Saturday, 16 March 2013 11:12

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(11 votes)

መልክአ ኢትዮጵያ - ፱

ከሬኖ - ኔቫዳ ወደ ሳንፍራንሲስኮ ቤይ ጉዞ ለማድረግ ወፍ ሲንጫጫ ከመኝታችን ተነስተን መንገድ ስንጀምር በሁለት ምክንያት ልቤ በሐሴት ይዘምር ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያቴ በምስልና በዝና የማውቀውን ረጅሙን የጎልደን ጌት ድልድይ (Golden Gate Bridge) እና በፓስፊክ ኦሽን መሃል ለመሃል የሚገኘውን አልካትሬዝ (Alcatraz) እስር ቤት ለመጎብኘት የሰዓታት ጊዜ ስለቀረኝ ነበር፡፡ እርግጥ ነው እግዜር ለአሜሪካ ሲል ዕድሜና ጤና ለሆሊውድ ፊልም ሠሪዎች ይስጥላት እና ካለሁበት ኾኜ እነዚህን ቦታዎች ለበርካታ ጊዜ በፊልም ጎብኝቻቸዋለሁ፡፡ ጉብኝቱን ልናደርግ የተነሳነው በመኪና በመኾኑ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመኪና ማቋረጥ አዲስ ነገር የማየት እና የማወቅ ፍላጎቴን በመጠኑም ቢሆን ሊያሟልልኝ እንደሚችል አስቀድሜ መገመቴ የመደሰቴ ሁለተኛው ምክንያት ነበር፡፡

መቼም በኛ አገር ባንገለገልባትም አገልግት መስጠት ከጀመረች ስለሰነበተችው መንገድ መሪዋ “ጂ.ፒ.ኤስ” ባለውለታነት ዝርዝር ነገር ለመንገር አልሞክርም፡፡ የመድረሻችን አድራሻ በተሞላላት መሠረት አራት ሰዓት ሊፈጅ ይችላል የተባለው 351 ኪሎሜትር ካልቆምን አራት ሰዓት እንደሚፈጅብን ነግራን የመንገድ ምልክቱን እየጠቆመችን እንደ አንድ መንገደኛ አብራን መጓዝ ጀመረች፡፡ ጥቂት እንደተጓዝን የካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ገባን፡፡ ወደፊት እየተወነጨፈ የሚተን እንጂ ከፊት በኩል የሚመጣ መኪና የለም፡፡ ሂያጅ እና መጪ መንገዳቸው ለየቅል ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በመንገድ አይታማም›› በማለት የገዢውን ፓርቲ የመንገድ ልማት ስኬት ሲያወድስ የሰማሁትን ካድሬ ታዘብኩት፡፡ ‹‹በመንገድ ያልታማ በምን ሊታማነው›› ስል ውጭ ውጭውን እያየኹ አጉረመረምኩ፡፡ መንገዱን ከእኛዋ አገር መንገድ ጋር ማወዳደር የሰው አገርን መዳፈር እንደኾነ ቢገባኝም ያገሬን መንገድ ትውስታ መግታት ግን አልቻልኩም፡፡ ጋዜጠኛም አይደለሁ በርከት ያሉትን ከተሞች በተለያየ ዓይነት የሚደላና የሚጎረብጥ መኪና ተጉዤባቸዋለሁ፡፡

