Sunday, 03 March 2013 00:00

ሦስቱ ዕጩዎ ች ከምርጫው በፊት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“እግዚአብሔር የፈቀደውን
ነው የምንሰራው”ብፁዕ አቡነ ማትያስ

“ከኔ ይበልጥ ወንድሞቼ
እንዲመረጡልኝ ነው የምመኘው”
(ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፤ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ)

“ፓትርያሪክም ብሆን ሊቀጳጳስ እርቁ ይቀጥላል
(ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ የሰሜን ጐንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ)
ለስድስተኛ ፓትርያርክነት እጩ መሆንዎን የሰሙት ከማን ነው?
ሰው ዝም ብሎ ያወራል፡፡ እገሌ ይሆናል ይባላል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እጩ ነህና እንድትመጣ አሉኝ፡፡ አሁን ባለፈው የካቲት 13 ነው አዲስ አበባ የገባሁት፡፡ እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ከኢየሩሳሌም ተነስቼ ስገባ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ተረቋል ተባለ፡፡ ያ ሕግ ታህሳስ 30 ለሲኖዶስ ይቀርባልና በሲኖዶስ አባልነትህ ና ተባልኩ፤ ሥራ ይበዛ ስለነበር አልተመቸኝም፡፡ ጥር 6 ቀንም ለሌላ ስብሰባ ና ተብዬ አልቻልኩም፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካ ዜግነት እንደነበርዎ ሰምቻለሁ…አሁንስ?
በፈረንጅ አቆጣጠር ከ1994-1995 ዓም ችግር ስለነበረብኝ የአሜሪካ ፓስፖርት ይዤ ነበር፡፡ አሁን ግን ተለውጧል፡፡ ይኼ ከአሁኑ ምርጫ ጋር አይያያዝም፡፡ ለምርጫው ብዬ ፓስፖርት አልቀየርኩም፡፡ በመሰረቱ የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ ሆኜ ከተመደብኩ በኋላ ሃሳቤ ወደ ኢትዮጵያዊነቱ ለመለወጥ ነበረ ተጓቶ ነው እንጂ፡፡ እንደዚህ አይነት እጬ እሆናለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡
ግን እንዴት የአሜሪካ ዜግነት ወሰዱ?
አይ እሱማ ---- የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ በነበርኩበት ጊዜ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ተፅእኖ ነበረብኝ፡፡ መንግስት ደህንነቶች ከተሳላሚዎች ጋር እየላከ ብዙ ችግር አስከትሎብኛል፡፡ በዚያ ምክንያት ወደአሜሪካ ተሰደድኩ፡፡ እዚያ የነበሩትን ምዕመናንም ሳገለግል ቆየሁ፡፡ በኋላ ሲኖዶሱ ጠርቶ የአሜሪካ ሊቀጳጳስነቱን አፀደቀልኝ፡፡
በወቅቱ ፓትርያሪክ ተወግዘው ነበር-----
መወገዙማ የመጣው እኔ ደርግን ስላወገዝኩ ነበር፡፡ ደርግን ሳወግዝ የነበሩት ሰዎች እንዴት መንግሥትን ያወግዛል ብለው ፓትርያሪኩን አሳሳቱና አውግዘውኝ ነበረ፡፡
በኋላ ስመጣ በስህተት ነው ተብሎ አነሱት፡፡ የተወገዝኩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለኃይማኖት ጊዜ ነው፡፡ የተነሳው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስም ለቀው አቡነ ያዕቆብ አቃቤ መንበር በነበሩ ጊዜ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከመሾማቸው ጥቂት ጊዜ በፊት ነው ይሄ፡፡
ከአቡነ ጳውሎስ ጋርም ለፓትርያሪክነት ተወዳድረው ነበር ይባላል…
እኔ አወዳድሩኝ ብዬ አላውቅም፤ አሁንም ድሮም፡፡ ብቻ ከየክልሉ ሁለት ሁለት ተወዳዳሪዎች ሲባል ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እኔ ሳላውቅ ተወዳድሬ እሳቸው ከአምስቶቹ እጩ ፓትርያሪኮች አንዱ ሆኑ፤እኔ ቀረሁ፡፡
ጠርተውኝ የመጣሁት ግን የመርቆሪዎስ ምክትል በነበሩት በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ጊዜ ነበር፡፡ መወገዜን እኔም አላውቅም ነበር፡፡ ምን ሆኜ? ስል እንዲህ ተላልፎብህ ተባልኩኝ፡፡
ብፁዕነትዎ ሲወገዙ ሌላ አቡነ ማትያስ መሾማቸው ትክክል ነበር?
