Saturday, 23 March 2013 13:23

የቤተሰብ እቅድ ዘዴ እና የምእተ አመቱ የልማት ግቦች....››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(1 Vote)

እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2000/ ዓመተ ምህረት ሲገባ እስከ 2015/ዓም ድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መንገዶች ሊሻሻሉ ይገባሉ በተባሉ የጤናና የልማት መርሀ ግብሮች ላይ 193/ አንድ መቶ ዘጠና ሶስት የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት እንዲሁም ወደ 23/ሀያ ሶስት የሚሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች እርምጃ መወሰድ ይገባዋል ከሚል ስምምነት ደርሰዋል፡፡ ነጥቦቹም ስምንት ሲሆኑ አንባቢዎች ታስታውሱአቸው ዘንድ እንደሚከተለው አስፍረናቸዋል፡፡ 1/ Eradicating extreme poverty and hunger, =የከፋ ድህነትንና ረሃብን ማስወገድ ፣ 2/ achieving universal primary education,

=በአለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ፣ 3/ promoting gender equality and empowering women, = የጾታ እኩልነትን ማስፈን እና የሴቶችንም አቅም መገንባት፣ 4/ reducing child mortality rates, = የህጻናትን ሞት መቀነስ፣ 5/ improving maternal health, = የእናቶችን ጤና ማሻሻል፣ 6/ combating HIV/AIDS, malaria, and other diseases, = ኤችአይቪ ኤይድስ ወባ እና ሌሎች በሽታዎችን መከላከል ፣ 7/ Ensuring Environmental sustainability, and = ቀጣይነት ያለው የአካባቢን ጥበቃ ማረጋገጥ እና 8/ Developing a global partnership for developments, =

በአለም አቀፍ ደረጃ ለልማት በጋራ መቆም ወይንም ህብረትን ማጠናከር፣ በእርግጥ አሁን እንደኤሮፓውያን አቆጣጠር 2013/ዓ/ም ላይ የደረስን ሲሆን የምእተ አመቱ ግብ ሊጠናቀቅ ሁለት አመት ይቀረዋል፡፡ ጊዜው ሲደርስም አለም አቀፉ ድርጅት ምን ያህሉ ግቡን እንደመታና ምን ያህሉ እንዳልተሳካ ይገልጻል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ምናልባትም ቀጣይ እርምጃ ይኖር ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል በተለይም በአራተኛውና በአምስተኛው ተራ ቁጥር የተጠቀሱት የህጻናትን ሞት መቀነስና የእናቶችን ጤንነት ማሻሻል እንዲሁም የኤችአይቪ ስርጭትን መከላከል የሚሉት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከሚሰራባቸው የስራ መስኮች መካከል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 21ኛ አመታዊ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ቀርበው ከነበሩት ጥናታዊ ጽሁፎች አንዱ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ እና የምእተ አመቱ የልማት ግቦች የሚል ነበር፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት ዶ/ር ሰሎሞን ኩምቢ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ ዶ/ር ሰሎሞን ኩምቢ እንደገለጹት የቤተሰብ እቅድ ዘዴን አጠቃቀምና የምእተ አመቱን የልማት ግቦች በማያያዝ በተደረገው ጥናት አገልግሎቱን መጠቀሙ እንደሰብአዊ መብት የሚቆጠር መሆኑን ይጠቁማል ፡፡ በኢትዮጵም በሕገመንግስቱ በአንቀጽ 35/ ላይ እናቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚመጣን ችግር ለማስወገድ የቤተሰብ ምጣኔን ለመጠቀም መብት አላቸው ይላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መረጃና አቅም የማግኘት መብት እንዳላቸውም የኢትዮጵያ ሕገመንግስት ይገልጻል፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለአንድ ቤተሰብ ወይንም ግለሰብ የሚሰጣቸው ጥቅሞችም አሉት፡፡ ጥቅሞቹም የጤና ፣የህብረተሰባዊ እና የኢኮኖሚ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ለምሳሌ የጤና ጥቅም አለው ሲባል ወሊድን መመጠን ከሚለው ብቻ ሳይሆን ካንሰርን ፣መቆሽሽን ወይንም ኢንፌክሽንን ፣በወር አበባ ጊዜ ሕመምን መቀነስ እና በተለይም የወር አበባ በሚታወቅ ጊዜ እንዲመጣ ማስቻሉ የአገልግሎቱን ጠቀሜታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ * የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከኢኮኖሚ አንጻር መመልከት ማለት ከምእተ አመቱ የልማት ግቦች በመጀመሪያው ላይ ከሚታየው ድህነትን መቀነስ ረሀብን ማስወገድ ከሚለው እሳቤ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ቤተሰብ በእቅድ ላይ ከተመሰረተ እና የቤተሰቡን መጠን ከወሰነ ለቤተሰቡ በሚያቀርበው ሀብት በበቂ ሁኔታ ለማስተዳደር ያስችለዋል፡፡ * ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ ተጠቃሚ በሚሆኑበት ጊዜ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል፡፡

