Saturday, 09 March 2013 12:31

የላብራቶሪ ውጤት ጠያቂው የባሕል ሐኪም

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(6 votes)

ካዛንችስ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በስተጀርባ ባለው መንደር ውስጥ የሚገኝ አንድ የባህላዊ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል መጠርያው ትኩረት ይስባል - “ኢትዮ ሱዳን ዘመናዊ የባህል ሕክምና” የሚል ነው፡፡ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙ ኢትዮጵያንና ሱዳንን፣ ዘመናዊና ባሕላዊ ቃላትን ካጣመረው ማዕከል ባለቤት ጋር ባደረገው ቆይታ ስለባህላዊ ህክምና፤ ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶችና ተያያዥ ጉዳዮች አንስቶ ተጨዋውቷል፡፡ አቶ ልበል ወይስ ሐኪም? “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህላዊ መድሐኒት ቅመማና ሕክምና ጥናት” በሚል ስያሜ የሚጠራ ማህበር አለን፡፡ ማህበሩ ከአንድ ሺህ አባላት በላይ አሉት፡፡ ባሕላዊ ይሁን እንጂ የምንሰጠው አገልግሎት ሕክምና ስለሆነ አንዳችን ሌላኛችንን የምንጠራው “ሐኪም” በሚለው ማዕረግ ነው፡፡ ሐኪም እሸቱ ገለቱ እባላለሁ፡፡

ውልደትና ዕድገትዎ የት ነው? በአዲስ አበባ አብነት አካባቢ በ1949 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ በዚያው መንደር በሚገኘው ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤትና ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በቀድሞ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ ከሥራ ጋር መተዋወቅ የጀመርኩትም በተማሪነት ዘመኔ ነው፡፡ መርካቶ አኑዋር መስጊድ ዙሪያ ራይዚንግ ሬዲዮ የሚያስመጡ አንድ አረብ ነጋዴ ነበሩ፡፡ ከልጃቸው ጋር አብረን እንማር ስለነበር፣ ከአባቱ ጋር አስተዋውቆኝ ሱቃቸው ውስጥ አብሬያቸው እየዋልኩ የኤሌክትሮኒክስ ሥራዎችን እሰራ ነበር፡፡ ያ አጋጣሚ ከአረቦች ጋር እንድተዋወቅና የባሕል ሕክምና ዕውቀት እንዳገኝ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል፡፡ ቤተሰብ ውስጥ፣ ባደጉበት መንደር ከባሕል ሕክምና ጋር በተያያዘ ያዩትና በጎ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል የሚሉት ነገር አለ? ምንም አልነበረም፡፡

ራይዚንግ ሬዲዮ የሚያስመጡት አረብ ነጋዴ ሥራውን ለቀው ወደ አገራቸው ሲሄዱ፣ ድሬዳዋ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባግሩስ የሚባሉ አረብ ዘንድ እንድሄድ በመከሩኝ መሠረት፣ እዚያ ሄጄ መሥራት ጀመርኩ፡፡ አዲስ አበባ እያለሁ ለትምህርት ቤቴ እግር ኳስ እጫወት ነበር፡፡ የአሜሪካ የሰላም ጓድ የእግር ኳስ ክለብ አባልም ነበርኩ፡፡ ድሬዳዋ ከሄድኩ በኋላም ከአረቡ ጋር እየሰራሁ ለድሬዳዋ ባቡር ክለብ ተጫውቻለሁ፡፡ በሉቺያኖ ነበር የምንሰለጥነው፡፡ ሆኖም ትኩረትና ፍላጎቴ ወደ ባሕል ሕክምና ስላመዘነ እግር ኳሱን አልቀጠልኩበትም፡፡ በድሬዳዋ ዕውቀቱን የማዳብርበት ዕድልም አግኝቻለሁ፡፡ የባሕል ሕክምና መስጠት የጀመሩት በድሬዳዋ ነው? አይደለም፡፡ የአዲስ አበባው ኤሌክትሮኒክስ ሱቅ ከብዙ አረቦች ጋር እንድተዋወቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገልኝ ሁሉ፣ የድሬዳዋው ባግሩስ ሱቅም ከብዙ አረቦች ጋር አገናኘኝ፡፡ ከእነዚህ አንዱ መሐመድ ዓሊ የሚባሉ የባሕል ሐኪም ነበሩ፡፡

