Saturday, 16 February 2013 12:15

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝን “ዕጣ ወጥቶልኝ” አነጋገርኳቸው!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

* ተቃዋሚዎች የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚያከራየን አጣን አሉ!
* የሆቴል ባለቤቶች “ለምን እንደጭራቅ ፈሩን” ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ!

በተለያዩ ጊዜያት ከአገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የመገናኘትና ኢንተርቪው የማድረግ ውጤት አልባ ሙከራዬን በተመለከተ በማቀርባቸው መጣጥፎች የተነሳ አንድም ትላልቅ ባለስልጣናትን የማግኘት ከፍተኛ ረሃብ አሊያም ወደ ፖለቲካው ሙያ የመግባት ፅኑ ፍላጎት እንዳለኝ የሚያስቡ የዋሆች አይጠፉም ብዬ እገምታለሁ፡፡ (ሥራዬን በአቋራጭ ማመልከቻ እንደማስገባት እየቆጠሩት) እነሱ ይሄን ማሰባቸው ኃጢያት ነው የሚል አቋም ባይኖረኝም በመርህ ደረጃ ሃሳባቸው የአመለካከት ችግር ያለበት መሆኑን በማያዳግም መልኩ መንገር ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ (የኢህአዴግን መግለጫ መሰለ አይደል?) እናላችሁ --- ለእኒህ የዋሆች አንድ ቀልድ አዘል ቁምነገር ልነግራቸው ፈለግሁ (እንደኢህአዴግ መፈረጅ ስለማልወድ ነው!)
ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነ ነው፡፡ አንድ ወጣት ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ኀይሌ ገብረሥላሴ ወደ ፖለቲካው ሊያተኩር ነው የሚለውን ወሬ ጮክ ብሎ ለጓደኞቹ ያወራል፡፡ ከጓደኞቹ መካከል ይህንን ጨዋታ ከጎኑ ለተቀመጡ አዛውንት ሊያጋራ የፈለገው ወጣት ወደሳቸው ዞር ብሎ -
“ይህን ታሪክ ሰሙ አባባ?”
“የትኛውን?”
“ኃይሌ ገ/ሥላሴ “ሩጫውን ትቼ ፖለቲካው ላይ ላተኩር ነው የምፈልገው” አለ የተባለውን”
“ምን ነካው እሱ ደሞ ---- ከእውነት ወደ ውሸት ይሄዳል እንዴ?” ሲሉ ዘበቱ አዛውንቱ፡፡
መቼም የአገር ሽማግሌ አይጥፋ ነው (እንደ ኀይሌ የሚሰማ ሲገኝ ነዋ!) ይሄው ከዚያ ወዲህ ጀግናው አትሌታችን “ፖለቲካ ለምኔ!” በማለት ሙያው ላይ አተኩሮ በመትጋት ላይ ነው - እውነቱ ላይ ማለት ነው፡፡ ለነገሩማ የፖለቲካ ጠበኞች አስታራቂ ሽማግሌ ሆኖም አይቶታል - ፖለቲካ ውሸት (የዋሾዎች) መሆኑን፡፡
የ97 ምርጫን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ፣ ከየቤታቸውና ቢሮአቸው ተለቃቅመው የታሰሩትን (ኢህአዴግ “ራሴን ከናዳ ለማዳን ነው ያሰርኳቸው” ብሏል!) የቅንጅት አመራሮች ለማስፈታት የተቋቋመው የአገር ሽማግሌዎች ኮሚቴ አባል እንደነበረም አይዘነጋም፡፡

(አንዳንድ በ97 ምርጫ የተዘረሩ የኢህአዴግ አባላት “ቅንጅት” የሚለውን ቃል ሲሰሙ ይበረግጋሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ?)
