Saturday, 16 March 2013 10:51

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም፣ የአቶ መለስ ምትክ ወይስ የፕሬዝዳንት ግርማ?

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(7 votes)

አሁን በቀጥታ አንድ ጥቅስ ታነባላችሁ፤ የሀሳቦቹን ተጠየቂያዊ (Logical) ጥምረት ትታችሁና የአሁኑ ሀገር ተረካቢ ወጣት ላይ የተጣለውን ተስፋ በመልካም ጐኑ አድንቃችሁ ብቻ ይህን ጥቅስ አንብቡት፤ “የትላንት ፖለቲከኞች ዛሬም እንደ ትላንቱ በጥላቻ ፖለቲካ ላይ ተቸክለው በቀሩበት ወጣቶቻችን በሚዛናዊ ቅኝት ረጅም ርቀት መጓዝ መጀመራቸው ለአገራችን እጅግ በጣም ትልቅ ተስፋ ነው… ወጣቶቻችን የመለስን ምክሮች በውስጣቸው አስቀርተው የህይወት መመሪያቸው ማድረግ መጀመራቸውም መለስን እንዳላጡት ይልቁንም በእያንዳንዳቸው ታዳጊ ልቦና ውስጥ ትንሽ ቦታ እንደሠጡት፣ እርሱንም መሆን እንደጀመሩ የሚያመላክት ነው፡፡ እናም መለስ በሰማኒያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተተክቷል ስንል ከእውነታ ብዙም ያልራቅንበት ምክንያት መለስን በወጣቶቻችን ሚዛናዊ አስተሳሰብ ወስጥ ማግኘት በመጀመራችን ጭምር ነው፡፡” (ገፅ 33፣ አፅንኦቱ የእኔ ነው)፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበውን ጥቅስ ሃሳብ፣ ምንጩን ከመጥቀሴ በፊት ደግማችሁ አንብቡትና ከወቅቱ የተለያዩ ሀገራዊ ክስተቶች ጋር አናቡት - በቃ፡፡ ለሀገሩ መልካም የሚመኝ ሁሉ፣ በሀገር ተረካቢው ትውልድ ላይ የተጣለው ተስፋ በራሱ፣ ልቡን በሀሴት ሞቅ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ የሀገሩን እጣ ፈንታ በወጉ እየመረመረና እየመዘነ የፖለቲካ ሥርዓቱን መስመር በማሲያዝ የሚታትር ተተኪ ትውልድ የሌላትን ሀገር፣ ማንም ጤነኛ ዜጋ አይፈልጋትም፤ ተስፋ በተጣለባቸው ወጣቶች መደሰትም፣ ከዚሁ የሀገርን እጣ ፈንታ በእውቀት ከመወሰን አጠይቆት የመጣ ነው፡፡ አሁን ከላይ ወደ አነበባችሁት ጥቅስ ልመልሳችሁ። ጥቅሱ የተወሰደው፣ ኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ ማስተጋቢያዬ ናት ከሚላት “አዲስ ራዕይ” መፅሔት፣ ከጥቅምት 2005 ዓ.ም ልዩ እትም ነው፡፡

ልዩ እትም መፅሔቷ፤ “ለዋና አዘጋጇ ለጓድ መለስ ዜናዊ መታሰቢያነት…” በሚል፣ አቶ መለስ “ለሰው ልጆች ምቾት የተፋለሙ የዘመን ስብዕና” ስለመሆናቸው የተለያዩ መረጃዎችን እያጣቀሰች አስተንትናለች፡፡ ኢህአዴግ በዚች የንድፈ ሀሳብ መፅሔቱ አቶ መለስ፣ የሁሉም ነገር ፈጣሪ፣ ጀማሪና አስፈፃሚ መሆናቸውን የገለፀበት ድፍረትና ትጋት የተመለከተ፣ በታጋዩ መሪ ሰብእና ቢኮራና ቢፅናና እንኳ፣ አዕምሮው የተወሰኑ ጥያቄዎችን ማጫሩ አይቀርም፡፡ የንድፈ ሃሳብና የትግበራ መሀንዲሱን ያጣ የፖለቲካ ድርጅት፤ ብዙ መደናገር፣ ብዙ መርበትበት፣ ብዙ መሳከር፣ ሊገጥመው እንደሚችል ስለሚጠበቅ ዜጐችን ማሳሰቡ አይቀርም፡፡ በሀገራቸው ቀርቶ በዓለም ፖለቲካ ላይ ተፅእኖ ማሳደር የቻሉት አቶ መለስ፤ በሥራ እንደባከኑ፣ ያውም “የመንግሥት ሌቦች” ባሏቸው በሆዱ አደር ካድሬዎቻቸው “ቆሽታቸው እያረረ” በሁሉም ጉዳይ እሳቸው ካልተገኙና ካልተናገሩ ምን ዋጋ አለው የሚሉትን ሁሉ ለማስደሰት ያለ እረፍት እንደባዘኑ እስትንፋሳቸው መቋረጡ፣ እንኳን ኢህአዴግን ሌላውንም አስደንግጧል፡፡

