Saturday, 09 March 2013 11:16

በህንፃ ግንባታ ላይ በደረሠ አደጋ የ3 ሠዎች ህይወት ጠፋ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ባንቢስ አካባቢ ለረጅም ህንፃ ግንባታ እያገለገለ በነበረ “ሊፍት ክሬን” ላይ በደረሠ አደጋ 3 ሠዎች ህይወታቸው አለፈ፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከቀኑ 9፡30 አካባቢ በደረሠው አደጋ የግንባታ ስራው አልቆ ሠራተኞች የመወጣጫ ሊፍቱን በማውረድ ላይ ሣሉ ነው አደጋው የደረሰው ብለዋል - የህንፃ ተቋራጩ ኩባንያ ጀነራል ፎርማን አቶ ግርማ ሚዳ፡፡ ብርሃኑ አለሙ የተባለው የጉልበት ሠራተኛ አስከሬን ከህንፃው ጀርባ በሚገኝ አንድ ፔንሲዮን ጣራ ላይ ቆርቆሮውንና ኮርኒሱን ደርምሶ በማለፍ አልጋው ላይ መገኘቱን የገለፁት አቶ ግርማ፤ አህመድ መሃመድ እና ክፍሌ ዋቢ የተባሉት ሠራተኞች በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው ሣለ ህይወታቸው ማለፉንና የሁሉም አስክሬን ወደየቤተሠቦቻቸው መላኩን አስታውቀዋል፡፡ የፔንሲዮኑ ግቢ ውስጥ ሆነው ከፍተኛ የጣራ ድብደባ ድምፅ መስማታቸውን የሚናገሩት የፔንሲዮኑ ባለቤቶች፤ ወዲያው የክፍሉን በር ከፍተው ሲመለከቱ በደም የተጨማለቀው የወጣቱ አስከሬን አልጋው ላይ ተጋድሞ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ “ባማኮ” የተሠኘ የህንፃ ግንባታ ተቋራጭ በሚያስገነባው በዚህ ህንፃ ከዚህ ቀደም በደረሰ ተመሣሣይ አደጋ የአንድ ሠው ህይወት መጥፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች በግንባታ ወቅት አስፈላጊው የአደጋ ጥንቃቄ ሁሉ እንደሚደረግ የተናገሩት የድርጅቱ ጀነራል ፎርማን፤ ሠራተኞችም የአደጋ መከላከያ አድርገው እንደሚሠሩ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡

Read 3151 times