Sunday, 03 March 2013 00:00

የግብፅ ወጣት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን እየጐበኙ ነው

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(2 votes)

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ሥራ ላይ የሚያሰማራቸው ወጣት ዲፕሎማቶች የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ እያካሄዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሃመድ በድሪ የሚመሩት ሠላሳ ወጣት ዲፕሎማቶች ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን ያነጋገሩ ሲሆን ካለፈው ረቡዕ እስከ ዛሬ ባህርዳር ከተማ እና አካባቢውን እየጐበኙ ነው፡፡ ዲፕሎማቶቹ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በተወያዩበት ወቅት በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር መሃመድ ኢድሪስ እንደተናገሩት፤ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ በግብጽ መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ወደፊት ሀገር የሚመሩትን የሁለቱን ሀገራት ወጣት ዲፕሎማቶች በማቀራረብ ረገድ የሰሞኑ ጉብኝት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር መሃመድ በድሪ በበኩላቸው፤ ከወጣት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ጋር ለመተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ መምጣታቸውን ተናግረው “ዛሬ ጠዋት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ‘ወደ ሁለተኛ ቤታችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ’ ብለውናል፡፡ ሁለተኛ ቤታችን ሳይሆን ቤታችን ነው ያለነው፣ ከግብጽ ወደ ግብጽ ነው የመጣነው፡፡” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በግብጽ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2804 times