Saturday, 16 March 2013 12:05

“ሀገር ፍቅር” በመብራት ምክንያት የተቋረጠው ትያትር ሊቀጥል ነው

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(6 votes)

የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በመብራት መቋረጥ ምክንያት ትያትር ካቋረጠ ሁለት ወር ሊሞላው ነው፡፡ ትያትር ቤቱ መብራቱን ቶሎ ባለማስጠገኑ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትያትር ተመልካቾች እየተመለሱ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመድረክ ግብአትነት ተገዝተው የነበሩ መብራቶች ሥራ ላይ ባለመዋላቸው የመንግስት ንብረት እየባከነ መሆኑን የትያትር ቤቱ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በተለመደው መርሃ ግብር በሳምንት ዘጠኝ ትያትሮች የሚያሳየው ሀገር ፍቅር፣የግል ኢንተርፕራይዞች በዋጋ ጭማሪ አለመደረግ ምክንያት ትያትር ማሳየት በማቆማቸው በሳምንት አምስት ትያትር እያሳየ ቢቆይም መብራት ተበላሽቶ ባለመጠገኑ ትያትር ማሳየት ከነአካቴው ለማቋረጥ ተገዷል፡፡

የተበላሸውን የትያትር ቤቱን መብራት ለማስተካከል ጨረታ የወጣ ቢሆንም እስካሁን ውጤት እንዳላመጣና ሰሞኑን ግን አዳዲስ የመብራት መሳርያ መተከሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀላሉ ሊጠገን የሚችል ግብአተ ኤሌክትሪክ ባለመሰራቱ መንግሥት ከፍተኛ ገቢ አጥቷል የሚሉ ምንጮች፣ ተመልካቾችም ያለአግባብ መንገላታታቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ የትያትር ቤቱን የሥራ ሃላፊዎች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በመብራት፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ በእድሳት ምክንያት ሥራ በማቋረጣቸው በብቸኝነት ትያትር እያሳየ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር እንደነበር ታውቋል፡፡

Read 5185 times