Saturday, 02 February 2013 17:07

ከጅማ እስከ ደቡብ አፍሪካ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

ስደትና የስደተኝነት ኑሮ እንደ ልምድ የሚቆጠር ከሆነ ግርማ በዳዳ የካበተ የስደትና የስደተኝነት ኑሮ ልምድ አለው፡፡ ወደ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካና የመን በመሰደድ የስደተኝነትን አስከፊ ኑሮ ለበርካታ አመታት ተጋፍጧል፡፡ እናም ለጅማው ልጅ ለግርማ በዳዳ ስደት ብርቁ አይደለም፡፡ የሠላሳ ዘጠኝ አመት ጐልማሳ የሆነው ግርማ አስከፊውን የስደተኝነት ኑሮ ዛሬም እየገፋ የሚኖረው በየመን ሁለተኛ ታላቅ ከተማ በሆነችው በኤደን ከተማ ባሳቲን ሰፈር ውስጥ ነው፡፡
የየመን የስደት ጉዞና የባሳቲን ሰፈር የስደተኝነት ኑሮ ክብሩን፣ ስሙንና ቅስሙን ብቻ ሳይሆን አዕምሮውንም አሳጥቶታል፡፡ በኤደን የባሳቲን ሠፈር ብቻ ከሚገኙት በርካታ የአዕምሮ በሽተኛ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ውስጥ ግርማ አንዱ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ በየመን ከሚገኙት በመቶ ሺ ከሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ውስጥ እድለኞች ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉትን ማግኘት አይቻልም ባይባልም እጅግ ከባድ ፈተና መሆኑን ግን ማንም አይጠራጠርም፡፡ አይክደውምም፡፡
የህይወት እጣ ፈንታ በመጨረሻው በየመን ሀገር በኤደን ከተማ ባሳቲን ሠፈር ውስጥ ቢጥሉትም የግርማ በዳዳ እድለ ቢስ ቀጫጭን እግሮች ከጅማ የገጠር አካባቢ ተነስተው በሰፊውና በረጅሙ የስደት አውራ ጐዳና ላይ ገስግሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የጣሉት በደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና በምትገኘው ዚምባብዌ ላይ ነበር፡፡
ከመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የኤደን የመስክ ቢሮ የተገኘው የግርማ ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ተወልዶ ያደገው በኦሮምያ ክልል ጅማ ዞን ሶከሩ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ አባቱና ሁለት ታላላቅ ወንድሞቹ በቡና ምርት ላይ የተሠማሩ መካከለኛ ገቢ አላቸው የሚባሉ ገበሬዎች ናቸው። ግርማም ያደገው ከአመታት በፊት ወላጅ እናቱ በመኖሪያ ቤታቸው በጀመሯት ትንሽዬ ኪዮስክ ውስጥ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በመሸጥ ነው። የእሱ እድሜ ከፍ እያለና አዋቂ እየሆነ ሲመጣ፣ እናቱ ደግሞ እያረጁ ሲሄዱ የሱቁን ስራ ሙሉ በሙሉ ተረክቦ ማከናወን ጀመረ፡፡ ገና የአስራ ዘጠኝ አመት አፍላ ወጣት እያለ እናቱ ሲሞቱም ሱቁን አወረሱት፡፡
ያኔ አባቱም ሆነ ወንድሞቹ የሱቁን ባለቤትነት በማጽደቅ ይልቁንም የበለጠ እንዲያስፋፋው ዙሪያ መለስ ድጋፍ አድርገውለት ነበር፡፡ እሱም ምንም እንኳ አባቱና ወንድሞቹ የፈለጉትን ያህል ባይሆንም ቀድሞ ከነበረበት ሁኔታ በተሻለ ሱቋን አስፋፍቶ መነገድ ያዘ፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሠፈሩ ልጆችና ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር የነበረው ግንኙነት ድንበሩን ያልሠበረና የተወሰነ ነበር፡፡ የሱቅ ነጋዴ እንደመሆኑ መጠን በፈለገውና እንዳሻው ጊዜ እየወጣ አብሯቸው ጊዜ ማሳለፍ አይችልም ነበር፡፡ ከጓደኞቹ ጋር የሚገናኘውና አብዛኛውንም ጊዜ መጫወት የሚችለው እነሱ ወደ ሱቅ ሲመጡ ነው፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር ሱቁ ውስጥ አልፎ አልፎ እየተገናኙ ጫት መቃም ጀመሩ፡፡ በየቀኑ ጫት ከሚቅሙት ጓደኞቹ መካከል አንዱ ሁለት ወንድሞቹ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ነበሩ፡፡
