Saturday, 09 February 2013 12:29

የፕላስቲክ ጠርሙሶች ተደጋጋሚ አገልግሎትና የጤና ጠንቃቸው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

የተጣራ ተፈጥሮአዊ የማእድን ውሃን በፕላስቲክ ጠርሙስ አሽጐ ለገበያ በማቅረብ ረገድ ሃይላንድ የተሰኘው ፋብሪካ ቀደምት ነው፡፡ የማእድን ውሃን ለአገራችን ህዝብ ያስተዋወቀው ይህ ፋብሪካ፤ለጥቂት አመታት ሲሰራ ቆይቶ በከፍተኛ ኪሳራ ከገበያ ቢወጣም ስሙን ለታሸጉ ውሃዎች መጠሪያነት ትቷል፡፡ ዛሬም ድረስ አብዛኛው ሰው በተለያዩ ፋብሪካዎች እየተጣሩና እየታሸጉ የሚወጡትን የተፈጥሮ የማእድን ውሃዎች ሃይላንድ ውሃ እያለ ነው የሚጠራው፡፡ ከአመታት በፊት ከፍ ባለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች ወይም ከውጭ አገር የሚመጡ ዲያስፖራዎች ብቻ ይጠቀሙት የነበረው የታሸገ ውሃ፤ ዛሬ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የተለመደና የሚዘወተር ሆኗል፡፡

ሁለት ሊትሩን የታሸገ ውሃ በአራት ብር ገዝቶ መጠቀም ብርቅ በነበረበት በዚያ ዘመን፤ የፕላስቲክ ውሃ ይዞ በየጐዳናው መታየት እንደዘመናዊነትም ይቆጠር ነበር፡፡ ለጊዜ ምስጋና ይግባውና ዛሬ በአገራችን የተለያዩ ፋብሪካዎች እየተዘጋጁና እየታሸጉ ለገበያ የሚቀርቡ በርካታ የማእድን ውሃዎች ገበያውን አጥለቅልቀውታል፡፡ 

የዛሬ ፅሁፌ የሚያተኩረው በውሃ ምርቱ ላይ ሳይሆን ለታለመላቸው አገልግሎት ከዋሉ በኋላ እንደገና እየታጠቡ ለሌላ ጥቅም በሚውሉት የፕላስቲክ ጠርሙሶች ዙሪያ ነው
እነዚህ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ከየሆቴሎች፣ ካፌዎች፣ ሆስፒታሎች፣ መዝናኛ ስፍራዎችና ከግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ሥራውን እንጀራዬ ባሉ ግለሰቦች እየተሰበሰቡ ለዳግም አገልግሎት ዝግጁ ወደሚያደርጉ ሰዎች ይተላለፋሉ፡፡
የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙሶቹ በአብዛኛው በመጀመሪያው ዙር የአገልግሎት ዘመናቸው እምብዛም የመቆሸሽና የመበላሸት እድል አይገጥማቸውም፡፡ ከተደጋጋሚ አገልግሎት በኋላ ግን የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ውስጣቸው እየወየበ፤ እየሻገተና እየተበላሸ ስለሚሄዱ የእጥበት አገልግሎት ማግኘት አለባቸው፡፡
የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ በተለያዩ ሁኔታዎች የቆሸሹና የተበላሹ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዘይት እቃነት ሲያገለግሉ የቆዩ፣ ወተትና ልዩ ልዩ ፈሳሽ ነገሮችን በመያዝ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ፣ ለውሃ ሽንት መክፈያነት ጥቅም ላይ የዋሉ፤ በርካታ አይነት የፕላስቲክ ጠርሙሶች ለእጥበት ይዘጋጃሉ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ውሃ እንደልብ በማይገኝባቸው ከተሞች ደግሞ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ በከተማዋ የፕላስቲክ ጠርሙሶች እጥበት ወደሚካሄድባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በመዘዋወር ሁኔታውን ለማየት በሞከርኩበት ወቅት ያጋጠሙኝ እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምልከታዬን የጀመርኩት ከኡራኤል ቤተክርስቲያን ወደ 22 በሚወስደው መንገድ ላይ ባለውና በተለምዶ አጐዛ ገበያ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በወራጅ ወንዝ ከሚካሄደው የፕላስቲክ ጠርሙስ እጥበት ነበር፡፡