አንዲት ሴት ትምህርቷን ከቀጠለች የተሻለ ስራ በመስራት ገቢዋም በዚያው መጠን ሊያድግ የሚችልበት መንገድ ሊመቻች እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ከምእተ አመቱ የልማት ግቦች 2ኛውን ተራ ቁጥር ስንመለከት ትምህርትን ማዳረስ የሚል ሲሆን የወሊድ መቆጣጠሪያን መጠቀም ትምህርትን በተገቢው መንገድ ለማጠናቀቅ ያበረታታል ፡፡ * ሶስተኛውን የምእተ አመቱን የልማት ግብ ስንመለከት ሴቶች ትምህርት በመማራቸው በኢኮኖሚም እየበለጸጉ መምጣት እንዲሁም የጾታ እኩልነታቸውን ማስከበር በውሳኔ ሰጭነት ከቤታቸው ጀምረው በተለያዩ ደረጃዎች እንዲሳተፉ ያስችላቸዋል፡፡ ፖሊሲን በመንደፍና በማጽደቅ ረገድም የበኩላቸውን እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ሴቶች የወሊድ መከላከያን በተጠቀሙ ቁጥር ከቤተሰብ ብዛት አንጻር ሊፈጠር የሚችለውን ጫና በመቀነስ ከባሎቻቸው ጋር በመነጋገር ፣መረጃን በማግኘት የተሻለ ሕይወትን ለመምራት አይቸገሩም፡፡

ከጋብቻ በፊትም ወሊድ እንዳይኖር ፣ጎጂ ባህሎችን ለማስወገድ፣ ከጋብቻም በሁዋላ ተገቢውን እርቀት በመጠበቅ እና የወሊድ መጠንን በመወሰን ሕይወትን በተሻለ መንገድ ለመምራት ያስችላል፡፡ ዶ/ር ሰሎሞን በስብሰባው ላይ ከጠቀሱት ነጥብ አንዱ (Contraceptive prevalence rate) እድሜያቸው የግብረስጋ ግንኙነት ለመፈጸም የደረሱና መውለድ እድሜ ውስጥ ያሉ (15-19) ምን ያህሎቹ የወሊድ መቆጣጠሪጠያን ይጠቀማሉ አይጠቀሙም የሚለውን የሚመለከት ነበር፡፡ ከተለያዩ አገሮች ልምድም ከመቶኛው ሲሰላ በእኛ ሀገር ተጠቃሚዎቹ 29ሺህ ሲሆኑ ዘመናዊ ውን የወሊድ መከላከያ የሚጠቀሙት ግን 27 ሺህ ያህል ናቸው፡፡

