Saturday, 16 February 2013 13:16

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(9 votes)

ከወንጌል ጋራ የጥንት ባልንጀሮች ነን፡፡ ጎጆ ስትቀልስ ሚዜዋ ነበርኹ፡፡ የአሜሪካን ምድር በመርገጥ ግን በአምስት ወራት ትቀድመኛለች፡፡ምናልባት ካገኘኋቸው ወዳጆቼ መካከል አጭር ቆይታ ያላት እርሷ ሳትኾን አትቀርም፡፡አገር ቤት ሳለች የአንድ ትልቅ የግል ኩባንያ የዴስክ ሥራ አስኪያጅ ነበረች፡፡ጥሩ ትዳርና ሁለት ልጆች አሏት፡፡ባልና ሚስት የራሳቸው ገቢ ቢኖራቸውም ከገቢያቸው ከግማሽ በላይ የቤት ኪራይ ይወስደዋል፡፡ ይኸው በኑሮ ውድነት ተመርራ ዋሽንግተን ገብታ ቀርታለች፡፡
እኔና ወንጌል በዋሽንግተን ዲሲ ዐሥራ ስድስተኛው መንገድ ላይ ነን፡፡ የዱሮ ተጫዋችነቷ ጠፍቷል፤ ከኢትዮጵያ ስትነሣ የነበረው ተስፋዋ እንደ ጉም በኗል፤ ከስታ ገመምተኛ መስላለች፤ ከፊቷ ላይ ማንበብ የቻልኹት ብስጭትንና ተስፋ መቁረጥን ብቻ ነው፤ እንደ አነጋገሯ የመኖሪያ ፈቃዷን ጨርሳ ባሏንና ልጆቿን አምጥታ አብራ የመኖር ሕልሟ በቶሎ የሚሳካ አልመሰላትም፡፡ በኑሮ ተስፋ ከመቁረጧ የተነሳ ቀና ቀናውን አያናግራትም፡፡ ይህን ስሜቷን ስልክ ስደውልላትም ከድምፅዋ ተረድቼው ነበር፡፡
በአካል እንደተገናኘን ‹‹ስንገናኝ እነግርሻለኹ›› ወዳለችኝ ጉዳይ ተንደርድሬ ገባኹ፡፡ምን እየሠራች እንደኾነ ጠየቅኋት፤‹‹ሞግዚትነት ተቀጥሬ›› አለችኝ፡፡ ከረምረም ስል ባልንጀሮቼ የሥራ መደባቸውን ሲነግሩኝ እንደመጀመሪያው ጊዜ መደንገጥ ትቻለኹ፤ ቢኾንም ግን ቀደም መሥሪያ ቤቷ በሰጣት መኪና ተመቻችታ የቢሮ ሥራዋን ያውም በእልቅና ስትሠራ የማውቃት የልብ ጓደኛዬ እንዲህ ክፍት ብሏት ስለሞግዚትነት ሥራዋ ስትነግረኝ መስማት በቀላሉ የማልፈው አልኾነልኝም፤ ውትወታዬን ቀጠልኹ፡፡
ወንጌል አሜሪካ እንደገባች የተቀበላት ሜሪላንድ የሚኖረው የአክስቷ ልጅ ነበር፡፡የመኖሪያ ፈቃድ ለማመልከትና ሕጋዊ ሂደቱን ለመከታተል ዋሽንግተን ዲሲና ዙሪያዋ ይሻላል ስለተባለች ጉዳይዋን ሳትጨርስ ቦታ መቀየር አልፈለገችም እንጂ አካባቢውን አልወደደችውም፡፡ መኖሪያ ፈቃድን ያለ ሥራ መጠባበቅ፤ያለ እርሱ ደግሞ ሥራ መፈለግ አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ሥራ መፈለግ የጀመረችው እንደገባች ነው፡፡ ሰሚ ካለ ሲናገሩ ደስ ያሰኛልና ክራሞቷን መተረክ ስትጀምር ብስጭቷ እየቀለላት መጣ፡፡