አትሌት ኃይሌ በሽምግልና ሰበብ ወደ ፖለቲከኞቹ መቅረቡ ትልቅ ተመክሮ ሳይሰጠው የቀረ አይመስለኝም - የሦስተኛ ዓለም ፖለቲካን እርም ለማለት!! (ሩጫ ነፃነት ይፈልጋል አቦ!) ይሄን ሁሉ ያመጣሁት መቼም ለምን እንደሆነ ሳትገነዘቡ አትቀሩም ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔም ከኃይሌ ተምሬአለሁና ፖለቲከኛ ወይም ባለሥልጣን የመሆን ህልምና ምኞት የለኝም ልላችሁ ፈልጌ ነው (ፖለቲካ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም ያለው ማን ነበር?) ግን ደግሞ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛልና ኪሳራ ቢሆንም ፖለቲካ ማውራቴ፣ ፖለቲከኛ ማማቴ (ሱስ እኮ አይደለም!) አይቀርም - ምርጫ ስለሌለኝ (ፖለቲካ እንጀራዬ ነዋ!)
“የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል” የምትለዋ ሐረግ ምን እንዳስታወሰችኝ ታውቃላችሁ? የገጣሚ ኑረዲን ዒሳን “እኔ ምን አገባኝ” የምትል ግጥም!
እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሃረግ
እሱ ነው ሃገሬን ያረዳት እንደበግ
የሚል ግጥም ልፅፍ
ብድግ አልኩኝና
ምን አገባኝ ብዬ
ቁጭ አልኩ እንደገና፡፡
እኔ ግን በአገር ጉዳይ ምን አገባኝ ብሎ መቀመጥ አልፈጠረብኝም (ዕድል ይሆን ፍርጃ?) በነገራችሁ ላይ መቼና የት እንደሆነ ባላስታውስም የተከበሩ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣“በአገራችሁ ጉዳይ ምን አገባኝ አትበሉ!” የሚል ምክር የለገሱ መሰለኝ፡፡ አሁን እንግዲህ በርዕሴ ላይ እንደጠቆምኩት “ጠ/ሚኒስትሩን አነጋገርኳቸው!” ያልኩትን ጉዳይ ላብራራላችሁ፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ አዲሱ ጠ/ሚኒስትራችን (ግን ለምንድነው ሁሌ አዲስ የሚመስሉኝ?) የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ እንደ ቱባ ባለሥልጣን (ያውም የአገር መሪ!) ፈፅሞ አይከብዱም፡፡ ፊታቸው ላይ የወዳጅነትና የፍቅር መንፈስ እንጂ የመጠራጠርና የተዓብዮ ስሜት አይታይባቸውም (ዓይኔ ይሆን እንዴ?) በእርግጥ ከዚህ ቀደም ከኢቴቪና ከአዲስ አበባ መስተዳድር ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉትን ኢንተርቪው ስከታተል ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ በአጭሩ ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? ባለሥልጣን ባለሥልጣን ሳይሆን ሰው ሰው የሚሸቱ ጠ/ሚኒስትር ሆኑብኝ ልል ፈልጌ ነው (ማን ይሆን “ሰዓሊ ከመሆንህ በፊት ሰው ነህ” ያለው?) ለምን እንደሆነ ባላውቅም ጠ/ሚኒስትሩ “ትንሽ ቆይተው----ሥልጣን ሲጥማቸው ይለወጣሉ” የሚል አጉል ጥርጣሬ አደረብኝ፡፡ የብዙ አፍሪካ አገራት መሪዎችን ታሪክ ስላነበብኩ ይሆን? (“before and after power” ታሪካቸውን ማለቴ ነው!) የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችማ ቀላል ይለወጣሉ መሠላችሁ! (የሆሊውድ ፊልም ላይ እንዳለችው “ማያ” እኮ ነው እየተቀያየሩ ህዝባቸውን ግራ የሚያጋቡት - አንዴ ሰው ሌላ ጊዜ ወፍ፣ አንዴ ጉንዳን ሌላ ጊዜ ደግሞ ድመት እየሆኑ!) ብቻ አንድዬ ይጠብቀን!!
ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር በቅርቡ ባደረጉት ልዩ ቃለምልልስ፣ “ከአሁኑና ከንጉሱ ዘመን የፓርላማ ሥርዓት ይበልጥ ነፃነት የሰፈነበት የትኛው ነው?” ሲባሉ፣ ሁለቱ ፓርላማዎች ለየቅል መሆናቸውን ገልፀው፣የአሁኑ “የፓርቲ ዲሲፕሊን” የሚባል ነገር ስላለ ለግለሰቡ “ፍፁም ነፃነት” የሚሰጥ አይደለም ብለዋል (የዲፕሎማሲ ችሎታቸውን ለአንዳንድ የኢህአዴግ አመራሮች ተመኘሁላቸው!) እናላችሁ----ይሄ “የፓርቲ ዲሲፕሊን” የሚሉት ክፉ አባዜ፣እኚህን “ሰው ሰው የሚሸቱ ጠ/ሚኒስትር” እንዳይለውጥብን ክፉኛ ሰጋሁ፡፡ (ፓርቲው የጠ/ሚኒስትርነት “ኩፍጥና” ያንሳቸዋል ብሎ ከገመገማቸው እኮ አለቀልን!)
እኔና እሳቸው በተገናኘንባት የጠ/ሚኒስትር የማትመስል ትንሽዬ ቢሮ ውስጥ ስንታይ፣ አንድ የአገር መሪና ዘወትር ከስጋት ተላቅቆ በማያውቅ የግል ፕሬስ ውስጥ የሚባትል ጋዜጠኛ አንመስልም ነበር፡፡ አስተማሪና ተማሪ እንጂ! በነገራችሁ ላይ የእንግሊዝኛ ጋዜጦቻችን አዲሱን ጠ/ሚኒስትር “ኃይሌ” በሚል አሳጥረው እንደሚጠሯቸው ያወቅሁት በቅርቡ ነው፡፡ እንግዲህ ዝርዝሩን ባላውቅም ከሳቸው ጋር የተገናኘሁት ከግል ፕሬስ ኢንተርቪው ለማድረግ “እጣ ወጥቶልኝ” እንደሆነ የሰማሁት ከአለቃዬ ነው፡፡ (“የፕሬስ ነፃነት በእጣ” የተባለ አይመስልም?) ከሁሉም ያልገባኝ ግን ምን መሰላችሁ? ለምን “አርነት የወጡ ሃሳቦች” የምትል ሚጢጢዬ የግጥም መፅሃፍ በእጄ እንደያዝኩ ነው፡፡ በእርግጥ ገጣሚውን ዳዊት ፀጋዬን በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ የግጥሙን መፅሃፍም ፈርሞበት ነው ያበረከተልኝ፡፡ (ኢንተርቪው እንጂ የ“አርነት” ጥያቄ አቅርብ አልተባልኩ!) አልፎ አልፎ ፊትለፊቴ የተቀመጡትን ጠ/ሚኒስትር እየቃኘሁ፣በአብዛኛው ግን ግጥሞቹን ያለቀልቤ እያነበብኩ ሳለ ነው፣ ፕሮቶኮሏ ኢንተርቪውን እንድጀምር ምልክት የሰጠችኝ፡፡ በደመነፍስ መፅሃፍዋን ገልጬ “ለአንተ ስል”
የምትለዋን የዳዊት ግጥም ፈቃዳቸውን ሳልጠይቅ ላነብላቸው ተዘጋጀሁ (ምን ፈልጌ እንደሆነ ግን ለራሴም አልገባኝ!)ንባብ ከመጀመሬ በፊት ቀና ብዬ የጠ/ሚኒስትሩን በመነፅር የተከለሉ ዓይኖች ቃኘት አደረግሁ - የደስታ ብርሃን ይረጫሉ፡፡ ቢያንስ ግጥም እንደማይጠሉ ገባኝ (በሆዴ“አቦ ይመችዎት!” ያልኩኝ መሰለኝ)
ሰዎች በረሃብ ሲያልቁ
አፋቸውን በአንተ እንዳያላቅቁ
ፍትህ በምድር ሲጠፋ