በቤተክርስትያን ባህላችን ሁለት ጳጳሳት በአንድ ስም አይጠሩም፡፡ ግን ያን ጊዜ ተደረገ፡፡ በአቡነ ተክለኃይማኖት ላይ ግፊት አድርገው ነው፡፡ ሆነ ብለው የእኔን ስም ለመውሰድ ያደረጉት ነው፡፡ ስመለስ ግን ፀፀት ውስጥ ገቡ፡፡
ብፁዕነትዎ ፓትርያሪክ ቢሆኑ እርቀ ሰላሙ በምን መልክ ይቀጥላል?
እርቀሰላሙ እንደሚቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ተናግሯል በዚያው መሰረት ይቀጥላል፡፡ ከሲኖዶስ የተለየ ሃሳብ ሊኖረኝ አይችልም፡፡
በፓትርያሪክነት ቢሾሙ በኢየሩሳሌም የቤተክርስትያኒቱን ይዞታ ለማስመለስ ምን ለመስራት አቅደዋል?
ፓትርያሪክ የመሆን ጉዳይ ሳይሆን እኔም ሆንኩ ሌሎቹ እንዲገፉበት ቅዱስ ሲኖዶሱን እገፋፋለሁ ከሆንኩ አለሁ ማለት ነው፡፡ ካልሆንኩ ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሥራዬ ብሎ ከግብፅ ኦርቶዶክስ ጋር ተነጋግሮ አንድ መፍትሄ እንዲገኝ ጥረት ይደረጋል፡፡ ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት ብቀየርም ይሄ ይቀጥላል፡፡
ፓትርያርክ ቢሆኑ ከአምስተኛ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ምን የተለየ ነገር ይሰራሉ?
መቼም እግዚአብሔር የፈቀደውን ነው የምንሰራው፡፡ ቤተክርስትያኒቱ ትክክለኛውንና ቀጥተኛውን መንገድ አንድትይዝ፣ በውስጧ ያለው ሁሉ መንፈሳዊነትን የተጐናፀፈ እውነተኛነትን የተከተለ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ በተቻለ መጠን ይህንን ወደ እውነተኛው መንገድ ለመመለስ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡
ከአቡነ ጳውሎስ ስራዎች በጣም የሚያደንቁት ምንድነው?
ቅዱስነታቸው ዓለም አቀፍ ሰው ነበሩ፡፡ በዚህም ቤተክርስትያኒቱን አስተዋውቀዋል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ለጳጳሳት ማረፊያ አሰርተዋል፡፡
ቤት አልነበረም፡፡ መሰብሰቢያ አዳራሽ አልነበረም፣ ቤተመፃህፍት አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁለቱን አደንቅላቸዋለሁ፡፡
መሻሻል ይገባቸዋል በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ለአቡነ ጳውሎስ አስተያየት አቅርበው ያውቃሉ?
አንዳንድ ስህተቶች ሳይ እነግራቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ በስብከተ ወንጌል፣ በኃይማኖት አጠባበቅ በኩል የኃይማኖቱን ሥርዓት ያልጠበቁ ሰባኪዎች… በዘፈቀደ ሲሆን እናገራለሁ፡፡
ይቀበሉዎት ነበር?
