Saturday, 16 February 2013 12:05

መንግስት አይፈረድበትም፤ እንደብዙዎቻችን በስሜት ይተኮሳል!የኢትዮጵያ ቡድን ድንገት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብቅ ሲል፣ በሆይሆይታና በትኩሳት ተውጠን ዋንጫውን ተሸክመው የሚመጡ መስሎን አልነበር? በፖለቲካና በኢኮኖሚ በኩልም መንግስት ሆይሆይታ ላይ ነው - የመሻሻል ጭላንጭል አየሁ ብሎ አገሪቱ የአለም አንደኛ የሆነች ያስመስላል። ከአምስት አመት በፊት፤ ኢትዮጵያ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ የቱን ያህ

Written by 
Rate this item
(3 votes)
  • የኢትዮጵያ ቡድን ድንገት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብቅ ሲል፣ በሆይሆይታና በትኩሳት ተውጠን ዋንጫውን ተሸክመው የሚመጡ መስሎን አልነበር?
  • በፖለቲካና በኢኮኖሚ በኩልም መንግስት ሆይሆይታ ላይ ነው - የመሻሻል ጭላንጭል አየሁ ብሎ አገሪቱ የአለም አንደኛ የሆነች ያስመስላል። 
  • ከአምስት አመት በፊት፤ ኢትዮጵያ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ የቱን ያህል የእልቂትና የመበታተን አደጋ ውስጥ እንደሆነች፣ ገደል አፋፍ ላይ እንደቆመች መንግስትና ኢህአዴግ ሲነግሩን ነበር - ያለ ኢህአዴግ ትበታተናለች እያሉ። 
  • የኢቴቪ ዜናና ዘገባዎችን የሚመለከት ሰው፤ ገበሬዎች በሃብት የተጥለቀለቁ ይመስለዋል - በመስኖ፣ በምርጥ ዘር፣ በቴክኖሎጂ። ከአምስት አመት በፊት እንደነበረው ዛሬም 12 ሚሊዮን ገበሬዎች በእርዳታ የሚተዳደሩ ናቸው። 
  • የባለስልጣናትን ሪፖርት የሚያደምጥ ሰው፤ ለወጣቶች የስራ እድል የተትረፈረፈ ይመስለዋል - በሁለት አመት በከተሞች ውስጥ ከ1.5 ሚ በላይ የስራ እድሎች ተከፍተዋል ስለተባለ። ግን አምና የተፈጠረው ስራ ዘንድሮ የለም።

 ሃሳብና ስሜት፣ “በልኩ ካልሆነ” ... ማለትም ከእውኑ ሃቅ ጋር ካልገጠመ፤ “ከእውነት የራቀ ስህተት” ይሆናል። “ልክ ሲያጣ” ደግሞ፤ “ጭፍንነት” ይባላል። ሲብስበትስ? ሃሳብና ስሜት ከእውኑ ተፈጥሮ ጋር ዝምድናው ጨርሶ ሲሰረዝስ? ያኔ አእምሮ ተቃውሷል ማለት ነው። ኢትዮጵያም ይሄውና እንደተቃወሰች ሺ አመታት ተቆጥረዋል። ህመሟ ምንድነው በሉኝ። ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የጭፍንነት በሽታ ነው የሚያሰቃያት - ስር የሰደደ “ልክ የማጣት” በሽታ! ሁለት የበሽታ ምልክቶች ሲፈራረቁባት አታዩም? ብዙውን ጊዜ ብርድ ብርድ ይላታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ በትኩሳት ያነድዳታል። በ60ዎቹ ዓ.ም እንዲሁም በ97ቱ ምርጫ የተግለበለቡትን ትኩሳቶች አስታውሱ። በየመሃሉ የነገሱትንና አሁን የሰፈነውን የፖለቲካ ድንዛዜም ተመልከቱ። 