“ማረፍ እፈልጋለሁ… እረፍት እንዴት እንደሆነ ማየት እፈልጋለሁ!” እያሉ የተመኙትን ሳያገኙ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸው፣ የሰብአዊ ፍጡርን ልብ ሁሉ በሀዘን ይሰብራል፡፡ ሀዘናችን የሚከፋው ደግሞ፣ መንግሥት ወይም ኢህአዴግ፣ እረፍት አጥብቀው የተመኙትን ታላቅ መሪ፣ ለትንሽ ጊዜ እንኳን እንዲያርፉ ሳይፈቀድና ሃላፊነት የመሸከም ብቃቱን ሳያሳይ፣ ሰውዬው ጭንቅላታቸውን ያለ እረፍት በሥራና በነገር ወጥሮ፣ ህልፈተ ህይወታቸውን አፋጥኖባቸው ይሆን!? ብለን መጠርጠር ስንጀምር ነው፡፡ ጥርጣሬያችን መሰረት የለሽ እንዳልሆነ የምንገምተው ደግሞ፣ መለስ ለመንግሥታቸውም ሆነ ለድርጅታቸው ኢህአዴግ “ሁሉንም ነገር” መሆናቸውን ፓርቲው እራሱ አስረግጦ ከሚያስተነትንበት መሰረት ላይ ቆመን፣ የሀገሪቷን እጣ ፈንታ ጥቂት ለማሰላሰል በሞከርን ጊዜ ሁሉ ነው፡፡ ፓርቲው፣ የእኚህን ታላቅ የፖለቲካ ልሂቅ ጭንቅላት፣ “አንድ ግራም ጉልበት” እስኪቀራቸው ድረስ አሟጦ ከተጠቀመባቸው በኋላ ሁሉ፣ እራሱን ችሎ መቆም የማይችል ልፍስፍስ ተቋም የሚሆን ከሆነ፣ ቢያንስ በሁለት ወንጀል የዛሬው ትውልዶች እንከሰዋለን፡፡

አንደኛ፣ የባለ ርዕይ ታላቅ ሰብእና የተጐናፀፉ መሪያችንን ያለ እረፍት አሰርቶ ለህልፈተ ህይወት በማብቃት፤ ሁለተኛ፣ እንደነ ኢዴፓ የመሳሰሉ አርቆ አሳቢ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ሁሉም፣ እንዲከስሙና ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ምርጫ ሲደርስ ተደራጅተው “እንዲጮሁ” አድርጓል የሚል እሮሮ እየቀረበበት፣ በተጨባጭ ሀገር የሚረከብ ተተኪ የፖለቲካ ተቋም በሌለበት በአሁኑ ጊዜ፣ በባለ ርዕዩ መሪ ስም እየማለና እየተገዘተ ያለምንም ተጨባጭ ሥራ ሰባት ወር ሙሉ የሀገሪቱን የመለወጥ እድል በመወሰኑ የሚሉ ክሶችን እናረቃለን። የዛሬው ትውልድ ክሱን ይዞ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ባይችል እንኳ፣ ጉዳዩን ወደ ህሊናው መዝገብ ቤት መመለስ አያቅተውም፤ ለዚህ ደግሞ፣ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ ተገልጋይ ወይም ተጧሪ መሆን ሳያስፈልገው፣ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ካድሬ ነው የሚል መርሆ አንግቦ የሀገሩን እና/ወይም የመንግሥቱን እጣ ፈንታ ይጠይቃል፡፡

በሕሊና መዝገብ ቤት የተከማቸ የትውልዱ ክስ፣ ውስጥ ውስጡን ተብላልቶ ከመገንፈሉ በፊት፣ የታላቅ መሪን ርዕይ ያነገበ አውራ የፖለቲካ ፓርቲ፣ እንዴት አንድ እውነተኛ ተተኪ መርጦ፣ ለተተኪው መሪ ሙሉ አቅም መፍጠር ይሳነዋል!? በዚህ መጣጥፍ መጀመሪያ ላይ ወደ አነሳነው የ”አዲስ ራዕይ” ጥቅስ ስንመለስ፣ “መለስ በሰማኒያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተተክቷል ስንል ከእውነታ ብዙም ያራቅንበት ምክንያት መለስን በወጣቶቻችን ሚዛናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ማግኘት በመጀመራችን ጭምር ነው” የሚለው አባባል ግርምት ሊፈጥርብን ይችላል፤ ምክንያቱም መፅሔቷ፣ መለስ በህይወት እያሉ የማይፈልጉትን የግለሰብ ተክለሰውነት ግንባታ (Personality cult) ከመጠን በላይ ለጥጣ ከሰበከችበት እውነት ጋር ይጣረሳልና፡፡

