Print this page
Monday, 07 November 2011 12:46

ሰውን “ሰው” የሚያደርገው ምንድነው? ከእኛ ይልቅ የጥንቶቹ ዘመናዊ ነበሩ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(3 votes)

ሦስት ታላላቅ ሰዎች በአራስነታቸው በቅርጫት ተደርገው ወደ ወንዝ ተጥለዋል፡፡ ያውም በወላጅ እናቶቻቸው፡፡ (ካማተብን በኋላ ስንቀጥል) 
የመጀመሪያው ባለታሪካችን ድንጋይ ላይ ታሪኩ ተቀርፆ የተገኘ ግብፃዊ ነው፡፡ የሴማዊ ሥርወ መንግሥት መስራች የሆነው ንጉስ ሳርጎን (Sargon) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ሺህ 360 ላይ በፃፈው የህይወት ታሪኩ እንዲህ ይላል፡፡
“እኔ ንጉስ ሳርጎን፣ ኃይል ያመዘነልኝ የአካድ (AKKAD) ገዢ እናቴ ድንግላዊ የቤተመቅደሱ አገልጋይ ነበረች፡፡ አባቴን አላውቅም፡፡ እናቴ በምስጢር ፀንሳኝ ኖሮ በምስጢር ወለደችኝ፡፡ ትንሽ የቅርጫት ሣጥን አበጅታ እዚያ ከትታኝ ወደ ወንዝ ጣለችኝ፡፡ ብዙ ከተንሣፈፍኩ በኋላ አኪ (AKKI) ሁዳድ ላይ ደረስኩ፡፡ አኪ መስኖ ሲመራ አግኝቶ ከወንዙ አወጣኝ፡፡ እንደ ልጁም አሣደገኝ …” ይላል፡፡

ሁለተኛው ተመሣሣይ ባለታሪካችን የብሉይ ኪዳኑ ሙሴ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት 1ሺህ 5 መቶ አመት አስቀድሞ፣ በግብፅ ልሳነ ምድር ፈርዖን የእብራውያን ሴቶች ወንድ ልጅ ከወለዱ ወደ ወንዝ እንዲጥሉ ባዘዘበት ጊዜ ሙሴ ተፀነሰ፡፡ ተወለደም፡፡ እናቱ “መልካም እንደሆነ ባየች ጊዜ” ይላል ኦሪት ዘፀአት “ሦስት ወር ሸሸገችው፡፡ ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፡፡ ህፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝ ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው፡፡”ሙሴም በፈርዖን ልጅ ተገኝቶ በቤተመንግስት ውስጥ በልዑልነት አደገ፡፡
ሦስተኛው ባለታሪካችን ደግሞ ፈረንሳዊ ነው፡፡ የሒሳብ ሊቁ ዴ-ላምብርት፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ላምብርት፤ ከትዳር ውጭ በመወለዱ እናቱ የሰው አፍ ፈርታ በቅርጫት አድርጋ ወደ ወንዝ ለቀቀችው፡፡
ወንዝ ዳር ሲንሳፈፍ አንድ “ባለእጅ” አግኝቶ እንደ ልጁ አሣደገው፡፡ አድጐ በጂኦሜትሪ ከዘመኑ አስፈንጥሮ የሚያስብ አስደማሚ ሰው ሆነ፡፡
ወዲያ ወዲህ ሳንል፣ ወደ ፅሁፋችን እንብርት ዘለቅን፡፡ እነዚህን ሰዎች “ሰው” ያደረጋቸው ምንድነው? ምላሹን በማድበስበስ የፅሁፍ ዕድሜ ለመግዛት መጣር ተገቢ አይደለምና “ፍርጥ” እናድርገው፤ “ሰው ነው” ለካ ሰው እንደ ጥንቱ ብሉኮ “እስ - በሱ” ድርና ማግ እየሆነ ነው ምድርን ያለበሳት? (ከተገረምን በኋላ ስንቀጥል)
