Saturday, 09 March 2013 11:11

የኤግዚቢሽን ማእከል ክፍያ በ10 አመት በ10 እጥፍ ጨምሯል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

የኤግዚቢሽን ማዕከል የጨረታ ዋጋ በአስር ዓመት ውስጥ በአስር እጥፍ መጨመሩ እንዳሳሰባቸው አዘጋጆችና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ለበርካታ ጊዜ ሲጫረቱና ሲሰሩ የቆዩ ነጋዴዎች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በየጊዜው የጨረታ ዋጋ በማሻቀቡ አንዳንድ አዘጋጆች ከሥራው እያፈገፈጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለመጪው አዲስ ዓመት የቀረበው የጨረታ ዋጋ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር መጠጋቱ አሳስቦናል ያሉት አዘጋጆቹ፤ የዋጋው መናር የጨረታ ተሳታፊዎችንም ሆነ ጐብኚዎችን ያሸሻል ብለዋል፡፡ “የጨረታው ዋጋ በበዛ ቁጥር ላለመክሰር ስንል የተሳታፊዎች የቦታ ዋጋ ላይ እንጨምራለን” የሚሉት አዘጋጆቹ፤ ይህ ደግሞ ለተሳታፊ ነጋዴዎች ማፈግፈግ ምክንያት ይሆናል ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው ኤግዚቢሽንና ባዛር ማዘጋጀት የጀመረው ከ15 ዓመት በፊት እንደነበር የገለፁ አንድ አዘጋጅ፤ ስራው በባህሪው አስጊና አስቸጋሪ በመሆኑ ብቻም ሳይሆን ከዋጋው ንረት የተነሳ የ2006 ዓ.ም ጨረታ ላይ አለመሳተፋቸውን ገልፀዋል፡፡

የ2004 ዓ.ም አዲስ አመት የጨረታ ዋጋ 3.7 ሚሊዮን ብር እንደነበር የገለፁት ሌላው አዘጋጅ፤ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር መጠጋቱ ብዙዎችን አስደንግጧል ብለዋል፡፡ የ2006 ዓ.ም ጨረታን 4.9 ሚሊዮን ብር በማቅረብ ያሸነፈው የ“አንድነት ፕሪንተር” ማርኬቲንግ ማናጀር ፍሬወይኒ ገብረየስ፤ ድርጅታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉንና በጨረታ ሰነዱ ላይ ያለውን የሶስት አመት ዋጋ በመመልከት የጨረታ ገንዘቡን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ በገንዘብ ብናሸንፍም አሸናፊነታችን አልተረጋገጠም ያሉት ማርኬቲንግ ማናጀሯ፤ አዲስ በመሆናቸው የጨረታ ዋጋው ተወደደ አልተወደደም ለማለት እንደማይችሉ ነገር ግን በጨረታው ሰነድ ላይ በተቀመጠው መሠረት ተገቢ የመሰላቸውን ዋጋ አቅርበው ማሸነፋቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በሞባይል ንግድ ላይ የተሰማሩ የ38 ዓመት ነጋዴ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የቦታ ዋጋ ንረት ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት ከተሣታፊነት ራሳቸውን ማግለላቸውንና አዲስ ተሳታፊ ጓደኞቻቸውም በስራው ደስተኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነገር ግን በመጫረት የሚታወቅ ትልቅ ድርጅት ያላቸው ግለሰብ በሰጡት አስተያየት፤ የማዕከሉን ልክ ያጣ ንረት መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሊያረጋጋው እንደሚገባ ጠቁመው ቢቻል ቋሚ ዋጋ ኖሮት አዘጋጆች በሶስትም ይሁን በሁለት አመት ተራ እየደረሳቸው ቢያዘጋጁት የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ በጉዳዩ ላይ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ለጨረታ ዋጋው መናር ምክንያት ተጫራቾቹ ራሳቸው እንጂ ማዕከሉ የጨረታ መነሻ ዋጋ እንደማያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡ “በበኩላችን የአዘጋጆቹ፣ የተሳታፊውም ሆነ የጐብኚው ፍላጐት ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ መሄዱን እንጂ ጫና መፈጠሩን አናውቅም” ብለዋል፡፡ የአፍሮ ዳን ባለቤት አቶ ዳንኤል ወርቅሸት ግን የስራ አስኪያጁን ሃሳብ አይቀበሉም፡፡ “ምንም እንኳ ማዕከሉ የጨረታ መነሻ ባያስቀምጥም በፊት በቀረበው ላይ 10 እና 20 ፐርሰንት ጨምረን እንድናስገባ በጨረታ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል፡፡” በማለት ለዋጋው ንረት የማዕከሉም እጅ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት በበኩላቸው፤ በዋጋ ንረት የተነሳ በተሣታፊም ሆነ በጐብኚው ላይ መቀዛቀዝ እንዳልታየ ተናግረዋል፡፡

Read 1933 times Last modified on Saturday, 09 March 2013 11:23