በእግር ኳስም ተመሳሳይ የትኩሳትና የድንዛዜ ምልክቶች በብዙዎች ላይ ተፈራርቀዋል። የእግር ኳስ ስሜት ከጣራ በላይ ሲንበለበል እንደነበር ለማወቅ ብዙ መመራመር አያሻም፤ ይድነቃቸው ተሰማ ለዘመናት ዝነኛ ሆነው የዘለቁት ለምን ሆነና? ግን ትኩሳቱ ቦታውን ለቅዝቃዜ መልቀቁ አልቀረለትም። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋንጫ ተራራቀች። ለሰላሳ አመት የዘለቀውን ልክ ያጣ የተስፋ መቁረጥ ድንዛዜን፤ ዘንድሮ ከተንቀለቀለው የስሜት ጡዘት ጋር አጣምራችሁ ተመልከቱት። አገሪቱ ላይ ለሺ ዘመናት የተፈራረቁት ሁለት የበሽታ ምልክቶች፤ ዛሬም አልተለይዋትም።
ታዲያ “አገር ታመመች፣ ኢትዮጵያ ተሰቃየች” ሲባል፤ ምሳሌያዊ አነጋገር እንደሆነ አትዘንጉ። በምሳሌያዊ አነጋገር ታጭቀን እያደግን፤ “አገር” የሚባለው ነገር፤ ከምር አካልና ህይወት ያለው ፍጡር እየመሰለን ብዙ ጥፋት ደርሷል። “ለራስህ ጥቅም ሳታስብ ለአገርህ ሙትላት!”፣ “ከራስህ በፊት የአገርህን ጥቅም አስቀድም! ኢትዮጵያ ትቅደም” እየተባለ ስንት ሰው አልቋል። እናም... ለሺ አመት የታመመች አገር ሁለት የበሽታ ምልክቶች ይፈራረቁባታል ያልኩት፤ ባለፉት ሺ አመታት አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን በአመዛኙ በምን አይነት ሕይወት እንዳለፉ ለመግለፅ ነው።
“ልክ የማጣት” ወይም የጭፍንነት አባዜ ያልለቀቃቸው ብዙ ኢትዮጰያውያን፣ ከስኬት ርቀው በውድቀት ውስጥ ተሰቃይተዋል ለማለት ነው የፈለግሁት። ብርድ ብርድ እያላቸው ሲኮራመቱና እያሰለሰ ትኩሳት ሲያንገበግባቸው ስንት ዘመናቸው! አንዳንዴ፤ “ውድቀት መፍትሄ የሌለው የእጣፈንታ ወይም የእርግማን ሸክም ነው” በሚል ልክ ያጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አገሪቱን እየወረራት፤ በድንዛዜ የመኮራመት አባዜ ይነግስባታል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፣ ስኬትና ለውጥ፣ እድገትና ድል በአንዳች ልዩ “ተአምር” የሚገኝ ትንግርት ይመስል፤ ልክ ያጣ የስሜት ትኩሳትና የሆይሆይታ ማዕበል ያጥለቀልቃታል። ትንሽ የመሻሻል ጭላንጭል ብልጭ ጎላ ብላ ከወጣች፤ በቃ... አገር ይቀወጣል።
ትንሽ የኢኮኖሚ መነቃቃት ብልጭ ስላለች፣ መንግስት የሚያደርገውን ሲያሳጣው አትመለከቱም? አገሪቱ፣ የኬንያውያን የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ ገና አስር አመት የሚያስፈልጋት ቢሆንም፤ ኢቴቪን በየእለቱ የሚከታተል ሰው ግን ኢትዮጵያ የአለም ቁንጮ የሆነች ሊመስለው ይችላል። ያው፤ የኢትዮጵያ መንግስትና የመንግስት ጋዜጠኞችኮ ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም፤ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ድንዛዜና ትኩሳት ይፈራረቅባቸዋል። አሁን የትኩሳት ፈረቃ ላይ ናቸው። እንደ እግር ኳሱ ሆይሆይታ ማለት ነው። ግን አይዘልቅም። በአንዳች ተአምር እውን እንዲሆን የሚጠብቁት የስኬት ውጤት፤ በጭፍን ስሜት እየተግለበለቡ የሰበኩለት ልዩ “ትንግርት” የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀርስ? ስኬትና እድገት፣ በአንዳች ተአምር እውን አይሆንማ።