ሳርጎን፣ ሙሴና ዴ-ላምብርት ከሚንሣፈፉበት ወንዝ ብቻ ሣይሆን ከገጠማቸው መጥፎ ዕጣ-ፈንታ ጭምር ነው በደጋጐቹ እጆች ነፃ የወጡት፡፡ ያ ባይሆንና ዛሬ እኛ እንደምናደርገው የጎዳና ወንዝ ያመጣቸውን ጨቅላዎች ገላምጠን እንደምናልፈው ደጋጐቹ እጆች ቢሰበሰቡስ ኖሮ? (አማተብን) ታላቅ ዛፍ የሚወጣት ዘር መና ሆና ልትቀር፡፡
ሰውን ሰው የሚያደርገው ሰው ነው፡፡ ሰው ያለሰው ”ሰው” ሲሆን የታየው በግሪኮቹ አማልክቶች መለኮታዊ ገድል ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የሮማ ከተማን የቆረቆሩት ወንድማማቾች ሬሙለስና ሬሙስ በህፃንነታቸው የእንጀራ አባታቸው አሙሊዎ ቢጥላቸው፣ የተቀደሰችው ተኩላ ጡት እያጠባች ሞግዝታ አሣደገቻቸው፡፡ ምንም እንኳን ሁለቱ ወንድማማቾች የተኩላ የአደራ ልጅ ቢሆኑም አሳዳጊያቸውን ሳይሆን ዘራቸውን ተከትለው “ሰው” ሆኑ፡፡ ሮማንም ቆረቆሩ፡፡ (ፅሁፋችን እዚህጋ’ኮ ቢገታ “ሰውን ሰው” ያደረገው ተኩላ ነው” ተብሎ ሊቀር ነበር፡፡ ግን እንቀጥላለን የጥቂት አራዊታዊ ተሳትፎዎችን እየዘከርን) አማልከተ አማልክት ዜውስ “አማልቲያ” ከተባለች ፍየል ነው የተገኘው፡፡ ቴዲ ደግሞ ከላም፡፡ ሮማን ከውድቀት የታደጋት ቶክቻው ጐተስ አራዊቶች በደቦ ያሳደጉት የአራዊቶች ሁሉ ጉዲፈቻ ነው … (ነጠብጣቡ አቋረጥነው እንጂ አላበቃም ማለት ነው)
እውነታው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ሰውን ሰው ካላሳደገው “ሰውነቱን” ከየትም አያገኘውም፡፡ ሰው “ሰው” ለመሆን ከሰው መወለድ ብቻ አይበቃውም፡፡ “ሰው” በሚያደርጉ ሰዋዊ ተክህኖዎች በኩል ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሰው ዘሩን ሳይሆን አስተዳደጉን ነው የሚከተለው፡፡ ካስፈለገ አርስቶትልን መጠየቅ ይቻላል፡፡ “የሰው ልጅ ሁለት ልደት አለው” በማለት ምላሽ ይሰጠናል፡፡ በአካል መወለድ እና በባህርይ መወለድ አንድ ልጅ በአካል ከእናት መወለዱ ብቻ “ሰው” አያደርገውም፡፡
በባህርይ ከማህበረሰብ መወለድ ይጠበቅበታል፡እንግዲህ በቅርጫት ወደ ወንዝ ወይም በዱላ ወደ ጐዳና የተጣለ ልጅ ዋነኛ አደጋው “ሁለተኛ ልደቱን” ማጣቱ ነው፡፡ “የመጀመሪያ ልደቱንማ አንዴ አግኝቶታል፡፡ ተኩላም ጡት እያጠባ ያሳድገዋል፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡፡
