Saturday, 09 March 2013 11:01

ሴንሰርሺፕ!

Written by  ነ.መ
Rate this item
(1 Vote)

ጥር 5 2005
(የእንስሳትና የሰው ትራጆ - ኮሜዲ)
(After all, the highest form of censorship is assassination!)
(- George Barnard Shaw)
አይጢቷ ግጥም ፃፈች፣ ርዕሱ “ድመት” የሚል
“ድመት ባይርባት ኖሮ፣ አታሳድደኝም ነበር”
ብላ ብዕሯን በመቀመር፡፡
ድመት ያንን አገኘች፤
“አይጥ” የሚል ርዕሱ፤ የመልስ - ምት ግጥም ፃፈች
“ከአፈጣጠሯ ነው እንጂ! ድመት ጨካኝ እንዳልሆነች፡፡”

የቤቱ ባለቤት ሰውየ ፣ የሁለቱን ግጥም አገኘ፣
“አሃ! ተነሱብኝ ማለት ነው!?
አደጉና በኔ ላይ፣ ግጥም መፃፍ ጀመሩ?
እንደተኛሁ በጭለማ፣ ነቅተው ወረቀት በተኑ?!
ጅላጅል ፍሪክ! ስንለው
ትውልዱ ከፋ ማለት ነው!
በቃ! ሁለቱም ይቀጡ!
ለዚያችም ወጥመድ ይዘርጋ፣ ለዚችም ገመድ አምጡ!!”
ብሎ ፍርዱን ሰጣቸው፡፡

ይህን ያስተዋለ ውሻ፣ ነገረ -ሥራው ቢገርመው
“የዚህ አገር ሰው እንዲህ ነው፣
ባልገባው ነገር ይፈርዳል
በገባው ነገር ይናቃል!!” አለ በውሻኛ ቃል፡፡

ያቺም በወጥመድ ተይዛ፣ ያቺም በገመድ ታሥራ
ሲሰዳደቡም ሰማና፤
“ወይ እነዚህ ፍጡሮች
ይቺም ያለዕዳው ዘማች፣ ያቺም አለ ዕዳው ዘማች
ሲሞቱም አይማማሩ?
ጠላት ሆነው እንደኖሩ?
ጠላት ሆነው ሊሞቱ?! ጠላት ሆነው ሊቀሩ?

ጌታችንም ጨካኝ አውሬ!
አንዳቸውንም ሳያነብ፣ ሁሉን ሁሌ በመጠርጠር
በቀሉን ብቻ በማመን፣ በቋፍ በሥጋት የሚኖር
አንዱን ጥፋት ለማጥፋት፣ ሌላ ጥፋት የሚሠራ
ቁጥቋጦዎችን ለመንቀል፣
ካገሩ መከታ ጋራ፣ የሚጣላ ከተራራ፡፡
እረዲያ ድመት፣ እረዲያ አይጥ
ኧረዲያ ሰው፣ የሰው ፈሊጥ
ማንም ከማንም ላይሻል፣ ማንም ከማንም ላይበልጥ
አገር እንደበሬ ጠልፎ፣ ጥሎ ለመብላት መሯሯጥ
መንተፋተፍ…መተላለፍ…መጠላለፍ ሁሉን ማርገፍ
ኧረ ምረቱን ያምጣልን፣ እንዲህ ሆኖ ማንም አይተርፍ!!”
ውሻ ይሄን ብሎ ሲያበቃ፣ አህያ ሲጫን አየና፤
ከልቡ አዘነ ክፉኛ፡፡
“የዚህ ሁሉ መዘዝ ትርፉ፣ ለኔና ለዚህ ለጌኛ!
እዚህ አገር የሚጠቃው
ወይ ላገሩ ታማኝ ነው
አሊያም ያው ተሸካሚው ነው!!”
አለና ደጃፍ ላይ ተኛ፡፡

Read 3719 times