የባሕርዳር ጎንደሩ፣ የደሴው፣የመቀሌው፣ከአዲስ እስከ ሞያሌ፣ የባሌው፣የሐረር ድሬደዋው፣ ሁሉንም አስታወስኳቸው መኪናው፣ሰዉ፣ከብቱ የመንገድ ብልሽቱ፣ጥበቱ፣የመሄጃውም መምጫውም መንገድ አንድ መኾን ካሁን ካሁን ከአንዱ መኪና ተላተምን የሚለው የሰቀቀን ስጋት፣አሰቃቂዎቹ አደጋዎች ብቻ ሁሉም ከፊቴ እየመጡ ድቅን አሉ፡፡ በዚህኛው መንገድ ስፋት እና ጥራት ልቤ ጥፍት አለ ‹‹አይ መንገድ›› አልኩ፡፡ የኛዎቹ የምርቃታቸው ዜና መንፈቅ ሳይሞላው ፍርስርሳቸው ወጥቶ ከላይ የለበሰው አስፋልት ከስረኛው ድምድማት ጋር ተቀላቅሎ የሚፈጠረው አባጣ ጎርባጣ ለስንት አደጋ መንስኤ እንደሚኾን ታወሰኝ፡፡ የእኛ አገር መንገዶች አሳዘኑኝ፡፡ መስመራቸውን ይዘው ከሚወናጨፉት መኪኖች ውጪ በመኪናው መንገድ ላይ ምንም የሚታይ ነገር የለም፡፡ መንገዱ ደስ ይላል፡፡ እይታዬን ከዋናው መንገድ ላይ አነሳሁ እና ግራ እና ቀኙን መመልከት ጀመርኩ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ስሰማው የኖርኩት የእምዬ ኢትዮጵያ ጋራ ሸንተረር እና ልምላሜ ጠፋብኝ፡፡ ስለ አገሬ ጋራ ተራራ፣ደን….. በግጥም፣በዘፈን……ብቻ በሁሉም ነገር ከመስማቴ ብዛት በልምላሜ ከእርሷ የሚበልጥ አገር ያለም አይመስለኝ ነበር፡፡

ለነገሩ ዱሮ ዱሮ እርሷ አንደኛ ነበረች ይላሉ፡፡ እኔ እንኳን ከስድስት ዓመት በፊት ነገሌ ቦረና ጎብኝቼው ወደ ነበረው ተፈጥሮ ደን በቅርቡ ሄጄ ቦታ የተሳሳትኩ እስኪመስለኝ አደናግሮኛል፡፡ዕለት ዕለት እየኮሰመነ የኪነጥበብ ባለሞያዎቹን አሳጥቷቸው መሰለኝ፡፡ ግራቀኝ በከፍታ የተሰደሩት ተራራዎች በበረዶ ተሸፍነው ላያቸው አረንጓዴ ለብሷል ዛፎቹ በረዶው ላይ የበቀሉ ይመስሉ ነበር፡፡ መንገዱን ያለምንም ጥሩንባ እና ስጋት ተያይዘነዋል፡፡ ‹‹ይሄኔ ስንት አህያ እና ከብት በጥሩንባ አስደንብረን ከመንገድ እናስወጣ ነበር›› ስል ተቆጨሁ፡፡ የእኛ አገሮቹ ባለሥልጣኖች ከአገር ሲወጡ በየትኛው መንገድ ይኾን የሚጓዙት? እንደው ትንሽ እንኳን በሰው አገር አይቀኑም ? መቼም አንዴ ሥልጣኑን ከያዙት ምናለ ከሰው እኩል ቢደርጉን? ቢያንስ ለስማቸው ተገቢ መጠሪያ ያገኙ ነበር፡፡

መንገዱ አውቄ የረሳሁትን ኋላቀርነት አስታወሰኝ ‹‹የታሆ ናሽናል ፎረስትን›› ሳይማ በሰው አገር ደን እየተዝናናሁ ዓለሜን መቅጨት ትቼ በአገሬ ገዢዎች ብስጭት አልኩ፡፡ በተወሰነ መንገድ ርቀት ባሉ መውጫዎች (Exits) ጎዳናዎቹ ለመንገደኞች የተዘጋጁ ማረፊያዎች (Rest Areas) አሏቸው፡፡ የማረፊያ ቦታዎቹ ጽዳት እና ውበት በአግባቡ የተያዘ እንደኾነ ያስታውቃል፡፡ የተሟላ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ምግብ፣ቀዝቃዛ እና ትኩስ መጠጦች እንደልብ ይገኛሉ፡፡ አነስተኛ ሱፐርማርኬቶች የነዳጅ ማደያዎችም አሏቸው፡፡ ንጽሕናቸው የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት በማረፊያ ስፍራው በሚገባ የተካተቱ ነገሮች ናቸው፡፡ ማረፊያዎቹ በሁሉም የአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ አብዛኞቹ በመንግሥት ባለቤትነት እየተዳደሩ እንደሚገኙ ተመልክቻለሁ፡፡ ከዚህ ጉዞዬ በኋላ ከቦስተን ኒዩርክ - ዲሲ- ከዛም አትላንታ የተጓዝኩት በመኪና ነበር እና በሰው አገር መንገድ እስኪወጣልኝ ቀንቻለሁ፡፡