Lucien Malson የተባለ የሥነ-ልቦና ተመራማሪ አንድ አስደናቂ መፅሐፍ ፅፏል፡፡ ርዕሱ “Wolf Children” ይሰኛል፡፡ የሚተርከው በህፃንነታቸው ተጥለው አውሬ ስላሳደጋቸው ልጆች ነው፡፡ ስለ ልጆቹ የቀረቡት አንዳንድ መዛግብት እንደሚጠቀሙት ልጆቹ የአሣዳጊዎቻቸውን የአውሬዎች ባህርይ የሚያንፀባርቁና ከአካላቸው ውጭ ምንም የሰው ጠባይ የማይታይባቸው ናቸው፡፡ በ1799 ዓ.ም መካከለኛ ፈረንሳይ ውስጥ አንድ የ11 ዓመት ልጅ ከተኩላዎች ጋር ተዳብሎ ሲኖር ይገኛል፡፡ ዤን ኢታርድ “ቪክቶር” የሚል ስም ስላወጣለት ስለዚህ ልጅ ባህርይ ተከታታይ ጥናት አድርጓል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ልጁ በሦስት ስፖርተኞች ከጫካ ተጠምዶ ተያዘ፡፡ ልጁ የቀረበውን ሰው ሁሉ በአውሬ ቁጣ በጥፍሩና በጥርሱ ለማጥቃት ይሞክር ነበር፡፡ ከተኩላዎች ጋር በማደጉ፣ ምግቡ ከውሾች ጋር ሲሰጠው ብቻ በደስታ እየተሻማ አጐንብሶ በአፉ ይመገባል፡፡”
ዤን ኢታርድ 200 ያህል ገፆች በሸፈነ የክትትል ሪፖርቱ ቪክቶር ያሳየውን ለውጥ መዝግቦ ይዟል፡፡ አራት አመት በፈጀ የማረም ጥረት ልጁ በመጠኑም ቢሆን ከአውሬነት ሊላቀቅ ችሏል፡፡
የማልሰን “ዎልፍ ችልድረን” መፅሐፍ ከ1344 እስከ 1961 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ አውሬዎች ያደጉ 54 ልጆችን በሰንጠረዥ ይዟል፡፡ ከተኩላዎች በተጨማሪ ድቦች፣ ዝንጀሮዎች፣ የሜዳ በጐች፣ አቦሸማኔዎች፣ ግሥላዎች … የሰው ልጆችን ከወደቁበት አንስተው አሳድገዋል፡፡ የማልሰን ማጠቃለያ ግን “The fact is that human behavior does not depend on heredity to the same extent as animal behavior.” የሚል ነው፡፡ (የሰው ልጅ እንደ እንስሳት ከወላጆቹ የወረሰው ጠባይ ላይ ተመርኩዞ የሚኖር እንዳልሆነ ነው እውነታው የሚያስገነዝበን እንደ ማለት ነው)
ማልሰን ሰውን “ሰው” የሚያደርገው አውሬ አይደለም፡፡ እያለን ነው፡፡ እርግጥ ሰው የገዛ ልጆቹን ሲጥል ክቡራንና እመ ክቡራት አውሬዎች አንስተው በማሳደጋቸው ሳናመሰግናቸው አናልፍም፡፡ ደግሞም’ኮ አቅቷቸው ጥለዋቸው ባይሆንም ሰርቀን የእነሱን ደቦሎች፣ ቡችሎች፣ ጫጩቶች፣ ግልገሎች … አሳድገናል፡፡ ብቻ ሰው በመሆናችን፣ በማሰብ ልቀታችን፤ እየተመራን ከአውሬዎች በተሻለ ወልደን የመጣል ብቃት አዳብረናል፡፡ (ሳናስበው ልንማረር ነው እንዴ? በሉ፣ “ጐመን በጤና” ወደሚተረትበት ልሣነ ምድር እንዳማረብን)