የዚህ ልጅ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ወሬውና ጨዋታው የነበረው ታዲያ ስለ ደቡብ አፍሪካ ድንቅና ተአምራዊ ሀገርነትና ሁለቱ ወንድሞቹ በደቡብ አፍሪካ ስለሚኖሩት የድሎት ኑሮና ስለከፈቱት ቢዝነስ ብቻ ነበር፡፡
ጓደኛው ስለደቡብ አፍሪካና ስለ ወንድሞቹ አውርቶ ቢበቃው ኖሮ በእውነት መልካም በሆነ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እሱም ወንድሞቹን ለመቀላቀል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ እየተዘጋጀ እንደሆነና እነሱም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሄዱ ያደርገው የነበረው ግፊት ቀላል አልነበረም፡፡
በተለይ ከሌሎቹ ይልቅ የሱቅ ባለቤት በመሆኑ የተሻለ አቅም በነበረው በግርማ ላይ የፈጠረው ተጽእኖ ማንም በቀላሉ ሊቋቋመው የሚችለው አልነበረም፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ቢሄድ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይህን የንግድ ልምዱን ተጠቅሞ ሚሊየነር መሆን እንደሚችል፣ አለበለዚያ ግን እድሜ ልኩን ከሱቅ ነጋዴነት ሳይወጣ በድህነት እየማቀቀ እንደሚኖር በወጣ በገባ፤ ባለፈ ባገደመ ቁጥር ግርማን ይሰብከው ነበር፡፡
ዊልያም ጀምስ የተባለ እንግሊዛዊ የስነ - መለኮት ተመራማሪ በ1902 ዓ.ም “The varieties of Religious Experience” በተሰኘው መጽሐፉ “ሰንሰለት ከተሰነጠቀበት ቦታ የበለጠ ጥንካሬ የለውም” በማለት ጽፎ ነበር፡፡
ዊልያም ጀምስ ይህን በማለት ለማስረዳት የሞከረው፣ የሰዎች ደካማ ጐን ምን ያህል ስኬታቸውን በቀላሉ የማበላሸት አቅም ያለው መሆኑን ነው። በእርግጥም ይህ ልጅ ስለ ደቡብ አፍሪካ የተሳሳተ መረጃውን ባልተቋረጠ ሁኔታ በግርማ አዕምሮ ውስጥ በመጠቅጠቅ በትልቁ መዶሻ እየቀጠቀጠው የነበረው የግርማ ሰንሰለት ከተሰነጠቀበት ቦታ ላይ ነበር፡፡
ግርማ የጓደኛውን ይህን ያልተቋረጠ ሃይለኛ ቅስቀሳና ግፊት ሁሌም በጥሞና ቢያዳምጠውም ተግባራዊ አደርገዋለሁ ብሎ ስላልቆረጠ መጀመሪያ አካባቢ በልቡ ጉዳዬ ብሎ አልጣፈውም ነበር። በሌላ አነጋገር ጓደኛው ስለ ደቡብ አፍሪካ የምድር ላይ ገነትነት ቀን በቀን እየሰበከ የግርማን ሰንሰለት ከተሠነጠቀበት ቦታ ላይ በትልቁ መዶሻ ቢቀጠቅጠውም በቀላሉ መስበር አልቻለም ነበር፡፡
ነገሮች በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ፡፡ ይሄው ጓደኛቸው ለሶስት ተከታታይ ቀናት በግርማ ሱቅ ውስጥ በሚያካሂዱት የከሰአት በኋላ የጫት ፕሮግራም ላይ መገኘት ሳይችል ቀረ። በአራተኛው ቀን ምክንያቱን ለማወቅ ቤተሰቦቹን ሲጠይቁ ወደ አዲስ አበባ መሄዱ ተነገራቸው፡፡
ዳግመኛ መገናኘት የቻሉት ከስምንት ቀናት በኋላ ሄዶበት ከነበረው ከአዲስ አበባ እንደተመለሰ ነበር። ያን ቀንም ቢሆን የተገናኙት እንደወትሮአቸው ጫት ለመቃም ሳይሆን ለአንዲት አፍታ ቆም ብሎ በቀጣዩ ቀን እሱም ወንድሞቹ ወዳሉበትና በአፍሪካ የምትገኝ የምድር ላይ ገነት እያለ ወደሚያቆላምጣት ደቡብ አፍሪካ እንደሚሄድ ሲነግራቸው ነበር፡፡ እንዳለውም በቀጣዩ ቀን ሁሉንም ጓደኞቹን አቅፎ እየሳመ ተሰናብቶ በአንዲት ክርክስ ያለች ሎንቺና ተሳፍሮ በጠዋቱ ወደ ጅማ አቀጠነ፡፡ ከጅማም ወደ አዲስ አበባ፡፡ ከአዲስ አበባም ወደ ደቡብ አፍሪካ፡፡
