Saturday, 16 March 2013 11:02

ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 ገናና መንግስታት ተቃዋሚዎችን በኢንተርኔት ያጠምዳሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በኢንተርኔት አማካኝነት የተቃዋሚዎችን መረጃ ለመሰለልና እንቅስቃሴያቸውን ለመከታተል የሚያገለግል ማጥመጃ ሶፍትዌር (Trojan horse) የሚጠቀሙ 25 አገራት እንዳሉ የገለፀ አንድ የካናዳ የጥናት ተቋም፤ ኢትዮጵያን በማካተት የበርካታ አገራትን በስም ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አስተባብሏል፡፡ ማጥመጃው ሶፍትዌር በተለያዩ መንገዶች የቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን አልፎ እየሾለከ ወደ ኮምፒዩተር መግባት የሚችል ሲሆን፤ መረጃዎችን ለመምጠጥ፣ ፓስዎርዶችን ለመስረቅ፣ የስልክና የስካይፒ ግንኙነቶችን ለመቅረጽ፣ በተለይም የኢሜይል መልእክቶችን ለመሰለል ያገለግላል ተብሏል፡፡

በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ “ስር ሲቲዘን ላብ” የተሰኘው የጥናት ተቋም ረቡዕ እለት ይፋ ባደረገው ማስጠንቀቂያ፤ ሰዎች በኮምፒዩተርና በሞባይል ስልክ ውስጥ የሚያስቀምጡት መረጃ እንዲሁም የሚለዋወጡት መልእክት ለስለላ የተጋለጠ ነው ብሏል፡፡ እንዲያውም በኮምፒዩተራችሁ ላይ የተገጠሙ ማይክሮፎኖችና ካሜራዎችን በመጠቀም ቤት ውስጥ የምታደርጉት እንቅስቃሴና የምትናገሩት ነገር ሁሉ፣ የስለላ አይንና ጆሮ ውስጥ ሊገባ ይችላል ብሏል፡፡

ለስለላ ያገለግላል የተባለውና “ፊንፊሸር” የተሰኘው ማጥመጃ ሶፍትዌር በተገኘባቸው አገራት ሁሉ፣ መንግስታት በተቃዋሚዎችና በዜጐች ላይ ስለላ ያካሂዳሉ ማለት ባይቻልም፤ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ገናና (authoritarian) መንግስታት እጅ ውስጥ መግባቱ ግን አሳሳቢ ነው ብሏል ተቋሙ፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ስለማጥመጃ ሶፍትዌሩ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡

Read 5220 times