Saturday, 16 February 2013 11:58

ዶ/ር ዮናስ አድማሱ፣ የህልፈት ጊዜውን የተነበየ የሥነጽሑፍ ምሁር!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ፈር መያዣ:- “በታላቁ የሥነጽሑፍና የቋንቋ ሊቅ በዶ/ር ዮናስ አድማሱ ሕይወትና የኑሮ ልምድ ዙሪያ አንዳች ነገር የሚጽፍ እርሱ ማን ነው?” ብላችሁ ስትጠይቁት ተሰማው፡፡ እርሱም ቀድሞ ጠርጥሮ ነበር - ጋሽ ዮናስ ለዚህ ጽሑፍ ቅራቢ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር አስተማሪውና አማካሪው ነበር፡፡ በተለይ ይህ ፀሐፊ፣ የመመረቂያ ወረቀቱን ከ1951-1960 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንጉሱ ፊት ሣይቀር ይቀርቡ በነበሩ “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” እና ገጣሚያን ማህበረ ፖለቲካዊ አመለካከትና ሂስ ላይ በማድረጉ ጋሽ ዮናስን የበለጠ ለማወቅ እድል አገኘ፡፡
ጋሽ ዮናስ የታላቅ ወንድሙን የዮሐንስ አድማሱን ፈለግ ተከትሎ፣ ከነሐይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው)፣ ታምሩ ፈይሳ፣ አበበ ወርቄ፣ ኢብሣ ጉተማ ወዘተ. ጋር በውድድር ያሸነፈባቸውን ግጥሞች በኮሌጅ ቀን አቅርቧል፡፡ ዶ/ር ዮናስ እራሱም ተጠኝ የኮሌጅ ቀን ገጣሚ ስለነበረ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ነፍስ ገዝቶ፣ በነፈስም በስጋም ተጣብቷል፤ ስለዚህ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ፣ ስለሞጋቹ የሥነጽሑፍ ባለሟል ሕይወትና ክህሎት በወፍ በረርም ቢሆን ለመመስከር፣ ለአቅመ ፀሐፊነት ደርሷል፡፡
ለዛሬ በሕይወት ልምዱና ገጠመኞቹ ዙሪያ በጥቂቱ እናወጋለን፡፡ በአማርኛ ሥነጽሑፍ ንድፈ ሃሳብ አፍላቂነቱና በምርምር ሥራዎቹ ዙሪያ መረጃዎችን እያጣቀስን አካዳሚያዊ መጣጥፍ ለማስነበብ ደግሞ ለሣምንት ቀጠሮ እንይዛለን፡፡
ፀሐፊው፣ የእስከዛሬ አንቱታውን ትቶ፣ “አንተ” እያለ የተረከው፣ የመገናኛ ብዙሐን ቀልብ የሚስበው የዶ/ር ዮናስ የኪነጥበብ ሰውነት ሙያው ከሚፈቅደው የአነጋገር ዘልማድ ጋር እንደሰመረ እንዲፀና በሚል የተደረገ ትጋት እንጂ፣ አጉል ድፍረት እንዳልሆነ በትሁትነት ይገልፃል…
ከረሜላ፣ ቸኮሌትና ማስቲካ ይዞልን የሚመጣ መምህራችን…
በወርሃ ጥር፣ 2000 ዓ.ም ጋሽ ዮናስ የግማሽ መንፈቀ ዓመቱን ኮርስ ማጠቃለያ ሲያስተምር እጅግ ተመስጦ ነበር፡፡ “ለማስተማር ብቻ ተብለው የሚፈጠሩ የተለዩ ሰዎች አሉ፤ ሁሉም መምህር መሆን አይችልም!” የሚለውን የሥነ ትምህርት ፈላስፎችን አባባል ለማመን ከፈለጉ፣ ዶ/ር ዮናስ ሲያስተምር መመልከት ነበረብዎት… የውጭና የሀገር በቀል ንድፈ ሃሳቦችን እያረቀቀ፣ የአማርኛ ሥነጽሑፍን ሲያስተነትንና ሲፈክር ተማሪዎቹ አፋችንን እንደከፈትን እንቀራለን… በአካዳሚክ እውቀቱና በሕይወት ልምድ እውነቱ የሚያረቃቸው የሥነጽሑፍና የቋንቋ ሀቲቶች (ዲስኩርስ) እንደ ባህርማዶ ለስላሳ ሙዚቃ በተመስጦ ነው የምናዳምጣቸው፡፡ የሀቲቶቹን እና/ወይም የንድፈ ሃሳቦቹ ረቂቅነትን የምንመረምረው፣ የተመስጦ ሰበካውን ገታ አድርጐ እነዛኑ ሀቲቶች ገልብጦ “በፈርሱ” የጠየቀን ጊዜ ነበር…
