Print this page
Saturday, 02 March 2013 11:59

“የእንቁላል ከረጢት ካንሰር ...ይበልጥ ገዳይ ነው”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(3 votes)

“እንደሚታወቀው ካንሰር በአለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ...ለምሳሌ እንደ ኤችአይቪ ወባ የመሳሰሉት ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ አጀንዳ ቀርቦ መፍትሔ በስፋት እየተፈለገለት የሚገኝ ሲሆን ካንሰር ግን ልዩ ትኩረት አግኝቶ አያውቅም፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ነገሩ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ ውስጥ ከካንሰር ጋር በተያያዘ ድህረ ምረቃ እና በተለይም ደግሞ ከማህጸን ካንሰር ጋር በተያያዘ ለማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስቶች ትምህርት በመሰጠት ላይ ነው፡፡ በማህጸን ፍሬ ላይ የሚወጡ እጢዎች ከ30-50 ኪሎ ግራም ድረስ ክብደት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይህ እጢ በኦፕራሲዮን ከወጣ በሁዋላ ወደካንሰርነት ተለውጦአል ወይንስ? የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ በሁዋላ ትክክለኛው ሕክምና ይሰጣል፡፡ የመዳን ያለመዳን እድሉም እንደ እድሜ እና እንደካንሰሩ ደረጃ ይለያያል...ይህ ሕመም እጅግ አስቸጋሪና ጥንቃቄ የተሞላው ሕክምና ማድረግን ስለሚሻ በመሰጠት ላይ ያለው ትምህርት እጅግ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል”
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው የማህጸን ፍሬ እጢ ወይንም ካንሰርን የሚመለከት ሲሆን ከላይ ያነበባችሁትም ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ መምህር እና ረዳት ፕሮፌሰር እንዲሁም የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
ኢሶግ፡ የማህጸን ፍሬ ምንድነው?
ዶ/ር ዳዊት፡ የማህጸን ፍሬ ወይንም እንቁላል ማለት የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ መያዣ እንደሚባለው ሲሆን የወንድ ልጅ ወደ ውጭ ወጥቶ የሚታይ ሲሆን የሴት ግን ሆድ እቃ ውስጥ ከማህጸን ጋር ተያይዦ የሚገኝ ነው፡፡ የማህጸን ፍሬው ወይንም እንቁላሉ በግራ እና በቀኝ በኩል የሚገኙ ሲሆን ሴትን ልጅ ሴት የሚያሰኛትን ባህርይ የሚሰጥ አካል ነው፡፡
ኢሶግ፡ የማህጸን ፍሬ ጥቅሙ ምንድነው?
ዶ/ር ዳዊት፡ የማህጸን ፍሬ ማለት በጣም ትናንሽ አካላት ሲሆኑ ጥቅማቸው ግን ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ ፍሬዎች ሴትነትን የሚያመነጭ ሆርሞንን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ የሴትነት ባህርይ ማለት ለምሳሌ ጡት፣ የሰውነት ቅርጽ በተለይም መቀመጫ አካባቢ ያለው ውፍረት የመሳሰሉት ከእንቁላሉ ስራ ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ሂደት ሲሆን ከዚያም በላይ ሴት ልጅ በየወሩ የወር አበባ እንዲኖራት እና ማህጸኑዋ በትክክል በየወሩ እንዲሰራ ለማድረግ እንዲሁም ልጅ ወልዶ ለማሳደግ የሚያስችል የሴት አካል ነው፡፡
ኢሶግ፡ አፈጣጠሩን እንዴት መግለጽ ይቻላል?
የማህጸን ፍሬ ያለበትን ማእቀፍ ልክ እንደከረጢት አድርጎ ማሰብ ይቻላል፡፡ እንቁላሎቹ በከረጢቱ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በመካከላቸው ደግሞ የደም ስርና የተለያዩ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በሶስቱም ቦታዎች ማለትም ከከረጢቱ ብቻ የሚነሳ፣ ከእንቁላሎቹ እንዲሁም በሁለቱ መካከል ካለው ቦታ የሚነሳ እጢ ወይንም ካንሰር ይኖራል፡፡
ዶ/ር ዳዊት፡ በሶስቱ ቦታዎች ከሚነሳው እጢ ወይንም ካንሰር የትኛው ይበልጥ ሴቷን ይጎዳል?