ከዋና ከተማ እጅግ በራቁት ‹‹ገጠራማ ስፍራዎች›› ሳይቀር የዋና መንገድ መውጫዎች እና ማረፊያዎች ለሚፈለገው ነገር መስተንግዶ ይሰጣሉ፡፡ ‹‹ገጠራማ ስፍራዎች›› የሚሉት እነርሱ እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ እንዴት እላለሁ፤እኔማ ገጠር ምን እንደሚመስል አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ያሉትን ማረፊያ ቦታዎች እንኳን በገጠር በከተማም አላውቃቸውም ፡፡ ሳክራሜንቶ እና ኦክላንድ በዚሁ መንገድ ላይ የሚገኙ በመኾናቸው እነሱንም ቃኘት እያደረግን በሳንፍራንሲስኮ እና በኦክላንድ መካከል የሚገኘውን በዓለም በርዝመቱ አንደኛ የተባለለትን የሳንፍራንሲስኮ - ኦክላንድ ቤይ ድልድይን (San Francisco–Oakland Bay Bridge) አቋርጠን አራት ሰዓት የሚፈጀው መንገድ ስምንት ሰዓት ፈጅቶብን ከምሳ በኋላ ወደ ተቃጠለችው አገር ሳንፍራንሲስኮ ደረስን፡፡ ኦክላንድ ቤይ እ.ኤ.አ በ1936 ዓ.ም በመሠራቱ ሳፍራንሲስኮ የሚገኘውን ‹‹ጎልደን ጌት›› የተሰኘውን ድልድይ በስድስት ወር ዕድሜ ይበልጠዋል፡፡

የሁለቱም አሠራር እና መሐንዲሶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ውበታቸውም ከዐይኔ ልክ በላይ ኾኖብኛል፡፡ ለወሬ እንዲመቸኝ ስልም ከመላው ዓለም መጥተው መንገዱን ካጨናነቁት ቱሪስቶች ጋር እየተጋፋሁ በጎልደን ጌት ድልድይ ላይ ቆሜ ፎቶ ማንሳትና መነሳት ጀመርኩ፡፡ ግን ብዙም አልዘለኩበትም፡፡ የጠርዙ መጨረሻ የት እንደኾነ የማይታየው ሐይቅ ላይ አፈጠጥኩ፡፡ ዙሪያውን በውሀ ተከቦ መሀል ለመሀል ጉብ ካለው እስር ቤት በስተቀር በሐይቁ ላይ የሚታይ ነገር የለም፡፡ ይህንን ውብ ድልድይ ከቤታቸው አሻግረው እያዩ ለመዝናናት ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ታሪካዊ ቤት ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገዝተው ሙሉ ለሙሉ በማፍረስ እንደገና ሠርተው ‹‹አሁን በደንብ ታየን›› በማለት የብዙሀን መገናኛ ቀልብ ስበው የነበሩትን ባለሀብቶች ታሪክ አስታወሰኝ፡፡ እኔም ባገኘሁት ዕድል ተጠቅሜ ምስሉን ለዘመናት በአይምሮዬ ለማስቀመጥ እየተዟዟርኩ ትክ ብዬ አየሁት፡፡በእውነት ያምራል፡፡ ድልድዩ ላይ ቆሜ ከርቀት የምትታየኝ የሳንፍራንሲስኮ ከተማ ውበትም ከሩቅ ይጣራል፡፡ችምችም ያሉ የሚመስሉት የከተማዋ ሕንጻዎች በአንድ ላይ አብረው ያጓጓሉ፡፡ ሰዓቱ ወደ ምሽት እየገፋ ቢሆንም ምሳ ለመብላት ወደ ከተማው መንገድ ጀመርን በአስጎብኚዎቼ ምርጫ እስር ቤቱ ከቅርበት ወደሚታይበት የቱሪስቶች መናህሪያ ‹‹ፒሮች›› ተጓዝን፡፡ ቢኒ የተባለ ዘመዴን ባገኘኹት ክፍተት ለማግኘት እዛው አካባቢ ቀጠርኩት እኛም ወደዛው ጉዞ ጀምርን፡፡