ብስጭታቸው እንዳይከፋ
እምነታቸው እንዳይላላ
ነፍሳቸው አንተን እንዳትጠላ፣
“እግዚአብሄር የለም እንዴ?” ሲሉ
“አዎ የለም” የምለው
ስለ አንተ ብዬ ነው፡፡
ቀና ብዬ ሳያቸው መሳቅ ፈልገው ራሳቸውን የገደቡ ዓይነት ስሜት አነበብኩባቸው - ገፅታቸው ላይ፡፡ ግን ለምን በነፃነት አልሳቁም? (ሺ ዓመት አይኖር!) ትዝ ይላችኋል---- የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና!) በሚሊኒየም በዓል ላይ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ ከባለቤታቸው ጋር በሱዳንኛ ዘፈን ሲደንሱ? ለምን እንደሆነ አላውቅም፣የዛን ዕለት ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ለጠ/ሚኒስትሩ ሌላ ግጥም ልደግምላቸው ከጅሎኝ ነበር፡፡ (ነፍሴ first thing first ያለችኝ መሰለኝ) በእርግጥ እሳቸውም ሁለተኛ ግጥም እንዲነበብላቸው የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ (ጥያቄው በግጥም ንባብ እንዲቀየርላቸው ተመኝተው ይሆን እንዴ?) እውነት ለመናገር ግን በደስታ ስሜት ተጥለቅልቄ ነበር! (ግጥም ይወዳሉ ማለት ነው አልኩ - ለራሴ እየደጋገምኩ!) ግን ለምን ደስ አለኝ? “ግጥም መውደድና አለመውደድ ከባለሥልጣን ሥራና ባህርይ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም” የሚል ሃሳብ ድንገት ወደአዕምሮዬ መጣብኝና ደስታዬን ከመቅፅበት ነጠቀኝ- ምቀኛ! ሃሳቡ እንኳን ስህተት ያለው አይመስልም፡፡ አምባገነን መሪ ምን ግጥም ቢወድ እኮ ከአምባገነንነቱ ላይ አይቀንስለትም! (ግጥም ሰብዓዊነት ያላብሳል ያለው ማነው?) ለነገሩ ከኢህአዴግም ከተቃዋሚዎችም ስንት ባለቅኔ ፖለቲከኞች እኮ አይተናል፡፡ (ቅኔ መቀኘትና ዲሞክራሲን መቀኘት ግን ለየቅል ናቸው!)
ለአይን መግለጫ ያህል አንዷ ግጥም በቂ እንደሆነች በማሰብ በቀጥታ ወደ ጥያቄዎቼ ለመግባት ወሰንኩ፡፡

እሳቸውም ፈተና እንደሚጠባበቅ ትጉህ ተማሪ በትኩረት እየተጠባበቁኝ ነበር፡፡ ለነገሩ የ87 ሚ. ህዝብ ህልቆ መሳፍርት ጥያቄዎችን መመለስ ከየትኛውም ምድራዊ ፈተና የበለጠ ሊከብድ እንደሚችል ለማወቅ “ኒዩክለር ሳይንስ ማጥናት” አይጠይቅም፡፡ በተለይ ከድህነት ለመላቀቅ መከራዋን በመብላት ላይ ያለች ምስኪን አገር የመምራት ሃላፊነት ድንገት ትከሻው ላይ ለወደቀበት “የዩኒቨርስቲ ምሁር”!!
