Saturday, 23 February 2013 11:39

እንጨዋወት

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

“…ለፍቅር ደንቦችና መመሪያዎች መገዛት አለብሽ…”
“…ስለ ፍቅራችን ያለ ቅድመ ሁኔታ መደራደር እፈልጋለሁ…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ! ስሙኝማ…ሰሞኑን የ‘ፍቅረኞች ቀን’ ነው ምናምን የሚባል ነገር ‘ተከበረ’ አይደል! አንድ ሰሞን “ኧረ’ባካችሁ ይሄ ነገር ከእኛ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፣” ብለን ‘ስንንጫጫ’ ከረምን፡፡ ግን አገሯ የእኛዋ ጦቢያ ሆነችና ‘ፈራንካ’ በልጣ “ተልባ ቢንጫጫ…” ተባለና ጭራሽ የአየር ሰዓቱን ሞልቶት አረፈ፡፡ 
በዚህ ቀን ቀላል ቢዙ ነው እንዴ የሚሠራው! ግን በጣም የሚገርመኝ…ጥያቄ መጠየቅ ይችላሉ የምንላቸው፣ በ‘ሞቅ ሞቅ’ ሳይሆን በምክንያታዊነት ማሰብ ይችላሉ የሚባሉ ሰዎች ሁሉ ቀይ በቀይ ሆነው ስናይ…የሆነ ትንሽ የሚያስቸግር ነገር ነበረው፡፡
እኔ የምለው…የ‘ላቭ’ ነገር ካነሳን አይቀር…ደብዳቤ መጻጻፍ ቀረ ማለት ነው! የምር እኮ…በፊት ጊዜ እንዲህ ዘመኑ ‘ተሻሽሎ’ ሁሉ ነገር “እጅ በእጅ…” (ፒያሳ ተገናኝቶ፣ መርካቶ ተኝቶ… አይነት ነገር ማለት…) ሳይሆን …አለ አይደል…‘ሌተር’ ምናምን መስመር ባለው ሉክ ወረቀት ተጽፎ፣ በትንሽ ልጅ ለእንትናዬዋ ተልኮ መልሱን ለመቀበል በሰንበት ቤተክርስትያን፣ በአዘቦት ቀን ጉልት ድረስ እየተከተሉ…ምን አለፋችሁ ፕሮጀክት በሉት፡፡ ዘንድሮ ሁሉ ነገር እንዲህ ቀላል ሊሆን!
ምን ይመስለሀል አትሉኝም…ዘንድሮ ደብዳቤ እንደ ድሮው “የሰማይ ርቀቱ፣ የጨረቃ ድምቀቱ…” ምናምን የሚባል ነገር የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ‘ቦተሊካ’…አለ አይደል… አፋችንን ሁሉ ለውጦብናላ!
ለምሳሌ ሰውየው የዘመኑ ‘ቦተሊካ’ ቀመስ ነው እንበል፣ ደብዳቤው እንዴት ይመስለኛል መሰላችሁ…
“ይህን ደብዳቤ ስፅፍልሽ በእኔና በአንቺ መካካል ስለሚኖረው ግንኙነት የረጅም ጊዜ ራዕይ ሰንቄና የእኔንም የአንቺንም ዘለቄታዊ ጥቅም ባማከለ መልኩ እንደሆነ እንድታውቂልኝ፡፡ ሆኖም ለብቻ የሚሆን ነገር ስለሌለ በእኔና በአንቺ መሀል ውጤታማና ምሳሌ ሊሆን የሚችል አደረጃጃት ሊዋቀር ይገባል፡፡ ይህንን ራዕይ ከግብ ለማድረስ በአንቺ በኩል ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጧትም ማታም ስላንቺ የማስብበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሆኖም የአንቺ አካሄድ ሚናውን የለየ ስለማይመስለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተሽ እንድታስቢበት ያስፈልጋል፡፡
ሆኖም ሁኔታውን በትእግስት ይዤ እከታተለዋለሁ፡፡ ከአንቺ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለማጠናከር የሚደረገው ጉዞ እልህ አስጨራሽና ፈታኝ እንደሚሆን ይገባኛል፡፡
ሆኖም የእኛ መፋቀር የማይዋጥላቸውና ማደናቀፍ የሚያስቡ ካሉ ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንመክራቸዋለን፡፡ የፍቅር ግንኙነታችን አካሄድ ካልጣማቸው መንገዱን የሽሮ ሜዳን ጨርቅ ያድርግላቸው.፡ ከአንቺ ቀጥተኛ የሆነ ምላሽ እፈልጋለሁ፡፡ በአንድ በኩል ግንኙነቱን የምትፈልጊው በሌላ በኩል የማትፈልጊው እየመሰለኝ ሁለቱን ወገን እያጣቀስሽ አብረን መቀጠል የምንችለበት ሁኔታ የለም፡፡ልዩነቶች አሉ የምትይ ከሆነም ተቀምጠን ለመነጋገር ፍቃደኛ እሆናለሁ፡፡ ግን ይህ እንዲሆን መጀመሪያ ለፍቅር ደንቦችና መመሪያዎች መገዛት አለብሽ፡፡ ይህን ደብዳቤ ሳቀርብልሽ ከጊኒ ቢሳውና ከሞንጎሊያ ተሞክሮ በመነሳት እንደሆነ ልገልጽልሽ የምፈልግበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ይህ የፍቅር ግንኙነት እኔና አንቺ በየደረጃው ተጠቃሚ የምንሆንበት ይሆናል፡፡