ስፍራው ከዋናው መንገድ ዳር ቢሆንም ወደ ቦታው ለመድረስ ተዳፋቱን የወንዝ አካባቢ በጥንቃቄ ወርዶ መጠጋት ያስፈልጋል፡፡ ገና ወደ አካባቢው መጠጋት ሲጀምሩ ታዲያ የወራጁ ወንዝ ውሃ ሽታ ይተነፍጋል፡፡ እዚህም እዚያም የሚታየውን እዳሪ በጥንቃቄ አልፌ ወደ ስፍራው ተጠጋሁ፡፡ ውሃውን ማየቱ ያሳቅቃል፡፡ ለእጥበት የተዘጋጁት የፕላስቲክ ጠርሙሶች በየቦታው ተከማችተው አነስተኛ የላስቲክ ተራሮችን ፈጥረዋል፡፡ ብዛታቸውን ያየ አካባቢው የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ማምረቻ ሊመስለው ሁሉ ይችላል፡፡
አንዳንድ መረጃዎችን ሊሰጠኝ የሚችል ሰው ፍለጋ አይኔን አንከራተትኩ፡፡ የእኔ በስፍራው መገኘት እንግዳ ከሆነባቸው ሁለት ወጣቶች ጋር ተፋጠጥን፡፡ ከዚያም አንደኛው መፋጠጡን ለመስበር በሚመስል ስሜት “ምን ጠፋብሽ?” አለኝ፡፡ ለወጣቶቹ ጋዜጠኝነቴን መንገር ለስራዬ እንቅፋት እንደሚሆን ገምቻለሁ፡፡ ወጣቶቹ ስፍራውን መኖሪያቸው፣አጠባውን ደግሞ እንጀራቸው አድርገው የሚኖሩ በመሆናቸው ጋዜጠኛን በቀና ዓይን ሊመለከቱ አይችሉም፡፡ ስለዚህም እንደነሱ በአጠባ ስራ ላይ የተሰማራ ሰው ፈልጌ እንደመጣሁ ነገርኳቸው፡፡ ስሙን ሲጠይቁኝ ድንገት አፌ ላይ የመጣውን ስም ተናገርኩ፡፡ “አዲስ ነው ነባር?” ወጣቶቹ ጠየቁኝ፡፡ ጥያቄው ያልጠበቅሁት ቢሆንም “ኸረ ነባር ነው” አልኩ ደፈር ብዬ፡፡ ትንሽ አሰብ አደረጉና እኔ በነገርኳቸው ስም የሚጠራ ሰው በዚያ አካባቢ እንደሌለ ነገሩኝ፡፡ ፊቴን ወደመጣሁበት ከማዞሬ በፊት “እናንተ እዚህ ነው የምትሰሩት?” ስል ጠየቅኋቸው - የማሰብያ ጊዜ ለመግዛት በማሰብ፡፡ አዎንታቸውን ገለፁልኝ፡፡ “ቆያችሁ?” ደግሜ ጠየቅኋቸው፡፡