ያኔ፤ አገሪቱ እንደገና ተመልሳ ወደ ተስፋ ቢስነትና ወደ ድንዛዜ እየተንሸራተተች ትገባለች። እንዲህ ሁለት የበሽታ ምልክቶች እየተፈራረቁ በዥዋዥዌና በአዙሪት ስንት ዘመን ተቆጠረ? ደግሞምኮ፤ “ልክ የማጣት” የጭፍንነት ህመምን ብቻ ሳይሆን ሁለቱ የበሽታው ምልክቶቹን በጣም ስለተላመድናቸው ለብዙ ሰዎች እንደ “ኖርማል” የሚቆጠሩ ሆነዋል። እስቲ የፖለቲካውና የኢኮኖሚውን ነገር ከማየታችን በፊት የእግር ኳሱን ዡዋዥዌና አዙሪት ትንሽ እንየው።
“ባርሴሎናን ያስናቀ ቡድን”
የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን ከ30 አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲገባ፣ ትንሽ የለውጥ ፍንጭ መሆኑ አይካድም። ታዲያ በዚህ ትንሽ የመሻሻል ጭላንጭል ተደስተን፤ ምንጩንና ምክንያቱን ለይተን ለማወቅና ይበልጥ የሚያድግበትን መንገድ ለመፍጠር ብርታት አገኘን? ማለትም በደንብ ለማሰብ ተነቃቃን? ጥያቄው ራሱ “ይደብራል” - ለብዙ ሰዎች። በእርግጥ፣ ብዙ ሰው “በደንብ ለማሰብ” ባይነቃቃም፤ በሆነ መልኩ ተነቃቅቷል። እንዲያውም፣ ከአፍሪካ ዋንጫ ጋር ተያይዞ ለተወሰነ ጊዜ፤ “የህዝብ ንቅናቄ ተቀጣጥሏል” ማለት ይቻላል (በዘመኑ የፖለቲካ ቋንቋ እንናገር ከተባለ)። የቢሮ ውስጥና የድራፍት ላይ ወሬው፣ የራዲዮና የጋዜጣ ዘገባው በብርሃን ፍጥነት እንደ ሰደድ እሳት አገር ምድሩን ሲያንቦገቡገው ማየት ያስደንቃል።
የብሄራዊ ቡድን አባላትን ለመሸለም፣ ከየአቅጣጫው ይሰበሰባል የተባለው ገንዘብስ ቀላል ነው እንዴ? በስፖርት ውድድሮች አውራ (በአለማቀፉ የኦሎምፒክ መድረክ) የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቁ ኢትዮጵያዊያን ሻምፒዮኖች ከ100ሺ ብር በላይ እንዳልተሸለሙ አትርሱ። የእግር ኳስ ቡድንኑ በአፍሪካ ዋንጫ “ከቀናው” ግን፣ እያንዳንዱ ተጫዋች ሁለት ሚሊዮን ብር ገደማ ሽልማት እንዲያገኝ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ይሰበሰባል መባሉ ራሱ...፣ “የህዝብ ንቅናቄ ተቀጣጠለ፤ የእግር ኳስ ሰራዊት ተነቃነቀ” የሚያስብል ነው። በእርግጥ፤ በወቅቱ ጥርጣሬ የገባቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ያጠራጠራቸው ነገር ምን እንደሆነ በቀላሉ ልትገምቱት ትችላላችሁ። “ገንዘቡ ተሟልቶ ይሰበሰባል ወይ?” የሚለው ጥያቄ ነበር ያሳሰባቸው።

ብሄራዊ ቡድኑ ለዋንጫ ደርሶ ሻምፒዮን እንደሚሆን እርግጠኛ እስከመሆን ደርሰዋላ።
መጀመሪያ ላይማ፤ ስለ ዋንጫ የሚያስብ ሰው ብዙ አልነበረም። ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመግባት በመቻሉ ብቻ ብዙዎች ረክተዋል። ግን በውድድሩ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ ጥሩ ተፎካካሪ ሊሆን ይችላል? ጥያቄው ወደ ምኞት፣ ከዚያም ወደ እምነት ለመለወጥ ጊዜ አልፈጀበትም። ቡድኑ ወደ ጥሎ ማለፍ እንደሚደርስ ብዙ ሰዎች በስሜት ወደ መናገር የተሸጋገሩት እንዴት እንደሆነ፤ በየት በየት በኩል አጥር ጥሰው እንደዘለሉ ለማስታወስ ያስቸግራል። ግን በዚህ አላበቃም። ቡድኑ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ቢያልፍስ? እንዲያው ለግርምት ያህል ሽው ያለው የምኞት ስሜት፣ እንዴት እንደሆነ ሳይታወቅ እግር አብቅሎ መራመድ ይጀምራል።
