Saturday, 16 February 2013 12:22

የውጭ አገራት ምግቦች ቅምሻ (“Ethnic food/ Saturdays”)

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(1 Vote)

ለአንድ አመት የልምድ ልውውጥ ካምፓላ በቆየሁበት ወቅት አብራኝ የምትኖር ታንዛኒያዊት ጋዜጠኛ ነበረች
(housemate እንደማለት) አንድ ቀን ምግብ እየበላሁ አገኘችኝና “ብዩ” አልኳት፡፡ “ምንድን ነው የምትበይው?” ብላ በመጠየፍ ጠየቀችኝ፡፡ ላስረዳት ሞከርኩ፡፡ ግን ሊገባት አልቻለም፡፡ ለመንካትም ተጠይፋው አለፈችና ወደ መኝታ ቤቷ ገባች፡፡ ትንሽ ቆይታ እሷም የሚቆረጠም ነገር ይዛ ወጣችና “እንብላ” አለችኝ፣ “ምንድን ነው?” ስላት “Big ants” አለችኝ፣ (የተቆላ ጉንዳን ማለቷ ነው) እኔም በተራዬ ፊቴን አጨማድጄ እንደማልሞክረው ነገርኳት፡፡ እስቲ አስቡት ---- እንኳንስ ጉንዳን ሌላም ነገር ቢሆን ያለመድነው ከሆነ ለአበሻ ሆድ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙም ባይጠቅመንም ሆዳችን ቁጥብ ነው ወይም ኩሩ! የተገኘውን በጄ ብሎ መቀበል አለመደበትም ወይም አላስለመድነውም፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ጓደኛሞች የጀመሩት ፕሮግራም ነበር - “Ethnic food/Fridays” ይባላል (በኋላ ላይ Saturdays ሆኗል) ነገርዬው ብዙ ውስብስብ ነገር የለውም፡፡ በመዲናዋ የሚገኙ የውጭ አገራት ምግብ ቤቶችን (ሬስቶራንስ) እያደኑ የየአገሩን ምግብ መቅመስ ነው - ዓላማው (አድቬንቸር ነገር ልትሉት ትችላላችሁ) እነዚህ ምግብ ቀማሽ ጓደኛሞች ለራሳቸው የEthnic food አባላት የሚል ስያሜ ሰጥተዋል፡፡
እስካሁን አባላቱ በመዲናዋ ከሚገኙ የውጭ አገር ምግብ ቤቶች መካከል የሱዳን፣ የአርመን፣ የየመን፣ የግሪክ፣ የቱርክ፣ የሊባኖስ፣ የካናዳ፣ የኮሪያ፣ የቻይና፣ የህንድ፣ የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የታንዛኒያ፣የጣሊያን እና የፈረንሳይ ሬስቶራንቶች በመሄድ የየአገሩን ምግቦች እንደቀመሱ ይናገራሉ፡፡ የሜክሲኮ፣ የጀርመን፣ የታይና እና የስፓኒሽ ሬስቶራንቶች ግን እነሱ ሳይደርሱባቸው በተለያዩ ምክንያቶች በራቸውን በመዝጋታቸው የምግብ ቅምሻውን ሳያከናውኑ ቀርተዋል፡፡
“ሁላችንም በየቀኑ በቤታችንም ሆነ ከቤታችን ውጪ የለመድናቸውና የምንበላቸው ምግቦች ይኖራሉ፡፡
የኢትዮጵያም ሆነ የሌሎች አገሮች ምግቦች፡፡ በሳምንት አንድ ቀን እየተገናኘን በከተማዋ በሚገኝ የውጪ አገር ሬስቶራንት በመሄድ ቀምሰናቸው የማናውቃቸውን የተለያዩ አገራት ምግቦችን እንቀምሳለን፡፡” ይላሉ አባላቱ፡፡
ለዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት በስፖርት ጋዜጠኝነት የሚሰራው ኤልሻዳይ ነጋሽ በተለያዩ አገራት ሬስቶራንቶች ያጋጠመውን ሲገልፅ “በከተማዋ የሚገኙ እነዚህ ሬስቶራንቶች በሚገባ ስላልተዋወቁ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ደውሎ ቦታ ለማስያዝም የስልክ ቁጥራቸው ከየት ይመጣል፡፡ በዚያ ላይ ፌስቡክ እንኳን የላቸውም፣ የስልክ ማውጫ ላይ ስልካቸው አይገኝም፣ ጋዜጣ ላይም አይተዋወቁም” ያለው ኤልሻዳይ፣ ከለመደው ወጣ ያለ ምግብ በመብላት በኩል ችግር እንደሌለበት ይናገራል፡፡ ሆዱን ለዓለም አቀፍ ምግቦች አዘጋጅቶታል እንበል ይሆን?