ጋሽ ዮናስ ለማድነቅም ንፉግ አይደለም፡፡ ከተመስጦው መለስ ብሎ የሚጠይቀውን ውስብስብና አመራማሪ ጥያቄ የመለሰን ተማሪ፣ እስከ ጥግ ነው በአድናቆት የሚያመሰግነው፡፡

ያን ጊዜም አንድ ተማሪ የጋሼን ውስብስብ ጥያቄ መልሶ፣ ወሰብሰብ ያለ ሌላ ጥያቄ ጋሼን ሲጠይቀው …ጋሼ በሀሴት ፊቱ በራ… ወዲያው “…በዚህ ኮርስ A (ኤ) ሰጥቼሃለሁ… በዚህ ክፍለ ጊዜ አለመምጣት ትችላለህ! በቃ! ” አለው፡፡ የጋሽ ዮናስን ውስብስብ ጥያቄ መልሶ አድናቆት ማግኘት ትልቅ ክብር ስለሆነ፣ ሁላችንም በመላሹ ተማሪ ቀንተናል፡፡
በዚህ ጊዜ ታዲያ፣ ጋሽ ዮናስ ከኪሱ የተለያዩ ከረሜላዎችን አውጥቶ ለእያንዳንዳችን የድህረ ምረቃ ተማሪዎቹ በፍቅር ሰጠን፤ ወዲያው፣ በደስታና በአክብሮት ከረሜላችንን መብላት ጀመርን፤ ምክንያቱም፣ የያን ጊዜው የ65 ዓመቱ ጋሽ ዮናስ እሱም ከኛ ጋር ከረሜላውን ወደ አፉ ብሎ ነበርና፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር ዮናስ ተማሪዎቹን ለመፈተን ሲጠራ፣ ቀድሞ በመፈተኛ ክፍሉ የእያንዳንዳችንን የፈተና ወረቀት በየመቀመጫችን አስቀምጦልን ይቆያል፡፡ ከፈተና ወረቀቶቹ ላይ ታዲያ ከረሜላ፣ ማስቲካና ቸኮሌት አይጠፉም…
በ”አማርዝኛ” የሚሳለቀው የቋንቋዎች ሊቅ
ዶ/ር ዮናስ፣ ተማሪዎቹ ይሁኑ የሥራ ባልደረቦቹ፣ በእውቀትም ይሁን በድንገት አማርኛና እንግሊዝኛ እየቀላቀሉ ጉራማይሌ ሲያወሩ ከሰማ፣ እንደሁኔታው ለዘብ አድርጐ በስላቅ ሊተቻቸው ይችላል፤ “ኧረ ይኼ አማርዝኛ አልገባኝም” በማለት፡፡ ወይም በቁጣ ሊወርፋቸው ይችላል፤ ‹‹አንጀባ አታብዙ!... ይኼ አማርዝኛችሁ አገር አጠፋ›› በማለት፡፡ “አማርዝኛ” ጋሽ ዮናስ፣ ለአማርኛና ለእንግሊዝኛ ድብልቅ የቋንቋ አጠቃቀም የሰጠው ስያሜ ይመስላል… ጋሼ ዮናስ የግዕዝ፣ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቃላት ስንጽፍ ወይም ስናነብ ከተደናቀፍን የቃሉን ስርወቃል (ወይም ግንድ) ከምንጩ እየቀዳ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሳይታክት ያርመናል… በቋንቋዎቹ ካለው ጥልቅ እውቀቱ የበለጠ፣ እኛ ተማሪዎቹን ለማረም ያለው ቀናነቱ በብዙዎቻችን አዕምሮ ገዝፎ ይታያል…
አስገራሚው የዶ/ር ዮናስ ቢሮ