ገና የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሳይከፈት፤ ትኩሳት ባነደደው የብዙዎች ስሜታዊ አእምሮ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግማሽ ፍፃሜውን አልፎ የዋንጫ ፍልሚያ ላይ ደርሷል። አሳሳቢው ነገር፣ ስፖርተኞቹ ዋንጫ ይዘው ሲመጡ፤ ቃል የተገባላቸው ሽልማት ተሟልቶ ይሰጣቸዋል? የሚለው ጥያቄ ነው። “ውድድርና ብቃት” እና “ትኩሳትና ተአምር” እየተቀላቀሉ፣ የቀን ህልምና የቀን ሃሳብ እየተምታቱ፣ “ህዝባዊው ንቅናቄ” ፍጥነቱን እየጨመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ሆነ - ያለ ፍሬን እንደሚንደረደር መኪና። ልክና ስፍር አጥቶ በሚጦዝ ስሜት ሆይሆይታው ቀለጠ።
አሰልጣኙና ተጫዋቾቹ፣ በዚህ የስሜት ግልቢያ ውስጥ ተዋናይ ላለመሆን በእጅጉ ቢጠነቀቁም፣ ሆይሆይታውን ሊቋቋሙት አልቻሉም። ተቆጣጣሪ አእምሮ ያጡ ተአምራዊ የትኩሳት ትረካዎች ማቆሚያ አልተገኘላቸውም... “ቡድኑ ዋንጫውን ተሸክሞ ከመጣ... ደግሞም ተሸክሞ ይመጣል። አጨዋወታቸውኮ ባርሴሎናን ያስንቃል። በዚህ አይን ሜሲ ምኑን ተጫወተው?... ቃል የተገባው ሽልማት አያሳስብም። የገንዘቡ በጊዜ ይሰበሰባል። ይልቅስ አስጨናቂው ነገር ሌላ ነው። የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫ የሚደርሰው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ከሆነ፤ ዳኛው ማዳላቱ አይቀርም። በዚያ ላይ የኢትዮጵያ ቡድን አሸንፎ ሲወጣ፣ አደጋ ሊደርስበት ይችላል”... ምን አለፋችሁ፤ አገር በትኩሳት ማዕበል ተናጠች።
በሰላሳ አመታት የውድቀት ታሪክ ስሜቱ ተሽመድምዶ፤ እንደ እጣ ፋንታ ወይም መፍትሄ እንደ ሌለው እርግማን ሸንፈትን ተሸክሞ፣ ሙትት ብሎ የደነዘዘው መንፈስ፤ ትንሽ የመሻሻል ጭላንጭል ሲያይ ምን እንዲሆን ትጠብቃላችሁ? “ለብርቱ ጥረት የሚያነሳሳ ቁጥብ የመነቃቃት መንፈስ” እንዲፈጠር ከጠበቃችሁ ተሳስታችኋል። መነቃቃት ሳይሆን ትኩሳት ነው የተፈጠረው - በሆይሆይታ የቀለጠ ጡዘት። ትንሽዬ የመሻሻል ጭላንጭል ብልጭ ስትል፤ በአንዳች “ተአምር” ብሄራዊው ቡድን የአፍሪካ አንደኛ ሆኖ ቁጭ አለ - በስሜት የተበጠበጠ አእምሯችን ውስጥ። ዋንጫ የሚያስገኝ አንዳች ልዩ “ተአምር”፣ እንደተጠበቀው ከተፍ አለማለቱን ስናይስ? ወደ ቀድሞው ድንዛዜ መመለስ በአገራችን በጣም የተለመደ ባህል ነው።
በፖለቲካና በኢኮኖሚ - ድንዛዜና ትኩሳት
በአገራችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የምናየው ሁኔታም ከእግር ኳሱ ስሜት ጋር ይመሳሰላል። ለካ፣ መንግስትም የአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ህዳሴን ነጋ ጠባ በሚንቀለቀል ፕሮፓጋንዳ የሚጠዘጥዘን፣ ልዩ የማጋነን ሱስና የፕሮፓጋንዳ ጥም ስላለበት አይደለም። ያው እሱም፣ ትናንሽ የመሻሻል ጭላንጭሎችን ሲመለከት፣ እንደ አብዛኞቻችን ናላው እስኪዞር ድረስ በትኩሳት ስለሚንገበገብ ነው። ለአመታት በድንዛዜ ተውጠው የነበሩ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላትስ በ97ቱ ምርጫ፤ ትኩሳት ነግሶባቸው እንዴት እንዴት እንዳደረጋቸው ታስታውሱ የለ? ያው የመንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት ጋዜጠኞች፤ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላትኮ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ናቸው - ድንዛዜና ትኩሳት የሚፈራረቅባቸው። ለዘመናት የተቆራኘን ባህል ነዋ።
ውድቀትን እንደ እርግማን ቆጥሮ፣ ለውጥ እንደማይመጣ አምኖ፣ በተስፋ ቢስነት “የባሰ አታምጣ” እያለ በድንዛዜ ይቀመጣል - በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በእግር ኳስ። ድንዛዜን ተከናንቦ ሲኮራመት፤ ቢቀሰቀስ እንኳ አይሰማም። ትናንሽ የመሻሻል ጭላንጭሎች ብቅ ብቅ ሲሉ እንኳ ለማየት ፈቃደኛ አይሆንም። ውድቀትን እንደ እርግማን፣ ስኬትን እንደ ተአምር እየቆጠረ ምኑን ያያል! የለውጥ ምንጮችንና የስኬት ስረ መሰረቶችን ለይቶ ለማወቅ ጠንካራ ፍላጎት አይኖረውም። ለዚህም ነው፤ የ97ቱ የተሟሟቀ የምርጫ ውድድር ለብዙ ሰዎች እንደ አንዳች ተአምር የሚሆንባቸው። አለበለዚያማ ከ95 ዓ.ም ጀምሮ፣ በፖለቲካው መስክ የመሻሻል ጭላንጭሎች ብቅ ብቅ ሲሉ ማየት ይቻል ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማዋከብ፣ እንዲሁም ምሁራንን የማንቋሸሽና ጋዜጠኞችን የማስፈራራት አፈና እየቀነሰ ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም፣ “ወያኔ” የሚለውን የዘወትር አጠራር እየተዉ፣ ኢህአዴግ ወይም ገዢው ፓርቲ ማለትን የጀመሩት ያኔ ነው።

በ97ቱ ምርጫ ላይ ጎላ ብሎ የታየው የለውጥ ጭላንጭል፤ በአንዳች ተአምር ከሰማይ የወረደ ሳይሆን በጥቃቅን የለውጥ ምንጮች ምክንያት የተከሰተ መሆኑ ብንገነዘብ ኖሮ፤ ብዙ ሰው ወደ ስሜት ትኩሳት ይገባ ነበር?
እነዚህን የመሳሰሉ የፖለቲካ ጥቃቅን የለውጥ ጭላንጭሎች የታዩበት ዘመን፤ በኢኮኖሚም በኩል የለውጥ ፍንጮች ብቅ ብቅ ብለዋል። የቢዝነስ ሰዎችን በጠላትነት ይፈርጅ የነበረው ኢህአዴግ አቋሙን በማለዘብ፣ የኢንቨስትመንት ህጉን ያሻሻለው በ1995 ዓ.ም ነው። የተለያዩ አላስፈላጊ ገደቦችንና ቁጥጥሮችን በተወሰነ ደረጃ ሲሰረዙ፤ በተንዛዛ ቢሮክራሲ ተተብትቦ ለነበረው የንግድ ፈቃድና የኢንቨስትመንት ምዝገባ ትንሽ መፈናፈኛ ይሰጣል። ባለፉት አመታት በአገራችን የታየው የኢኮኖሚ የለውጥ ጭላንጭል፤ በአንዳች ተአምር የተፈጠረ ሳይሆን፤ ከጥቃቅን የለውጥ ምንጮች የፈለቀ እንደሆነ መንግስት ባይዘነጋ ኖሮ፤ አሁን እንደሚታየው በትኩሳት እየነደደ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ብሎ ያስቸግር ነበር?
