Print this page
Saturday, 16 March 2013 13:47

በሻምፒዮንስ ሊጉ የእንግሊዝ ክለቦች የበላይነት አክትሟል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

58ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍፃሜ ምእራፍ ሲሸጋገር የውድድሩ የሃይል ሚዛን እንግሊዝን ሸሽቶ ለስፔንና ጀርመን ክለቦች እያጋደለ መምጣቱ ተረጋገጠ፡፡ ዘንድሮ ለሩብ ፍፃሜ የበቁት ስምንት ክለቦች ከአምስት አገራት የተውጣጡ ሲሆኑ ፤ ሶስቱ የስፔን ክለቦች ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና ማላጋ፤ ሁለት የጀርመን ክለቦች ባየር ሙኒክና ቦርስያ ዶትመንድ እንዲሁም የጣሊያኑ ጁቬንትስ፤ የቱርኩ ጋላታሰራይ እና የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዠርመን ናቸው፡፡

ከ17 አመታት በኋላ የእንግሊዝ ክለቦች ሳይወከሉ ቀርተዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ባለፉት 13 አመታት በነበሩት የውድድር ዘመናት የጣሊያን ክለቦች በ2001፣ በ2002 እና በ2009 እኤአ፤ የጀርመን ክለቦች በ2003፣ በ2004 እና በ2008 እኤአ፤ የስፔን ክለቦች በ2005 እኤአ በሩብ ፍፃሜ ለመግባት አልሆነላቸውም ነበር፡፡ የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር የእንግሊዝ ክለቦች የበላይነት በስፔን ላሊጋ እና በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች እየተሸረሸረ መምጣቱን እንደሚያሳይ ሲናገሩ ፤ የሪያል ማድሪዱ ጆሴ ሞውሪንሆ በበኩላቸው የእንግሊዝ ክለቦች ከአውሮፓ እግር ኳስ ሃያልነት ርቀዋል ለማለት ጊዜው ገና ነው ብለዋል፡፡

ለዋንጫው ድል ሁለቱ የስፔን ክለቦች ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና ከፍተኛ ግምት ሲኖራቸው የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ተፎካካሪ ነው፡፡ የቱርኩ ክለብ ጋላተሳራይ በቀድሞ ክለባቸው የሻምፒዮንስ ሊግ ድልን ያጣጣሙትን አንጋፋዎቹን ዲድዬር ድሮግባ እና ዌስሊ ስናይደርን በመያዝ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለሩብ ፍፃሜ ስለበቃ ስኬታ ተብሏል፡፡ የጀርመኑ ቦርስያ ዶርትመንድ በአስደናቂ የቡድን መንፈሱ፤ የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዠርመን በተጠናከረ አቅሙ እንዲሁም የጣሊያኑ ጁቬንትስ በጠንካራው የተከላካይ መስመሩ ለዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ማራኪ ገፅታ እንዳላበሱ ተወስቶላቸዋል፡፡ የጣሊያኑ ጁቬንትስ ከ7 አመታት በኋላ፤የጀርመኑ ቦርስያ ዶርትመንድ ከ15 አመታት በኋላ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዠርመን ከ18 አመታት በኋላ ለሩብ ፍፃሜ መብቃታቸው ነው፡፡

ባለፉት ሶስት አመታት በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲደበዝዝ የቆየው የእንግሊዝ ክለቦች ተፎካካሪነት ዘንድሮ በጥሎ ማለፍ ምእራፍ ማብቃቱ የፕሪሚዬር ሊጉ የበላይነት ሙሉ ለሙሉ ማክተሙን አሳይቷል፡፡ እንግሊዝን በመወከል ተሳታፊ ከነበሩት 4 ክለቦች መካከል ማን ሲቲ እና የአምናው የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ቼልሲ የተሰናበቱት ከምድብ ማጣርያው ነበር፡፡ ማን ዩናይትድና አርሰናል ደግሞ ሩጫቸው በጥሎ ማለፍ ምእራፍ አብቅቷል፡፡ ዘ ጋርዲያን በሰራው አሃዛዊ ስሌት መሰረት በዘንድሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የእንግሊዝ ክለቦች አሸናፊነት በአራተኛ ደረጃ የሚመደብ ሆኗል፡፡ በአሸናፊነት ግንባር ቀደም የሆነው የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ54 በመቶ ውጤታማነቱ ነው፡፡ የስፔኑ ላሊጋ በ53 በመቶ ፤የጣሊያን ሴሪኤ በ50 በመቶ ውጤታማነታቸው ተለክቷል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ውጤታማነት በ39 በመቶ ዝቅተኛው ነው፡፡ የጋርድያን ዘገባ እንዳመለከተው የእንግሊዝ ክለቦች ዘንድሮ ባሳዩት ድክመት በሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ ኮታ ላይ ቅናሽ እንዲመጣባቸው ሊያደርግ ይችላል፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለሊጎች በሚሰጥ የተሳትፎ ኮታ ወቅታዊ ደረጃ የስፔኑ ላሊጋ በ85.882 ነጥብ የመጀመርያ ደረጃ ይዟል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ79.82 ሁለተኛ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ76.75 ሶስተኛ እንዲሁም የጣሊያን ሴሪኤ በ63.4 ነጥብ አራተኛ ላይ ናቸው፡፡ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በዚሁ የሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ ኮታ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ወደ 3ኛ ደረጃ መውረዱ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ለእንግሊዝ ክለቦች ለሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ቀጥታ ተሳትፎ የነበረው የአራት ክለቦች ኮታ ወደ ሶስት ይወርዳል ተብሏል፡፡ ዴይሊ ቴሌግራፍ በሰራው ዘገባ ደግሞ የእንግሊዝ ክለቦች ከሻምፒዮንስ ሊጉ ጥሎ ማለፍ በመሰናበታቸው ለሩብ ፍፃሜ ፤ለግማሽ ፍፃሜ እና ለዋንጫ ጨዋታ በመድረስ በነፍስ ወከፍ እስከ 35 ሚሊዮን ፓውንድ የገቢ ድርሻም አጥተዋል፡፡

ከሻምፒዮንስ ሊጉ ጥሎ ማለፍ የተሰናበተው ማን ዩናይትድ በተሳትፎው እስከ 34 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያገኝ በተመሳሳይ ምእራፍ የቀረው አርሰናል እስከ 29.7 ሚሊዮን ፓውንድ ይኖረዋል፡፡ በምድብ ማጣርያው የተሰናበቱት የአምናው ሻምፒዮን ቼልሲ እስከ 29.4 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም ማን ሲቲ 27.8 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ እንደሚኖራቸውም የዴይሊ ቴሌግራፍ ስሌት አመልክቷል፡፡

Read 3829 times
Administrator

Latest from Administrator