ከጃኬቴ ኪስ ውስጥ ያወጣሁትን ማስታወሻ ደብተር ገልጬ፣ጠ/ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ባሉ ቁጥር “የመለስን ራዕይ እናሳካለን” በማለት እንደፀሎት የሚደጋግሙትን ትክት ያለ ንግግር የተመለከተ ጥያቄዬን በማስቀደም ቃለምልልሱን አሃዱ ልል ወደድኩ፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤አንዳንድ የህብረተሰብ ወገኖች ጠ/ሚኒስትሩ ትክክለኛ ራሳቸውን ሆነው የምናያቸው መቼ ነው ሲሉ ይደመጣሉ (ጠ/ሚኒስትሩ አምልጧቸው ሳቅ አሉ) እውነቴ ነው ጠ/ሚኒስትር… ሁልጊዜ ሲናገሩ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ንግግር ከማስታወስና “የመለስን ሌጋሲ እናስቀጥላለን!” ከማለት ውጭ የራስዎትን አቋም የሚያንፀባርቅ ነገር ተናግረው አያውቁም፡፡ እንደውም ዳያስፖራ ያሉ ተቃዋሚዎች፤የምዕራቡ ዓለም “ጐስት ራይተር” ሲሉ ሰምታ ኢትዮጵያም “ጐስት ፕራይም ሚኒስትር” ፈጠረች እያሉ እንደሚቀልዱ ሰምቻለሁ… በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራርያ ቢሰጡ ጥሩ ይመስለኛል…
(ጠ/ሚኒስትሩ እንደገመትኩት የስሜት ለውጥ አላሳዩም፤ ዘና ብለው መመለስ ጀመሩ፤ጥያቄዬ ቀድሞ ደርሷቸው ይሆን እንዴ? አልኩ - ለራሴ፡፡ ግን እንዴት ሆኖ? ወዲያው ትኩረቴን ወደመልሳቸው አደረኩኝ) ማንም ምንም ቢል የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ አሁንም ወደፊትም የመለስን ሌጋሲ ነው የምናስቀጥለው፡፡ ፓርቲው ለዚህ ትግል ሲመርጠኝ የመለስንና የፓርቲያችንን ራዕይ ከጓዶቼ ጋር ሆኜ እውን ለማድረግ ነው ቃል የገባሁት፡፡ ከዚህ የበለጠም ሆነ ከዚህ ያነሰ አይደለም የእኔ ሚና፡፡ የአገርና የፓርቲ ራዕይ ግለሰቦች በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር አይደለም፡፡ ጉዳዩን በዚህ መልኩ ብናየው ሳይሻል አይቀርም (እንዴ---በየት መልኩ?) (ቀጣዩን ጥያቄ አስከተልኩ) በቅርቡ “ጅሃዳዊ ሐልካት” የተሰኘ በአክራሪነት ዙርያ ያጠነጠነ ዶክመንታሪ በኢቴቪ ሲሰራጭ እንኳን፣የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ንግግር ነው የተደመጠው፡፡ ይሄ ደግሞ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ ፈጥሯል፡፡ ይሄን ብዥታ ማጥራት የሚገባ አይመስልዎትም?
ምንም ብዥታ የለም፣ ሁሉም ነገር ጥርት ያለ ነው፡፡ በሁሉም ረገድ ሌጋሲውን የማስቀጠል ዓላማ ይዤ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ፓርቲውም ለትግል ያጨኝ ይህን አደራ እንድወጣ ብቻ ነው (መልሳቸውን በአጭሩ ገቱት)
አሁን ደግሞ ወደ ተቃዋሚዎች እናምራ -------- ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ 28 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ አግኝተው፣15 ሆቴሎች አዳራሽ አናከራይም በማለታቸው የምንሰበሰብበት አጥተናል የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ሳይሰሙ የቀሩ አይመስለኝም------
(ቅንነት የጎደላት የምትመስል ፈገግታ ብልጭ አደረጉና መናገር ጀመሩ) ቅሬታውን እንኳ አልሰማሁትም… እኔ የማውቀው የማተምያ ቤቶቹን ብቻ ነው፡፡ እሱን አንተም እንደምታውቀው፣ነፃ አገር ውስጥ እንደምንኖርና ማንኛውም ባለስልጣን ቢሆን ማተምያ ቤት ደውሎ የ“አንድነት” ጋዜጣን አታትሙ የማለት መብት እንደሌለው ገልጬ፣ነገሩ በዚያው ተቋጭቷል፡፡ የአዳራሹን እንኳን ይሄው ካንተ መስማቴ ነው፡ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ የማተምያ ቤቶቹ ችግር እኮ እርስዎ እንደሚሉት አልተቋጨም፡፡ አንድነት ፓርቲ እንደውም የራሱን ማተምያ ቤት ለማቋቋም የገንዘብ ማሰባሰብያ (Fundraising) ፕሮግራም ሰሞኑን ማዘጋጀት ጀምሯል፡፡