አብዛኛው ሰው የስኬት ዋና ምንጮችን ከስረ መሰረታቸው የመመርመር ዝንባሌ የለውም። በዚያው መጠንም ውድቀት ውስጥ ደንዝዞ፤ ጥቃቅን የመሻሻል ፍንጮችንና ጭላንጭሎችን የማየት ፍላጎት የለውም። የማይጨበጡ የተስፋ መና ይሆኑበታል። ውድቀት እንደሆነ የማይላቀቁት እርግማን ነው ብሎ ለሚያስብ ሰው፤ ማንኛውም ስኬት በየትኛውም አቅጣጫ ከከንቱ ህልም ያለፈ ትርጉም አይኖረም። ታዲያ የመሻሻል ጭላንጭሎችን እያዩ በማያዛልቅ ተስፋ ልብን ማንጠልጠል ምን ዋጋ አለው? ምንጫቸው ምንድነው ብሎ መመርመርስ ምን ጥቅም አለው? ሊያያቸው አይፈልግም። ቢያያቸውም ከቁም ነገርም ሳይቆጥር ያጣጥላቸዋል።
ግን ከዚያስ? የመሻሻል ጭላንጭሎቹ ጎላ ጎላ ሲሉና የለውጥ ምልክቶች መታየት ሲጀምሩስ? ... የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለተከታታይ አመታት ከአስር በመቶ በላይ እድገት ሲያስመዘግብ፣ የፓርቲዎች ክርክር በነፃነት ሲሰራጭና የምርጫ ፉክክር ሲሟሟቅ፣ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሲያልፍስ? ያኔ ብዙ ሰው በአግራሞት እያየ፤ “ተአምር ነው፤ ለማመን ይከብዳል!” ይላል። ቢሆንም “ለማመን ይከብዳል” እያለ፣ ማመን ይጀምራል - በ”ተአምር” ያምናል። የስኬት ምንጮችን ከስረ መሰረታቸው ለይቶ ለማወቅ ፍላጎት ስላልነበረው፤ ማንኛውም አይነት የስኬት ጭላንጭል ሲያጋጥመው፤ “ይሄ በአንዳች ተአምር የተገኘ ውጤት ነው” ብሎ ሊያምን ይችላል። ውድቀት እንደ እርግማን ከሆነበት፤ ስኬት ደግሞ እንደ ትንግርት ይሆንበታል። ከአንድ ስትተት ወደ ሌላ ስህተት እየዘለለ ይገባል። እርግማንን በማመን በድንዛዜ ውስጥ የከረመ ሰው፣ ተአምርን በማመን ከመቅፅበት ወደ ሆይሆይታ ይሻገራል።
በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ፣ ያኔ በ97ቱ የምርጫ ወቅት፣ በአንዳች ምትሃት ለውጥ እንደሚመጣ አምኖ፣ “ዛሬውኑ ገዢውን ፓርቲ አስወግጄ ትንግርታዊ ለውጥ ካላየሁ” የሚል ሆይሆይታ የተፈጠረው በትኩሳት አባዜ ሳቢያ ነው - የስኬትን ምንጭ ካለመገንዘብ ጋር የተያያዘ አባዜ። የስኬትን ምንጭ በአግባቡ የሚገነዘቡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩን ኖሮማ፣ ገዢውን ፓርቲ በማስወገድ ተአምራዊ ለውጥ እንደማይመጣ አይጠፋቸውም ነበር። “ስልጡን የፖለቲካ ለውጥ እውን የሚሆነው፤ በአንዳች ተአምር ሳይሆን፣ በረዥም ጊዜ የነፃነት አስተሳሰብን በማስፋፋት ነው” የሚል የስኬት ስረ መሰረት ስላልተገነባ፤ የቀድሞው ድንዛዜ ከመቅፅበት ወደ ትኩሳትና ወደ ሆይሆይታ ተቀየረ። በ2002 ምርጫ 99.9 በመቶ አሸነፍኩ የሚለው ኢህአዴግም እንዲሁ፣ አገሪቱ የእልቂትና የብተና አፋፍ ላይ ነች ሲል እንዳልነበረ፤ ድንገት ተነስቶ የኢትዮጵያ ህዳሴ ተበሰረ እያለ ትንግርታዊ ትረካዎችን ሲያራግብ የሰማነው የጤንነት አይደለም - ትኩሳት ነው። በፈጣን እድገት የአለም አንደኛ ሆኛለሁ ብሎ ተአምራትን እየሰበከ፤ ከ2007 በኋላ የእርዳታ እርዳታ አልፈልግም ብሎ ያውጃል። የትኩሳት ነገር... በቃ፤ የምትናገረውን ያሳጣል። 99.9 በመቶ በማሸነፍም፣ ተቃዋሚዎችን እንዳያንሰራሩ በማንኮታኮት ወይም አገሬውን 1ለ5 አደራጅቶ እለት በእለት የህዝቡን እንቅስቃሴ በመቆጣጠርም፣ የህዳሴ ለውጥ አይመጣም። እንዲያውም ከነባሩ የኢትዮጵያ ባህል ንቅንቅ አለማለታችንን ነው የሚያሳየው። ያለ ተፎካካሪ አገሪቱን ሰጥ ለጥ አድርጎ በብቸኝነት የመግዛት ፍላጎትኮ ለዘመናት የዘለቀ ነባር የኢትዮጵያ ባህል ነው።
