Sunday, 03 March 2013 00:00

“ሶሻሊዝም” ደርግ ከራሽያ የጦር መሣሪያ እርዳታ ጋር የተቀበለው ርዕዮተዓለም ነው!?

Written by  ገዛኸኝ ፀ. (ፀጋው)
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሳምንት ብርሃኑ ሰሙ የተባሉ የአዲስ አድማስ የዘወትር ፀሐፊ፣ “145 ዓመታት የፈጀ ትግልና ውጤቱ” በሚል ርእስ አንድ ፅሁፍ አስነብበዋል፡፡ ፀሐፊው፣ “በአገራችን የዘመናት ጉዞ ችግር ብቻ ሳይሆን እድገትም እንዳለ፣ የኢፌድሪ የመከላከያ ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለ10 ቀናት የቆየው ትርኢት በብዙ ሰዎች ከመጐብኘቱም ባሻገር ብዙዎችን አወያይቷል” የሚል ሃሳብ አንስተዋል፤ ቀጥለውም፤ ስለ ኤግዚቢሽኑ “በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ብዙ ስለተባለለት በአድናቂዎች የተሰጡትን ሃሳብ በመጋራት፣ ለመሆኑ እዚህ ደረጃ መድረስ እንዴት ተቻለ? ለሚለው ጥያቄ ካለፉት ዘመናት ጥረትና ድካሞች የተወሰኑትን ለማመልከት እሞክራለሁ” በማለት ከአፄ ቴዎድሮስ ሴባስቶፖል እስከ ኢህአዴግ “የህዳሴ ሄሊኮፕተር” የተለያዩ መረጃዎችን እያጣቀሰ ማለፊያ ፅሁፍ አስነብበዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ፣ አፄ ምኒልክ ስላቋቋሙት የጥይት ፋብሪካ፣ የመጀመሪያው ወታደራዊ ሰልፍና ትርኢት በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ስለመደረጉ ወዘተ ወደኋላ ተመልሰው ታሪካዊ ዳራውን እያጣቀሱ የቀዳሚዎቹ ነገሥታትን ታሪክ ለመዘከር ሲነሱ፣ ምክንያታቸውን በግልፅ ለማስቀመጥ አልፈለጉም፡፡
የቀድሞዎቹን ባለታሪኮች ተግባራት ሳያወሱ፣ አዲስ የተገኘ ስኬት አድርገው ሲያቀርቡ፣ በተፈጠረባቸው ቁጭት ተነሳስተው ይህን መጣጥፍ መፃፋቸውን የምንረዳው ግን በመጣጥፉ የመጨረሻ አንቀፅ ላይ ነው፡፡ በተለይ፣ የፅሁፉን ማዕከላዊ ጭብጥ ጠፍሮ ያሰረ የሚመስለው “አገር በአንድ ትውልድ እንደማትገነባ ማወቅ ብልህነት ነው!” የሚለውን ዐ.ነገር እስክናነብ የፅሁፉን መነሻ ሃሳብ አስረግጦ መናገር ይከብዳልና፡፡
ፅሁፉ በተለይ ከተነሳበት ዓላማ አንፃር፣ የተሳካለት አስተማሪ ፅሁፍ መሆኑ መመስከር ይገባል፡፡ በዚህ በብዙ ማስረጃ በተጠናቀረ መጣጥፍ ውስጥ ግን፣ እንኳን በማስረጃነት ለመረጃነትም አቅም ያጣ አንድ ሃሳብ መነሳቱን በትሁትነት ልጠቁም እወዳለሁ፡፡ “ሶሻሊዝምን ያመጣው የጦር መሣሪያ ችግር” በሚለው ንዑስ ርእስ ስር፣ “ደርግ በምስራቅ የአገራችን ክፍል ተቀስቅሶ የነበረውን ጦርነት ለመመከት ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎች ያስፈልጉት ነበር፡፡ ስለዚህም ንጉሡ ክፍያ የፈፀሙበትን የጦር መሣሪያ ከአሜሪካ ለመረከብ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ ይሄን ጊዜ ነበር ደርግ ፊቱን ወደ ራሽያ ያዞረው፡፡ በዚያ አጋጣሚ ከጦር መሣርያ ጋር አብሮ አገራችን የገባው ሶሻሊዝም፤ አገሪቱን ለፖለቲካዊ ምስቅልቅልና ለኢኮኖሚያዊ ድቀት ዳርጓት አለፈ” የሚል በብዙ መልኩ የታሪክ መፋለስን የሚያስከትል የተሣሣተ ሀሣብ አንሥቷል፡፡
በዚህ አንቀጽ የተነሣው ሀቅነት (fact) የጐደለው ሸውራሪ ታሪክ ሦሥት መሠረታዊ ተጠየቆች ይነሡበታል፡፡ የመጀመሪያው፣ “ሶሻሊዝምን ወደ ሀገራችን ያሥገባው ደርግ ነው” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው “ሶሻሊዝም ወደ ሀገራችን የገባው ከጦር መሣሪያ ጋር ነው፤ ወይም ለጦር መሣሪያ ሢባል ነው” የሚል ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ፣ “አገሪቱን ለፖለቲካዊ ምስቅልቅልና ለኢኮኖሚያዊ ድቀት የዳረጋት ሶሻሊዝም ነው” የሚል ነው፡፡ ከሦሥቱ ንጥረ ሀሣቦች የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ሀቅን የገደፉ ታሪኮች መሆናቸውን በቀጥታ ማሣመን ሢቻል፣ ሦስተኛው ንጥረ ሀሣብ እውነት (Truth) ሥለ መሆኑና አለመሆኑ የተለያዩ ማስተንተኛዎችን ማስረጃ ማድረግ ይጠይቃል፤ የሀቅነት (fact) ጉዳይ ግን አልነሣበትም፡፡ የርዕዮተ ዓለም ጣጣ፣ ብዙ ጊዜ የሀይማኖት ጣጣ ነውና፤ ሀይማኖት ደግሞ ዝም ብሎ ማመንን ይፈልጋል!
