Print this page
Monday, 25 March 2013 11:09

ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ የ3ጂ ፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ኢትዮ ቴሌኮም ከሲ.ዲኤም.ኤ እና ከኢ.ቪ.ዲኦ ቀጣይ የሆነውን ሦስተኛ ትውልድ ፈጣን የ3ጂ ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡የ3ጂ ፈጣን ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት የቀረበው ለሦስት የአገልግሎት ዐይነት ተጠቃሚዎች ሲሆን ለ1GB ከተጨማሪ 150 ሜጋ ቢት ልዩ ጥቅም ጋር በ400 ብር፣ ለ2GB ከተጨማሪ 200 ሜጋ ቢት ልዩ ጥቅም ጋር በ600 ብር እንዲሁም 4GB ከተጨማሪ 350 ሜጋ ቢት ልዩ ጥቅም ጋር በ800 ብር ወርሃዊ ክፍያ ጥቅም ላይ እንደሚውል ኢትዮ ቴሌኮም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ከመጋቢት 12 ቀን 2005 ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን የገለፀው ድርጅቱ በቅድመና በድህረ ክፍያ መጠቀም ለሚፈልጉም አገልግሎቱ በምርጫ ቀርቧል፡፡ደንበኞች ከመጋቢት 12 እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ባለው የአንድ ወር የማስተዋወቂያ ጊዜ አገልግሎቱን መጠቀም ከጀመሩ ለማስጀመሪያ ከተቀመጠው የመቶ ብር ክፍያ ነፃ ሆነው መጠቀም እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡ ባለ ከፍተኛ ፍጥነት እንደሆነ የተነገረለት አዲስ የ3ጂ ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎቱን በድህረ ክፍያ ለማግኘት ለሚፈልጉ ደንበኞች የአገልግሎቱ ክፍያ የሚፈፀመው በወር መጨረሻ ላይ ሲሆን ከተመደበው የጥቅል አገልግሎት በተጨማሪ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ደንበኞች በተጠቀሙት የፍጆታ መጠን በመደበኛው የአገልግሎት ክፍያ መሰረት በሜጋ ቢት 46 ሳንቲም የሚከፍሉ መሆኑን መግለጫው አብራርቷል፡፡

የ3ጂ ዳታ ወይም ኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ በ3ጂ ዶንግል ከሆነ 799 ብር እንዲሁም በዋይፋይ ራውተር ከሆነ 1529 ብር የሚጠይቅ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በቅድመ ክፍያ ጥቅል አገልግሎቱን መጠቀም ለሚፈልጉ ደንበኞች የማስደወያ ካርድን በመጠቀም ሂሳቡን መሙላት የሚኖርባቸው ሲሆን በጥቅም ላይ ያልዋለ የቅድመ ክፍያም ሆነ የድህረ ክፍያ የጥቅል ኢንተርኔት ወይም ዳታ አገልግሎት ወደሚቀጥለው ወር የማይተላለፍ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም፤ አዲሱ 3ጂ አገልግሎት ከነባሩ የሚለየው ቀድሞ ሥራ ላይ የነበረው 3ጂ ሲም ካርድ የዳታና የድምፅ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አዲሱ 3ጂ ግን የሚሰጠው የዳታ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ አዲሱ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑም በመሆኑ ከኢ.ቪ.ዲኦ ጋር የፍጥነት ልዩነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የሞባይል ኢንተርኔትና ሲ.ዲኤም.ኤ ኔትወርክ በማይሠሩበት፣ የ3ጂ ሲምካርድ እና ኢ.ቪዲኦ በኔትወርክ መንቀራፈፍ ደንበኞች በኢትዮ ቴሌኮም ላይ በሚማረሩበት ወቅት አዲስ አገልግሎት የመጀመሩ ፋይዳ ምንድነው? የችግሩስ መንስኤ ምንድን ነው? በሚል የተጠየቁት አቶ አብዱራሂም፤ ለኔትወርክ መቋረጥና ዘገምተኝነት የኀይል መቆራረጥና የፋይበር ኦፕቲክ ኬብል መቆራረጥን በዋነኛ መንስኤነት አስቀምጠዋል፡፡ የኀይል መቆራረጥ ከመሥሪያ ቤቱ አቅም በላይ ቢሆንም በኮንስትራክሽን ሥራና በሕገወጦች የሚቆራረጠው የፋይበር ኬብል ሌላው ለኔትወርክ መቆራረጥ ዋነኛ ምከንያት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ “ከኬብልና ከኀይል መቆራረጥ የሚመጣ የኢንተርኔት ኔትወርክ መጓተት እንጂ በአገልግሎቱ ላይ ችግር የለም” ብለዋል፡፡

Read 9735 times
Administrator

Latest from Administrator