እንደውም፣ የታይታና ጉራ የማይወዱት ባለ ርዕዩ መለስ አንድ ጊዜ ቀና ብለው የተደረገውን ሁሉ ቢያዩና “አዲስ ራዕይንም” ቢያነቡ፣ “ኢህአዴግ የመላዕክት ስብስብ አይደለም ያልኳችሁን እረሳችሁ? እኔም ብሆን መልአክ አይደለሁም፤ ባይሆን ነገን እያሰቡ ዛሬን ተግቶ መሰራትን ለምጃለሁ እንጂ!... ኧረ ለመሆኑ የእኔ ራዕይ ምንድን ነው?... ምኞቴ፣ የእኔን ፈር እያያችሁ በራሳችሁ እንድትጓዙ እንጂ፣ እኔን እያመለካችሁ በቁማችሁ እንድትፈዙ አይደለም!” የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ወደ ጥቅሱ ስንመለስ፣ “መለስ በሰማኒያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተተክቷል ስንል ከእውነታ ብዙም ያራቅንበት…” የሚል አደናጋሪ ገለፃ ፈጦ ይታየናል። ይህ ማለት ደግሞ፣ “ከእውነታው ብዙም ባይሆን፣ ትንሽ ግን መራቃችን አልቀረም” ማለት ነው፡፡ የዚህ ከእውነት የመራቅ ልኬታ፣ የአንድምታው ትርጓሜ የሚገለጠው፣ መለስን እንኳን ሰማኒያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ይተካቸዋል ወይ? ብለን ስንጠይቅ ነው፡፡

የዛሬ ዘመን ተጋሪ ትውልዶች ከአቶ መለስ የወረስነውን የመንፈስ ፅናት፣ ግልፅነትና ሀገራዊ ኃላፊነት ተረክበን እንደሳቸው የወጣትነት ዘመን ቅልብጭ ያለ ጥያቄ መጠየቅም እንችላለን፤ መለስን እንኳን 80 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ይቅርና “ጠቅላይ ሚኒስትር” ሀይለማርያም ደሳለኝ እንኳ ሊተኳቸው ችለዋል ወይ? ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም፣ ድንቅ የሆነ የአካዳሚክ ብቃት ያላቸው፣ ህዝብ የማስተዳደርም ሆነ ሀገር የመምራት ልምድና እውቀት የማያንሳቸው፣ በፈሪሀ እግዚብሔር የተሟሸና በሰከነ መንፈስ የታሸ የአመራር ዘይቤ የሚከተሉ ብልህ መሪ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡ አርቆ አሳቢው ባለርዕይ መሪያችን አቶ መለስም፣ ይህን ብቃታቸውን ሳይመረምሩ፣ ሀይለማርያምን ከጐናቸው አያስቀምጡም፤ ወሳኝ የሆኑ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር) መሥሪያ ቤቶችን እየመሩ እንዲለማመዱ አይፈቅዱም፤ ብሎም የነገ መንበራቸውን ተረካቢ እንዲሆኑ አያዘጋጇቸውም ብለን የአቶ ሀይለማርያምን ብቃት ልናምን እንችላለን፡፡

በሌላ በኩል፣ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም፣ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይኼ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲሰጡ አልታዩም። “ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን አፍርሰው፣ እስላማዊ መንግሥት ለማቋቋም የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች አሉ” በማለት፣ መንግሥት ባቀረበው ክስ ላይ እንኳ፣ የመጨረሻው ሀላፊነት የሳቸው ሆኖ እያለ፣ የእሳቸውንና የመንግሥታቸውን አቋም ሲገልፁ አልታዩም፤ ይልቁንም፣ አቶ መለስ ቀድመው ያስተላለፉት ሀሳብ ነበር እየተደጋገመ የቀረበው፡፡ በዚህም ይሁን በሌላ ምክነያት ታዲያ አቶ ሀይለማርያም፣ ህገመንግስቱ የሚፈቅድላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣንና ሀላፊነት እየተጠቀሙ፣ ሀገሪቷን ማስተዳደራቸው ጥርጣሬ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡

ከአቶ ሀይለማርያም በተሻለ ዶ/ር ደብረፂዮን፣ ዶ/ር ቴዎድሮስና አቶ ደመቀ በአንፃራዊነት የፖለቲካ ውሳኔ በሚሹ መድረኮች ላይ ጐልተው ይታያሉ። እንደውም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባልተለመደ መልኩ አዘውትረው በተለያዩ “የምረቃ ቦታዎች” መታየታቸው፣ “አቶ መለስን ነው የተኩት ወይስ ፕሬዝዳንት ግርማን?” የሚል ጥያቄ ያጭርብናል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሥልጣን ዘመን ያልነበሩ፣ ሦስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችም፣ የአቶ ሀይለማርያምን ህገመንግስታዊ ሥልጣንና ሀላፊነት ወይ ሳይሻሟቸው፣ ወይ ሳይቀሟቸው ይቀራሉ? ብለን ብንጠራጠርም አይገርምም፡፡

Read 5151 times