ላለፉት ሁለት አመታት በዚሁ ስፍራ በፕላስቲክ ጠርሙስ አጠባ ላይ ተሰማርተው እንደቆዩ፣ ከተለያዩ ስፍራዎች እየተሰበሰቡ የሚመጡትን የፕላስቲክ ጠርሙሶች በወራጁ የወንዝ ውሃ እያጠቡ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚያደርጉና ደንበኞች በተለያዩ ቦታዎች እንዳሏቸው፣ ከደንበኞቻቸው የሚበዙት የኡራኤል ፀበልተኞች እንደሆኑና አንዱን የፕላስቲክ ጠርሙስ በአንድ ብር ሂሳብ እንደሚሸጡ ነገሩኝ፡ “በወንዙ ወራጅ ውሃ?” ያሉት ነገር አስደንጋጭ ነበር፡፡ “በዚህ ውሃ? በዚህ?” አልኳቸው ግራ ተጋብቼ “አዎ ውሃው ተቀድቶ በዕቃ ላይ ሲቀመጥ እኮ ንፁህ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጠርሙሶች ደግሞ ውስጣቸው ውሃ ስለሚኖር እሱንም እያጠራቀምን እንጠቀምበታለን”
ወጣቶቹ ያሉትን ለማመን በጣም ይከብዳል፡ ወራጁ የወንዝ ውሃ የሰገራ ቤት ፍሳሽ የሚመስልና ሽታው የሚተነፍግ ነው፡፡ በዚህ ቆሻሻ ውሃ የታጠበ የፕላስቲክ ጠርሙስ ገዝተው ፀበል እየቀዱ የሚጠጡትን የኡራኤል ጠበልተኞች ለአፍታ አሰብኳቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ከያዛቸው ደዌ ለመፈወስ እምነታቸውን ተስፋ አድርገው ለፀበል የሚሄዱ ህሙማን በተቅማጥ፣ በታይፎይድ፣ በኮሌራና በሆድ ውስጥ ትላትል ህመሞች ተሰቃይተው ለሞት የሚዳረጉባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ ከሦስት አመታት በፊት በፃድቃኔ ማሪያም የጠበል ስፍራ እንዲህ ዓይነት ችግር ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ቀጣዩን የፕላስቲክ ጠርሙሶች አጠባ ቅኝት ለማድረግ የመረጥኩት ለመልሶ ግንባታ በፈረሰው እሪበከንቱ አካባቢ ነበር፡፡ ከኡራኤል የጫነኝ ታክሲ “ፒያሳ ባቋራጭ” እያለ እሪበከንቱ መሀሉ ላይ አወረደኝ፡፡
የፈራረሱት ቤቶች ክምር ስፍራውን የጦርነት ቀጠና አስመስሎታል፡፡ ዋናውን አስፋልት መሀል ለመሀል የሚያቋርጥ አነስተኛ ወንዝ አለ፡፡ እዚህም የፕላስቲክ ጠርሙስ እንደጉድ ይታጠባል፡፡ በቤቶች ፍራሽ መሀል የፕላስቲክ ጠርሙሶች ተቆልለው ይታያሉ፡፡ ስፍራው እንደ ኡራኤሉ ለመጠጋት እምብዛም የሚያስቸግር ባለመሆኑ ነገሩን ቀረብ ብዬ ለመመልከትና የሚያናግረኝ ሰው ፍለጋ ዙሪያ ገባውን እየቃኘሁ ወደ ወንዙ ተጠጋሁ፡፡
እሱባለው ተፈሪ በዚህ አካባቢ ተወልዶ ያደገ የሃያ ሁለት አመት ወጣት ነው፡፡ ትምህርቱን ከ10ኛ ክፍል አቋርጦ ያገኘውን ተባራሪ የቀን ሥራ እንዲሰራ ኑሮ አስገድዳዋለች፡፡ በመልሶ ልማት መኖሪያ ቤታቸው ፈራርሶ ወደ ሃያት ኮንደሚኒየም ከሄዱ በኋላም የእሱ ውሎ እዚህችው የቀድሞ ሰፈሩ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚካሄደው እጥበት በንፅፅር የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