የጋሽ ዮናስ ቢሮ፣ በስድስት ኪሎ ግቢ በማህበራዊ ሳይንስ ህንፃ ውስጥ፣ ከባህር ጠለል በላይ ሦስተኛ ፎቅ ጋ ይገኛል፡፡ በበርካታ መጻሕፍት የተጨናነቀው ይህ ቢሮ፣ ከበሩ ፊት ለፊት ሲቆሙ በስተቀኝ፣ ታዋቂው የሥነጽሑፍና ፎክሎር መምህርና ተመራማሪ የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ቢሮ ያዋስነዋል፡፡ በፊት ለፊት የታዋቂው የሥነልሣን ሊቅ የፕሮፌሰር ባየ ይማምና ባልደረቦቻቸው ቢሮዎች ያዋስኑታል… “ያለ ቀጠሮ ወደ ጋሼ ቢሮ መዝለቅ ፈጽሞ የተከለከለ ነው” ባይባልም፣ እንዲሁ ዘው ማለት የሚያስከፍለው ነገር ይኖራል፡፡ ዶ/ር ዮናስ በተለይ አጣዳፊ ሥራ ይዞ፣ ኮምፒውተሩ ላይ ተጥዶ ካገኙት ዝም ብሎዎት ሥራውን ሊሠራ ይችላል፤ በተለይ ያለ ቀጠሮ ከሆነ የመጡት፡፡ በሩን ደጋግመው እየቆረቆሩ ሰላም ከነሱት “የለሁም!” በማለት በመጀመሪያ በለሆሳስ ሊመልስ ይችላል፡፡ ደግመው ከቆረቆሩ ብስጭት ብሎ በመነሳት “የለሁም ስል አትሰማም!” በማለት ሊቆጣ ይችላል፡፡ ድንግጥ ብለው ከቆሙ፣ አያስችለውም ወዲያው መለስ ይልና፣ “ምን ፈልገህ ነው?“ ይላል… የጋሼን ጸባይ ያለመደ ተማሪ እንኳን ቢሮው ድረስ ሄዶ ቀርቶ፣ በመንገድ ሲያገኘው ሁሉ ይሸሻል፣ ይርበተበታል … ጋሽ ዮናስ ግን ይሄን አይነት መሸማቀቅ አይፈልገውም፤ ባህሪውን ያወቀ ተማሪ ግን የምሩን ተናዶ ቢቆጣ እንኳ፣ ሳይፈራ የደቂቃዎችን ክፍልፋይ ዝም ብሎ ካሳለፈው ወዲያው ምልስ ይላል… ጋሼ ሆዱ ገርና ቅን እንደሆነ፣ በአፉ ቢቆጣ እንኳን በሆዱ እንደማይቆርጥ ታዲያ፣ ከተወሰነ የጊዜ ቆይታ በኋላ ሁሉም ተማሪዎቹ ያውቃሉ፤ ያውቁታልም…
ጋሽ ዮናስ ሲቀልድ፣ በዘመንኛ ቋንቋ “ሲፎግር”፣ ሲጫወት… ይችልበታል፤ ተማሪዎቹ የማታለል ሙከራ ካደረግን፣ “እሣት የላስኩ የሱማሌ ተራ ጩልሌ ነኝ… ” በማለት ስቆብንና ተሳልቆብን ያልፋል…
አንድ ቀን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ተመካሪው እያለ፣ ደውሎ ለመምጣት ቀጠሮ ይቀበላል፡፡ በበነጋው ጋሽ ዮናስ ወደ ቢሮው ሲገባ ጠብቆ በቀጠሮው መሠረት ወደ እዚያው ያቀናል፡፡ ቢሮው ገርበብ ብሎ ሲያገኘው ከፈት አድርጐ ይገባና ይቆማል፡፡
ጋሽ ዮናስ “ምን ልታደርግ መጣህ?” አለው በቁጣ፡፡ ቀጠሮ እንዳለው ተናግሮ ተዝናንቶ ሲቆም፣ ጋሼ፣ “እኔ በእናንተ ማበድ አለብኝ… ደውለህ ነው መምጣት አላልኩህም!” በማለት ብስጭት ብሎ የሚማታበት “አለንጋ” ከጠረጴዛው ሲፈለግ፣ ተመካሪ የድህረምረቃ ተማሪው ፍንጥር ብሎ ከቢሮው ወጣ፡፡
የጋሽ ዮናስን ጸባይ ስለሚያውቅ ብዙ አልተደናገጠም፡፡ አንድ ሁለት እርምጃ ተራምዶ ሞባይሉን አወጣና ደወለ… ጋሼ ከቢሮው ውስጥ ሲስቅ ይሰማዋል፡፡ ወዲያው ስልኩ ተነሳ፤ “ምን ፈለግህ?” የሚል የለሆሳስ ድምጽ ተሰማ… “አይ ዛሬ ቀጠሮ ነበረኝ፤ ደውዬ እንዳስታውስ ተነግሮኛል!” ከማለቴ የጋሼ ሣቅ፣ ከሞባይሌም ከቢሮውም ተሰማኝ፡፡ እየሳቀ፣ “ና! አሁን ” አለኝ፡፡
ስህተቴ ሲገባኝ፣ ከቢሮው ሣልርቅ ወዲያው ደውዬ መጠየቄ ገርሞታል… በመልካም ፈገግታ ለ40 ደቂቃ ስመከር ቆየሁ… ወደ ዶ/ር ዮናስ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ የሚገቡት ብዙ የሚገርምዎት ነገር ሊያጋጥምዎት ይችላሉ… ጠረጴዛው በካኪ ፖስታ ታሽገው የሚታረሙ ወይም የታረሙ ወረቀቶች ተቆልለው ያያሉ - በአንድ ጠርዝ ላይ፡፡ የተለያዩ የታሸጉ ምግቦች፣ በጠርሙስ የተሞሉ የተለያዩ የከረሜላ፣ የቸኮሌት አይነቶች ይመለከታሉ፡፡