ለፍቅራችን መረጋጋጥ አስቀድመን በጋራ የነደፍናቸውን አቅጣጫዎች በተግባር ማዋል የሁለታችንም ሀላፊነት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጓደኛና ቤተሰብ ላማክር የምትዪው ነገር እነሱ ባይኖሩም ጥቅምም ጉዳትም እንደሌለው ልትገነዘቢ የሚገባበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
እኔ በተከታዮቹ ስምንት ወራት ፈጣን ለውጦችን በማስመዝገብ ለጋብቻ የሚያበቃንን ስትራቴጂ ነድፌ በንቃት እየተንቀሳቀስኩ ነው ያለሁት፡፡ በገጽታ ግንባታ በነደፍኩት አቅጣጫ ለማገኛቸው ሰዎች ሁሉ ያንቺን መልካም ስብእና፤ ደንቦችና መመሪያዎች በሚፈቅዱት አግባብ እያብራራሁ ነው፡፡
በእርግጥኝነት የምነግርሽ ከእኔ ሌላ እንዲህ አይነት አማራጭ የሚያስቀምጥ ሌላ ሰው ወይም አካል እንደማይኖር ነው፡፡”
እናላችሁ…እንትናዬዋ ይሄንን ደብዳቤ አራት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ፣ ሁለት ጊዜ ግማሹን፣ አንድ ጊዜ አንድ አራተኛውን ካነበበች በኋላ ምን ብላ የምትመልስ ይመስለኛል… “እባክህ ደብዳቤውን እንደገና በአማርኛ አብራርተህ ጻፍልኝ፡፡” ቂ…ቂ…ቂ….
ደግሞላችሁ…ሌላኛው፣ እንዲሁ የዘመኑ ‘ቦተሊካ’ ነፋስ በሌላ አቅጣጫ የነፈሰበት ሊጽፍ የሚችለው ደብዳቤ…
“ይህንን ደብዳቤዬ ስጽፍልሽ የእኔና የአንቺ ፍቅር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ባለበት ወቅት ነው፡፡ የእኔና የአንቺ ግንኙነት መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሷል፡፡ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንደሚጎድልሽና ራስሽ እከተለዋለሁ የምትይውን የፍቅር መንገድ እየናድሽ መሆኑን ልገልፅልሽ እወዳለሁ፡፡ ለመነጋገር ቅድመ ሁኔታዎችን መደርደርሽ ተቀባይነት የሌለውና የእኔን ጥቅም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡ ሀሳቤን በዝርዝር ላስረዳሽ ስሞክር እንዳልናገር የማድረግ አምባገነናዊ አዝማሚያዎች አይብሻለሁ፡፡ ስለ ግንኙነታችን ወቅታዊ ሁኔታ መነጋገር ሲገባን የትውልድ መንደሬ የት እንደሆነ መጠየቅሽ ፍቅር ውስጥ የጎጥ አስተሳሰብን ለማስረጽ የምታደርጊው ጥረት አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡
ደግሜ ልነግርሽ የምፈልገው በዚህ ጉዳይ ላይ ካንቺ ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ፍቃደኛ መሆኔን ነው፡፡ ሆኖም አንቺ በየጊዜው ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥሽ መሠረታዊ የፍቅር ህጎችን የሚጋፋ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡ የፍቅር ግንኙነታችንን ከሚሸረሽሩ ሁኔታዎች እንድትቆጠቢና የፍቅር ሜዳውን ያለ አድልዎ ለእኔ ክፍት ማድረግ እንደሚገባሽ ልትገነዘቢ ይገባል፡፡
በእኔና በአንቺ ጉዳይ የምታማክሪያቸው ወዳጆችሽና ጓደኞችሽ ታማኝነትና ተቀባይነት በእኔ በኩል ጥያቄ ውስጥ መግባቱን በዚህ አጋጣሚ ልገልጽልሽ እወዳለሁ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ አስፈላጊ ከሆነ ፔቲሽን ፈርሜ ልልክልሽ እችላለሁ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በሚያግባቡን የጋራ ጉዳዮች ላይ መደራደር እፈልጋለሁ፡፡
ላንቺ ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ የድርድር በሮችን በመዝጋት ምህዳሩን የሚያጠቡ ሁኔታዎች በመደርደር መብቴን እየተጋፋሽኝ ነው፡፡”
እናላችሁ…እንትናዬዋ ይሄንን ደብዳቤ አራት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ፣ ሁለት ጊዜ ግማሹን፣ አንድ ጊዜ አንድ አራተኛውን ካነበበች በኋላ ምን ብላ የምትመልስ ይመስለኛል… “እባክህ ደብዳቤውን እንደገና በአማርኛ አብራርተህ ጻፍልኝ፡፡” ቂ…ቂ…ቂ….