አጣቢዎቹ አንገታቸው እየተቆረጠ ማንጠልጠያ በተበጀላቸው ጀሪካኖች ውሃ ሞልተው ፕላስቲክ ጠርሙሶቹን ያጥባሉ፡፡ በአንድ ጀሪካን ውሃ ሊታጠቡ የተዘጋጁትን የፕላስቲክ ጠርሙሶች መቁጠር ጀመርኩና ሳልጨርስ ታክቶኝ ተውኩት፡፡ ግን ከመቶ በላይ መሆናቸውን አውቄአለሁ፡፡ እሱባለውና ባልደረቦቹ በፕላስቲክ ጠርሙስ አጠባ በቀን ከ30-40 ብር እንደሚያገኙ ነግረውኛል፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙሶቹን ከየሥፍራው እየሰበሰቡ ለሚያመጡላቸው ሰዎች፣ ለአጣቢዎችና ለአዟሪዎች ከፍለው ለመሸጥ የሚያዋጣቸውን ገንዘብ ተምነው ለሽያጭ ያውሏቸዋል፡፡ ፕላስቲክ ጠርሙሶቹን በየፀበሉ ሥፍራ፣ በሶላት ሰዓት በመስጊዶች አካባቢና በአንዳንድ ሱቆች እያዞሩ ነው የሚሸጧቸው፡፡ አንዱን የፕላስቲክ ጠርሙስ 0.60 ሣንቲም ሂሳብ እንደሚሸጡትም እሱባለው አጫውቶኛል፡፡
እነዚህ እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ እየተዘጋጁ ለገበያ የሚቀርቡትና በየፀበሉ ሥፍራ የሚገኙ ህሙማን በብዛት የሚጠቀሙባቸው የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣በጤና ላይ ስለሚያስከትሉት ጉዳትና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ማብራሪያ ይሰጡኝ ዘንድ በአሳሳቢ ጤና ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ዶ/ር አበራ ቋሜ ጠይቅኋቸው፡፡
የፕላስቲክ ጠርሙሶች በባህርያቸው ከአንድ ጊዜ በላይ አገልግሎት መስጠት የማይችሉ መሆናቸውን የጠቆሙት መምህሩ፣ፕላስቲክ ጠርሙሶቹ የተሰሩበት ማቴሪያል ከጥቃቅን ኬሚካሎች በመሆኑና ኬሚካሎቹ ደግሞ በባህሪያቸው ውሃ ውስጣቸው በቆየና የአገልግሎት ዘመናቸው በተራዘመ ቁጥር ወደ ውሃ ውስጥ የመግባት ባህርይ ስላላቸው በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በተደጋጋሚ መጠቀም አይመከርም የሚሉት ዶክተሩ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጠርሙሶቹን አገልግሎት ላይ ለማዋል ከታሰበ ግን በጥንቃቄና በአግባቡ ንጽህናቸው ሊጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ተዘዋውረን በተመለከትንባቸው አካባቢዎች ያስተዋልነውን የፕላስቲክ ጠርሙሶች አስተጣጠብ አንስተንላቸውም፣ በአብዛኛው ቦታ የተለመደና ከፍተኛ የጤና ችግር በማስከተል ላይ ያለ ሃይ ባይ ያጣ ጉዳይ መሆኑን ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በፃድቃኔ ማርያም ፀበል ሥፍራ ተከስቶ የነበረውን የተቅማጥ፣ ትውከትና ሐተት በሽታ ያስታወሱት ዶክተሩ፣ ክስተቱ በበርካታ ፀበልተኞች ላይ ከባድ የጤና ችግር ፈጥሮ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በንጽህና ጉድለት የሚከሰቱት የተቅማጥና ትውከት በሽታዎች በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶባቸው ሊሰራባቸው የሚገባ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ በፀበል ቦታዎችና ህብረተሰቡ በአንድ ቦታ ላይ በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች እየዞረ መሥራት እንዳለበትም ዶ/ር አበራ አስገንዝበዋል፡፡

 

 

Read 2289 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 15:09