ይቀበሉኛል ግን ነገሩ ከባድ ይሆንና የተባለው መቶ በመቶ ላይሰራ ይችላል፡፡ መቻቻል ጥሩ ነገር ይመስለኛል መቻቻል ከሌለ ሁከት ነው ያለው፣ የሕዝቡንና የሀገር አንድነት ለማስጠበቅ ተቻችሎ መስራት ያስፈልጋል፡ሌላ ምርጫ የለም፡፡ አንዱ ሌላውን ሳይቀማ መኖር መቻል አለበት፡፡


===============
በፓትርያርክነት ቢመረጡ ምን ለመሥራት አቅደዋል?
እግዚአብሔር አምላክ ለዚያ ካደረሰኝ ከዚያ በኋላ ነው የምናገረው፡፡
ነገር ግን እኔ የምመኘው ከአራቶቹ እጩዎች መካከል ለሀገር ለወገን ለቤተክርስትያን የሚያስብ አባት እግዚአብሔር እንዲሰጠን ነው፡፡ ለዚህም እግዚአብሔርን በፀሎት እጠይቃለሁ፡፡ ቅድሚያ ከኔ ይበልጥ ወንድሞቼ እንዲመረጡልኝ ነው የምመኘው፡፡ ነገር ግን ይሄን ጥቆማ ላደረጉት ወገኖቼ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ለእጩነት በመጠቆምዎ ምን ተሰማዎት? እንደሚመረጡ ጠብቀው ነበር?
እዚህ ደረጃ እደርሳለሁ፣ ጨርሶ እጠቆማለሁ የሚል ሀሳብ አልነበረኝም፡፡
በመጠቆሜም ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ለምን ትለኝ እንደሆነ ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ከአርባ ሚሊዮን በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ሕዝብ ማገልገል ከባድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከወደደ ደግሞ ይኼን ሕዝብ ለማገልገል አንተ እንደፈቀድክ ይሁን ብዬ ነው የተውኩት፡፡
ብዙ ቋንቋዎች እንደሚናገሩ ሰምቻለሁ----- ምን ያህል ይችላሉ?
አፌን የፈታሁት በኦሮምኛ ነው፡፡ አማርኛ፣ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛና በመጠኑ ጣሊያንኛ እናገራለሁ፡፡ አማርኛን፣ ግእዝንና እንግሊዝኛን በትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ ጀርመንኛን ቅድስት ቤተክርስትያን አሁን በህይወት ከሌሉት ከእነ ብፁዕ አቡነ ይስሀቅ ጋር ወደ ምዕራብ ጀርመን ልካኝ ነው የተማርኩት፡፡
በእነዚህ ቋንቋዎች በመግባባቴ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ጣልያንኛውን ደግሞ ስድስት አመት ተኩል እዚያ በመቆየቴ ነው የቻልኩት፡፡ ኦሮምኛ በመናገሬ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ኦሮሚኛ ተናጋሪ ካህናት ጥቂት ናቸው፡፡
ከብሔረሰቡ ተመርጬ ጳጳስ በመሆኔ ይደንቀኛል፤ የእግዚአብሔር ምርጫ ነው፡፡ ተልእኮውን ያፋጥናል፡፡ ህብረተሰቡ በአስተዳደርም ሆነ በወንጌል ስብከት ይበልጥ በሚረዳው ቋንቋ ማስተማር እንዲሁም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ለመግባባት ቋንቋ መቻል ጥሩ ነው፡፡ ኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ከፈቀደ በርካታ ቋንቋዎችን ብችል እወዳለሁ፡፡ በቋንቋ አላመልክም፣ የማመልከው በኢትዮጵያዊነቴ ነው፡፡ በእምነቴ አማራ፣ ኦሮም በሚል አልከፋፍልም፡፡
ፓትርያርክ ቢሆኑ ለእርቀሰላሙ ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?