ምንም እንኳን፤ መገዛትን የማናውቅ ህዝብ ብንሆን፣ ምንም እንኳ “ወንድ ልጅ ከወለዳችሁ ወደ ወንዝ ጣሉ” የሚል ባዕድ የፈርዖን ጌታ ባይኖርብን … አገራችን የልጆች ገነት አልነበረችም፡ ምክንያቱም ጦርነት፣ ረሃብ፣ በሽታ “ሠልስቱ አጋዕዛት” (ሦስቱ ገዢዎች) በሆኑበት ግዛት የህፃናት ገሃነም እንጂ ገነት ሊኖር ስለማይችል ነው፡፡ ይልቅ ግርም የሚለን በዚህ ሁሉ የጦርነት መዓት፣ በዚያ ሁሉ የረሃብ ዶፍ፣ በዚያ ሁሉ የበሽታ መቅሰፍት መካከል ህፃናት እምን ጥግ ተሸጉጠው ጅምር የትውልድ ጉዟቸውን ያጠቃልሉ ይሆን? የሚለው ነው፡፡ (ተአምረ ተአምራት ብለን ስንቀጥል)
በጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ መካከል ልጅ የማሣደግ የወላጅነት ፍዳው ብዙ ነው፡፡ ጭንቀቱ ከላይ እስከ ታች ያጠቃለለም ይመስላል፡፡ እስኪ በዚህ ታሪክ ዋቢነት እውነታውን እናረጋግጥ፡-
አንድ ጊዜ ነው አሉ …
… ንጉሥ ምኒልክና ንጉስ ተክለኃይማኖት በስምምነትና በፍቅር ሲኖሩ እንደ ማንኛውም ወራጅ አደራ ቃል ተለዋወጡ፡፡ “እኔ ብሞት የልጆቼን ነገር አደራ” አሉ ንጉስ ተክለ ኃይማኖት፡፡ “እኔም ቀድሜህ ከሞትኩ የልጆቼን ነገር አደራ” አሉ ንጉስ ምኒልክ (የወላጅነት ሥጋቱ የት ድረስ የተንሰራፋ ነው ጃል?) ያም ሆነ ይህ ንጉስ ተክለኃይማኖት በሞት ይቀድማሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉስ ምኒሊክ ንጉሰ ነገሥት ሲሆኑ ቃላቸውን ጠብቀው የንጉሥ ተክለኃይማኖትን ልጅ ራስ ኃይሉ የጐጃም አስተዳደሪ ሆነው በአባታቸው እግር እንዲተኩ አደረጉ፡፡ ሆኖም አዲሱ ተሿሚ በህዝቡ ላይ የአስተዳደር በደል እየፈፀሙ ስላቃቱ፣ አፄ ምኒልክ እንጦጦ ያስጠሩዋቸውና ለሰባት ቀን እንዲታሰሩ ያዛሉ፡፡ ራስ ኃይሉ እስር ላይ እንዳሉ ተረስተው ሰባት ዓመት ደብረ ብርሃን ስለታሰሩ እንዲህ በማለት ለአፄው ላኩባቸው፡፡
“ሟች አደራ ይላል እሺ ይላል ቀሪ፣
መቼም የለ ብሎ ቆሞ ተናጋሪ፤”
ነገሩ አፄ ምኒልክን እጅግ አድርጐ ህሊናቸውን ቆረቆራቸው ይባላል፡፡ “አስኮነነኝ” በሚል ራሱን ፈትተው በቅሎ ከነመጣብሩና ብር ጨምረው ሰጥተው፣ አስደሰተው፣ ከሰው ወደ ጐጃም ላኳቸው፡፡ አደራ ሰጪና ተቀባይ ከምድር በላይ ከፍ ባለው ህሊና በተመዘገበው ውል ይወቃቀሳሉና በሁለቱ መካከል ያለ ልጅ ሁልጊዜም ከለላው አይጓደልም፡፡
ራስ ኃይሉ የአጤ ምኒልክ የአደራ ልጅ ነበሩ ማለት ነው፡፡ በጥንታዊት ኢትዮጵያ በችግር ፅናት ኅብረተሰቡ ህፃናትን ወደ ጎዳና “ፈሰስ” እንዳያደርግና ማህበራዊ ምሥቅልቅሎሽ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከያ ትግግዝ ይደረግ እንደነበር አንዳንድ የባህል ቅሪቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከአደራ ልጅ በተጨማሪ ጉዲፈቻ፣ የጡት ልጅ፣ የክርስትና ልጅ፣ የማደጎ ልጅ፣ የቤት ውልድ ….