ኤክሰለንት! ፓርቲዎቻችን እንዲህ ችግር ፈቺ ነው መሆን ያለባቸው፡፡ ኢህአዴግም ሊያግዛቸው ይችላል፡፡ ያው ለአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ስርአት መጠናከር አነሰም በዛም አስተዋፅኦ እንዳላቸው ፓርቲያችን ያምናል፣ ስለዚህ ነገሩን የዲሞክራሲ ሥርዓትን እንደማጎልበት በመቁጠር የማተምያ ማሽኑ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ እናግዛቸዋለን፡፡
(ጆሮዬ የሚሰማውን ማመን አቃተው) ይሄ ደስ የሚል ሃሳብ ነው ጠ/ሚኒስትር--- ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በትብብር ቢሰሩ እኮ ጥቅሙ ለአገር ነው… (ሆኖም አላስጨረሱኝም) በትብብር መስራት የሚለው እንኳ አያስኬድም፡፡ የኢህአዴግና የተቃዋሚው መስመር ፈፅሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ጉዞአችን ለየቅል ነው፡፡ ኢህአዴግ የጠራ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አቅጣጫን ነው የሚከተለው፡፡ በዚህ ሂደት ደሞ ኪራይ ሰብሳቢዎችን በየጣቢያው እያራገፈ፣ ልማታዊ ኃይሎችን አቅፎና ደግፎ ነው ወደ ግቡ የሚደርሰው፡፡ ስለዚህ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያስተባብረን የጋራ ዓላማ የለንም፡፡ በመርህ ደረጃ ግን ህዝቡ አማራጭ እንዳያጣ የተቃዋሚዎችን መኖር እንደግፋለን (ኢህአዴግን ያመነ አልኩ - በሆዴ!) እሺ የሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ አጣን ለሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን መፍትሄ ይሰጧቸዋል? (በተስፋ መቁረጥ ስሜት ነው የጠየቅኋቸው)
ዌል… ኢህአዴግ እንግዲህ ሆቴልም አዳራሽም የለውም፡፡ ምናልባት እነ መድረክ እንደ ጦር የፈሩትን የምርጫ ስነምግባር ደንቡን ለመፈረም ፈቃደኛ ከሆኑ፣ በፓርቲዎች የጋራ ምክክር መድረክ በጉዳዩ ላይ ተወያይተን መፍትሄ ልንፈልግለት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ፓርቲዎቹ እኮ ከህዝብ ጋር መገናኘት አልቻልንም… ሆቴሎች በአድማ አናከራይም ብለውናል… እንደውም የመንግሥት እጅ አለበት እያሉ ነው…
አሁንም ስለማተምያ ቤቶች ስናገር ያልኩትን እደግመዋለሁ፡፡ እኛ ሆቴሎችን እየዞርን “ለመድረክ ፓርቲ አዳራሽ አከራዩ አታከራዩ” እያልን እጃቸውን መጠምዘዝ አንችልም፡፡ መብትም የለንም፡፡ ዲሞክራሲያዊ አገር ውስጥ እኮ ነው ያለነው፡፡ ግን ፓርቲዎቹ፤ “እነዚህ ሁሉ ሆቴሎቹ ለምን እንደ ጭራቅ ፈሩን?” ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ቆይ ለምን ፈሯቸው? እኔ የተቃዋሚ አመራር ብሆን ኖሮ ምክንያቱን ለማስጠናት እሞክር ነበር… ይሄ እኮ ስር የሰደደ ችግር ነው፡፡ ኢህአዴግ ለምሳሌ እንኳንስ የሆቴል አዳራሽ ኪራይ ሊከለከል ቀርቶ፤“የህዝብ ፓርቲ ስለሆነ ክፍያ አንቀበልም” በሚሉ የሆቴል ባለቤቶች ነው የተቸገረው፡፡ በርካታ አዳዲስ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች አዳራሻቸውን በነፃ እንድንጠቀም እየጎተጎቱን ነው፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲና ተቃዋሚ አንድ ሊሆን አይችልም--ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ በ97 ምርጫ የግል ባለሃብት በሆኑ ደጋፊዎቻቸው ላይ መንግስት በፈፀመው ማስፈራሪያና ወከባ ባለሃብቶች በግልፅ ተቃዋሚዎችን ለመደገፍና ለማገዝ ይፈራሉ ይባላል፡፡ ይሄ ችግር እንዴት ይፈታል ብለው ያስባሉ?
