Print this page
Saturday, 16 March 2013 10:58

የአፍሪካ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈጠራ ጉባዔ በአ.አ ሊካሄድ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

አስራ አምስት የአፍሪካ አገራት የICT ሚኒስትሮቹን ጨምሮ ከ500 በላይ ተሣታፊዎች የሚገኙበትና የተለያዩ የICT ማህበረሰብ ክፍሎች በጋራ የሚሠሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል የተባለ የአፍሪካ ኢንፎርሜሽን ፈጠራ ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡ የፊታችን ማክሰኞ በሸራተን አዲስ ይከፈታል ተብሎ የሚጠበቀው ጉባዔ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የተቀናጀ አሠራርን ለሀገራትና ለግሉ ሴክተር የመፍጠር ሚና እንደሚኖረው አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ የጉባኤውን መከፈት አስመልክቶ ትናንት በመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ ውስጥ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ምክትል ሚኒስትሩ አቶ ፒተር ጋትኮት እንደተናገሩት፤ ጉባዔው ለአፍሪካ አገራት የግንኙነትና የልምድ ልውውጥ ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ባሉ አገራት ICT መጠቀም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ መንግስት የICT ልማትን ስትራቴጂ አማራጭ አድርጐ እንደሚጠቀምበትም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮቴሌኮምን ወደ ተሻለ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገርና የህብረተሰቡን ፍላጐት በበቂ ሁኔታ ለማርካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ሚኒስትሩ፤ ድርጅቱን ወደ ግል ይዞታነት ለማዛወር ዕቅድ እንደሌለና በዘርፉ ያሉና የተለያዩ የICT ሥራዎችን ግን ከግሉ ሴክተር ጋር በትብብር ለመሥራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ጉባዔው ለአስራ አንደኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በኢትዮጵያ ጉባዔው የሚካሄደው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ዓመት የጉባዔው ተሳታፊዎች ቁጥርም በ100 እንደሚጨምር የጉባዔው አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡

Read 2493 times