በአጭሩ፤ በፖለቲካ በኩል ያየናቸው የለውጥ ጭላንጭሎች፤ በስኬት ስረ መሰረት ላይ የተገነቡ ስላልሆኑ፤ በሆይሆይታ፣ በትኩሳትና በግርግር ውስጥ ብዙም ሳይቆዩ በነባሩ የጥላቻና የመጠፋፋት ረግረግ ተውጠው ይቀራሉ። እናም “ተአምረኛው”፣ “ትንግርታዊው” ለውጥ የውሃ ሽታ ይሆንና፤ ትኩሳቱና ሆይሆይታው ትርጉም ያጣል። ከዚህ ውድቀት ጋር ቀስ በቀስ ድንዛዜ ይነግሳል። “ተወው ባክህ! የኢትዮጵያ ፖለቲካ መቼም አይለወጥም! ከእርግማን አይለይም” የሚል ስሜት የተጫጫነው ሰው ይበዛል። በጭፍንነት ሳቢያ የሚፈጥር አዙሪት ነው - ዡዋዥዌ። ከውድቀት ጋር የእርግማን እምነትና ድንዛዜ ይነግሳል - ዝምታና ቁዘማ የበዛበት ድንዛዜ። ከዚያ ደግሞ ከለውጥ ጭላንጭል ጋር የተአምር እምነትና ትኩሳት ይቀጣጠላል - ሆይሆይታና ግርግር የበዛበት ትኩሳት። ያው ትኩሳትም የጭፍንነት ምልክት ስለሆነ፤ ውጤቱ አያምርም - እንደገና ተመልሶ ወደ ውድቀት፣ ወደ እርግማን እምነትና ወደ ድንዛዜ ይገባል።
የእድገትን ጭላንጭል የሚያዳፍን ሆይሆይታ
የአገሪቱ ኢኮኖሚም እንዲሁ ከተመሳሳይ አዙሪት ወይም ከዡዋዥዌ አላመለጠም። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የመሻሻል ጭላንጭል ጎላ ብሎ የወጣው የሚሌኒየሙ መባቻ 2000 ዓ.ም በተቃረበበት ወቅት ነው። ያለ ተጨባጭ ምንጭ በአንዳች ተአምር የተከሰተ ጭላንጭል አይደለም። የንግድ ፈቃድና የኢንቨስትመንት ምዝገባ ላይ ከ95 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ በተደረጉ መጠነኛ ማሻሻያዎች አማካኝነት ነው፣ የለውጥ ጭላንጭል ብቅ ያለው። ለአምስት ተከታታይ አመታት ከአስር በመቶ በላይ እድገት ተገኝቷል ተባለ።
ከዚያማ መንግስትን ማን ይቻለው? እድገቱኮ ገና ጭላንጭል ነው። አገሪቱ ገና ከድህነት ፈቀቅ አላለችም። የመጨረሻው የድህነት ጠርዝ ላይ ከሚገኙ አስር የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ነች። ቢሆንም፤ በዚያችው ጭላንጭል ሆይሆይ ማለት ተጀመረ። መንግስት በስሜት ጦዘ። “ለአፍሪካ በአርአያነት የሚጠቀስ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገበ ልማታዊ መንግስት” ተብሎ ተዘመረ። መንግስት ይበልጥ ከኢኮኖሚው እንዲወጣና ነፃ ገበያ እንዲስፋፋ ከማድረግ ይልቅ፤ “ኢኮኖሚውን በስፋት የሚቆጣጠር ልማታዊ መንግስትን እናጠናክራለን” የሚሉ መፈክሮች በየአቅጣጫው ተስተጋቡ።
የእድገት ጭላንጭል ለመታየት የበቃው በምን ምክንያት እንደሆነ ተረስቶ፤ መንግስት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከዳር ዳር ለመቆጣጠር ሰፊ ዘመቻ ከፈተ። የ95ቱ ማሻሻያ ተንኮታኩቶ፣ በአላስፈላጊ ቁጥጥሮችና በተንዛዛ ቢሮክራሲ ኢንቨስትመንትን የሚተበትብ አዲስ አሰራር የታወጀው በ2002 ዓ.ም ነው። የአገር ኢኮኖሚ የሚያድገው፤ ሁሉም ሰው የራሱን ሕይወት ለማሻሻል በሚያደርጋቸው የግል ጥረቶች፣ የግል ኢንቨስትመንቶችና የቢዝነስ ስራዎች ሳይሆን፤ በመንግስት ቁጥጥርና ድጎማ ነው ተብሎም፤ በዚያው አመት እቅድ ወጥቷል - የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ።
