Sunday, 03 March 2013 00:00

ለቤተ አምልኮና ለሁለገብ ህንፃ ግንባታ የሚፈለገው ቦታ አወዛገበ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ውስጥ ንብረትነታቸው የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የሆኑ ቤቶችን ለንግድ ሱቅ አገልግሎት ተከራይተው ሲጠቀሙ የነበሩ ነጋዴዎች ከኤጀንሲው ጋር የነበራቸው ውል ሣይቋረጥ የክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር ቦታው ለቤተ አምልኮ እና ሁለገብ ህንፃ ግንባታ ስለሚፈለግ በአስቸኳይ ልቀቁ ማለቱ ውዝግብ አስነሣ፡፡
የክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር አካላት በተደጋጋሚ የፖሊስ ግብረ ሃይል ይዘው በመመላለስ ንብረታችሁን አንሡና ቤቶቹን ልቀቁ የሚል ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፉ የተናገሩት ባለ ንግድ ሱቆች፤ እኛ በውላችን የምናውቀው ያከራየንን አካል ስለሆነ እሡ ውላችሁን አቋርጫለሁ የሚል ትዕዛዝ ካላስተላለፈ አንለቅም ማለታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል። ስለ ጉዳዩ ያከራያቸውን የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲን ሲጠይቁ፤ “እኛ ከእናንተ ጋር ያለንን ውል እስካላቋረጥን ዝም ብላችሁ ስሩ” ማለቱን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ። በቅርቡ ባደረጉት የውል ስምምነት እድሣትም፣ ከጥር 1 እስከ መጋቢት 30 የሚቆይ ስምምነት ከመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር መፈራረማቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ሁለቱ የመንግስት አካላት ችግራቸውን ተነጋግረው መፍታት ሲገባቸው የክፍለ ከተማው አመራሮች በፖሊስ ግብረ ሃይል በመታገዝ ውክቢያ መፍጠራቸው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በቀበሌ ቤትነት ተመዝግበው የነበሩ አምስት ቤቶች ከአንድ አመት በፊት በተመሣሣይ አላማ እንዲፈርሡ ተደርጐ በቦታው ላይ ምንም ሣይሠራበት መቆየቱን የሚናገሩት ግለሠቦቹ፤ አካባቢው ሠፊ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት በመሆኑ የገቢ ምንጭ ፈጥረን ቤተሠቦቻችንን እያስተዳደርን ባለበት ወቅት አሣማኝ ባልሆነ ምክንያት እንድንለቅ መደረጉ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ በአካባቢው መሪ ፕላን ላይ ቦታው ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል መሆኑ የተመለከተ ቢሆንም ከሊዝ ነፃ ተደርጐ ለኢትዮጵያ ህይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን የቤተ አምልኮ ግንባታ መፈቀዱም የከተማው አስተዳደር መሪ ፕላኑን በማስፈፀም ረገድ ጉድለቶች እንዳሉበት አመላካች መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አዲስ እጅጉ በበኩላቸው፤ ክፍለ ከተማው ጉዳዩን ከኤጀንሲው ጋር በመሆን መፈፀም ሲገባው ተከራዮቹን ማስጨነቁ አግባብ አለመሆኑን አመልክተው፣ የውዝግቡ መነሻ ቤተ ክርስቲያኗ ለግምት ካሣ ክፍያ የተተመነላትን 1.8 ሚሊዮን ብር ለኤጀንሲው ከፍላ በጊዜው ባለማጠናቀቋ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡ አሁን ግን ቤተክርስቲያኗ የሚፈለግባትን ገንዘብ ከፍላ ባሣለፍነው ሣምንት በማጠናቀቋ፣ ለተከራዮቹ የውል ማቋረጫ ደብዳቤ ተፅፎላቸው በቀናት ውስጥ እንዲደርሣቸው ይደረጋል፤ ይህንንም ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ እንዲያስፈፅም ትዕዛዝ ተላልፎለታል ብለዋል፡፡
ከተከራዮቹ ጋር የተዋዋላችሁት ስምምነት ግለሠቦቹ እስከ መጋቢት 30/2005 ዓ.ም ቤቱን እንዲገለገሉበት ይፈቅዳል፤ ይሄን እንዴት ልታስታርቁት ነው ብለናቸውም፤ መንግስት ቦታውን ለልማት ሲፈልገው በማንኛውም ጊዜ ውሉ ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስምምነት በአከራይ ተከራይ ውላቸው ላይ መስፈሩን አቶ አዲስ አስታውቀዋል፡፡
በተመሣሣይ በአካባቢው በባለቤታቸው ስም የተመዘገበ የግል ይዞታ እንደነበራቸው የገለፁልን አቶ ወንድማገኝ መኮንን ካሣ፤ ተሠጥቷችሁ ትነሣላችሁ ሲሉን ቦታው ላይ ሠፍሮ የሚገኘው ግለሠብ አቅሙ ካለው ቅድሚያ የማልማት እድል ይሠጠዋል የሚለውን የህግ ድንጋጌ ዋቢ በማድረግ አቅሙ ስላለን ማልማት እንችላለን ብለናቸው፣ ብር በባንክ ዝግ የሂሣብ መዝገብ አስገቡ ካሉን በኋላ፣ ቦታው ለእናንተ አይፈቀድም ተሸጧል፣ ካሣችሁን ውሠዱ ብለውናል፡፡ እኛ ግን ካሣውን ለመውሠድ ፈቃደኛ ስላልሆን የሚመለከተው አካል ጉዳያችን በአንክሮ እንዲመለከት እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ማናጅመንት ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ተገኝ ጦፎ፤ ጉዳዩ ለሠባት አመታት የዘለቀ መሆኑን፣ ለቤተክርስቲያኗ የሊዝ ቦርዱ ቀደም ብሎ በ2003 ያስተላለፈውን ውሣኔ እስከ ዛሬ ባለማስፈፀማቸው ቅሬታ እንደቀረበባቸው፣ ለዚህም ሲባል ክፍለ ከተማው የማስፈፀም ሃላፊነቱን ለመወጣት ግለሠቦቹን ማንሣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እርምጃውን ሊወሠድ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ “እኛ ከተከራዮቹ ጋር ምንም ግንኙነት የለንም፤ የተላለፈውን ትዕዛዝ በአግባቡ ማስፈፀም ነው ሃላፊነታችን፤ በዚህ ሂደት ነው ችግሩ የተፈጠረው” ያሉት አቶ ተገኝ፤ በቦታው ላይ ቤት ያላቸው ግለሠቦች እና የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ካሣ ተከፍሏቸው፣ የቀበሌ ቤቶቹ ደግሞ ምትክ ቤት ተሠጥቷቸው እንዲነሡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት አግባብነት የሌለው እርምጃ ተወስዷል የሚል አካል ካለ በህግ መጠየቅ እንደሚችል የሚናገሩት ሃላፊው፤ “እኛ በደንቡ መሠረት ከቤተክርስቲያኗ ካሣውን ተቀብለን በመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ አካውንት እናስገባለን፣ ሂሣቡ መግባቱን ስናረጋግጥ አካባቢውን ወደ ማፅዳት እርምጃ እንገባለን፤ በዚህ አግባብ ነው ቦታው እንዲፀዳ እየተደረገ ያለው ብለዋል፡፡

Read 3901 times