Monday, 25 March 2013 11:15

በኤርትራ የሰለጠኑ ታጣቂዎች በሱዳኖች ትብብር ተያዙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኤርትራ ውስጥ ሰልጥነው በጋምቤላ ክልል ድንበር አቋርጠው ጥቃት ሊፈፅሙ የነበሩ ታጣቂዎች በሰሜንና ደቡብ ሱዳን መንግስታት ትብብር ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው መሠጠታቸውን ምንጮቻችን አመለከቱ፡፡ ስልጠና ካገኙበት ከኤርትራ ተነስተው ሰሜን ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን አልፈው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ በሶስቱ አገሮች መሀል ባለው የፀጥታ የትብብር ስምምነት መሠረት ለክልሉና ለፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሀይሎች ተላልፈው ተሠጥዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በሰላም እጃቸውን እንዲሠጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ባለመቀበላቸው በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸውን ያጡ እንዳሉም የጠቆሙት ምንጮቹ በክልሉ በተፈፀሙ የተለያዩ የሽብር ተግባሮች እጁ እንዳለበት የሚጠረጠረውና በአስመራ ለረጅም ጊዜ የኖረው ኦማን ካውንዳን ጨምሮ አስራ አንድ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ባለፈው አመት በጋምቤላ ክልል የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎች ላይ እና በክልሉ በኢንቨስትመንት በተሰማሩ ፓኪስታንያውያን እንዲሁም በክልሉ ፖሊሶች ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል በመንግስት ይፈለግ የነበረው አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ኡሞድ ኡዶል ወደ ደቡብ ሱዳን ሄዶ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አብረውት ከነበሩ ታጣቂዎች የተወሰኑት ተገድለው አብዛኛዎቹ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ሲታይ እሱ ተሠውሮ ሲፈለግ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በፌደራል መንግስት ፀረ ሽብር ግብረ ሀይልና የፀጥታ አካላት ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደሉንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማረጋገጡ ይታወቃል፡፡

Read 3503 times