Saturday, 09 February 2013 11:15

“ጅሃዳዊ ሐራካት” ሕገመንግሥቱን ይፃረራል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳ
Rate this item
(20 votes)

‹‹ዶክመንታሪው በፍርድ ሂደቱ ላይ ጫና እየተፈጠረ መኾኑን ያስረዳል›› (የተከሳሽ ጠበቃ)

‹‹ባለቤቴን የበለጠ እንዳከብረው አድርጎኛል›› (የአቡበከር አሕመድ ባለቤት)

‹‹ሚዲያው ፈርዷል፤ከዚህ በኋላ ዳኞች የሚወስኑትን ለመገመት አይከብድም››(የሕግ አማካሪ)
‹‹በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተረጋገጠውን የእምነት ነጻነት በመቃረን፤ የተለየ እምነት፣ አስተሳሰብና አሠራር እንዳይኖርና ሃይማኖታዊ መንግሥት መመሥረት የሚል ፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ ሲንቀሳቀሱ ነበር፤›› ተብለው የተከሰሱትን 29 ሰዎችና ሁለት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት “ጀሃዳዊ ሃራካት” በሚል ያስተላለፈው ዶክመንታሪ ፊልም ‹‹ሕገ መንግሥቱን ይፃረራል›› ሲሉ የሕግ ባለሞያዎችና ቤተሰቦቻቸው ተቹ፡፡ 

