዎቹ ጋር በወር አንድ ጊዜ አጠቃላይ ስብሰባ የሚደረግ ሲሆን በሆስፒታሉ ከሰራው ጋር የሚገኛኙት የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በሙሉ ወደጤናጣቢያዎች እየወረዱ የጎደለውን ነገር የማየት ስራ እንዲሰራ ከስምምነት ተደርሶአል፡፡ ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር የሚሰሩ ሳላይት ጤና ጣቢያዎችን በምን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ እና ያለውን ክፍተት ማሟላት እንዲሁም ምላሾችን በተገቢው በመመርመር አስፈላጊውን ማድረግ በሆስፒታሉ የተዋቀረው ቡድን ስራ መሆኑ የታመነበት ስለሆነ የእናቶችንና ጨቅላዎችን ሞት ምክንያት ከማወቅ አንጻር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እሙን ነው እንደ ዶ/ር ያለምወርቅ፡፡

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአለምአቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር በሚያደርገው እገዛ በኢትዮጵያ ከ9/መንግስታዊ ሆስፒታሎችና 45/ ጤና ጣብያዎች ጋር በመተባበር የእናቶችን ሞት ሁኔታ ለማወቅ ለሚሰራው ስራ እንዲረዳ በየሆስፒታሎች መረጃ ለመሰብሰብ እንዲያስችል አንዳንድ ኮምፒዩተር ገዝቶ አከፋፍሎአል፡፡ ዶ/ር አብነት ሲሳይ ከደብረማርቆስ ሆስፒታል የኮምፒዩተሩን አገልግሎት ሲገልጹ ከአሁን ቀደም ባለው አሰራር የህመምተኞች ካርድ በአካል የሚቀመጥ ሲሆን ከቦታ ጥበት የተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ አሁን ግን ኮምፒዩተሩን በማግኘታችን ...ለምሳሌ የዛሬ ሶስት አመት አንዲት እናት ታክማ የነበረ እና ሐኪሙዋ በሌለበት እንደገና ለሕክምና ብትመለስ በኮምፒዩተር የተያዘ መረጃ ካለ በቀላሉ ችግርዋን ለመረዳት እና በወቅቱ ባለው ሐኪም ለመረዳት ትችላለች፡፡ ስለዚህ የህሙማኑን መረጃ በተሙዋላ መንገድ ለረጅም ጊዜ ለማስቀመጥ የሚረዳ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

Read 6747 times