ሦሥቱም የታሪክ ሀሣቦች የተነሡበትን ዘመን ጣጣ ብቻ ተናግረው የሚያርፉ አይደሉም፤ ይልቁንም፣ ዛሬም ድረሥ እየተፈከሩ (እየተተነተኑ) የሚናገሩት እውነት ይኖራል፡፡ ሥለዚህ፣ መሠረቱን የሣተው የታሪክ አንቀጽ፣ የማስተካከያ ምላሽ የሚያስፈልገው፣ ከዚህም ዘመን ተሻጋሪ ጦሱ ሣቢያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ “ደርግ፣ በምሥራቅ የሀገራችን ክፍል” ተቀሠቀሠበት የተባለው ጦርነት፣ ከሱማሌ ጋር የተደረገው ጦርነው ነው፡፡ በዚያድ በሬ የሚመራውን የሶማሌን ወራሪ ጦር ለማክሸፍ ከ18ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ከፍለውበታል፡፡ የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም የጦር አመራር ብቃት በተፈተነበት በዚህ የወራት ጦርነት፣ ኢትዮጵያ፣ ከተለያዩ የአረብ ሀገራትና ከአሜሪካ ትጥቅና የጦር መሣርያ ከሚረዳው የዚያድ በሬን ጦር ለመመከት የሚያሥችል ሠራዊት አልነበራትም፡፡ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጣው ከ3መቶ ሺህ በላይ ጦር፣ መጋቢት 20 ቀን 1969 ዓ.ም በተቋቋመው “የታጠቅ ጦር ሰፈር” ለጥቂት ወራት ሠልጥኖ፣ ወዲያው እናት ሃገሩን ከወራሪ ነፃ ለማውጣት በየጦር ግንባሩ መሠለፉን፣ የታሪኩ ባለቤቶች ዛሬም በሀገር ፍቅር ስሜት የሚተርኩት ሀቅ ነው፡፡
ታዲያ፣ የኢትዮጵያ ጦር ዋና አጋፋሪ የነበሩት ፕሬዚዳንት መንግስቱ፣ “ትግላችን” (2004 ዓ.ም) በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 396፣ “አፄ ኃይለስላሴ … በአገራትን በአሥመራ ከተማ ወታደራዊ መደብ በመስጠት፣ አረቦችን፣ ሶሻሊስት አገሮችንና ጠቅላላውን የዓለም ሰላም ወዳድና ዲሞክራቲክ ኃይሎችን ጠላትነት የገዙበት የሰሜን አሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ህዝብ በተከበበትና ከፍተኛ የጦርነት አደጋ ባንዣበበበት ጊዜ ነው ኢትዮጵያን በመክዳት፣ ከወራሪው የሶማሌ መንግሥትና ከውስጥ ገንጣይና አስገንጣዮች ጎን በመቆም የወታደራዊውን ተራድኦ ያቆመው እንጂ እኛ አንቀበልም ብለን አልነበረም፡፡ አሜሪካዊያን ያደረሡብን አደጋ የገንዘቡ መጠን ብቻ ሣይሆን፣ ካለብን የጊዜ ችግር አንፃር ያልተጠበቀ ሥለነበር በጣም ብናዝንም አልተደነቅንም፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ አብራክ የወጡ ልጆቿ፣ ኋላቀርና ደሀ በመሆኗ እነሱ የፈለጉትን ስላልሰጠች ወይም ስላላሟላች ብቻ ከድተዋት ከፊሉ ከአሜሪካኖቹ ጋር ሲሰለፉበትና ሌሎች ከአረቦች ጋር ተሰልፈው ሲወጓት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጀሚካርተር ምን ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ፣ አቶ ብርሃኑ እንዳሉት፣ አሜሪካ ፊቷን ሥታዞር የኢትዮጵያ ደጋፊ የሆነችው ቀደም ሲል ሶማሊያን ስትደግፍ የነበረችው፣ ራሽያ ነች፡፡ በርግጥ፣ “ህዝባዊ ቻይናና ዩጎዝላቭያም” ቀድመው የተወሠኑ የጦር መሣሪያዎች ረድተዋል፡፡ ሥለዚህ፣ የአሜሪካ መንግሥት ፊቱን ማዞሩ፣ ራሽያም ወደ ደርግ ማዞሩ ሀቅ ነበር፡፡ ችግሩ ግን፣ ሶሻሊዝም ከጦር መሣሪያ ጋር ገብቷል የሚለው ነው፡፡ ቀጥሎም የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም፣ የአገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ምስቅልቅል ሥለማውጣቱ በእርግጠኝነት መነገሩ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም መቀንቀን የጀመረው በአፄ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ (አ.