************* የተለያየ ቁጥር የተሰጣቸው ‹‹ፒሮች›› የሚገኙበት የአሳ ዘር ሁሉ በተለያየ መልክ ተሠርቶ የሚሸጥበት ምግብ ቤቶች የሚገኝበት አካባቢ የነበረው ግርግር እና የሰው ብዛት አሜሪካ ውስጥ እኔ ካየኹት ሁሉ የላቀውን ቦታ ይይዛል፡፡ ምግቡ የሚገዛው በግፊያ ነው፡፡ ቤቶቹ ሰዉን የማስተናገድ አቅማቸው አነስተኛ ስለኾነ ሰዉ ውጭ ላይ ባለው ሰፊ መዝናኛ ቦታ ባገኘበት ተቀምጦ እና ቆሞ ይመገባል፡፡ በየቦታው የተለያዩ ትርኢቶች ይታያሉ፡፡ ጎዳና ላይ ተሰጥተው በሙሉ የሙዚቃ መሳሪያ ሙዚቃ እየተጫወቱ ገንዘብ የሚሰበስቡ ወጣቶችን ተመልክቼ አገሬ ቢኾን በሙሉ ባንድ ሂሳብ ቢያንስ ተከራይቶ ስንት እና ስንት ገንዘብ ሊያመጣ እንደሚችል አሰላሁት፡፡ የቦታው ግር ግር ሰላም ይነሳል፡፡ እንዲያ ከሩቅ ያጓጓችኝ ከተማም ቀርቤ ሳያት እምብዛም ኾነችብኝ፡፡ በኤሌትሪክ ለሚሠራው የከተማ አውቶብስ ተብሎ የተሰቀለው ሽቦም ለልብስ ማሽጫ የተዘጋጀች አገር አስመስሏታል፡፡ ወዳጄ ቢኒን ካገኘኹት በኋላ ይህንኑ ትዝብቴን ስነግረው ‹‹በርግጥ ከተማዋ ግርግር ናት፡፡

ይኼ አካባቢ ደግሞ ቱሪስቶች ስለሚበዙበት በጣም ይጨናነቃል እንደውም ዛሬ አነስተኛ የሚባል ሰው ነው ያለው›› አለኝ፡፡ ገና ምኑንም ሳላይ መደምደም እንደሌለብኝ መከረኝ፡፡ መንገዶቿ የተጣበቡ መኾናቸውን አምኖልኝ እርሱ ግን ከተማዋን ከመልመዱ የተነሳ ከሳንፍራንሲስኮ ውጪ አገር ያለ እንደማይመስለው ነገረኝ፡፡ ከተማዋን ከእነ ችግሮቿ ወዷት ይኖራል፡፡ ‹‹ሥራም እንደልብ ይገኝባታል›› አለኝ እርሱ ለሚሠራው የታክሲ ሥራ ምቹ ናት፡፡ ቢኒ በምቾት ወሬ ጀምሮ በቤት ችግር የጭንቅ ወሬ አላስበላ አለኝ፡፡ ‹‹አይ አሜሪካ መች አሟልታ ትሰጣለች›› አልኩ፡፡ ቤት በረከሰበት ቦታ ሥራ እንደልብ አይገኝም፡፡ ሥራ ባለበት ደግሞ ቤት፡፡ ሁለቱም በተሟላበት ደግሞ ቢሉ በርከት ብሎ ይመጣል፡፡ የጎበዙት ጠንክረው በመማር እና በመሥራት ሁሉንም አሸንፈው ይኖራሉ፡፡ ቢያንስ እነርሱ ቢያጡ እንቅልፋውን ነው፡፡ ቢኒ በሌሎች ከተሞች እስከ 800 ዶላር ሊገኝ የሚችል ቤት በ2500 ዶላር እኳን አጥተው ፍለጋ ላይ መኾናቸውን ነገረኝ፡፡