“ምግቦችን ለመቅመስ በታደምንባቸው ሬስቶራንቶች በሙሉ ትእዛዝ እንዲቀበሉን ሳይሆን ስለምግቦቹ ዝርዝር ነገሮችን በመንገር ከምናዘው ምግብ ምንነት ጋር እንዲያስተዋውቁን ነው የምንነግራቸው፡፡
በዚህ በኩል ደግሞ የግሪክ ሬስቶራንት ጥያቄያችንን በሚገባ ተረድቶ እንደፈለግነው አገልግሎት ሰጥቶናል፡፡ ከአባላቱ ውስጥ የአሳማ ስጋ የማይመገቡ ይኖራሉ፣ አለርጂ የሆኑባቸው ምግቦች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ስለዚህ አስተናጋጆቹን ስለምግቡ በዝርዝር ነው የምንጠይቃቸው፡፡ በሁሉም ሬስቶራንቶች ቀድመን “we are complete idiots please guide us not serve us” እንላለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ጋ ፍላጐታችን ይሳካል ማለት አይደለም፡፡ ቻይኒዝ ሬስቶራንት ሜኑው በቻይኒኛ ነው፣ አበሾቹ አስተናጋጆች ስለምግቡ ብዙም አያውቁም፡፡ ቻይናውያኑ ደግሞ የቋንቋ ችግር አለባቸው፡፡ ስለዚህ ፍላጐታችንን ማሟላት አልቻሉም፡፡
ባለሬስቶራንቶቹ አዲስ ባህል ማስተዋወቅ ከፈለጉ የደንበኛቸውን ፍላጐት ለማሳካት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ የአገራቸውን ባህላዊ እና ለየት ያሉ ነገሮች ለምሳሌ ሙዚቃዎችን ማካተት ይኖርባቸዋል፡፡” ሲል የታዘበውን ይገልፃል፡፡ምንም እንኳን እዚህ በአገራቸው ያሉ አያሌ የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች ብዙ ጉድለት እንዳለባቸው ባይካድም በውጪ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ግን የአገራቸውን ባህል በማስተዋወቅና ድባቡንም በመፍጠር ረገድ አድናቆት የሚቸራቸው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ከኢትዮጵያ ውጪ ቢሆኑም ግድግዳ ላይ የሚሰቀለው ጌጥ እና ስዕል፣ የሚሰማው ሙዚቃ፣ የምግብ አቀራረቡ እና የቡና አፈላሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለሽ እንዲመስልሽ ያደርጋል፣ አዲስ አበባ ያሉት የውጭ አገራት ሬስቶራንቶችም የአገራቸውን ድባብ ለመፍጠር መሞከር አለባቸው፡፡
ካናዳ ሬስቶራንት ያጋጠመን በካናዳ ከተሞች እና ሆኪ የተሰየሙ የምግብ አይነቶች በሜኑ ዝርዝር ላይ አይተን ብናዝም፣ ከምናውቀው ምንም የተለየ ነገር አላገኘንም፣ የተለመዱ እንደ ቺዝበርገር አይነት ምግቦችን ነው የበላነው፡፡ የታንዛኒያን ምግብ ደግሞ አርብ አርብ ኤምባሲው ውስጥ ስለሚዘጋጅ እዛ ሄደን ነው የቀመስነው፡፡ ሁሉ ነገር ስጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ስሙን ሰምተሽው የማታውቂውን ምግብ ስታዢ አዲስ የሚሆንብሽ የምግቡ ጣእም ብቻ አይደለም፣ መጠንም (portion) ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዴ ለአንድ ሰው ያዘዝነው ምግብ ሦስት ሰው የሚያጠግብ ሆኖ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን እኔ በግሪክ ሬስቶራንት ተደስቻለሁ፡፡ ቱርክ ሬስቶራንት ሻይ እና ቡና በነፃ ተስተናግደናል፤ ሱዳን ሬስቶራንት ደግሞ ዋናውን ምግብ ሳይሆን ጣፋጮቹን ወድጄያቸዋለሁ፡፡ ሻይ ቡና ከማዘወትርበት ቦታም አንዱ ሆኗል፡፡” በማለት ስለጎበኛቸው ምግብ ቤቶችና ስለቀመሳቸው ምግቦች አጫውቶኛል - ኤልሻዳይ፡፡ስመኝሽ የቆየ ቀደም ሲል በሰብሰሃራን ኢንፎርመር ጋዜጣ ላይ አሁን ደግሞ በፍሪላንሰርነት የምትሰራ የቀማሾቹ ቡድን ሌላዋ አባል ናት፡፡