እርሳቸው ወደ ሙያው እንድገባ አበረታተውኛል፡፡ ከእርሳቸው ብዙ ዕውቀትም አግኝቻለሁ፡፡ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ በባሕል ሐኪምነታቸው ከሚታወቁት ከሐጂ አሕመድ ኑሩ ጋር ሠርቻለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ዕውቀቱን ካዳበርኩ በኋላ ነበር ራሴን ችዬ መሥራት የጀመርኩት፡፡ አሁን በአዲስ አበባ፣ በቆቃና በሞጆ ሦስት ቅርንጫፎችን ከፍቼ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ የማዕከልዎ መጠሪያ ላይ “ዘመናዊ የባህል ሕክምና” ሲሉ ምን ማለት ፈልገው ነው? ወደዚህ ሙያ ከመጣሁ በኋላ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት እየተዘጋጀ የባሕል ሐኪሞች የምንሳተፍበት ስልጠና አለ፡፡ በአንድ ወቅት በፓስተር ኢንስቲትዩት በኩል ከፊሊፒንስ በመጡ አሰልጣኞች ለስድስት ወራት ስልጠና ተከታትያለሁ፡፡ የምሰጠው ባሕላዊ ሕክምና ቢሆንም የእኔን እርዳታ ፈልገው የሚመጡ ሰዎች የነገሩኝ ምልክት ያመኛል ያሉትን የማይገልጽ ከመሰለኝ፣ሐኪም ቤት ሄደው የላብራቶሪ ማረጋገጫ ይዘው እንዲመጡ የማዝበት ጊዜ አለ፡፡

ከስለታማ ነገሮች ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ሥራ አልሰራም፡፡ ለንጽሕና ልዩ ትኩረት እሰጣለሁ፡፡ ባሕላዊ ሕክምና ከመንፈሳዊ አሰራር ጋር የሚያያዝ ነገር አለው ይባላል፡፡ ምንድነው የሚያገናኘው? ሕክምናውን በመንፈሳዊ አሰራር እየታገዙ የሚሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ ተከታታይነት ያለው የራስ ምታት ወይም አንድ ሰው ሥራ መስራት እየቻለ ሥራ ጠል የሚያደርገው ችግር ዓይነ ጥላ ይባላል፡፡ በባሕል ሕክምና መድሐኒት አለው፡፡ የእርስዎ ማዕከል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሱዳናዊያንም የባሕል ሕክምና እንደሚሰጥበት ማስታወቂያው ይገልፃል፡፡ በትክክል የሱናዳዊያን የባህል ህክምናም ይሰጣል? ከላይ ልገልጽልህ እንደሞከርኩት እኔ የባሕል ሕክምና ዕውቀቱን ያገኘሁት ከውጭ አገር ዜጎችና ከኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ መርካቶ አንዋር መስጊድ አካባቢ አገኛቸው የነበሩ ሱዳናዊያን በባሕል ሕክምናቸው ዙሪያ ብዙ ዕውቀት ለግሰውኛል፡፡

በምሰጠው አገልግሎት ከሱዳኖቹ ያገኘሁትን ዕውቀት ስለምጠቀም ነው ተቋሜን “ኢትዮ ሱዳን” ያልኩት፡፡ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሐኪም ማሞ ኃይሌ፤ ለመድሐኒት ቅመማ የሚጠቀሙበት እጽዋት ማልሚያ ግቢ ነበራቸው፡፡ እርስዎስ እጽዋቱን ከየት ነው የሚያገኙት? ለሕክምና የምንጠቀምባቸውን መድሐኒቶች የምንቀምመው ከእጽዋትና ከእንስሳት ተዋጽኦ ነው፡፡ እኔ እጽዋት ማልሚያ የለኝም፡፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የባሕል ሕክምና ባለሙያዎች የሚያስፈልጉንን እጽዋት የሚያቀርቡልን ሰዎች አሉ፡፡ አርሲና ከሚሴን ከመሳሰሉ ቦታዎች ያመጡልናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሐኪም ማሞ ኃይሌ ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ከእርሳቸው የወሰድኩት ብዙ ዕውቀት አለ፡፡ በማህበራችን ስብሰባ ላይ ስንገናኝ ብዙ ነገር ይመክሩኝ ነበር፡፡ በባሕል ሕክምና ዘርፍ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ የባሕል ሕክምና ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ስለሚደብቁ ለዘርፉ ዕድገት እንቅፋት ሆኗል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? እኔ እራሴን ወክዬ መናገር የምችለው፣ ሙያውን ለማወቅ ፍላጎት ያለው ካለ ዕውቀቴን ለማካፈል ፈቃደኛ መሆኔን ነው፡፡