‹‹አንጋፋ ደላላ ሴትዮ አሉ ተባልኹና በተነገረኝ መሠረት ደወልኹ፤››አለችኝ አሜሪካ ገብታ ሥራ በደላላ መፈለጉ ያሳደረባትን መገረም በፈገግታ እየገለጸች፡፡ ‹‹ለሴትዮዋ የአክብሮት ሰላምታ ካቀረብኹ በኋላ፣ እንደው እናቴ ሥራ ፈልጌ ነበር አልኋቸው፤ ድምፃቸው በጣም ያስፈራል፡፡ በዚያው ላይ ጎተት አድርገው ነው የሚያወሩት፤›› ስለደላላዋ ስታወሳ መሣቅ ጀመረች፡፡
‹‹ወልደሻል? አሉኝ፤ አዎ፣ ማዘር፤ አይ፣ ልጅ ካለሽማ ጣጣሽ ብዙ ነው፤ ለመኾኑ መኪና አለሽ? አዎ፣ አለኝ፤ ምን ማለት እንዳለብኝ ስለተነገረኝ መልሱ አልከበደኝም፤መኪና መኖሩ ጥሩ፤ ሥራው ሁለት ሰዓት ተገብቶ ስምንት ሰዓት የሚያስወጣ ነው አሉኝ ቆፍጠን ብለው፡፡ አስተዛዝኜ ማዘር እንደሱማ ማምሸት አልችልም፤ ልጅ….አላስጨረሱኝም፤ ቀድሞውንም ብያለኹ እናንተ ልጅ ያላችሁ ሰዎች ጣጣችሁ ብዙ ነው፤ ለጊዜው ያለኝ ሥራ ይኸው ነው፤ ስልኩን ሊዘጉብኝ ሲሉ ቶሎ አልኹና እሺ ማዘር አንድ እኅቴ ነበረች፤ እርሷ ግን ትሠራዋለች ግን….ግን ምን? ቆጣ አሉ ፈራ ተባ እያልኹ ወረቀት የላትም አልኋቸው፤ በስጨት ብለው… እኔ ወረቀት ለሌለው ሰው ሥራ የለኝም፤ እባክዎን በጣም ተቸግራ ነው ተለማመጥኋቸው፤ መኪና አላት፤ ወረቀት የላትም እያልክዎ…እንደዚህ ያለ ጉዳይ በአካል..›› ብለው ዘጉብኝ፤›› ወንጌል በገጠመኞቿ መሣቋን ቀጥላለች፡፡
‹‹ሌላ ሥራ ደግሞ ተገኘልኝ፡፡የልብስና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቅ ነው፡፡ባለቤቶቹ ሕንዶች ሲኾኑ ሌላ ቅርንጫፍ ውስጥ የምትሠራ ልጅ ነበረች ያገኘችልኝ፡፡ ዕድሌ ኾኖ ግን እንደነገ ሥራ ልጀምር እየተዘጋጀኹ ሱቁ ተዘረፈ ተባለ፤››ፊቷ ቅጭም አለ፡፡ ‹‹ሙሉ ለሙሉ ነው የተዘረፈው? ከዚያ ተዘጋ?›› አልኋት፡፡ ‹‹አይ አይደለም፤ ከተዘረፈ በኋላ ሰዎቹ ወረቀት የሌለው ሰው መቅጠር ፈሩ ተባለ፡፡››አለችኝ ዕድሏን እያማረረች፡፡