እነዚህ ነባር የህፃናት መጠጊያ ባህላዊ “ቤቶች” ህፃናት በህይወት እንዲቆዩ የሚያግዝ ዘዴ ብቻ አይደለም፡፡ ሁለተኛው “ሰው የመሆን” ልደት በተገቢው ሳይጓደል የሚከናወንበት ተቋም ነው፡፡ ለምሳሌ የጉዲፈቻን አፈፃፀም እንይ፡-
አንድ የጥንት ማህበረሰብ ሴት ጉዲፈቻ ወስዳ ህፃን ለማሳደግ ስትወስን ያለባትን የወላጅነት ግዴታ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ በተለይ ልጅዋን ከአራስ ቤት የምትቀበለው ከሆነ እንደወለደችው ሁሉ ለመታረስ ቡሉኮ ትጋርዳለች፡፡ ቅቤ ተቀብታ ሙክት ታርዶላት፣ የገንፎ እህል ተዘጋጅቶላት አርባ ቀን ከቤት ሳትወጣ ትታረሳለች፡፡ ጎረቤት፣ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ እንደወለደች ተቀብሎ የአራስ ጥሪ ይዞ ይመጣል፡፡ የጉዲፈቻ አባትም በበኩሉ እንደ ወላጅ አባት ለጉዲፈቻ አራስ ሚስቱ ሙክት ያርዳል፡፡ ወንድ ከሆነ ጥይት ይተኩሳል፣ እንኳን ደስ ያለህ ይባላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ነፍስን ከሥጋ በሚለይ መሃላ አባትነቱ ይረጋገጣል፡፡ “ከልጆቼ ብለየው ይለየኝ፣ ከልጆቼ ብነጥለው ይነጥለኝ፣ ከልጅነት መብቱ ብፍቀው ከሰማይ መዝገብ ይፋቀኝ …” ይላል፡፡ በዚህ መንገድ የባዕድ ወላጆች ጋር የሚያድገው ልጅ ከሌሎች የተለየ አድልኦ አይደረግበትም፡፡ በመሆኑም ጉዲፈቻው ልጅ ከተወለዱት ልጀች እራሱን ነጥሎ ማየት ከመቸገሩ የተነሳ ሲያድግ እውነታውን ለመቀበል ያዳግተዋል፡፡ (ልንጨዋወት ተገናኝተን መማረራችንን ማስቀረት ተስኖን ቆየን) ይሄንን ነባር ባህላዊ “ቤት” ስናፈርስ ነው የዛሬ ልጆች “ወላጅ አልባ” ለመባል የበቁት፡፡ “ወላጅ አልባነት” ወደ “ትውልድ አልባነት” የሚመራ ጅምር ጉዞ መሆኑን የተረዱት የጥንቶቹ ናቸው፡፡ እነርሱ ያበጁትን መከላከያ “ቅጥር” ዋጋ አሳጥተን አፍርሰን ለተንጋጠጠ ማኅበራዊ ቀውስ እራሳችንን አጋልጠናል፡፡
ልጆቹን ከጥቃት የሚከላከል ማህበራዊ አደረጃጀት ያለው ኅብረተሰብ፣ እንደኛ ምንም ከሌለው ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ትውልድ የበለጠ ሥልጡን ነው፡፡ ከአሁኖቹ ከእኛ፣ የጥንቶቹ እነሱ የተሻሉ ዘመናዊ አኗኗር የነበራቸው ዘመናዊዎች ነበሩ ለማለት ነው፡፡

 

Read 5677 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:53