ካሁን በፊት ያስተማርኳቸው ወጣቶችም አሉ፡፡ ዕውቀቱን ለመገብየት ፍላጎት፣ ጽናትና ትዕግስት ግን በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በባሕል ሕክምና ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ ሕክምናም የሚሰጡ መድሐኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ይኖራቸዋል፡፡ ችግሩን ለህመምተኞች በምን መልኩ ነው የምትገልፁት? ለህመምተኛው የሰጠሁትን መድሐኒት ከተጠቀመ ከሰዓታት በኋላ ሆዱን በማሻር መፍትሔ እንደሚያገኝ ነግሬው ማስቀመጡ ካልቆመለት፣ማርከሻው ምን እንደሆነ አስቀድሜ እነግረዋለሁ፡፡ ቡና መጠጣት አንዱ ማርከሻ ነው፡፡ የባሕል ሐኪሞች የሚቀምሙት መድሐኒት ጠቀሜታቸው ብቻ ሳይሆን ጉዳታቸው ምን እንደሆነ ቀድሞ የሚታወቅበት ሁኔታ አለ? የባሕል ሐኪሙ የሰጠው ሕክምና ጉዳት ቢያደርስ ተጠያቂነቱ ምን ይመስላል? እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በማህበራችንም በመንግሥትም የተለያዩ ሥራዎች ተሞክረዋል፡፡

ማህበራችን የአባላቱን የሕክምና መስጫዎች እየዞረ ይጎበኛል፡፡ ታካሚዎች ላይ ጉዳት አድርሰው የታሸጉ የባሕል ሕክምና ማዕከላትም አሉ፡፡ መንግሥት ዘርፉን ለማበረታታት እየሞከራቸው ካሉ ተግባራት አንዱ፣ የባሕል ሐኪሞች በምርምር ለሚያገኙት መድሐኒት፣ በአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በኩል መዝግቦ ዕውቅና ለመስጠት መታሰቡ ነው፡፡ እኔም በቅርቡ ሁለት የምርምር ውጤቶቼን የማስመዝገብ እቅድ አለኝ፡፡ በሙያዎት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገርም መስራት እንደሚችሉ ማህበራችሁ የፃፈልዎትን ደብዳቤ አይቻለሁ፡፡ በምን መመዘኛ ነው ይህ ዕውቅና የተሰጠዎት? ጥቂት የማይባሉ የእስራኤል ፈላሻዎች እኔ ዘንድ እየመጡ ለህመማቸው መፍትሔ ሲያገኙ፣ እስራኤል ሄጄ እንድሰራ ጠየቁኝና ለማህበራችን አመለከትኩ፡፡ ማህበሩ የትብብርና የዕውቅና ደብዳቤ የፃፈልኝ በተለያየ ጊዜ አገልግሎቴን አግኝተው የተጠቀሙ ግለሰቦችን ምስክርነት አጣርቶ ነው፡፡ የሰላም አምባሳደርነት ሠርተፊኬት ተበርክትዎሎታል፡፡