እቅዱ፤ በአምስት አመት ውስጥ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጥፍ ለማሳደግ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ለ3 ሚሊዮን ዜጎች ስራ ለመፍጠር፣ የግብርና ምርትን በሃምሳ በመቶ ለማሳደግ፣ ኢንዱስትሪውን በ150% ለማሳደግ ያስችላል ተብሎ ሲወደስ ሰምታችሁ ይሆናል። መቼም ይህን እድገት እውን ለማድረግ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል።

ታዲያ፣ በእቅዱ መሰረት፣ የዜጎች የኢንቨስትመንት ድርሻ 30 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። የመንግስት የኢንቨስትመንት ድርሻ ደግሞ 70 በመቶ ገደማ። በሌላ አነጋገር፤ ተአምራዊ እድገት የሚመጣው በመንግስት በኩል ነው።
ለእድገት ጭላንጭል መነሻ የሆኑት መጠነኛ የነፃ ገበያ ማሻሻያዎችን በማፍረስና በተቃራኒው የመንግስትን ቁጥጥር በማሳበጥ እንዴት እድገት ይገኛል? በአንዳች ተአምር? በስሜት የተጥለቀለቀው መንግስት ለእንደዚህ አይነት ጥያቄ ጊዜ አልነበረውም። “እንዲያውም ከአምስት አመት በኋላ የእርዳታ እህል አንፈልግም” ብሎ አወጀ። እንግዲህ ያኔ 12 ሚሊዮን ያህል ተረጂዎች ነበሩ። ዛሬ፣ ከሁለት አመት ተኩል በኋላ፤ የተረጂዎቹ ቁጥር ቀንሷል? በጭራሽ። አሁንም 12 ሚሊዮን ገደማ የገጠር ነዋሪዎች ያለ እርዳታ መኖር አይችሉም። በእቅዱ ላይ እንደሰፈረው፤ ኢንዱስትሪው በ20 በመቶ እያደገ ነው? በጭራሽ። እንደታቀደው፤ የግብርና ምርት በ8.5 በመቶ እያደገ ነው?
የታሰበው ያህል እድገት እየተመዘገ እንዳልሆነ የአለም ገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቢቆይም፤ መንግስት ብዙ ዘግይቶ ሰሞኑን እውነታውን በመቀበል ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው መሰረትም፤ የ2004 የግብርና ምርት እድገት ወደ 5 በመቶ የሚጠጋ ነው። የስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2005 ዓ.ም የእርሻ ምርት ጥናታዊ ግምት እንደሚያሳየው ደግሞ፤ የዘንድሮውም እድገት ከዚህ የተሻለ አይሆንም። በዚህ ስሌት የግብርና ምርት በሃምሳ በመቶ ለማደግ ዘጠኝ አመት ያስፈልገዋል።
እንደተባለው፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል እያገኙ ነው? ካቻምና ግማሽ ሚሊዮን ወጣቶች፣ አምናም እንዲሁ ግማሽ ሚሊዮን ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት አማካኝነት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው በተደጋጋሚ ሰምተናል። እውነታው ግን ከዚህ “ተአምራዊ ለውጥ” በእጅጉ ይለያል። ለተወሰነ ጊዜ የተወሰኑ ወጣቶች ስራ ያገኛሉ - ከመንግስት በኮንትራት እየተሰጣቸው። ኮንትራቱ ሲያልቅ፣ ስራቸው ሲቋረጥ ሌሎች ወጣቶች በሌላ ኮንትራት ለተወሰነ ጊዜ ስራ ይሰጣቸዋል። በጥቅሉ ሲደመር፤ ከሚሊዮን በላይ ሊሆን ይችላል። ስራ የተቋረጠባቸውን የምንቀንስ ከሆነ ግን፤ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ብዙም ፈቅ እንዳላለ እንገነዘባለን። በእርግጥ፣ መንግስት ገና ከሆይሆይታ ስላልወጣ፤ ይህንን እውነት አሁኑኑ ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ውሎ አድሮ ግን፤ የስራ አጥነት ችግር አግጥጦ መታየቱ የማይቀር ነው። ውሎ አድሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ አይደል? ዡዋዡዌ ነው።

Read 3605 times