የወንጌል የመጨረሻ አማራጭ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ጽ/ቤት ደውላ ስልኳን ማስቀመጥ እንደኾነ ተነገራት፡፡ የመኖሪያ ፈቃድ (ወረቀት) የማይፈለግበት ሥራ የሐበሻ ልጆችን መጠበቅ ስለሆነ እዚያ ሥራ እንደማታጣ አረጋግጠውላታል፡፡ በኮሚዩኒቲው ቢሮ ውስጥ የተለያዩ ማስታወቂያዎች ይኖራሉ፤ ሥራና ሠራተኛ ፈላጊው ደውሎ ስሙንና ስልኩን ያስቀምጣል፡፡ወንጌል በተነገራት መሠረት ስልኳንና ስሟን አስቀመጠች፡፡ ‹‹ስልኬን በተውኁላቸው በስድስተኛው ቀን አንድ ልጅ ስልክ ደወለልኝ፡፡ሞግዚት የፈለገው ለአንዲት ጓደኛው እንደኾነ ነግሮኝ በቴሌ ኮንፍረንስ ለሦስት አገናኘን፤ልጅ ለመጠበቅ በወር አንድ ሺሕ ዶላር ተስማምቼ ከሜሪላንድ ወደ ዲሲ ከተዛወርኁ አንድ ወር ከዐሥራ አምስት ቀኔ፤›› አለችኝ፡፡
ሥራው ብዙም ሳይቆይ አስጠልቷታል፤ነገር ግን መላቀቂያ መንገድ አጥታለች፡፡‹‹በሞግዚትነት የቀጠረችኝ ልጅ አንዳች ነገር የማውቅ አይመስላትም፡፡ በእርሷ አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ የመጣ ሰው ምንም አያውቅም፡፡ ንግግራችን እኔ ልጅ እንድጠብቅና የልጇን ምግብ እንድሠራለት፣የእኛን ምግብ ደግሞ ተራ በተራ እንድናበስል፣ የተረፈውን ሥራ ደግሞ እርሷ ልትሠራ ተስማምተን ነበር የጀመርኁት፡፡ልጆች ስላሉኝ ልጅ መጠበቅ ለእኔ አሰልቺ አልነበረም፤›› አለች በቁጭት፡፡
“በገባኹ በማግሥቱ…ይቅርታ… ቤቷን ታጸጃት፤›› አለችኝ በተሞላቀቀ ድምፅ፡፡ዝም አልኁ፡፡ ዕቃ ገዝታ መጥታ፣ “ይህ ኦሊቭ ዘይት ይባላል፤ ለቤቢ ብቻ ነው የምትጠቀሚው፤ ይህ ደግሞ…” እያለች እየዘረዘረች አሳየችኝ፤ እኔም ሰማኋት፡፡ በአንድ ጊዜ ከልጅ ሞግዚትነት ወደ ቤት ሠራተኝነት ተቀየርኹ፤ እየከረምኹ ስሄድ ጭራሽ ልጁን ትታልኝ እኩለ ሌሊት መግባት ጀመረች፤›› ወንጌል ተንገፈገፈች፡፡
‹‹በዐሥራ አምስት ቀን አንዴ ዕረፍት ለመውጣት የተነጋገርነው ቃል ታጥፎ በጭቅጭቅ ነው የወጣኹት፡፡ በሩን ቆልፈሽ ከልጁ ጋራ ወደ ውጭ ዞር ዞር ማለት ትችያለሽ ያለችውንም እንዳልተናገረች ያህል ቁልፉን ይዛብኝ ትወጣለች፡፡ስጠይቃት፣ ባክሽ እዚህ ወሬኛ ብቻ ነው ያለው ይቅርብሽ፣ አትውጪ፤ ትለኛለች ለእኔ ያዘነች መስላ፡፡››
‹‹ወንጌልዬ እንዲህ ከተማረርሽ ለምን ከእርሷ ቤት አትወጪምና ሌላ ሥራ አትፈልጊም?›› ስል ጠየቅኋት፡፡ ‹‹እሱማ ወግ ነበር፣ ግን እንዴት አድርጌ ደመወዜን እኮ አልሰጠችኝም፤ ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ እያለች ይኸው እስከ አሁን ታጉላላኛለች፡፡ማታ ማታ በገባች ቁጥር እስከሚበቃት እነግራታለኁ፤ እርሷ መቼ ሰበብ ታጣለች፡፡ ቢጨንቀኝ ላገናኘኝ ልጅ ደውዬ ነገርኁት፤ ይብሱኑ እርሱም እኔም ያበደርኋትን አልከፈለችኝም አለኝ፡፡ወይ አሜሪካ! ጉዷን አየኁላት፡፡›› መቼም መመረሯ መግለጫ የለውም፡፡