በሶስቱ ቦዎች ከሚከሰተው እጢ ወይንም ካንሰር ከእንቁላል ከረጢቱ ላይ የሚነሳው ካንሰር ይበልጥ ገዳይ ነው፡፡ ነገር ግን እንቁላሉ ላይ የሚከሰተው ካንሰር ወደሌላ ቦታ ስለማይዛመት በማደጉ ምክንያት ሆድን ማሳበጥ ፣ሽንትና ሰገራ ላይ ችግር መፍጠር የመሳሰሉትን ሕመሞች ያስከትላል፡፡ ነገር ግን ከታከመ ሊድን የሚችል እንጂ ገዳይ አይደለም፡፡ ይድናል ሲባልም ተፈጥሮ በእራስዋ ያደለችው ነገር ስላለ በዚያም በመጠቀም ነው፡፡ ያ ማለት ለምሳሌ.....አይን ፣እጅ ፣እግር ፣ኩላሊት የመሳሰሉት ሁሉ በተፈጥሮአቸው ሁለት እንደመሆናቸው አንዱ ቢታመም በአንዱ የመቆየት እድል ስላለ ነው ፡፡ እንደዚሁም የማህጸን ፍሬው ሁለት በመሆኑ አንዱ ቢጎዳና እስከ እንቁላሉ ቢወጣ ሌላኛው በካንሰር ካልተያዘ ስራውን ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
ኢሶግ፡ አንዲት ሴት የማሀጸን ፍሬ ካንሰር እንደያዛት አስቀድማ ልትገምት የምትችልባቸው መንገዶች ይኖራሉን?
ዶ/ር ዳዊት፡ አንዲት ሴት የማህጸን ፍሬ ካንሰር ይያዛት አይያዛት አስቀድማ ልታውቅ የምትችልበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ስለሆነም ለመከላከል ጥንቃቄ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዋና ገዳይ ነው የሚባለው፡፡ እስከአሁን በአለም ደረጃ ችግሩን አስቀድሞ ለማወቅ እንዲያስችሉ የተደረጉት ሙከራዎች ሁሉ ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ በአለም ላይ ከ1.5 ኀ ባላነሰ አንዲት ሴት በሕይወቷ ውስጥ ልታገኘው እና ልትሞት የምትችልበት በሽታ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ሕመሙን ቀድሞ ማወቅ አለመቻሉ ነው፡፡ ሕክምናውን በተመለከተ በሴቶች እድሜና በሚከሰተው ካንሰር አይነት ይወሰናል፡፡ በእድሜያቸው እስከሀያ አመትና በዚያ አካባቢ ያሉትን የሚይዘው ከእንቁላሉ የሚነሳው ካንሰር ሲሆን ይህም የመዳን እድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡
ኢሶግ፡ ከኦፕራሲዮን በሁዋላ እንደገና ልጅ የመውለድ እድሉ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ዳዊት፡ የመውለድ እድሉን በሚመለከት በካንሰር የተያዘው የእንቁላል ከረጢት አንዱ ብቻ ከሆነ አንደኛው ከረጢት መደበኛውን ተግባሩን መቀጠል ስለሚችል መውለድ ይቻላል ፡፡ ነገር ግን በሁለቱም እንቁላል ከረጢቶች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ጉዳት ከደረሰ ዋናው አላማ የልጅቱዋን ሕይወት ማትረፍ እንጂ ልጅ እንድትወልድ ማስቻል አይሆንም፡፡ ቢሞከርም ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶአልና ሁኔታውን አስከፊ ያደርገዋል፡፡ በተቻለ መጠን ግን ታማሚዋ ልጅ የመውለድ እድሉዋን እንድትጠቀም የተቻለው ሁሉ ይሞከርላታል፡፡ ይልቁንም ልጅትዋ ገና በልጅነትዋ የዘር ፍሬዎቹዋ እና ማህጸንዋ እስኪወጣ ድረስ ኦፕራሲዮን የምትደረግ ከሆነ በሴትነትዋ ልታገኝ የሚገባትን ብዙ ተፈጥሮአዊ ነገሮች ስለሚያሳጣት ከባድ ውሳኔ ነው፡፡ በትላልቅ ሴቶች ላይ የሚከሰተው ካንሰር ግን ገና ልጅ ይወልዳሉ ተብሎ የማይጠበቅ ስለሆነ ያለምንም ጥያቄ እስከማህጸኑ የሚወገድ ነው፡፡ ሕመሙ ካንሰር መሆኑ ሲታወቅ ማንኛዋም ሴት ከሐኪም ጋር በቅርብ በመመካከር መድሀኒቱን በትክክል በመውሰድ ሕመሙን ማዳን ይቻላል፡፡
ኢሶግ፡ ሕመሙ የሚገኘው እና በሕክምናው መረዳት የሚቻለው መቼ ነው?