ከማን ነው የተሰጠዎት? ሥራዬን አይተው ኮርያዎች ናቸው ሠርተፊኬቱን የሰጡኝ፡፡ በዘመናዊ ሕክምና ለምሳሌ ህመምተኛው ኦፕራሲዮን የሚደረግ ከሆነ ኃላፊነት እንዲጋራ የሚፈርምበት ሁኔታ አለ፡፡ በባሕላዊ ሕክምና ለሕይወት ዋስትና ምን ይደረጋል? እኔ በግሌ ማዳን የማልችለው ህመምተኛን ማከም አልችልም ብዬ የመመለስ ልምድ አለኝ፡፡ የሥራ ፈቃድ ከማን ነው የምታወጡት? የብቃት ማረጋገጫው ከማህበራችን ሲሰጠን፣ የሥራ ፈቃዱን ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ነው የምንወስደው፡፡ እርስዎ ሲታመሙ ወደ ባሕላዊ ህክምና ነው ወይስ ወደ ዘመናዊ ሕክምና የሚሄዱት? እኔ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነኝ፡፡ አሁን ድረስ ስፖርት ስለምሰራ የጤና ችግር የለብኝም፡፡ አጠቃላይ ምርመራ ለማድረግ ግን ሆስፒታል እሄዳለሁ፡፡ የቤተሰብ ዶክተርም አለን፡፡ ከባሕል ሐኪሞች ማንን ያደንቃሉ? ሐኪም ማሞ፣ ሐኪም ተክሌ፣ ሐኪም ሰለሞን፣ ሐኪም ተስፋዬ … ብዙ ናቸው፡፡ የባሕል ሕክምና የሚከለክላቸው የምግብ ዓይነቶች አሉ? መድሐኒት የወሰደ ሰው ስንዴ፣ በቆሎ፣ እንቁላል፣ የበረዶ ውሃ፣ ዶሮ፣ የበሬ ሥጋ፣ … ቢያንስ ለአንድ ወር እንዳይጠቀም ይመከራል፤ ምክንያቱም የሚከለከሉት ምግቦች መድሐኒቱ እንዳይሰራ ወይም በሽታው እንዲያገረሽ ስለሚያደርጉ ነው፡፡

በዘመናዊ ሕክምና መፍትሔ ላልተገኘላቸው በሽታዎች መፍትሔው አለን የሚሉ የባሕል ሐኪሞች አሉ፡፡ እርስዎ ስለ ካንሰርና ኤድስ ምን ይላሉ? ማንኛውም በሽታ ደረጃዎች አሉት፡፡ ነቀርሳ ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ወደ ደም ያልተሰራጨውን በሽታ እናድናለን፡፡ ወደ ደም የተሰራጨውን በሽታ ግን ማዳኑ ያስቸግራል፡፡ የህመምተኛ አቀባበላችሁ ምን ይመስላል? ምዝገባ፣ ማህደር መያዝ፣ ክፍያው … ታካሚው እንደመጣ ይመዘገባል፡፡ ክፍያው እንደየሰው አቅም ይለያያል፡፡ የመክፈል አቅም ከሌላቸው በነፃ ሕክምናውን የምንሰጥበት ሁኔታም አለ፡፡ መዝገብ አለን፡፡ መጨረሻ ላይ ታካሚዎች ከሕመማቸው ነፃ መሆናቸውን መዝገባቸው ላይ በፊርማቸው እንዲያረጋግጡ የምናደርግበት አሰራር አለ፡፡ እስካሁን ለምን ያህል ሰዎች አገልግሎት ሰጥተዋል? በሥራው ላይ ወደ ሃያ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ስቆይ በጣም ለብዙ ሰዎች ነው የሕክምና አገልግሎት የሰጠሁት፡፡ ቁጥሩን በትክክል መግለጽ ያስቸግራል፡፡

በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት ነገር ካለ … በባሕል ሕክምና ዘርፍ የተሰማሩ በጣም ብዙና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ የእነዚህ ባለሙያዎች ዕውቀት ለአገርና ለሕዝብ በተገቢው መልኩ እንዲጠቅም መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በስፋት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በማህበራችን፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ ጠንክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በዘርፉ ያለን ባለሙያዎችም ዕውቀታችንን ለማሳደግ መትጋት ይኖርብናል፡፡ እኔ ከቀጣዩ ዘመን ዕቅዶቼ አንዱ ዕውቀቴን ለማሳደግ የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰድ ነው፣ ለዚያም ዝግጁ ነኝ፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ባለቤቴንና ልጆቼን ጨምሮ ብዙ ሰዎችና ተቋማት ላደረጉልኝ ትብብር በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ፡፡

Read 8404 times