አቶ ተማም አቢዴሎ ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ ናቸው፡፡ የአቶ ጁነዲን ባለቤትን ጨምሮ 29 ተከሳሾች በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸው ጉዳያቸው በዝግ ችሎት እየታየ የተጠርጣሪዎችን ምስልና የተናገሯቸውን ንግግሮች በማሳየት “ጅሃዳዊ ሐራካት” በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዶክመንታሪ ፊልም ማስተላለፉን ይቃወማሉ፡፡ አቶ ተማም እንደሚሉት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 3 ያለውን የተከሳሾችን መብት በመጣስ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ፊልም ማስተላለፉ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው፡፡
አንድ ሰው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ያሉት መብቶች ተከሳሹ በራስ ላይ ያለመመስከር መብትን የሚጨምር እንደኾነ የጠቀሱት ጠበቃው፣‹‹ስለተከሰሰ ብቻ ራሱን እንዲከስና እንዲወነጅል እየተገደደ በቴሌቪዥን መቅረቡ በፍርድ ሂደቱ ላይ ጫና እየተፈጠረ መኾኑን ያሳያል›› ይላሉ፡፡ ‹‹ተከሳሾች በደረሰባቸው ከባድ ጫና ራሳቸውን ለመክሰስና ለመወንጀል ተገደዋል›› የሚሉት ጠበቃው፣ መቀረፃቸውን እንኳን እንደማያውቁ ከተከሳሾቹ አገኘኹ ያሉትን መረጃ ይገልጻሉ፡፡ በጠበቃው እምነት በዚህ መንገድ በማስገደድ የተገኘን መረጃ ይዞ በሕግ ባልተፈረደባቸው ንጹሐን ዜጎች ላይ ዶክመንታሪ መሥራቱ የፍርድ ሂደቱን ያዛባል፡፡
የአንደኛ ተከሳሽ አቡበከር አሕመድ ባለቤት ወ/ሮ ሩማና ሡልጣን ኢቲቪ ባስተላለፈው ዘገባ ማዘኗን ገልጻለች፡፡ ‹‹በፊትም የባለቤቴን ንጹሕነት ስለማውቅ አከብረው ነበር፤ አሁን ይብሱኑ እንዳከብረው አደረገኝ፤›› ትላለች ወ/ሮ ሩማና፡፡ በዶክመንታሪ ፊልሙ አቶ አቡበከር ‹‹ዋናው ዓላማ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ነው፤›› የሚል ንግግር ሲናገር መስማቷን የጠቀሰችው ወ/ሮ ሩማና፣ ‹‹ባለቤቴ ይህን ያለው የግብጹ ሙስሊም ብራዘርሁድ ዓላማ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ቀርቦለት የሰጠው ምላሽ›› እንደኾነ ታስረዳለች፡፡ ይኹንና በፊልሙ ቅንብር የእርሱ ንግግር ተቆርጦ ስለዓላማው እንደተጠየቀ በማስመሰል መቅረቡን በማስረዳት ወ/ሮ ሩማና ትከራከራለች፡፡
‹‹ይህ ዐይነቱ ፊልም የሚሠራው ቤተሰቡ እንዲሸማቀቅና አንገቱን እንዲደፋ ለማድረግና ተከሳሹን ሕዝብ እንዲጠላው በማቀድ ነው፤›› የምትለው የተከሳሽ አቡበከር ባለቤት፣ ‹‹እውነታው ግን ወደፊት የሚወጣ ነው፤ አሁንም ቢሆን በእውን እርሱ የተናገረው ሳይሆን የተቀነባበረ ሥራ መኾኑን ሕዝቡ ይረዳል፤›› ብላለች፡፡ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው በመታየት ላይ ስላሉ ተከሳሾች የሚዲያዎችን አዘጋገብ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሞያዎች፣ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹን ጥፋተኛ እስካላላቸው ድረስ ንጹሕ ኾነው የመገመት መብታቸውን የሚጋፋ መኾን እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ውብሸት ሽፈራሁ ‹‹ፍ/ቤት ወንጀለኛ ነው ብሎ ያልፈረደበት ሰው ሁሉ ነጻ ነው ለማለት ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ብዙሀን መገናኛ ትክክለኛ መረጃ እስካላቸው ድረስ በፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ ዘገባ መሥራታቸው ችግር እንደማይፈጥር ነገር ግን ፍርድ ሰጥቶ ከመዘገብ መጠንቀቅ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
የሕግ አማካሪው አቶ ደበበ ሀ/ገብርኤል በበኩላቸው÷ ሕገ መንግሥቱ በፍርድ ሂደት ያለ ማንኛውም ሰው እስከሚፈረድበት ድረስ ንጹሕ ኾኖ የመገመት መብት ያለው በመኾኑ ሕገ መንግሥታዊ መርሖቹ ሊጠበቁለት ይገባል፡፡ ‹‹ሕዝቡ ማወቅ አለበት የሚል ሐሳብ ቢኖር እንኳን የተከሳሹም መብት አለ›› የሚሉት አቶ ደበበ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከፍርድ ቤት ብይን በፊት ንጹሕ ኾኖ የመገመት መብት የአንድ ተጠርጣሪ መሠረታዊ መብት እንደኾነ በአጽንዖት ያስረዳሉ፤ የተጠቀሱትንም ዐይነት ጉዳዮች ማጣራት፣ ፍርድና ውሳኔ መስጠት የሚችለው ሚዲያ ሳይሆን ፍ/ቤት እንደኾነ ይናገራሉ፡፡
ዘገባውን አስቀድሞ ማሳየቱ የፍርድ ሂደቱን ያዛባል የሚሉት አቶ ደበበ÷ ከዘገባው የተነሣ የፍርድ ሂደቱ ሊዛባ የሚችልበትን ኹኔታ ያብራራሉ - ‹‹ዳኞች እንደማንኛውም የኅብረተሰቡ ክፍሎች ዘገባውን ያዩታል፤ በዘገባው ላይ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ያደረገው ተሳትፎ፣ እንዴት ወንጀሉን እንደሠራና እንደፈጸመ በሚዲያው ተላልፏል፤ ከዚህ በኋላ ዳኞቹ የሚያሳልፉት ብይን ምን ሊኾን ይችላል፤ ውሳኔ ለመስጠት ያስቸግራል፡፡አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ ይኾናል፤ ነገር ግን በፍርድ ሂደቱ ውስጥ ተከራክሮ ነጻ ሊወጣ ይችላል፡፡ በዳኛው አእምሮ ውስጥ ተከሳሹ ወንጀሉን ፈጽሞ ይኾናል አይኾንም የሚለውን ጥርጣሬ መፍጠሩ በራሱ አንድን ተጠርጣሪ ነጻ ሊያደርገው ይችላል፡፡ አሁን ግን አስቀድሞ ሚዲያው ፈረደ፡፡ ከዚህ በኋላ ዳኞች ለመወሰን የሚችሉትን ለመገመት አያዳግትም፡፡››