መፍትሄው አንድ ብቻ ነው፤ተቃዋሚዎች እንደ ኢህአዴግ ህዝባዊ ፓርቲ መሆን አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ የማተምያ ቤትና የስብሰባ አዳራሽ ችግር የማይገጥመው ገዢ ፓርቲ በመሆኑ አይደለም፤ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያለው ልማታዊ ፓርቲ ስለሆነ ነው፡፡ (በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢህአዴግ ጋር ሙግት መግጠም ጊዜ ማባከን ስለመሰለኝ አንድ ሁለት ከምርጫ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች ላቀርብላቸው ወሰንኩ)
…በሚያዝያ ወር ከሚካሄደው የአዲስ አበባና አካባቢ ምርጫ ጋር በተገናኘ የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሰይድ “ተቃዋሚዎች ቢኖሩም ባይኖሩም ትርፍም ኪሳራም የላቸውም” ሲሉ በመናገራቸው በተቃዋሚዎች ጎራ ከፍተኛ ቁጣና ቅሬታ ቀስቅሷል፡፡

የሞባይሌ ድንገተኛ ጩኸት ከተቀመጥኩበት አስፈንጥሮ ሊያስነሳኝ ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሞባይሉ የትኛው ኪሴ ውስጥ እንደተሰወረ አላውቅም፤አጣሁት - ግን ጩኸቱን ቀጥሏል፡፡ ኪሴዬን በርብሬ በርብሬ ቀና ስል ጠ/ሚኒስትሩ የሉም፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ መቀመጫቸውም የለም፡፡ እኔና እሳቸው የነበርንበት ጠባብ ቢሮም ራሱ የለም፡፡ እኔም ያለሁት ወንበር ላይ ሳይሆን አልጋዬ ላይ ነኝ - መኝታ ክፍሌ ውስጥ! ሁለተኛውን ትራስ “አርነት የወጡ ሃሳቦች” የምትለዋ የግጥም መፅሃፍ የተንተራሰች መስላ ተቀምጣለች፡፡ ከግል ፕሬሶች መካከል “ዕጣ ደርሶኝ” ጠ/ሚኒስትሩን ኢንተርቪው ላደርጋቸው ቢሮአቸው መግባቴ በእውኔ ሳይሆን በህልሜ እንደነበር የተገነዘብኩት ዘግይቼ ነው፡፡ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በህልሜ የጀመርኩትን ቃለምልልስ ሳልጨርስ ከመባነኔ የበለጠ ያናደደኝ ግን ላነብላቸው ያሰብኩትን ወሳኝ ግጥም ባለማንበቤ ነው፡፡ በህልምም ቢሆን ባነብላቸው ይሻል ነበር ብዬ ተፀፀትኩ፡፡ ከዚያም መፅሃፊቱን ጐተት አድርጌ እንደዘበት ገለጥ አደረግኋት - ልክ የታዘዘ ይመስል ገፅ 35 ለእሳቸው ያሰብኩት ግጥም ላይ አረፍኩ - “ህዝብ፣ እግዜር፣ መንግስት!” ይላል ርእሱ፡፡
እግዚአብሄር፣
ምን ብሎ ይመልስ የህዝብን እሮሮ?
መንግስትን፣
እንዲናገር እንጂ እንዳይሰማ ፈጥሮ!
ጠ/ሚኒስትሩ እቺን ግጥም ቢሰሙ ምን አይነት ስሜት ይፈጠርባቸው ይሆን? (በህልም አለምም ቢሆን ማለቴ ነው!)

Read 5976 times