እኔና ይህች የልብ ጓደኛዬ አዲስ አበባ ስንትና ስንት የአገር ጉዳይ እንዳልተጫወትን፣ ባላሰብኋት ቦታ ውላ ልጅ የጠበቀችበትን የሞግዚትነት ደመወዝ ተከልክላ ስትብከነከን አገኘኋት፡፡ ባላያት ኖሮ ይሄኔ ‹‹አንድ ነገር ላኪልኝ›› በማለት የሚቀድመኝ አልነበረም፡፡
አገሯ ያውም ሥራዋን ጥላ መምጣቷ ለወንጌል ቆጭቷታል፣ ግን ደግሞ ለመመለስ መወሰን አልቻለችም፡፡ ወረቀት ስታገኝ ነገሮች የተሻሉ ሊኾኑ እንደሚችሉ ተስፋ አድርጋለች፡፡ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ የመሥራት ዕድል ይኖራታል፡፡ ቀደምቱ እንዲህ የሚማረር ሰው ሲያገኙ፣ ‹‹አሜሪካ የምትታወቀው እየቆዩ ሲሄዱ ነው ይላሉ፤›› ልክ ሊኾኑ ይችላሉ፤ እየተቆየ ሲሄድ የማይለመድ ምን አለ?
ከወንጌል ጋራ የነበረኝ ቆይታ ጨርሼ ወደ ማደሪያዬ ሊመልሰኝ ለመጣው ዘመዴ የወንጌልን ጉዳይ አነሣኁለት፤ ‹‹ትለምደዋለች›› አለኝ ቀለል አድርጎ፡፡ ኢትዮጵያ እያለ የእንስሳት ሐኪም ነበር፡፡ለትምህርት እንደወጣ በዚያው ቀረ፡፡አሜሪካ እንደገባ እየተማረ ለመሥራት በአንድ ሆቴል ወስጥ በጽዳት ሠራተኝነት ተቀጥሮ ያጋጠመውን አጫወተኝ፡፡
“ከሁሉም ነገር በላይ መሮኝ የነበረው ማጽዳቱ አልነበረም፤ መስተዋት ከምወለውልበት ቡሩሽ ላይ እየተራገፈ ፊቴን የሚያበሰብሰኝ ቆሻሻ ውኃ ነበር፤›› አለኝ፡፡ ‹‹በየዕለቱ ሥራዬን ጨርሼ ስወጣ እንደ ጓደኛሽ እማረር ነበር፡፡ እየቆየች ስትሄድ ትለምደዋለች ያልኁት አገሩን ስታውቀው፣ሲስተም ውስጥ ስትገባ፣ መሥመር ስትይዝ፣ ነገሮችን በራሷ ማድረግ ስትጀምር እንዲህ እንደማትማረር ስለማውቅ ነው፡፡ያኔ ቢያንስ በቢል ብትማረር ነው፡፡››አለኝ፡፡
‹‹እኔ አንድ ጊዜ ውኃው ፊቴ ላይ በጣም እየፈሰሰ ሲያስቸግረኝ ሥራ አስኪያጁ ጋራ ገብቼ እባክህ ቀይረኝና ‹‹የማታ ሴኵዩሪቲ›› አድርገኝ ብዬ ለመንኁት፡፡›› የማታ ሴኵዩሪቲ ቁልፍ ተግባሩ እንግዳ ሲመጣ በር መክፈትና መዝጋት ነው፡፡ እንደተረዳኹት እንዲህ ያለው ሥራ ዳጐስ ያለ ጉርሻ ስለሚያስገኝ በዘመድ ካልኾነ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ሥራም ከመናቅ ባይቆጠረብኝ÷ የእንስሳት ሐኪሙ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ለጥበቃ ሠራተኝነትም እየተማፀነ ነው፡፡
