Saturday, 16 February 2013 11:52

“ሸንጐ ተሰብስቦ ለሚስቱ ዕውነቱን የማያወራ ባል አያጋጥምሽ!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ተፈላሳፊ ሰው ታርኖፖል የሚባል ቦታ ይኖር ነበር፤ ይላል አንድ የአይሁዶች ተረት፡፡ ይህ ፈላስፋ እያነበበና እየተመራመረ ሳለ የሰፈር ወጣቶች መጥተው “ምክር ስጠን፣ አስተምረን፣ አንድ ታሪክ ንገረን” እያሉ አስቸገሩት፡፡ ፈላስፋውም “ለምን አንድ የውሸት ተንኮል ፈጥሬ አላባርራቸውም?” ሲል ያስብና፤ “ልጆች ወደዚያ አሮጌ የእምነት ቦታ፣ ወደ ምኩራቡ ሂዱ፡፡ እዛ አንድ ትልቅ የባህር ጭራቅ ታያላችሁ፡፡ አምስት እግር፣ ሶስት ዐይን እና እንደ ፍየል ያለ ጢም ያለው ሲሆን መልኩ አረንጓዴ ነው” አላቸው፡፡ ልጆቹ ወደተባለው ቦታ ሮጡ፡፡ ፈላስፋው ምርምሩን ይሠራ ጀመር፡፡ እነዚያን ደደብ ወጣቶች ተጫወትኩባቸው እያለ በሆዱ ፈገግ አለ፡፡ ሆኖም ጥቂት እንደቆየ የብዙ ሰዎች ዱካ ሰማ፡፡ በመስኮት ሲመለከት መአት አይሁዶች ሲሮጡ ተመለከተ፡፡ “ወዴት ነው የምትሮጡት?” ሲል ጠየቃቸው “ወደ አሮጌው የእምነት ቦታ” አሉት፡፡ “አልሰማህም እንዴ? አንድ አረንጓዴ፣ ባለአምስት እግር የባህር ጭራቅ ታየኮ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ ፈላስፋውም በሆዱ “ተንኮሌ ሠራ ማለት ነው!” ብሎ ተደሰተ፡፡

ጥናቱን ቀጠለ፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ግን ሌላ ግርግር ሰማ፡፡ በመስኮት ሲመለከት፤ ሴቱ፣ ህፃኑ፣ ሽማግሌው ሁሉ ይሮጣል፡፡ “ምን ተፈጠረ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ “አንተ ፈላስፋ አይደለህም እንዴ? ስለ ጭራቁ አላወቅህም? አንድ ትልቅ የባህር ጭራቅ ከእምነቱ ቦታ ፊት ለፊት አለ፡፡ እሱን ልናይ መሄዳችን ነው! እንደ ፍየል አይነት ጢም ያለው አረንጓዴ ጭራቅ!!” ፈላስፋው እየሳቀባቸው ሳለ ዋናው አይሁዳዊ ቄስ - የእምነቱ ቦታ ኃላፊ፤ ከህዝቡ ጋር ሲሮጡ አያቸው፡፡ “የሰማያቱ ያለህ! ዋናው የእምነት አባት ካሉበትማ አንድ የታየ ጭራቅ ቢኖር ነው፡፡ እሳት ከሌለ ጭስ አይታይም!” አለና ፈላስፋው ባርኔጣውን አድርጐ፤ ካፖርቱን ደርቦ፤ ከዘራውን ይዞ፤ “ማን ያውቃል የጭራቁ መታየት እውነት ቢሆንስ?” እያለ ከህዝቡ ጋር መሮጥ ጀመረ፡፡ *** “አካፋን አካፋ እንጂ ትልቅ ማንኪያ ነው አንበል” ይላሉ ኬንያውያን፡፡ ይህን አባባል ስለማንነታችን፣ ስለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን፣ ስለፓርቲያችን፣ ስለሀገራችን፣ ስለመከላከያችን፣ ስለሥልጣናችን፣ ስለልማታችንም ሆነ ስለዲሞክራሲያችን ስናወሳ ብናስታውሰው ይበጀናል፡፡

የመዋሸት መጥፎነቱ ልክ እንደፈላስፋው እኛኑ ተብትቦ መልሶ እውነት እንዲመስለን ማድረጉ ነው፡፡ ስለግልፅነት እያወራን የበለጠ ሚስጥራዊ የምንሆን ከሆነ ያው መዋሸት ነው፡፡ ዛሬ ያልነውን ነገ ካልደገምነው ያው መዋሸታችን ነው፡፡ ሰውን በሸራ ኳስ እያጫወትን እኛ በካፖርተኒ የምንጫወት ከሆነ ያው ማጭበርበራችን ነው፡፡ ያለአቅማችን ጉልበተኛ ነን ማለትም ሆነ ጉልበተኛ ሆነን ምስኪን ኮሳሳ ነን ማለትም ያው መዋሸት ነው፡፡ እያየን አላየንም፣ እየሰማን አልሰማንም፣ እያጠፋን አላጠፋንም ማለትም ያው መቅጠፍ ነው! “ያብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክም” ያው መዋሸት ነው! “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለትም ያው መዋሸት ነው! አስገድደን የምንፈፅመውም ሆነ ዋሽተን የምናሳምነው፣ አሊያም በገንዘብ የምንደልልው፤ የዘወትሩን ሰው ቢያስጨበጭብልንም የክቱን ሰው ያሳዝናል፡፡