የሕግ አማካሪው ሚዲያው የመንግሥት መኾኑ ነገሩን እንደሚያከብደው አልሸሸጉም፡፡ እንደ አማካሪው ትችት÷ ምርመራውን ያካሄደው አካል ዶክመንታሪው እንዲዘጋጅ ማድረጉ በፍ/ቤት ያለውን ክርክር ያደክመዋል፡፡ ባደጉና ዲሞክራሲያዊ አገሮች ያሉት ሚዲያዎች እንዲሠሩ የሚደረገው በገለልተኝነት ነው፡፡ ዶክመንታሪውን ያቀረበው የመንግሥት ሚዲያ ነው፤ ስለዚህ የመንግሥት አቋም እንደሚንጸባረቅ ግልጽ ነው፤ ፍ/ቤቶችም የመንግሥት የፍትሕ ተቋማት ናቸው፤ የግል ሚዲያ ቢኾን አድራጐቱ ትክክል ባይኾንም ይሻላል ይላሉ፤ አማካሪው በንጽጽራዊ ገለጻቸው፡፡
ከፍርድ ቤት ብይን በፊት የተላለፈው ዶክመንታሪ ከፍ/ቤቱ ብይንና ውሳኔ በኋላ ስለሚኖረው ውጤት ተጽዕኖም አቶ ደበበ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ዶክመንታሪው ከፍ/ቤት ውሳኔ በኋላ ቢቀርብ አስተማሪ ሊባል ይችል ይኾናል›› የሚሉት አቶ ደበበ ‹‹አሁን ግን ተከሳሾቹ በፍ/ቤት ክርክር ነጻ ቢባሉ ሕዝቡ ምን ይላል? ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ናችሁ ተብሎ ምስላቸው በሚዲያ ቀርቧል፡፡ ሕዝቡ የሚያምነው በኢቲቪ የቀረበውን ነው ወይስ ሦስት ዳኞች ተቀምጠው የፈረዱትን ነው? ነጻነታቸውንስ ስንት ሰው ያውቀዋል?›› በማለት አቶ ደበበ ይጠይቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ የሲቪልና የፖለቲካ ቃል ኪዳን ስምምነት መብቶች (ICCPR) ከፈረሙት አገሮች አንዷ ናት፡፡ ይኸው ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነድ በአንቀጽ 14 የከሳሽና የተከሳሽ እኩልነትን ይደነግጋል፡፡ በወንጀል አድራጎት ክሥ ጊዜ ከሳሽ መንግሥት ስለሚኾን የእኩልነት መብቱ ሊጠነክር ይችላል በሚል ሰነዱ የሚያስቀምጠው ነገር አለ፡፡
‹‹እነዚህ ተከሳሾች በመንግሥት ሥር ናቸው፤›› የሚሉት አማካሪው፣ ብዙ ነገሮችን ለማግኘትና በቀላሉ ማሟላት ስለማይችሉ አገራችን በፈረመችው የሲቪልና የፖሊቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት መሠረት ራሳቸውን የመከላከል ችሎታቸው በውል መከበር ይገባው እንደነበር አቶ ደበበ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጅሃዳዊ ሓራካት›› የፍ/ቤትን የአሠራር ነጻነት እንደሚጋፋ በብዙዎች ተትችቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙን እንደሚያስተላልፍ ካስታወቀበት ወቅት ጀምሮ የተከሳሾቹ ጠበቆች ጉዳዩ ከሚታይበት ከፍተኛ ፍ/ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት እግድ በማምጣት ለኢሬቴድ ቢሰጡም ድርጅቱ ዶክመንታሪውን ከማስተላለፍ አልተከለከለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የተከሳሽ ጠበቆች በኢሬቴድ ላይ ክሥ በመመሥረታቸው የድርጅቱ ሓላፊዎች በትላንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ታዝዘው ነበር፡፡ ዳኛው ጉዳዩ በፍ/ቤቱ ሊታይ እንደማይችል ገልጸው፤ ይህም የኾነው ጠቅላይ ፍ/ቤት ክርክሩ እንይካሄድ ባስተላለፈው እግድ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ‹‹ምንም ዐይነት እግድ ሳይደርሰን እንዴት ውሳኔ ይሰጣል?›› ቢሉም ፍ/ቤቱ ጥያቄያቸውን ሳይቀበል የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን መስማቱን ቀጥሏል፤ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማትም ለየካቲት 6 ቀን 2005 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ጥቅምት 18 ቀን 2005 ዓም ክሥ ተመሥርቶባቸው በማዕከላዊ ምርመራና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከሚገኙት 29 ተከሳሾች ውስጥ አንዷ ሴት ስትኾን ሃያ ስምንቱ ወንዶች ናቸው፡፡ ተከሳሾቹ ለተወሰነ ጊዜ በግልጽ ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ ቢቆይም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ግን በዝግ ችሎት መታየቱን ቀጥሏል፡፡እስከ አሁን ባለው የችሎቱ ውሎ 197 የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል በ10 ተሰምቶ ያልቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በ16 ቀናት ውስጥ የ27ቱ ብቻ መሰማቱን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡

 

Read 7064 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 13:35