አንዳንዶች ለአሜሪካ የሚሰጡት ግምት የተጋነነ እንደኾነ የሚገባቸው ሀገረ አሜሪካን ከረገጡ በኋላ እንደ ኾነ ይናገራሉ፡፡ስደትን ወደውና ምርጫ በማጣት ተገደው የተቀላቀሉት ስሜታቸው ለየቅል ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አሜሪካን ይባርክ›› በማለት የአምላክ በረከት ሁሉ በእርሷ ላይ እንዲያርፍ እየተለማመኑ የሚኖሩ የመኖራቸውን ያህል፣ ወደ አሜሪካ ለመምጣት የወሰኑበትን ቀን የሚራገሙ፣ አገራቸውን አብዝተው እየናፈቁ የሚኖሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
በሳውዝ ዌስት አየር መንገድ ከሬኖ ወደ ቦስተን ሰባት ሰዓት በወሰደ በረራ ተጉዤ ቦስተን ሎጋን አየር መንገድ ደርሼ ከአውሮፕላኑ ስወጣ በር ላይ ዩኒፎርም የለበሱ ሦስት ወጣቶች ቆመዋል፤ አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በቋንቋው ሰላምታ ሰጠኹት፤ ድንግጥ አለ፡፡ ከከተማ ከተማ በሚደረግ ጉዞ ብዙም የአገሩን ሰው እንደማያገኝ ጠረጠርኁትና አልፌው ሄድኹ፡፡ሻንጣዬን ቆሜ እየተጠባበቅኹ ሳለ መጣና በፈገግታ ሰላምታ ሰጥቶኝ አንድ አቅመ ደካማ በጋሪ እየገፋ አልፎኝ ሄደ፡፡
አውሮፕላኑ ከታሰበው ሰዓት አስቀድሞ ስላረፈ ሊወስደኝ የሚመጣው ሰው ውጭው ብርድ ስለኾነ እስኪደውልልኝ እንዳልወጣ ስለነገረኝ ዕቃዬን አጠገቤ ሰብስቤ አንዱ አግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ አልኁ፡፡ጥቁር ሰማያዊ ሱሪና ሸሚዝና በቀይቡኒ ጉርድ ሹራብ ዩኒፎርም የለበሰው ያ የአገሬ ወጣት እየፈጠነ ወደ እኔ ተመልሶ መጣ፡፡
‹‹ሥራ ይዤ ያመለጥሽኝ መስሎኝ››አለኝ፡፡ ‹‹ሰው እየጠበቅኹ ነው›› አልኁት፡፡ ከየት እንደ መጣኹ ጠየቀኝ ነገርኁት፡፡ ‹‹የየት አገር ልጅ ነሽ?›› በሚለው ጥያቄ ቶሎ ተግባባን፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርስቲ የኬምስትሪ ተማሪ ነበር፡፡ በኢንተርንሽፕ ድሬዳዋ አስተምሯል፡፡ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በተወለደበት አገር ፍቼ ሲያስተምር ቆይቶ በደረሰው ዲቪ አሜሪካ ገብቷል፡፡ ‹‹ዲቪ ሲደርሰኝ እንዴት ደስ እንዳለኝ፤እኔ ብቻ ሳልኾን ቤተሰቦቼ ጭምር፤ የተደረገልኝ መሸኛ ራሱ. . .›› አለ ስለአመጣጡ ሲነግረኝ፡፡