በመዋሸት የተገነባ አመኔታ ከጥርጣሬ የፀዳ አይሆንም፡፡ አንድ ፀሀፊ እንዲህ ይለናል፤ “የመጠራጠር አዝማሚያችን፤ ከምክንያታዊነታችንና ከእውነታው እያራቀ እሚወስደን፤ በቡድናዊ አመለካከት ውስጥ ስንገባ ነው፡፡ ሁላችንም በየውስጣችን ያለውን ጥርጣሬ፤ የህዝብ ሞቅ-ሞቅና የመንገኝነት ባህል ያበረታታዋል፤ ያጋግለዋል፡፡ ዕምነተ-ሰብ (cultist) የሚያጠቃው ደጋፊ (ቲፎዞ) በቀላሉ ሥልጣን ይሰጣል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ተንኮለኛ አገዛዝን በፈለግህ ጊዜ፡- በሰዎች ያልተፈፀሙ ምኞቶች ላይ በመጫወት እነዚያን ህዝቦች እንደመንጋ ልትነዳቸውና ፍፁም ሠልጣን ልትጐናፀፍባቸው ትችላለህ፡፡ በፅኑ ማስታወስ የሚገባህ ነገር ደግሞ፤ እጅግ ስኬታማ የምትሆነው ሃይማኖትን ከሳይንስ ጋር ቀላቅለህ ስትጠቀም ነው፤ በጣም የረቀቀውን ቴክኖሎጂ ወስደህ፤ ከአንዳች ክቡር ዓላማ፣ ከማይጨበጥ እምነት ወይም አዲስ አይነት ፈውስ ጋር አጣብቀው፡፡ ያኔ መንጋው ህዝብ ይከተልሃል፡፡ አንተ ሳትሻ ልዩ ልዩ ትርጉም ይሰጥልሃል፡፡ አንተ የሌለህንና ያላሰብከውን ችሎታና ሥልጣንም ሰጥቶህ ቁጭ ይላል!” ይሄ እርግማን ነው፡፡ እርግማኑ በመንግሥትም፣ በተቃዋሚም፣ በሰባክያንም፣ በምዕመናንም አንፃር ብናሰላው ያው ነው፡፡ ህዝብን ማታለል ክፉ እርግማን ነው፡፡ የማታ ማታም ያስከፍላል፡፡

የሌለ ጀግና መፍጠርም ሆነ፤ ያለን ጀግና መካድ ሁለቱም ማታለል ነው፡፡ በከፋ መልኩ ሲታይ ራስንም ማታለል ነው፡፡ የሰው ዓላማ የኔ ነው ማለትና የሌላውን ስም የራስ ማድረግ፤ ከኢኮኖሚ ዘረፋም የከፋ ዘረፋ ነው፡- “ገንዘቤን የወሰደ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር የእኔም የእሱም የዚያም ነበር፡፡ ግና ስሜን የሰረቀኝ፤ የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ!” ይለናል እያጐ፤ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሳን፡፡ ውሸት እንደማግኔት መግነጢሳዊ ኃይል አለው፡፡ ማግኔት፤ በአንዳች የማይታይ ኃይል ባካባቢ ያሉ ነገሮችን ይስባል፡፡ እነዚያ ነገሮችም በፈንታቸው የመሳብ ኃይል ያበጃሉ - ባካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች በተራቸው ይስባሉ፡፡ ያንን ኃይል ይዘው ይቆያሉ፡፡

ሰዎችም በአንድ ውሸት ሲሳቡና ያንን ውሸት የራሳቸው ሲያደርጉ ከዚያ የሚለያቸው ኃይል አይኖርም፡፡ ኦርጅናሌ ዋሾውን እንደተአምረኛ ያዩታል፡፡ በዙሪያው ይከባሉ፡፡ እንደመንጋም ይነዳሉ፡፡ (ግሬት ዴ ፍራቼስኮ) በየፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳያችን አንፃር የሌለንን አለን፣ ያለንን የለንም ብለን ከዋሸንና ካሳመንን፤ ተከታያችን ሊደሰትበት፣ አልፎም ሊኮራበት ይችላል፡፡ ያም ሆኖ እንደማናቸውም ነገር ውሸትም ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት ጊዜ (expiry date) አለው፡፡ የዘንድሮ ካፒታሊዝማችን በሶሻሊዝማችን ላይ፤ ዲሞክራሲያችንም በፊውዳላዊ መሰረታችን ላይ፣ “ቫለንታይን ዴይም” በሌለ ፍቅራችን ላይ የተጣደ ከሆነ፤ በሽሮ ላይ ቅቤ ባናቱ ጠብ እንደማድረግ አይነት ነው፡፡ ሹሯችን ዛሬም ያችው ሹሯችን ናትና! ዋናው ነገር እውነቷን፣ እቅጯን አለመርሳት ነው፡፡ “ሸንጐ ተሰብስቦ ለሚስቱ እውነቱን የማያወራ ባል አያጋጥምሽ!” ነው ነገረ-ዓለማችን!

Read 5536 times