(ይሄን ያህል ነው እየተራራቅን ያለነው እላችኋለሁ፡፡)
ስሙኝማ…የፍቅር ደብዳቤን ነገር ካነሳን አይቀር … አለ አይደል… ከሆነ ‘ሳይት’ ያገኘሁትን ‘ዘመናዊ የፍቅር ደብዳቤ’ አንብቡልኝማ
“የተወደድሽው ሄለን
ከማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2001 ጀምሮ ካንቺ ጋር በፍቅር እንደ ወደቅሁ ሳስታወቅሽ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል፡፡
ነሐሴ 17 ቀን በአሥር ሰዓት ላይ በሁለታችን መካከል የተደረገውን ስብሰባ አስመልክቶ ራሴን እንደ ታሳቢ አፍቃሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ የፍቅር ግንኙነታችን በሙከራ ደረጃ ለሦስት ወራት ያህል ይካሄድና ውጤቱ ታይቶ ወደ ቋሚነት ይለወጣል፡፡
በእርግጥ የሙከራ ወራቱ በሚያልቁበት ሰዓት በተከታታይ የግንኙነት ስልጠናዎችና የግንኙነት ግምገማዎች ይኖራሉ፡፡ እነኚህም ግንኙነቱን ከአፍቃሪ ወደ ትዳር አጋርነት ደረጃ ለማሸጋገር ይረዳሉ፡፡ ለቡናና ለመሰል መዝናኛዎች የሚወጡ ወጪዎች ተሰልተው ለሁለታችንም በእኩል ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ከዛም ቀጥሎ ያንቺን የአፈጻጻም ብቃት ተከትሎ የወጪውን ከፍተኛ ክፍል ልሸፍን እችላለሁ፡፡ ሆኖም ከፍተኛ ወጪውን አንቺ ብትሸፍኝም ምንም ያህል ቅሬታ የሚሰማኝ አልሆንም፡፡
ይህ ጥያቄ በደረሰሽ በሠላሳ ቀናት ውስጥ ምላሹን እንድትሰጪኝ ይሁን፡፡ በዚሀ ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልመጣ ግን የፍቅር ጥያቄው ተሰርዞ ያለምንም ተጨማሪ ማሳሰቢያ ወደሌላ ሰው እንደምዞር አሳስባለሁ፡፡ ምናልባት ጥያቄውን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆንሽ ይህንን ደብዳቤ ወደ እህትሽ ብትመሪልኝ ደስ ይለኛል፡፡
አክባሪሽ ማክስ”
እሷዬዋ የሰጠችውን ምላሽ ደግሞ አንብቡልኝማ…
“የተወደድከው ማክስ
ይህ ደብዳቤ የጻፍክልኝን የፍቅር ጥያቄ ደብዳቤ ይመለከታል፡፡ የፍቅር ጥያቄህን ለመቀበል ተስፋ እንደማደርግ ሳሳውቅህ በደስታ ነው፡፡
ሆኖም ጥያቄውን ለመቀበል የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸውን ላሳስብህ እወዳለሁ፡፡ ያነሳሃቸው ነጥቦች ተስማምተውኛል፡፡ እባክህ በጡረታ ጊዜ ስለምታገኛቸው ጥቅማ ጥቅሞች አስረዳኝ፡፡ የምታገኛቸው ጉርሻዎች ጠቀም ያሉ መሆን አለባቸው፡፡
ይህንን የተገባ ቃል በተመለከተ አስተማማኝ ዋስትና መኖር አለበት፡፡ ሆኖም በአንተ በኩል ወጪን የመቀነስ ወይም የፍላጎት መቀዛቀዝ ከተከሰተ በማህበራት የህብረት ስምምነት ደረጃ የገንዘብ ካሳ ሊከፈለኝ ይገባል፡፡
ያለሁበትን ከፍተኛ ደረጃ ባገናዘበ ሁኔታ በተጨማሪ የቤት ኪራይና የመጓጓዣ ወጪዎች መሸፈን አለባቸው፣ በተጨማሪም ከጃጉዋር ያነሰ መኪና በእኔ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ላሳስብህ እፈልጋለሁ፡፡በተጨማሪም ዕዳ ሳልከፍል በፍጥነት የምሄድበት ሁኔታ ላይ ማዕቀቦች ሊጣሉ እንደማይገባ ተገንዘብልኝ፡፡ በግንኙነቱ አሁንም ፍላጎት ካለህ እባክህ መልሱን በአስቸኳይ ላክልኝ፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ታሳቢ አፍቃሪዎች ተመሳሳይ ደብዳቤዎች ልከውልኝ መልስ እየጠበቁ ናቸው፡፡
