Saturday, 16 March 2013 10:59

አቶ ዕቁባይ በረኸ ይግባኝ ተጠየቀባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የቀድሞ የሜጋ ማስታወቂያ ሥራ አስኪያጅና የኦዲዮ ቪዡዋል አሳታሚዎች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዕቁባይ በረኸ፤ የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በእርሳቸውና እና በሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ላይ አቅርቦት በነበረው የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ክርክር ጉዳይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘው ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በማቅረቡ ምክንያት የደረሳቸውን የፍርድ ቤት መጥሪያ አልቀበልም ብለዋል በሚል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ በትናንትናው ዕለት ልደታ በሚገኘው ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የነበሩት አቶ ዕቁባይ በአሁኑ ወቅት የሜጋ ሥራ አስኪያጅ አለመሆናቸውን በመግለጽ መጥሪያውን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይግባኙን ያቀረበው ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ ይግባኙን የጠየቀው በእርሳቸውና በድርጅቱ ላይ መሆኑን በመግለጽ ሁለቱን የይግባኝ አቤቱታዎች አጣምሮ ማቅረብ እንዲችል ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡ ሜጋ ኪነጥበባት ከ1997 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ገቢን አሳውቆ ግብርን ባለመክፈልና አትራፊ ድርጅት ሆኖ ሳለ እንደከሰረ በማስመሰል፣የደሞዝ ግብር እና ቫት አሟልቶ አልከፈለም የሚሉ ክሶች ሲቀርቡበት አብረው ተከሰው የነበሩት የድርጅቱ የቀድሞው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዕቁባይ በረኸ ጥፋተኛ ተብለው የተጣለባቸው የአራት ዓመት እስራት በገደብ ተነስቶላቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ አቶ ዕቁባይ በ2001 ዓ.ም ከሜጋ ከለቀቁ በኋ የግል ድርጅት አቋቁመው ‹‹ገመና›› የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥኝ ድራማ አሠናድቶ በማቅረብም ይታወቃሉ፡፡

Read 2248 times