ይህንን ከአለምአቀፋዊው ገጽታ ጋር ስናገናዝበው ወደ ግማሽ ያህል ዝቅ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌም የአለም አቀፉን ስሌት ስንመለከት በ1990 ዓ/ም ወደ 51 ሺህ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 60 ሺህ ይደርሳልለ፡፡ ነገር ግን ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ወደ 22.7 % ሲሆን የወሊድ መቆጣጠሪያን በመጠቀም ረገድ ኢትዮጵያ ከአለም ህብረተሰብ በግማሽ ያህል ዝቅ ያለች ናት ቢባልም ከሰሀራ በታች ካሉት ሀገራት ግን የተሻለች መሆኑዋን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ስሌቱ በጥቅል ሲታይ እንጂ ከሰሀራ በታች ካሉ እንደ ኬንያ፣ ማላዊ ካሉት ሀገሮች አሁንም ኢትዮጵያ ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኑዋ እሙን ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር መጠቀም ፈልገው ነገር ግን ያልቻሉትን (Unmeet Need) በልጦ ተገኝቶአል፡፡

የምእተ አመቱን የልማት ግቦች በሚመለከት በአራተኛ ደረጃ ከተቀመጠው የህጻናትን ሞት መቀነስ ጤንነታቸውን መታደግ የሚል ሲሆን ከዚህ አንጻር የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ከ10 እስከ 40ኀ የሚሆኑ ሕጻናትን ጤንነትን መጠበቅ ወይም ከሞት ማዳን ያስችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በአለፉት አስራ ሁለት አመታት ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ አመት በታች ያሉ 1.4 ሚሊዮን ያህል ሕጻናት ሞተዋል፡፡ አለምአቀፋዊ ጥናቶች እንደሚያስረዱት በትክክለኛው ሁኔታ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ቢቻል ኖሮ ከ144 ሺህ እስከ 570 ሺህ የሚሆኑ ሕጻናትን ሞት መቀነስ ይቻል ነበር ፡፡

ከምእተ አመቱ የልማት ግቦች በአምስተኛ ተራ ቁጥር የተቀመጠው የእናቶችን ጤንነት ከማሻሻል ጋር የተያያዘ ሲሆን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አንዱ ለእናቶች ጤና አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተገልጾአል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ እስከ 2012/ዓ/ም ድረስ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ቢቻል የእናቶችን ሞት ከ20-44 ኀድረስ መቀነስ ይቻላል ፡፡ ባለፉት 12/ አመታት ውስጥ በተካሄደው ጥናት እንደተረጋገጠው ግን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሁሉም ቦታ በትክክል ባለመዳረሱ በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ እሩብ ሚሊዮን የሚሆኑ እናቶች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

አገልግሎቱ እንደሚፈለገው ተዳርሶ ቢሆን ኖሮ ግን የእናቶችን ሞት ከ57/ሺህ እስከ 114/ሺ ድረስ ዝቅ ማድረግ ይቻል ነበር ዶ/ር ሰሎሞን ኩምቢ በጥናት ጽሁፋቸው እንዳመለከቱት፡፡ በስተመጨረሻም ዶ/ር ሰለሞን ለመፍትሔው ካስቀመጡአቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ *ህብረተሰቡ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚሰጠውን ጥቅም ተረድቶ በተግባር እንዲያውል፣ *ማህበራት የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለወሊድ ፣ መቆጣጠሪያ አገልግሎት መስፋፋትና ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ፣ *የወንዶችን ተሳታፊነት ማጎልበት፣ *የጤና ባለሙያው አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያበቃው እውቀትና ችሎታ እንዲኖረው ማድረግ ፣ *ፖሊሲዎች ፣ፕሮግራሞች፣ ፕሮጀክቶን ምን ለውጥ አመጡ ከሚል ምርምርና ስርጸት ማካሄድ እና በተሻሻለ ሁኔታ ተግባሩን ማከናወን... አስፈላጊ ነው፡፡

Read 4807 times