እህቴ ተቀጣሪና ደስተኛ መሆኗን በዚህ ጊዜ ላሳስብሀ እወዳለሁ፡፡
ምናልባት ያንተው፣
ሄለን”
አሪፍ አይደል! የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኛ ዘንድ እንዲሀ አይነት ነገር ቢጀመር የከተማው እንትዬዎች ቦርሳዎች ሁሉ በባለሌተርሄድ ደብዳቤዎች ይሞሉ ነበር፡፡ እዚህ አገር እኮ የሆነ ነገር ጫፍ ማስያዝ ነው…ከዛ በኋላ በተፈለገ አቅጣጫ ይተረተራል፡፡
ይቺን ቀልድ ስሙኝማ…እውነተኛ ፍቅር ማለት አንዲት ሴት አለቃዋን አግብታ የተቀረውን ህይወቷን ያለደሞዝ እሱን ማገለገል ማለት ነው፡፡ (ይሄ ነገር ‘ኤክስኪዩቲቭ ሴክሬታሪዎችን’ ለመንካት ምናምን ለማለት ነው እንዴ! ሳይገባንስ! ይቺን እንኳን “የእነእንትና ወገን ሳይሆን አይቀርም…” ተብለን ሳንጠረጠር እንጠይቅ እንጂ!)
እሷዬዋ ለሰውየዋ “ለአንተ ያለኝ ፍቅር አልቋል፡፡ ቀለበትህን እንካ፣ እኔ ጆኒን ነው የምወደው፣” ትለዋለች፡፡ እሱም “ለመሆኑ ጆኒ የት ነው ያለው?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ እሷም ሀሳብ ይገባትና “ለምን! ልትጣላው ነው እንዴ?” ስትለው ምን ቢላት ጥሩ ነው…“ለምን ብዬ ነው የምጣላው! ቀለበቴን ልሸጥለት ነው፡፡”
የዘመኑ ‘ትራንስአክሽን’ የገባው ማለት ይሄ ነው፡፡
እናማ “…ለፍቅር ደንቦችና መመሪያዎች መገዛት አለብሽ…”
“…ስለ ፍቅራችን ያለ ቅድመ ሁኔታ መደራደር እፈልጋለሁ…” አይነት የ‘ቫለንታይን ዴይ’ ደብዳቤዎች የምናነብበት ጊዜ ቢመጣ አይግረማችሁ፡፡ ዘንድሮ ያልተደባላለቀ ነገር ቢኖር…አለ አይደል… ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች…’ የሚናገሯቸው ነገሮች ናቸው፡፡ (አንዳንዴ ሳስበው “‘ተጠያቂዎቹ’ ሁሉ ፎቶሾፕ ሲ.ኤስ. ፋይፍ ምናምን ተጭኖላቸዋል እንዴ!” አይነት ነገር ለማለት ጫፍ ደርሼ እመለሳለሁ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…ይሄ ‘ቫለንታይን ዴይ’ ምናምን የሚባለው ነገር ሙሉ ለሙሉ ስላልገባኝ የሚያውቁትን ጠይቄ ለመረዳት አቅጣጫ የምይዝበትና ለወደፊትም ጊዜውን ያማከለ ቫለንታይን ተኮር ስትራቴጂና ግብ በምነድፍበት ሁኔታ እየተንቀሳቀስኩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
በተጨማሪም የግንዛቤ ምህዳሬን የሚያጠቡ ሁኔታዎችንና ተአማኒነታቸውና ተቀባይነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ማብራሪያዎችን በተጽዕኖ ላለመቀበል ግለሰባዊ አደረጃጀቴን ለማጠናከር እየሠራሁ መሆኔን እገልጻለሁ፡፡
ለሁሉም…. ቂ…ቂ…ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

Read 8114 times Last modified on Saturday, 23 February 2013 12:28