እሷ ደግሞ በኮሪያ እና በግሪክ ምግቦች ነው የተደሰተችው፡፡ “ግሪክ ሬስቶራንት አይቼ የማላውቃቸውን የአትክልት ዓይነቶች ጣት በሚያስቆረጥሙ መልኩ ተሰናድተው ቀምሻለሁ፡፡ አንዳንዶቹን ባውቃቸውም ሬስቶራንቱ ውስጥ ተሰርተው ባየሁበት መንገድ ኢትዮጵያ ወስጥ ተሰርተው አይቼ አላውቅም - ግሩም ሆነው የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ለካ እንደዚህም መሰራት ይችላል የሚያስብሉ ናቸው፡፡
የሱዳኑ ምግብ ጣእሙ ጣፋጭ ቢሆንም የሚዝለገለግ አይነት ስለሆነ ብዙም አልደፈርኩትም፡፡ የኮሪያ ምግቦች ጣፋጭ ሶሶች አሏቸው፡፡ ሜኑው ላይ ደግሞ የአሳማ ጆሮ ሳይቀር አለ፡፡ የሚገርመው ግን እጅግ ጣፋጭ መሆኑ ነው፡፡” ብላለች - ስመኝሽ፡፡በዘሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የሚሰራው ሌላው የቡድኑ አባል አለማየሁ ሰይፈስላሴ ደግሞ የየአገሮቹን ምግብ ለመቅመስ ሁለት ነገሮች ወሳኝ ናቸው ይላል፡፡
የምግቡ መጠን እና ጣእም፡፡ አንዳንዱ ምግብ ለቅምሻ ብቻ የተሰናዳ ያህል አንድ ፍሬ ይሆንና አያጠግብም፡፡ ጣእም ከልምድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አስተናጋጆቹን በመጠየቅ ወይም ያዘዘ ሰው በማየት ምግቡን እመርጣለሁ፡፡ ለምሳሌ የዳክዬ ጉበት መጠኑንም ሆነ ጣእሙን አታውቂም፡፡
የህንድ ምግብ ደግሞ ቅመም ይበዛዋል፡፡ ከኛ ጋር በጣም ይመሳሰላል፡፡ አንዳንዱ ስሙ ይማርክሽና ታዥዋለሽ፣ ሲመጣ ግን መሀሉ ላይ አንድ ትልቅ ሽንኩርት እና ዳር ዳሩ ያ የምታውቂው ሚትቦል (የስጋ ኳስ) ይሆናል፡፡ ለነገሩ ሁላችንም የተለያየ ምግብ ስለምናዝ አንዱ ከአንዱ ላይ ይቀምሳል፡፡
ፍቅር ጌትነት UN የምትሰራ የEthnic food አባል ናት፡፡ ለእሷ ደግሞ የፈረንሳይ ምግብ መጠኑ ባልጠበቀችው ሁኔታ ትንሽ ሲሆን በጣዕም ግን ወደር እንደሌለው ትናገራለች፡፡ በተለይ አይስክሬሙ፡፡ “ስለ ታንዛኒያ ምግብ ቀደም ሲል የሰማኋቸው መረጃዎች ብዙ እንድጠብቅ አድርጐኝ ነው መሰለኝ ምግቡን ስቀምሰው ብዙም አልወደድኩትም” ትላለች - ፍቅር፡፡
ሰላሳ ሆነው የጀመሩት ይሄ የEthnic food ቅምሻ ማህበር አሁን ወደ አስራ ሶስት ዝቅ ቢልም ቅምሻው ግን ቀጥሏል፡፡ እንግዲህ ምግብ ከበሉ በኋላ ሬስቶራንቱን ለቆ ከመውጣት በፊት የቢሏን ነገር (ሂሳቧን ማለቴ ነው) መዘጋጋት የግድ ነው፡፡ ምግቡን በጋራ እንደሚቀምሱ ሁሉ ሂሳቡንም በጋራ ነው የሚከፍሉት - የሚደርስባቸውን አስልተው፡፡
በታደሙባቸው የተለያዩ ሬስቶራንቶች እያንዳንዳቸው ከ70 እስከ 250 ብር አዋጥተው ከፍለዋል፡፡
በነፍስ ወከፍ 250 ብር ያስከፈላቸው በሁሉም ምግቦች ላይ እርጐ የማይጠፋበት የአርመን ሬስቶራንት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

Read 2565 times Last modified on Saturday, 16 February 2013 13:04