ዶ/ር ዳዊት፡ ሕመሙን አስቀድሞ መከላከል አለመቻሉ ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል እንጂ ጭርሹንም ሳይታወቅ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሴትየዋ ሕመም በሚሰማት ጊዜ የካንሰሩ ደረጃው ከፍ ያለ ነው ማለት ነው፡፡ የካንሰር ሕመሙ አንደኛ ፣ሁለተኛ ፣ሶስ ተኛ እና አራተኛ ተብሎ የሚከፈል ሲሆን ብዙ ጊዜ ታምመው ለሕክምና የሚቀርቡ ሴቶች ከሁለት እስከ ሶስተኛው ደረጃ የደረሱ ስለሆኑ በሕክምናው ሊረዱ ከሚችሉበት እድል ውጭ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን አንደኛ ደረጃ ላይ ሆነው ለሕክምና ቢቀርቡ እስከ 80ኀ ማዳን ይቻላል፡፡ ሕመሙ የሚሰማው ከእንቁላል ከረጢቱ ወጥቶ የማህጸን አካባቢን ነካክቶ ወደ ሆድ እቃ ውስጥ ሲገባ ... የሆድ እቃ ማበጥ፣ ሰገራና ሽንት ላይ ችግር ማስከተል፣ ምግብ አለመስማማት ፣ቶሎ መጥገብ ፣ የጨጉዋራ ሕመም ስሜት የመሳሰሉት ሲከሰቱ ነው፡፡ ለዚህ የሚመከረው በሆድ እቃ አካባቢ ሕመም ሲከሰት መታከም የሚገባው ሆድን ብቻ ሳይሆን ወደ ጽንስና ማህጸን ሐኪም ቀርቦ መታየት ያስፈልጋል፡፡ የህመም ስሜቱ ሊመሳሰል ስለሚችል የትኛው እንደሆነ አለስቀድሞ ማወቅ ስለማይቻል ምርመራ ማድረግ ይጠቅማል፡፡
ኢሶግ፡ የማህጸን ፍሬ ካንሰርን ለመከላከል ሴቶች ምን ሊያረጉ ይገባል?
ዶ/ር ዳዊት፡ ከማህጸን ፍሬ ከረጢት ወይንም ከማቀፊያው ላይ የሚነሳ ካንሰር ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ባልወለደች ሴት ላይ ነው፡፡ ጡት ያላጠባች ፣የእርግዝና መከላከያ ያልወሰደች ፣ እንዲሁም በቤተሰብ የጡት ፣የማህጸን ካንሰር የነበራት ሴት በካንሰሩ ለመያዝ ይበልጥ ተጋላጭ ትሆናለች፡፡ የእርግዝና መከላከያ ኪኒኖችን የሚወስዱ ሴቶች ብዙ ጊዜ በበሽታው አይጎዱም፡፡ ስለዚህ ሴቶች ለካንሰሩ አለመከሰት ሊያደርጉት ከሚገባቸው ጥንቃቄ በጣም ጠቃሚዎቹ ...
1/ ልጅ መውለድ ወይንም ፣
2/ የወሊድ መከላከያውን ኪኒን መጠቀም፣
የእርግዝና መከላከያውን ኪኒን የምትጠቀም ሴት የምትከላከለው እርግዝናውን ብቻ ሳይሆን ከንሰሩንም ይሆናል፡፡ አንዲት ሴት የወሊድ መከላከያውን መውሰድ እንደምትችል በሐኪም ከተረጋገጠ እርግዝናን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን እንደዚሁም ብትወስደው የማህጸን ፍሬ ካንሰርን ይከላከላል፡፡ ልጅ መውለድ የማህጸን ፍሬ ናንሰርን እንደሚከላከል የተረጋገጠ ሲሆን ልጅ መውለድ ሲባል ግን በተደጋጋሚ ብዙ ልጆችን መውለድ ሳይሆን ከአንድ እስከሁለት ልጅ መውለድ መፍትሔ ነው፡፡

Read 5137 times Last modified on Saturday, 02 March 2013 12:12