አ ዩኒቨርሲቲ) ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ ነበር፡፡ በርግጥ፣ ሥርነቀል ለውጥ ፈልገው ያ ትውልድ፣ በ1960ዎቹ ላይ ጫፍ ያደረሠውን አብዮትና የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም (ሶሻሊዝም) ለውጥ መነሻ የሆነው፣ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በንጉሡ ፊት ሣይቀር፣ ይቀርብ የነበረው “የኮሌጅ ቀን” በዓል ነው፡፡ በዚህ በዓል ላይ ይቀርቡ የነበሩት “የኮሌጅ ቀን” ግጥሞች በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በተጠመቁ ተማሪዎች የተገጠሙ ነበሩ፡፡ በተለይ በ1953 ዓ.ም “ደሀው ይናገራል” በሚል ርዕስ በታምሩ ፈይሳ የቀረበው ግጥም፣ ገና ከርዕሡ ጀምሮ ለርዕዮተ ዓለሙ ያደረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በርግጥ የዛን ጊዜው ተማሪዎች ማርክሲዝም ሌኒንዝምን በጥራዝ ነጠቅነት ጭምር ያነበንቡት እንደነበረ እራሣቸው በፃፉት ማስታወሻ ሁሉ ማጋለጣቸው ይታወቃል፡፡
ያ ትውልድ በ1951 ዓ.ም በግጥም የጀመረውን ትግል፣ በተለይ በ1959 ዓ.ም በተከበረው የኮሌጅ ቀን ኢምፔሪያሊዝም ያሏትን አሜሪካን ነቅፎና ሶሻሊሥት ቻይናን፣ ኩባን፣ አልባኒያን ወዘተ እንደሚደግፍ መፈክር ሁሉ ፅፎ፣ በአደባባዩ እስከ መሟገት ደረሠ፡፡ በ1960ዎቹ ላይ ያ ትውልድ ግማሹ ወደ ጫካ፣ ግማሹ በአፄው ስርአት ምትክ ወደ ቤተመንግሥት፣ ግማሹ አውሮፕላን ሁሉ ጠልፎ ወደ ውጭ ሀገር አመራ፡፡ ኢዲዩ ከሚባለው የባላባቱ ሥርአት ናፋቂ ከተባለ የፖለቲካ ድርጅት በቀር፣ ሁሉም ታጋዮች መጠኑና አፈፃፀሙ ቢለያዩም የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ያነበንቡ እንደነበር ይታወቃል፡፡
እዚህ ላይ፣ ሶሻሊዝምን ከጦር መሣሪያ ጋር አስገባ የተባለውን የደርግ መንግሥት ታግሎ ዛሬ ወደ ሥልጣን የመጣው ኢህአዴግም፣ በጫካ ይመራበት የነበረው ርዕዮተ ዓለም “የአልባኒያ ሶሻሊዝም” እንደነበር ይነገራል። ሥለዚህ አቶ ብርሃኑ፣ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም የኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥለማመሣቀሉ ሢናገሩ፣ የሶሻሊዝም ጦስ ከደርግም የዘለለ የዛሬ እውነታችን መሆኑን እየተናገሩ እንደሆነ፣ ተረድተውት ይሆን? በመሠረቱ፣ ኢህአዴግ እየተመራበት ነው የሚባለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ በብዙ መልኩ የቡድን መብትን ከሚያንፀባርቀው፣ ከሶሻሊዝም ርዕዮተዓለም ጋር እንደሚመሣሠል ዋቢዎችን እየነቀሱ ማስተንተን ይቻላል። እንደውም፣ የኢህአዴግ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የድርጅት አወቃቀር ዋና አጋሩ፣ የስጋም የነፍስም አርአያው የሆነው የቻይና መንግስት፣ በአንድ አውራ ኮሚኒስት ፓርቲ አይደል እንዴ የሚመራው? እባክዎ አቶ ብርሃኑ፣ የሶሻሊዝምን የትላንት ሀገር አጥፊነት እያስታወሱ፣ የዛሬ ኑሯችን ሥጋትና ምሬት አያፋጥኑት!?

Read 8565 times