በጠረጴዛው ሌላኛው ጫፍ፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ በላስቲክ የታሸጉ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ሊያዩ ይችላሉ፡፡
በጠረጴዛው መካከል ላይ የተለያዩ መፃሕፍት ለንባብ ተሰድረዋል … ገሚሶቹ መፃሕፍት ተገልጠው ተገልጠው በአፋቸው ተደፍተው ያያሉ… በጠረጴዛው በውስጥ በኩልም (በግርጌው) የተለያዩ መዝገበ ቃላት፣ የጥናት መጽሄቶች /ጆርናሎች/… መቆለላቸውን የሚያዩት፣ አንድ መጽሐፍ ገልጦ ከእንግዳ መቀበያ ወንበር ተነስተው ወደ እርሱ ጠረጴዛ ቀርበው ካነበቡ ወይም የተሰወረበትን መፃሕፍት እንዲያፋልጉት ከፈቀደ ነው፡፡
ከጠረጴዛው ጀርባ ታዲያ፣ ከምሣ በኋላ የሚያርፉበት ይመስለኛል ባለ ሦስት ቀጫጭን ስፖንጅ ተጣጣፊ ፍራሽ፣ በስርአት ተጣጥፎ የጠረጴዛውን እግር ተደግፎ ሊያዩ ይችላሉ፡፡
ትንሽ የኤሌክትሪክ ምድጃ፣ ተቀምጧል፡፡ የአንድ የመካከለኛ ሰው እጅ መዳፍ የሚጨብጠው ዓለት የሚመስል ድንጋይ ጠረጴዛው ስር ወይም ላይ ቁጭ ብለው ቢያዩ አይደንግጡ… ጋሼ ተማሪዎቹ ቶሎ ከቢሮው አንወጣለት ስንል ድንጋዩን እያሳየ ያስፈራራናል - እየቀለደና እየሳቀ ነው፡፡ ተማሪዎቹም ጋሽ ዮሐንስ ለየት ያለና ዘመናዊ ሰው እንደሆነ እናውቃለን… በነገራችን ላይ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የጠረጴዛውን ጀርባ ለመጨረሻ ጊዜ ያየው በሀምሌ ወር 2002 ዓ.ም ነበር፡፡
የህልፈተ ህይወት ጊዜውን የተነበየበት አጋጣሚ
በጥር ወር 2004 ዓ.ም በዋቢሸበሌ ሆቴል፣ የበድሉ ዋቅጂራን (ዶ/ር) ሁለተኛ የግጥም መጽሐፍ /“እውነት ማለት የኔ ልጅ”ን/ ለማስመረቅ “ዛጐል ቤተመፃሕፍት” ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ዶ/ር በድሉ የግጥም ስብስቡ “መታሰቢያነቱ ሀውልት ላልቆመላቸው ለዮሐንስ አድማሱ እና ለደበበ ሰይፉ” እንዲሆንለት በማድረጉ፣ ዶ/ር ዮናስ በዚህ ዕለት በመድረክ ላይ ንግግር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ፣ ወደ መድረኩ ሲመለከት፣ የመጽሐፍ ምረቃ በሚያበስረው “ባነር” ላይ አንድ ቃል ያያል፤ የዛጐል ቤተመፃሕፍት ሥራ አስኪያጅ የሆነውን እንዳለጌታ ከበደን ጠርቶ፣ “ዶ/ር ዮናስ ያን ካየ መናገሩ አይቀርም - መላ ፈልግ” ይለዋል፡፡
ጋሽ ዮናስ ወደ መድረክ ሲጋበዝ፣ “… ይኸው! የግጥም ‹መድብል› አይባልም፤ መድበል እንጂ!” በማለት የቃሉን ሥርዎ አመጣጥ በማብራራት ንግግሩን ጀመረ፡፡ ስለ ዮሐንስ አድማሱ ሕይወትና ሥራዎች አብራራ… በተለይ ዮሐንስ በባለቅኔውና ፀሐፌ ተውኔቱ ዮፍታሔ ንጉሴ ሕይወትና ሥራዎች ዙሪያ የሠራውን የምርምር ሥራ “በአሰናኝነት” አሰናድቶ እያጠናቀቀ መሆኑን ተናገረ፡፡ በመጨረሻ፣ “…ይኼ መጽሐፍ ታትሞ ሳላየው እግዚአብሔር እንዳይገለኝ!” በማለት “ፈጣሪውን” በሰከነ መንፈስ የተማፀነበት አጋጣሚ በቦታው የነበረን ሰው ሁሉ አሳዝኗል፡፡