ቤት የቤተሰቡ ዋና ችግር ኾኗል፡፡ካሉበት ቤት መቀየር ፈልገው ማሰስ ከጀመሩ አንድ ወር አልፏቸዋል፡፡ ግን ማግኘት አልቻሉም ቢኒ ምርር ብሎት ስለቤት ችግር ሲያወራኝ እንደዛ ያስፈነደቀኝን ያንን ሁሉ የመንገድ፣ የድልድዮች እና የሐይቅ ውበት ረስቼ አገሬ አዲስ አበባ የተመለስኩ መሰለኝ፡፡ በየጊዜው የሚጨምረው የቤት ኪራይ ዋጋና ቤት ፍለጋ ያለው ውጣ ውረድ ትዝ ብሎኝ ትክዝ አልኩ፡፡ ምናለ ባያስታውሰኝ ፡፡ ግን ቢኒ ምርጫ አለው፤ እንደነገረኝ አብዛኛው ሰው ከተማ ውስጥ እየሠራ ከከተማው ወጣ ብሎ ይኖራል፡፡ እንደሱ ማድረግም ይችላል፡፡እርሱ ለሥራው በጣም የሚመቸውን ፈልጎ ነው፡፡ ሥራው ቀዝቀዝ ወዳለበት ቦታ ቢሄድ ደግሞ ቤት በቅናሽ ያገኛል፡፡ እኛ አዲስ አበባ ካጣን የት እንሄዳለን? እንደነሱ ወጣ እንዳንል የት? ወደተገኘበት ወጣ እንበል ብንልስ እንኳን የውጭውን የውስጡንም የትራንስፖርት ችግር አልተቋቋምነው፡፡ ያውም የቤቶቹ ደረጃ ማለካኪያም የለው፡፡

እንዳው ያየሁትን ኹሉ ከአገር ጋር ማነጻጸር ምን አመጣው ስል ራሴን ወቀስኩት፡፡ ኑሮውን በአሜሪካ የሚያደርግ ሰው የመጀመሪያው ችግር ቤት ነው፡፡ የችግሩ መጠን ግን ከከተማ ከተማ እና ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ እንደሄደ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከትዳር አጋሩም ጋር ተጋግዞ ይሁን ለብቻው ቢከራይ በየወሩ ሊያወጣ የሚችለውን ወይም ትንሽ ጨምሮ በረጅም ዓመት በሚያልቅ ክፍያ በባንክ ብድር ቤት ገዝቶ የሚኖረው ሰው ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ካየሁት እና ከሰማሁት ተረድቻለሁ፡፡

በትምሕርት፣በሥራ አሊያም በተለያዩ ምክንያቶች እንደሄደ በቀላሉ ቤት ከሚያገኘው ሰው ውጪ የአብዛኛው ለፍቶ አዳሪ የመጀመሪያ የኑሮ ገጠመኝ በቤት ኪራይ ውድነት መማረር ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞች ባየኋቸው የኢትዮጵያውያን ሱቆች ውስጥ እና ሱቆቹ ባሉበት አካባቢ የተለጠፉት ማስታወቂያዎች ከ70 በመቶ በላይ ይዘት፤ “ሩም ሜት አፈልጋለሁ በእንደዚህ ያለ አድራሻ ላይ አንድ መኝታ ቤት የሚፈልግ ካለ ይደውልልኝ”፣ “ሩም ሜት እፈልጋለሁ አንድ ልብስ ማጠቢያ ማሽን በጋራ መጠቀም እንችላለን የሚፈልግ ካለ”፣ ‹‹ሩም ሜት የሚያጋራኝ ካለ መኝታ ቤት ብቻ››፣‹‹ውሃ፣መብራት፣ኢንተርኔት፣ልብስ ማጠቢያ ማሽንን በተሟላለት ቤት አንድ መኝታ ቤት አለኝ ሩም ሜት የሚፈልግ ካለ በዚህ ቁጥር ይደውልለኝ››፣ ‹‹የመኪና ማቆሚያ ቁጥር ያለው ጊቢ ውስጥ ያለ ቤት ነው ሩም ሜት የሚፈልግ ካለ››፣‹‹ሳሎን ቤቴን ማከራየት እፈልጋለሁ›› የሚል ነው፡፡ ማስታወቂያዎቹ ለተዳብሎ መኖር ፈላጊዎች በርካታ አማራጮችን የሚሰጡ ናቸው፡፡ የክፍሎቹ ዋጋ እንደ አገሩ እና ሰፈሩ የለያየ ነው፡፡ ውድ የሚባል ሰፈር እዳለው ሁሉ ረከስ ያለውም አለ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ውድ በሚባል አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቂቶቹ ካልኾኑ ተዳብለው አይኖሩም፡፡ የቤት ችግር በጣም የባሰባቸው ደግሞ ባለ አንድ መኝታ ቤት ውስጥ በአንድ ክፍል ሁለት አልጋ ዘርግተው ለአራት እና ለአምስት ይኖራሉ፡፡ በአንድ ክፍል ስቱዲዮ ውስጥም ለሁለት የሚኖሩ አሉ፡፡ እንደነገሩኝ ከኾነ ለጎበዞች ይህ ጊዜያዊ ችግር ነው፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ ከአንድ በላይ ደባል ጋር መኖር ከሚያተርፈው ገንዘብ ይልቅ አስቸጋሪነቱ ይብሳል፡፡ አንዲት ወዳጄ ዲሲ ውስጥ አምስት ሆነው ሲኖሩ የተረፋቸውን ምግብ በፕላስቲክ ሰሀን ከተው ስም ጽፈውበት ካልሄዱ ተመልሰው ማግኘት ይቸግራቸው እደነበር አጫውታኛለች፡፡ ይህ ደግሞ ካለው ጊዜ አንጻር ለመሥራት ስለማይመች እርስ በርስ ግጭት እንዳይፈጠር ስም ጽፎ መሄድን እንደመፍትሄ ይጠቀሙበት ነበር፡፡