ለእርቀሰላሙ እኔ ሳልሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሰረት መቀጠሉ ያስደስተኛል፡፡ ሊቃነጳጳሳቱ ሳይሆኑ ከጀርባቸው ያሉት ብሶት ያለባቸው ሁሉ ወደ እናት ሀገራችን ገብተው ሰላማዊ ኑሮ ቢኖሩ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለእርቀሰላም ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ በሩን ከፍቷል፡፡ በተከፈተው በር ገብተው ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ሀገራቸውን እንደእኛ ቢያገለግሉ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

=======================

ለፓትርያርክነት እጬ ሆነው መጠቆምዎን የሰሙት ከማነው?
ሲወራ ነው የሰማሁት፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ በፊት ወሬ ይሰማል፤እውነትና ውሸትነቱ አይታወቅም እንጂ፡፡ በሲኖዶስ ጉባዔ በይፋ ተነገረኝ፡፡
የምረጡኝ ዘመቻ መሰል ነገር በሀገረስብከትዎ እንደነበር ሰምቻለሁ…
ኧረ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ መኖሩን አላውቅም፡፡ እንደውም ጐንደር ከአምስቶቻችን እጩዎች ውጪ የሆኑ ሊቀጳጳስ መርጠው ማስተላለፋቸውን ነው የማውቀው፡፡
ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር ለፓትርያሪክነት ተወዳድረው ነበር፡፡ አሁን በእጩነት እንደሚመረጡ ጠብቀው ነበር?
አሁንም ሆነ ያን ጊዜ እጩ መሆኔን ተቃውሜ ነበር፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም ይህንኑ ተናግሬአለሁ፡፡ የሲኖዶሱ አባላት ዝም ቢሉም አራታችን ተናግረናል፤ ሁላችንም ተናግረናል፡፡ ለማሟያ ነው ሊያሰኝም ይችላል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሲመረጡ የአስመራጭ ኮሜቴ ሊ/መንበር ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ብትተውኝ ግን ብዬ ማመልከቴ አልቀረም፡፡
ስድስተኛው ቅዱስ ፓትርያሪክ ቢሆኑ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?
በዚያን ጊዜ ይገልፅልኝ ይሆናል፤አሁን ያሰብኩበት አይደለም፡፡
ለእርቀሰላሙ መቀጠል ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ይነገራል፡፡ እስቲ የሰሩትን ይንገሩኝ---
ከፍተኛ ጥረት ያደረግሁበት ነው፤አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም እያሉ እኔ ሃያ አመት ደብረታቦር ተቀምጫለሁ፡፡ ሃያ አመት ሙሉ የፋርጣ እና የእስቴ የደቡብ ጐንደር ካህናት፤“አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክ ሲሉ እንጂ አንድ ቀን እንኳ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሲሉ አልተሰሙም፤እንዲህ ማለት ቅዱስነትዎን የቤተክርስትያንንም ስርዓት በመቀበል ነው እንጂ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጠልተው አይደለም፡፡ አሁንም ይህ ሀገር ለቅዱስነትዎ ባለውለታዎ ነው፡፡ ስለዚህ ውለታዎን ለመክፈል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እንዲመጡ አሳስባለሁ” ብዬ ሁለት ሦስት ጊዜ ተናግሬአለሁ፡፡
መጥተው ሀገራቸው እንዲገቡ እንጂ በአቡነ ጳውሎስ ላይ ፓትርያሪክ እንዲሆኑ አይደለም፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ አሁን መንበሩ ላይ እንዲቀመጡ የሚሉ አሉ፤ እንዲህ ያለ ሀሳብ የለኝም፡፡ ምኞታቸው ሀገራቸው መግባት ነውና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አሁን ሀገራቸው እንዲገቡ ነው እንጂ ፓትርያርክ እንዲሆኑ አይደለም፡፡
ይህ አቋሜ በአቡነ ጳውሎስም ጊዜ አሁንም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰላሙ እንዳይንጠለጠል ነበር ምኞቴ፡፡ ሰላሙ እየተወለካከፈ እዚህም እዚያም ያሉት እያስቸገሩ ስለሆነ በተረጋጋ ጊዜ ይሻላል፤ አሁን ቤተክርስትያኒቱን የሚመራ አባት ይመረጥ ብለናል፡፡
ብፁዕነትዎ ፓትርያሪክ ቢሆኑ እርቀሰላሙ ከምን ይደርሳል? በምን ያህል ጊዜስ ይጠናቀቃል?
የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንጂ ትንቢት አልተናገርንም፡፡ ፓትርያሪክም ብሆን ሊቀጳጳስም ብሆን እርቁ ይቀጥላል፡፡ እዚህም ያሉት እዚያም ያሉት ቤተክርስትያን እንድትከፈል አይፈልጉም፡፡ ቤተክርስትያን እንዳትከፈል እርቁም እንዲጠናቀቅ ነው ምኞቴ፡፡
በስደት ካሉ ብፁአን አባቶች ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለዎት ይባላል፤እውነት ነው?
በስደት ካሉት ብፁአን አባቶች ጋር ተገናኝተንም አናውቀም፡፡ ሆኖም ስዊድን ያሉት አቡነ ኤልያስ ደብረታቦር ሳለሁ ይደውሉልኝ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አይገኙም ---- ለምንድነው?
ብዙ ጊዜ አልመጣም፡፡ ሀገሩም ሩቅ ስራውም ከባድ ነው፡፡ በዚያ ላይ ስራው ይበዛል፡፡ ደብረታቦርም ሳለሁ በዓመት አንድ ጊዜ ነው የምመጣው፡፡ ይህ በሌላ ምክንያት ወይም ከፓትርያሪኩ ክፍተት ኖሮን አይደለም፡፡ አቡነ ጳውሎስ እንደውም ወዳጄ ናቸው
አቡነ ጳውሎስ ሰሩት ከሚባሉ በጎ ሥራዎች የሚያደንቁት አለ?
ብዙ በጐ ተግባራት ነበሯቸው፡፡ ይህን የጳጳሳት መኖርያና መንበረ ፓትርያርክ አሰርተዋል፡፡ እንግዳ ተቀባይም ነበሩ፡፡ የመጣውን እንግዳ ማብላት ማጠጣት ይወዳሉ፡፡ ቤተክርስትያን ማገልገል ይወዳሉ፡፡አቡነ ጳውሎስን “ይኼ ስህተት ነው” ብለው የተናገሩበት ጊዜ አለ?
ሰው አብሮ ከኖረ እንዲህ ቢሆን ይሻላል መባባል አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ደብረታቦር አይሄዱም ነበር በስደተኞቹ ይሁን በሌላ ከበድ ይላቸው ነበር፡፡ ብዙዎቹ ውጭ ያሉት ብፁአን አባቶች ከዚያ አካባቢ ናቸው፡፡
አንድ ጊዜ ስለ ኤችአይቪ ለማስተማር፤ቡራኬም ለመስጠት፤ የሠራናቸውን ትምህርት ቤትና ቤተክርስትያን እንዲባርኩልን በሃያ አመቱ ውስጥ አንዴ ለመሄድ ፈቃዳቸው ሆኖ ነበር፡፡
እናም “ደብረታቦር ልንመጣ ነው፤ ጐብኝተን ምዕዳን ሰጥተን እንመለሳለን፤ አናድርም ባህርዳር ነው የምናድረው” አሉኝ፡፡ “ለአንድ ቀን መጥቶ የሚመለስ ሰው ወይ ለለቅሶ ወይ ዘመድ ለመጠየቅ ይመስላል እንጂ የፓትርያርክ ጉብኝት አይመስልም----” ብዬ ተከራክሬአቸው፤ የአውሮፕላን ትኬት አስቀይረው አርብ ሄደው እስከ እሁድ ቆይተዋል፡፡

Read 5788 times Last modified on Sunday, 03 March 2013 08:06