አሜሪካ ከደረሰ በኋላ ግን ተሰልፎ ዲቪ ሲሞላ ያሰባትን ያህል ኾና አላገኛትም፡፡ ከአውሮፕላን በር ላይ አዛውንት ተጓዦችን እየተቀበለ በጋሪ እየገፋ ወደ መኪና ያደርሳል፡፡ ለሚሠራለት ድርጅት በአንድ የሥራ ፈረቃ እስከ ኻያ ሰው በጋሪ ይገፋል፡፡ ከመምህርነት ወደ ጋሪ ገፊነት መሻገሩ ባያስደስተውም ፊት ለፊቱ ቆሞ የሚቆጣጠረው አለቃ ስለሌለው ከተማ ውስጥ ካለው ሥራ ይህኛው የተሻለ ኾኖ አግኝቶታል፡፡ ተመቻችቶ እያወጋኝ ሳለ የእኔ ስልክ ተደወለ፡፡ የሚቀበለኝ ሰው እንድወጣበት የነገረኝን አቅጣጫ እንዲጠቁመኝ እየጠየቅኹት ከተቀመጥኁበት ስነሣ እርሱ ከኪሱ ወረቀትና ስኪሪፕቶ አውጥቶ የኾነ ነገርመጻፍ ጀመረ፡፡
ስልክ ቁጥር ሊጠይቀኝ ነው ብዬ ሳስብ፤ ‹‹የቅድሙ ምን ነበሩ?›› ሲል ጠየቀኝ ጋሪ እየገፋ ወደሄደበት አቅጣጫ እየጠቆመ፤ ወደ ጠቆመኝ አቅጣጫ ዞሬ ‹‹የትኛው?›› አልኁት፡፡ ‹‹የገፋኋቸው ሴት ናቸው ወንድ?››አለኝ፡፡‹‹ኧረ እኔ አላስተዋልኋቸውም›› አልኁት፡፡ የሚገፋውን እያንዳንዱን ሰው ስሙን፣ጾታውንና ቦርዲንግ ፓሱ ላይ ያለውን ዝርዝር በያዘው ሰንጠረዥ ላይ መዝግቦ ካላሰፈረ ተቀባይነት የለውም፡፡ ወዲያውኑ ካልመዘገበ ጋሪ ከመግፋቱ በስተቀር የገፋው ሰው ወንድ ይኹን ሴት አያስታውስም፡፡ ወረቀቱን በእጁ ይዞ ስክሪብቶውን አፉ ላይ እንዳደረገ‹‹አዪዪዪ›› ብሎ ሐሳብ ገባው፡፡ ትክዝ እንዳለ መውጫው ድረስ ሸኘኝ፡፡
ሌሎች ባልንጀሮቼ አሜሪካን ካልተማሩባት ጋሪ እያስገፋች ታስቀራለች ያሉኝን አስታወስኹ፡፡ የኬሚስትሪ መምህሩ ያገሬ ልጅ መማር እንደሚፈልግ ነግሮኛል፡፡ጎረቤት ሰብስበው ‹‹እልል›› ብለው የሸኙትን እናቱን ከእኅት ወንድሞቹ ጋራ አዳብሎ እየረዳ መማር የማይታሰብ ነው፡፡ ካገሩ ባመጣው ዲግሪ ከጋሪ ገፊነት ያነሰ እንጂ የበለጠ ሥራ ማግኘት አይሞከርም፡፡ስለዚህ የሚገፋው ሰው ወንድ ይኹን ሴት ሳያይ በልማድ ሲገፋ ይውላል፡፡ ከአገር ቤት ተማሪዎቹ አንዳቸው ቢያገኙት ምን ይሉት ይኾን ስል አሰብኹ፡፡ ለነገሩ ምን ሊሉት ይችላሉ፣ አገሩኮ አሜሪካ ነው፡፡አሜሪካ ቁጭ ብሎ ሥራን መናቅ አይታሰብም፡፡ (ይቀጥላል)

Read 3989 times