አሪዞ-ፊኒክስ ውስጥ አንድ ሙሉ ቤት ለአምስት ተከራይተው ሲኖሩ ያጋጠሙኝ ኢትዮጵያውያን፤ እርስ በርስ ተከባብረው ተራቸውን ጠብቀው ቤት እያጸዱ፣በጋራ በሚገዙት አስቤዛ በተራ ምግብ እየሠሩ ለስድስት ዓመታት ያህል ከጸብ ውጭ ሆነው የኖሩ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ሁለቱ ለትዳር መፈላለጋቸውን ይፋ በማድረጋቸው ሌሎቹ ቤቱን ለቀው ወጥተውላቸው እርስ በእርስ ቤተሰብ ኾነው ይኖራሉ፡፡ ይህን የነገርኳቸው ሌሎች ደግሞ እንዲህ ያለው ነገር በዕድል የሚሳካ እንደሆነ አጫውተውኛል፡፡

************ እንደ ዕድልም ይሁን አጋጣሚ አሊያም እኔው እራሴ እየፈለኳቸው ኢትዮጵያ እያሉ የማውቃቸው እና የማላውቃቸው በዋናው በር ወጥተው በዋናው በር በኩል የገቡ ወይም እንደ ኬንያ፣ግብጽ እና በደቡብ አፍሪካ እና በሌሎች ከተሞች አድርገው አሜሪካ የገቡ በተለያየ የትምሕርት እና የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ዘመድ ጓደኞቼን አግኝቼ አሜሪካ እንዴት እንደተቀበለቻቸው እያመሰገኗትም እያማረሯትም አውግተውኛል፡፡ በፖለቲካ ምክንያት በመንግሥት ተሳደው በድንገት ከአገር ከወጡት ውጪ በፍላጎታቸው ከገቡት አብዛኞቹ አሜሪካ ገብተው የቤት ችግር ይገጥመናል የሚል ቅንጣት ስጋት አልነበራቸውም፡፡ በሌሎች አገራት የመረረን ስደት ቀምሰው፣ሥራቸውን ጥለው፣ንግድ ቤታቸውን ዘግተው፣በርካታ ገንዘብ ከፍለው፣ትዳራቸውን ልጆቻቸውን ጥለው በተዛባ መረጃ ወይም ያለምንም መረጃ ኑሯቸውን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ አሜሪካ ሲገቡ ከኢትዮጵያ አየር ጠባይ ጋር ከማይመሳሰለው በተለያየ ጊዜ ከሚቀያየረው አየር ጸባይ ጀምሮ የቤት ችግር፣መኖሪያ ፈቃድ የማግኘት ጣጣ፣የሥራ እጦት፣ድጎማ የሚጠብቀው አገር ቤት የሚገኘው ቤተሰብ እና ሌሎች በርካታ ችግሮች ተደማምረው ‹‹አዕምሮ ያናውዛል›› ይላሉ፡፡ ‹‹አሜሪካን ረጋ ብለው ዘዴኛ ካልኾኑባት ትሸውዳለችም›› ይሏታል፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4705 times