ጋሽ ዮናስ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበረ ባሳተመው “የዘመን ቀለማት” የግጥም መድበል ላይ፣ “ህዳር 6 ቀን 1935 ዓ.ም ቅዳሜ ሌሊት በዐሥር ሰዓት በአዲስ አባ ከተማ በደጃች ውቤ ሠፈር” መወለዱን እራሱ በከተበው የሕይወት ታሪኩ ተናግሯል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ገድለኛ፣ ከነቢዩ ዮናስ ስሙን ብቻ ሳይሆን ግብሩንም የወረሰ የሚመስለው ዶ/ር ዮናስ አድማሱ፣ ህልፈቱ እስከታወቀበት የካቲት 1 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ፣ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎቹን እያማከረ፣ እያነበበ፣ እየፃፈ ያለፈ ታላቅ ምሁር መሆኑ በተግባር አሳየ፤ እስከመጨረሻዋ የሕይወት ጠብታ መፃሕፍት ታቅፎ ለዘላለሙ ያንቀላፋ የቀለም ቀንድ!
እውቀት የሚቀምርባት አስገራሚ ቢሮውም ወዳጇ ጋሽ ዮናስ ለዘላለሙ ከተለያት በኋላ ሁሉ፣ የሥነጽሑፍ ሊቀሊቃውንቷ ህልፈት በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ እስከታወጀበት የደቂቃዎች ክፍልፋይ ድረስ፣ ይህቺ የቀለም መጥመቂያ ቢሮው፣ በበር ሥር የተላከላትን የተመካሪ ተማሪዎች የምርምር ፕሮፖዛል በአደራነት ስትቀበል ነበር… የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የዶ/ር ዮናስን እርፈት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ ከመስማቱ በፊት፣ የጋሽ ዮናስ የዶክትሬት ዲግሪ ተመካሪ ተመሪው የፕሮፖዛል ወረቀቷን ወደ 5 ሰዓት አካባቢ በበር ስር ማስገባቱን ሰምቷል…
የተስፋዋን ቀን ለማየት 12 ቀን ሲቀራት የተነጠቀች ነፍስ
ታዋቂው ባለቅኔና ለውጥ አራማጁ መምህር ዮሐንስ አድማሱ በ1967 ዓ.ም በድንገት በ37 ዓመቱ ሲቀሰፍ፣ በዮፍታሔ ሕይወትና ክህሎት ዙሪያ እያገባደደው የነበረውን የምርምር ሥራ አጠናቆ ማሳተም፣ በታናሽ ወንድሙ በጋሽ ዮናስ አድማሱ ትከሻ ላይ አረፈ፡፡
ከ35 ዓመት በላይ ሳይታተም የቆየውን የምርምር መጽሐፍ የህትመት ብርሃን እንዲያይ፣ እነ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ፣ ዶ/ር ዮናስን ሲያበረታቱ ቆይተዋል…
የተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮችን የሚያወሱ ዘመን ተሻጋሪ መጻሕፍት፣ ከተቀበሩበት ጉድጓድ እየወጡ፣ ከሻገቱበት ቦታ እየተራገፉ እንዲታተሙ ያደረጉትና ለዘላቂ የህትመት ሥራ መሠረት የጣሉት እነ ፕሮፌሰር ማስረሻ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የቦርድ አባላት፣ ፕሮፌሰር ማስረሻ፣ በዶ/ር ዮናስ አሰኛኘት ለህትመት የበቃውን መጽሐፍ፣ በልዩ ሁኔታ ለማስመረቅ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር የቁርጥ ቀን ቀጠሮ ይዘዋል… የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አርታኢና የጋዜጣ አምደኛው ብርሃኑ ደቦጭ የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም “በብሔራዊ ትያትር” አዳራሽ የዮሐንስን መጽሐፍ ለማስመረቅ ደፋ ቀና እያለ፣ ከዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ጋር ተገናኙ፡፡
ጋሽ ዮናስ የመጽሐፉን ህትመት ሳላይ እንዳልሞት በማለት በጉጉት የሚጠብቃትን ዕለት፣ የሦስት ታላላቅ የሥነጽሑፍ ባለሟሎች ጠንካራ የኪነት ክንድ ያረፈበት መጽሐፍ የሚመረቅባትን ያቺን ቀን እኔም በጉጉት እየጠበቅሁ ነው፤ በዚች ታሪካዊ ዕለት፣ ዮሐንስ አድማሱን የሚዘክር አንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ለማቅረብ እየተሰናዳሁ ነበርና፡፡
የዶ/ር ዮናስ አድማሱ ነፍስም ከ35 ዓመት በላይ ታግሣ የጓጓችለትን የተስፋ ቀን ለማየት 12 ቀናት ብቻ ቀርተዋት እያለ፣ እኔም ወጉ ደርሶኝ ከመምህሬ ከጋሽ ዮናስ ፊት፣ አብዮተኛው የኮሌጅ ቀን ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱን ለማውሳት 12 ቀናትን እየተጠባበቅሁ እያለ፣ የታላቁ የቀለም ቀንድ የጋሽ ዮናስን ህልፈተ ሕይወት በድንገት መስማት ምን ያህል ያስደነግጥ!?

 


ባንተ በኩል ፈካች
ነ.መ
የልቤን ማኅደር፣ ቆፍሬ ቆፍሬ፤
ያገር ውለታህን ልናገር አምርሬ፡፡
ምንም ቢደባለቅ፣ ብስሉ ከጥሬ
የፊደል ልሣኑ፣ ያው ይጫሃል ዛሬ፡፡
ምን ቢበረክቱ፣ የእኛ ነው የሚሉ
አገሩና ህዝቡ፣ ድሉም ሆነ ትግሉ
ቢከትቡ፣ ቢያውጁ፣ ገድል ቢያሳቅሉ
በደም የተፃፈ፣ ይጎላል ከሁሉ!!...(“ጐ” እና “ላ” ይላላል)
ለመሰነባበት፣ ጊዜው አልነበረን…(“መ” እና “ሰ” ይጠብቃል)
መቼስ ያቃል ኖሮን፡፡
ለመሰነባበት ጊዜም አልነበረህ…(“መ” እና “ሰ” ይላላል)
መቼስ ያቃል ኖሮህ!!
ብቻህን ሄደሃል፣ ያው ብቻህን ኖረህ፡፡
እንደ ጊዜው ባህል፣ ጥንት እኔ እንደማቅህ
ከመሬቱ በታች፣ ከዕውነት ጋር ተቀብረህ
መብራት የማያቆም፣ የንቁ ኮከብ ነበርክ፡፡
ጥንት ገና ዱሮ፣ ሰው የነበርን ቀን
ጭቆና ሲመረን፣ ግፍ ሲያንገፈግፈን
ልብ ለልብ ማውራት፣ እንዲህ ሳይቸግረን፤
የብዕሬን ዕንባ
ለአገሬ ሳነባ፤
ብታይልኝ ብዬ -
“አበባ” እሚል፣ ግጥም ልኬልህ ነበረ፡፡
እንዲህ መለስክልኝ
መቼም አይረሳኝ:-
“በጧት ቸግነሃል፣
በጧት ጀግነሃል፣
የለብህም ዕዳ፤
አበባህ ግጥም ናት፣ ሁልጊዜ ትፈንዳ!”
ይኸው ላንተም ተርፋ፣ ባንተ በኩል ፈካች
ታሪክ ያለው ትውልድ፣ መኖሩን አወጀች!!
(ለዮናስ አድማሱና ለትውልዳችን)
የካቲት 8/2005

 

Read 6247 times