Print this page
Saturday, 09 February 2013 10:41

‹‹አንድነት›› የማተምያ ማሽን ለመግዛት ገቢ ሊያሰባስብ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) በማተሚያ ቤት ዕጦት ምክንያት ለተቋረጠው የፓርቲው ልሳን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶች እና እርዳታዎችን አሰባስቦ የማተሚያ ማሽን ለመግዛት ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው በትናንትናው ዕለት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር ያህል የመንግሥት በሆነው ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየታተመ በየሣምንቱ ማክሰኞ ለገበያ ይቀርብ የነበረውን “ፍኖተ ነፃነት” የተባለ የፓርቲው ጋዜጣ ወደ አንባቢው ለመመለስ በውጭ እና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ደጋፊዎቹ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ በማሰባሰብ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የማተሚያ ማሽን ለመግዛት አቅዷል፡፡

በዕለቱ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደተናገሩት፤ በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመ ማንኛውም ፓርቲ የራሱን ልሣን የማሳተም መብት እንዳለው ሕጉ ቢደነግግም፤ መንግሥት ማተሚያ ቤቶች ላይ በሚያደርገው የተለያዩ ጫናዎች ምክንያት በተፈጠረ ፍርሀት ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን ደረሰኝ ማሳተም እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡

በማተሚያ ቤት ዕጦትም ለአባላቱና ለኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት የሚገለገሉበትን ጋዜጣ ማተም እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡ በማተሚያ ቤት ምክንያት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተጣለውን እገዳ ለመታገል የማተሚያ ማሽኑን መግዛት እና የሕትመት ውጤቱን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ፤ ከአስፈላጊነቱ ዓላማ በመነሳት የተለያዩ ጥናቶችን ሲያካሂዱ ቆይተው ማሽኑ ከአጋዥ መሣሪያዎቹ ጋር አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ እንደተረዱ ገልጸዋል፡፡

ማሽኑን ለመግዛት ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር መነጋገር መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን የፓርቲውን ዓላማ እና ፍላጎት ለማሳካት የሚደረገውን የገቢ ማሰባሰብ ፕሮጀክት ለማከናወን ሦስት ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን የገለፀው ‹‹የፍኖተ ነፃነት›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብዩ ኃይሉ ስለ ገቢ ማሰባሰቢያ እቅዱ እንዳብራሩት፤ መጽሐፍትን በመሸጥ፣ ከ30 ብር እስከ 1ሺሕ ብር ለሚለግሱ ኩፖን፣ ከተጠቀሰው ገንዘብ በላይ መለገስ ለሚፈልጉ የቃል ኪዳን ሰነድ መዘጋጀቱን እና ዓላማውን የሚደግፍ ማንኛውም ሰው በባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው ገቢ ማድረግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በኢንተርኔት ኦን ላይን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚቀጥሉት አራት ወራት የገቢ ማሰባሰቡን ሥራ እንደሚቀጥሉ ጠቁሟል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ በበኩላቸው፤ “ፍኖተ-ነፃነት” ለአባላቱና ለህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግም ቢሆን ሃሳቡን ማስተላለፍ ከፈለገ ሊገለገልበት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ፓርቲዎች በማተም ሥራ ላይ ሲሠማሩ ቀረጥ መክፈል እንደሌለባቸውም በህጉ ማስቀመጡን ገልፀው፤ ማሽኑ የሌላ ሰው የህትመት ሥራ እንደማይሠራና “ከፍኖተ-ነፃነት” በተጨማሪም በኦሮምኛና በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚሠራጩ የራሱን ኒውስሌተሮች የመስራት ሃሳብ እንዳለው ዶ/ሩ ገልፀዋል፡፡ የገቢ ማሰባሰቡ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ወራት እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተያያዘ ዜና የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የቋንቋ ምሑር ዶ/ር ኃይሉ አርአያ “ቋንቋና የቋንቋ ፖሊሲ” በሚል ርእስ ነገ ረፋድ ላይ በአንድነት ጽ/ቤት ጥናት እንደሚያቀርቡና ውይይት እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ በውይይቱ ተካፋይ እንዲሆን ግብዣ ቀርቧል፡፡

Read 4133 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 14:14
Administrator

Latest from Administrator