ይህ ጓደኛቸው ይህን ረጅም ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት ግን ለጓደኞቹ በተቻላቸው መጠን ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሰደዱን ነገር ችላ እንዳይሉት አደራ ሲላቸው፣ ለግርማ ግን ሁለት የስልክ ቁጥሮችና የአንድ ሰው ስም የተፃፈበት ቁራጭ ወረቀት በመስጠት “የእኔን ጉዳይ የጨረሰልኝ ያገራችን ሰው ነው፡፡ ደውልለት” በማለት በጆሮው ሹክ ብሎት ነበር፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ጓደኛው ለረጅም ጊዜ ሲቀጠቅጠው የነበረውን የግርማን ሰንሰለት መበጠስ የቻለው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ እንዴት ቢባል ግርማ ሀሳቡን የቀየረውና ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሄድን ጉዳይ ዋነኛ ጉዳዩ አድርጐ ቀን ከሌት ማሰላሰል የጀመረው ከዚህ ጊዜ በኋላ ስለነበር ነው፡፡
ግርማ ይህን ነገር በአብዛኛው በማመንታት ልብ እያሰላሰለ ጥቂት ወራት ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻ “የመጣው ይምጣ” በሚል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ቁርጥ አድርጐ ወሰነ፡፡
እናም ከእለታት ባንዱ ቀን ይህን ውሳኔውን ለአባቱና ለታላላቅ ወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ ሁሉም አልተቃወሙትም፡፡ በተለይ አባቱ “አዎ እዚህ ምንም ጠብ ከማይልባት ሱቅ ውስጥ ተቀርቅረህ ጫት ስትቆም ከምትውል እዛ ሄደህ የእድልህን ብትሞክር ይሻልሃል፡፡” ነበር ያሉት፡፡
ግርማ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሰደድ “የመጣው ይምጣ” በሚል የወሰነው ውሳኔ ልክ ቻይናውያን “ሁሌም ቢሆን ለስህተት ትንሽዬ ቦታ ተው” እንደሚሉት አይነት ነበር፡፡ አባቱ ባቀረበው የስደት ሀሳብ እንዲህ በቀላሉ በመስማማት ይደግፉኛል ብሎ ግን ጨርሶ አላሰበም ነበር፡፡ ግርማ ከዚህ በኋላ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ያ ጓደኛው “የእኔን ጉዳይ የጨረሰልኝ ያገራችን ልጅ ነው ብሎ ስልክ ቁጥሩን ጽፎ የሰጠውን “ያገራቸውን” ልጅ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ደወለ፡፡
ግርማ ያን ያገራችን ልጅ ነው የተባለውን ሰውዬ ለተከታታይ ሁለት ሳምንት በተሰጠው የስልክ ቁጥር እየደወለ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልሳካ ብሎት ተስፋ ቆርጦ፣ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጐ ለመተው እየዳዳው ባለበት ወቅት ነበር ድንገት በስልክ መገናኘት የቻሉት፡፡ ሰውየው ሰዎችን ወደ ውጪ ሀገራት በተለይም ወደ አረብ ሀገራት የሚልክ ደላላ ነበር፡፡ ከግርማ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ ከደቡብ አፍሪካ ይልቅ ወደ አረብ ሀገራት ቢልከው በክፍያውም ሆነ በቪዛ ጉዳይ እንደሚቀለው፣ የግድ ደቡብ አፍሪካ መሄድ አለብኝ ካለና ሰማኒያ ሺ ብር መክፈል ከቻለ ግን እንደሚልከው አስረዳው፡፡
ግርማ ደላላው የጠየቀውን የገንዘብ መጠን ሲሰማ ክው ብሎ ቢደነግጥም የቻለውን ያህል አጥብቆ ለመደራደር ሞክሯል፡፡ ለማስቀነስ የቻለው ግን አምስት ሺ ብር ብቻ ነበር፡፡
ደላላው ከ75 ሺ ብር ሽራፊ ሳንቲም እንደማይቀንስለት ሲረዳ ውሳኔውን በማግስቱ ስልክ ደውሎ እንደሚያሳውቀው በመንገር ተለያዩ፡፡ ወዲያውኑም ገንዘብ የሚያስቀምጥበትን ቀይ ቀለም የተቀባች ትንሽዬ የእንጨት ሳጥን ከፍቶ በውስጡ ተቀምጦ የነበረውንና በአይነት በአይነት በላስቲክ የታሰረ ገንዘብ አውጥቶ፣ ልቡ ጭንቀት ይሁን ደስታ ጨርሶ ባልለየለት ዝብርቅርቅ ስሜት አለመጠን እየመታበት መቁጠር ጀመረ፡፡ አንድ ሁለት፣ አስር፣ ሃያ፣ መቶ፣ ሁለት መቶ አንድ ሺ ጆሮው ላይ የሚያቃጭለው ደላላው መክፈል አለብህ ያለው 75 ሺ ብር ነው፡፡ እናም ልቡ እየመታበትና እጁም እየተንቀጠቀጠ ብሩን መቁጠር ጀመረ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 5893 times