Saturday, 16 February 2013 11:43

የ“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ውይይት አዘጋጆች ተሣታፊውን ይቅርታ ጠየቁ

Written by  ዓለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)
  • የካቲት 30 በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ይደረጋል
  • ተቃውሞው በጣልያን መንግስት ላይ ያነጣጠረ ነው

በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነትና ስፖንሰር አድራጊነት ባለፈው እሁድ በብሔራዊ ቲያትር በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ ላይ የተደረገው ውይይት ተሳታፊዎችን ቅር በማሰኘቱ አዘጋጆቹ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ፡፡ በየጋዜጦቹ ላይ በቀረቡት አስተያየቶች ላይ ምንም ለመናገር እንደማይፈልጉ የገለፁት አዘጋጆቹ፤ ተጋባዥ ሆነው የቀረቡት ምሁራን ላነሱት ቅሬታ “ቀድሞም ቢሆን ሁሉም ሰዎች ጥናታዊ ወረቀት ያቀርባሉ አላልንም፤ ግማሾቹ ሃሳብ ያቀርባሉ ነው ያልነው መድረኩን መጠቀም የእነሱ ፋንታ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ ጥሪው አልደረሰንም ለሚለው ቅሬታም ጥሪው የቀረበላቸው በስልክ በመሆኑ ስህተት መፈጠሩን ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ አርአያ ጌታቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

ከዚያ በተረፈ በእለቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋና ስነጽሑፍ መምህር ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው የእሳቸው ወዳጆች የሆኑ ምሁራን ሊገኙ አለመቻላቸውን፤ የተቀሩት ደግሞ ለዝግጅቱ አነስተኛ ግምት በመስጠት ቀርተው ሊሆን እንደሚችል አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡ “በአጠቃላይ ፕሮግራሙ የታሰበውን ያህል የተሳካ ነው ማለት ባይቻልም ህብረተሰቡ በራሱ ለንባብ ትኩረት ሰጥቶ አዳራሹ ሞልቶ መትረፉ ትልቅ ዋጋ የምንሰጠው ነው፡፡” ያሉት አስተባባሪው፤ ምሁራኑ ነገሮችን በቅንነት ተመልክተው ከመውቀስ ይልቅ ጅምሩን አበረታትተው ስህተቱን በቀጣይ እንዲታረም በመጠቆም ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነበር ብለዋል፡፡ አያይዘውም ከሰአት ጋር ተያይዞ ለሚቀርበው ቅሬታም መጽሐፉ ይዘቱ ትልቅ በመሆኑ በሰአት ካልተገደበ ሁለቱ ሰዎች ብቻ ቀኑን ሙሉ አስተያየት ሲሰጡበት ሊውሉ ስለሚችሉ ለተሳታፊው ይበልጥ እድል መስጠት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የካቲት 12 የሰማዕታት ቀንን ምክንያት በማድረግ ሰማያዊ ፓርቲ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚሳተፉበት እንደተዘጋጀ አቶ አርአያ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ሀገር ወዳድ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲታደም ጥሪ ያቀረቡት አዘጋጆቹ በእለቱ ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ውስጥ የፈፀመውን ጭፍጨፋ ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ካሣ መጠየቅ ሲገባው እንዴት ዝም ይላል በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እንደሚንሸራሸሩ ገልፀዋል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የጣሊያን አመራሮች ቤኔቶ ሙሶሎኒ በአርመኖች እና በአይሁዶች ላይ ከሠራው ሃጢያት ውጪ ሌላ በደል እንዳልፈፀመ እየተናገሩ መሆኑን የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤ ይሄንኑ በመቃወም የካቲት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ከስድስት ኪሎ አደባባይ እስከ ጣሊያን ኤምባሲ የተቃውሞ ሠልፍ በፓርቲውና በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አዘጋጅነት እንደሚደረግ አቶ አርአያ ተናግረዋል፡፡

Read 4664 times Last modified on Saturday, 16 February 2013 15:37